ባለ ራዕይ ይሞታል

ጎዳና ጎግያጎ

 

ድብን አድርጎ ነዋ! እንደ ራዕይ የሚገድል ነገር የለም ማለት ይቻላል። ካልሞተ ራዕዩ ክብር አይኖረውም። ባለ ራዕይ ሰላማዊ ሞት እንኳ አይሞትም። ተሰቃይቶ፤ ታሽቶ፤ በቀረብኝ እስኪል ድረስ ተገርፎ። በሚመራው ህዝብ ተገፍቶ፥ ተጠልቶ፤ በተነሳለት ወገን መሃል ተዋርዶ። አንዳንዴ በትንሽ በትንሹ። አንዳንዴ በሚዘገንን አኳኋን በድንገት፥ ያለ ዕድሜ በሚባል ሁኔታ በመቀጨት ወይም በመወገድ።   

candleየዓለማችን ታሪክ፥ የምድር ሁሉ ዘመንና ጊዜ የተሞላው ራዕይ ባስወገዳቸው ሰዎች አይደለምን? የእስራዔላውያን አባት የተባለውን አብርሃምን ውሰዱ። ራዕይ ታየኝ ብሎ ወጣ። ካገር ከምድሩ ተለይቶ፥ ያባቱን ቤት ውርስ ክብሩን ሁሉ ትቶ። ሞት አንድ በሉት። ብዙ ሳይርቅ ሚስቱ ልትወሰድበት ጥቂት የቀረው ፈተና አፋጠጠው። ለጉልበተኛ ሚስትን የሚያህል አሳልፎ ‘እህቴ’ ብሎ የመስጠት ሃሞት ከየት አገኘ? ሃሞት ወይስ ሞት? ሞቶ ካልሆነ በቀር ይቻላል በሉኝና እዚሁ ልቋጭ። ቀጥል ካላችሁ፥ ቁጠሩልኝማ። ያገሩን ቋንቋና የዘመዶቹን ወግ እንዳይረሳ ነው መሰል ይዞት የወጣው የወንድሙ ልጅ ሎጥ ጥሪት ብጤ ሲሰበስብ፥ የጠነከረ ወገን ሲያከማች፥ መቆራቆስ ከጀለ። አብርሃም ታዲያ ቁርሾ እንዳይጠነክር፥ ጮማውን ስፍራ ልልቀቅልህ ሲል የአጎትነት ወኔውን ተጠቅሞ ወይስ ሞቶበት? ሎጥ ከብትና ሎሌዎች ብቻ ሳይሆን ሚስት፥ ልጆች፥ የልጆች አሽኮርማሚዎች፥ ወዘተርፈ አሉት። አብርሃም ገና “ውጣ” ያለው የእግዚአብሔር ቃል ‘ፈተናውን አልጨርሰምና’ ነገ ከትናንት እምብዛም አይለይለትም። ቀስ በቀስ እየገደለ ያለው ራዕይ እንጂ ሌላ አይታየውም። በቃ ይውሰዳ። መሬት እንጂ ራዕዩን አልወሰደ? ‘ህዝብ ትሆናለህ፥ የህዝቦች አባት ትባላለህ፥ ህዝቦች ባንተ ይባረካሉ’ ብሎታል እንጂ ይህቺን መሬት ሙጭጭ ካላልክ ራዕይህ ይኮላሻል አላለው። ህዝብ ስሆን መሬቱን ከየት አገኛለሁ የሚሉ ዓይነት ጥያቄዎች መሞት አለባቸው። እንዲያውም፥ የወንድሙን ልጅ ሎጥን አደጋ ጣዮች እንዳያደባዩት፥ የበለጠ እንዲንሰራፋ ማገዝ እንጂ። እየሰፋ ያለው እየሰፋ ይሂድ፤ ለኔ ከሌላ ስፍራ ይዘጋጅልኛል ብሎ ማሰብ፥ ሰዶ ማሳደድ፥ የሞት ሞት አይደለም? 

መጽሃፍ ቅዱሳዊ ታሪክ ጋ ምን ወሰድን። ለነገሩ፣ ዛሬስ በኛ መካከል ሰዎች ራዕይ ታየን እያሉ አበሳቸውን ይቅሙ የለ? ስንቶች ሞቱ? ማንዴላ ለምሳሌ። ሃያ ሰባት ዓመት፥ ቁንጮ ዘመኑን፥ ብቻውን በሮቢን ደሴት ከከባድ ስራ ጋር ግዞት የጠጣውስ ከራዕይ የተነሳ አይደል? እኔ ታስሬ፥ ህዝቤ ነጻ ይውጣልኝ ብሏልና። አርፎ የተገዘተም አይመስለኝ። ነፍሱ በእጃቸው እንደሆነ አውቆ እያንዳንዷን ቀን እንደሞተ ሆኖ በመኖርም ጭምር እንጂ። ሰው ራዕይ ታየኝ እያለ ምን አንጦለጦለው ታዲያ? ራዕይኮ ይገድላል። ባለ ራዕይ ይሞታል። ስቅይት ብሎ ይሞታል። ታናሽ ልጁ ጽፋ ካስነበበችን መጽሃፍ ውስጥ ሮቤርት ፒርስ የተባለ ሚሲዮናዊ ህይወት ያለፈበት ውጣ ወረድ ራዕይን በሩቁ የሚያስብል አይደለምን? ‘ልቤ አምላኬን በሚያስለቅስ ነገር ያልቅስ’ ሲል በማስታወሻው የከተበው ሰውዬ ከጉብልነቱ ጀምሮ በጦርነትና በረሃብ ምክንያት ወላጅ ያጡ፥ የተቸገሩ ልጆች ሲያይ ልቡ እንደ ደማበት ኖሮ አለፈ። ቤቱ ተበተነ፤ ሚስቱን ልጆቹን በትኖ ወጣ፥ ከሰካራም ባለ ራዕይ ጋር ማን ይኖራል? ተቸግሮ የሚያስቸግር። የመጀመሪያ ልጁ ተቅበዝብዛ ራስዋን በገዛ እጅዋ አጠፋች። ከአቅሙ በላይ ራሱን እየገደለ ስላስቸገረ ያበረዱለት መስሏቸው አቋቁሞት ሲመራው ከነበረው ወርልድ ቪዥን ከተባለ አንጋፋ ድርጅት ውስጥ በቦርዱ ትዕዛዝ ስልጣኑን ተቀማ። ልጅ ሚስቱን ካጣበት የራዕዩ ልጅ ጭምር ተነጣጠለ። ሞት ሲያንስ አይባልም እዚህ? ቦብ ፒርስ መች አርፎ ታዲያ። ሳማሪታን ፐርስ የተባለ ሌላ ድርጅት ከመሰሎቹ ጋር አቋቁሞ መሞቱን ቀጠለበት። እስከ ዕለተ ሞቱ። እውነተኛ ራዕይ አይሞትም። “ባለ ራዕይ” መሰኘት ግን የሞት ማዕረግ ነው። በተለይ የእውነተኛ ራዕይ ባለቤት ከሆናችሁ ሞታችሁ፥ ምናልባትም አሰቃቂ አሟሟታችሁ ከተወሰነ፥ ከተቆረጠ ቆይቷል። ይቅርባችሁ። ምክሬ ነው። አይ ካላችሁ እቅጯን ይኸው። ባለ ራዕያን ይቀጫሉ። ጆን ኤፍ ኬኔዲና ማርቲን ሉተር ኪንግን ተመልከቱ። ባደባባይ ተረሸኑ። ለሰው ዘር መልካም ሰንቀው በተነሱ ሊያስወግዳቸው የሚዝት በዛ። አገኟቸውም። ግድል አደረጓቸው። እማማ ቴሬሳ በ18 ዓመት ዕድሜያቸው ራዕይ ከሞቀ ቤት ጎዳና ላይ አወጣቸው፤ አልተመለሱም። በካልካታ ህንድ ጎዳናዎች እየዞሩ፥ ኋላም በዓለም ሁሉ የተረሱትን፥ የተገፉትን እየጎበኙ፥ አብሯቸው ልቅሷቸውን እያለቀሱ፥ ሰቆቃቸውን እንደ ተካፈሉ አለፉ። የኛኑ አጼ ቴዎድሮስ መልሰን መላልሰን እናንሳ። ባይገድሉት አይዘበቱብኝም አለ፤ ባንዲት የሽጉጥ ጥይት። ራዕዩ እስከ ዛሬ ሃገሪቱን ተሸከማት። ምን አለፋችሁ፤ ራዕይ ይገድላል አልኳችሁኮ። አንዳንዱ በስራው ረጅም ሰዓት ስላሳለፈ ወይም ጉዞ ስለበዛበት፥ ወይም አንድ ሁለት ምሳ ስላለፈው፥ አሊያም አጨቃጫቂ ሰው ስለገጠመው ራዕይ አሰቃየኝ ይላል። ምን ተይዞ ጉዞ። ይህችማ ምን አላት? ለሞት ያልተዘጋጀ ‘ባለ ራዕይ’ ገና ህልም ላይ ነው። ለመግደል ወይም ለመዝረፍ ያሰፈሰፈውንማ ‘ባለ ራዕይ ነኝ’ ባይ በአደባባይ ሲደነፋ አይኑን ትክ ብላችሁ እዩ። ባለ ራዕይ ሳይሆን እንቅልፋም ነው። ቅዠት የተጠናወተው ስብዕናው የልጆችን ሰቆቃ፥ የእናቶችን ሃዘን፥ ያባቶችን ጭንቀት፥ የመሪዎችን ሸክም፥ የወጣቱን ተስፋ፥ ያዛውንቱን ምኞት የመጋራት ቀርቶ የማስተዋል ኣቅም የለውም። 

 

ራዕይ ያለህን ብቻ ሳይሆን ማንነትህን ጭምር መስዋዕት ማድረግ ይጠይቃል። ይህ ብቻ አይደለም። መልካም ራዕይ ያነገቡትን፥ ንብ ማር እንደሚከብ ጭላንጭል ብርሃን የናፈቁ ሁሉ ይከቧቸዋል። ተከታዮች። እና ተከታይ ካፈራ፥ ባለ ራዕይ ከራሱ ይልቅ ለተከታዮቹ በቅድሚያ ህይወቱን ይሰጣል። ‘ተኙልኝና ልረማመድባችሁ’ የሚለን ጩሉሌ እንጂ ባለ ራዕይ አይደለም። ‘ሙቱልኝ’ እንጂ ‘ልሙትላችሁ’ የማይለን ምንም የረባ ነገር አላየልንም። በርግጥም ራዕይ ታይቶህ ከሆነ ሞትህ፥ ሽልማትህ። በጥቂት በጥቂቱ፥ ከትናንት ዛሬ በበለጠ ካልሞትክ፤ አንተ እያለህ ወይም ጭራሽ ገዝፈህ ሳለህ ራዕይህ ከቀጨጨ ራስህን ፈትሽ። ራዕይ ሲገድል እንጂ ሲያንቦረቅቅ አላየንማ። መስዋዕትነት የተከማቸበት ራዕይ ብዙዎችን ይጠራል። ባለ ራዕይ የማይሞተው ራሱን በብዙዎች ውስጥ ያለ ስስት ስለ ዘራ እንጂ፥ ራሱ ብዙዎች አናት ላይ ወጥቶ ፊጥ ስላለ አይደለም። ራዕይ የመሪነት ልብ፥ አስኳል ነው። መሪነትም መስዋዕትነት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ። ዓለምን የማዳን ራዕይ ብቸኛው መንገድ ራስን አሳልፎ መስጠት እንደሆነ አወቀ። ያውም ለወዳጅ ሳይሆን ለጠላቶቹ በረከት ሲል። ሰጠም። አምላክ ሳለ ሰው ሆነ። ከሰዎችም የመጨረሻ። ሞት፥ ለዚያውም ለክፉዎች እንኳ ያልተገባ የተናቀ ሞት ሞተ። የአምላክነት ብሩን አውቆ ተወ። ስለዚህም እግዚአብሔር ከሁሉ በላይ ከፍ ከፍ አደረገው። ምላስም ሁሉ ጌታ ነው እንዲል፥ ጉልበትም ሁሉ ለርሱ ይንበረከክ ዘንድ አዘዘ። ከዚህ አምላካዊ ፈለግ የወረደ፥ ህዝብ እየኮሰሰ የሚያሰባ፥ ተከታይ እየተሸማቀቀ የሚያስኮፍስ ባለ ራዕይነት ለዓለም ሰላም፥ ለሃገር ዕድገት፥ ለህዝቦች አንድነትና ህብረት፥ ለመንፈሳዊም ሆነ ለምድራዊ በረከት የማይመጥን ቱልቱላ ነው። ባለ ራዕይ ከሆንክ ሞተህ አሳየን። ቸር ይግጠመን።

 መስከረም 2010 ዓ.ም