ቤተ ክህነት እና የዐቢይ ዕጣ
የአክሱም መንግሥት ክርስትናን ከሶርያ ከተቀበለበት ከ4ኛው ምዕተ ዓመት ጀምሮ ቤተ ክህነትና ቤተ መንግሥት ተለያይተው አያውቁም። ያም ማለት በመካከላቸው ሁሌ ስምምነት ነበረ ማለት አይደለም። ቀሳውስት ከመኳንንት ጋር አ-ብ-ረው በአፄ ቴዎድሮስ ላይ ተነሥተዋል። የተፋረሰውን ቤተ ክህነት አፄ ዮሐንስ እና ንጉሥ ምንሊክ በ1870 ዓ.ም ቦሩ ሜዳ ላይ አስማምተዋል፤ በስምምነቱ የአገርን አንድነት አስከብረዋል። አክራሪ እስላማዉያን፣ ድርቡሽና ግብጻዉያን እንዲሁም ጣልያን የኢትዮጵያን ህልውና በተፈታተኑበት ወቅት ሁለቱ አካላት አንድ ሆነው ተጋድለዋል። አቡነ ጴጥሮስ ራሳቸውን ሠውተው ሕዝቡን በወራሪ ላይ አሸፍተዋል። በእንዲህ ዓይነት ቤተ ክህነትና ቤተ መንግሥት ተደጋግፈው አንዱ የሌላውን ጥቅም እያስከበሩ ኖረዋል። ከአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ የምናየው ይህንን ነው።
የቤተ ክህነት አንድ የቆየ ልማዷ ያልተስማማትን ያለ ፍርሃት መናገር ነው፤ የመጀመሪያው ትውልደ ኢትዮጵያ ፓትርያርክ አቡነ ባስልዮስ አፄ ኃይለ ሥላሴን ፊት ለፊት ይናገሯቸው ነበር ይባላል። በሃምሳ ሁለት ዓ.ም. ጃንሆይ ውጭ አገር ሄደው እነ መንግሥቱ ንዋይ ግርግር አስነሱ። ባስልዮስ፣ ሠራዊቱ የጠየቀው የደመወዝ ጭማሪ ጃንሆይ ሲመለሱ እንደሚደረግለት ቃል ገብተው ያረጋጋሉ። ጃንሆይ ግን ጭማሪ አይሰጥም በማለታቸው ዋሾ ስላደረጓቸው ተቃውሞአቸውን ለመግለጽ ደብረ ሊባኖስ እንደ ገቡና፣ ጃንሆይም ገዳሙ ድረስ ሄደው እርቅ እንደ ጠየቁ ይነገራል።
ቤተ ክህነትና ቤተ መንግሥት አንዱ በሌላው ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገባ የደርግና የህወሓት/ኢሕአዴግ ሕገ መንግሥት ይከለክል የለ? እንል ይሆናል። ሐቁ ግን በወረቀት ላይ እንደ ሠፈረው አይደለም። ሁለቱም ሕዝቡን ስለሚጋሩ ተነጣጥለው መቆም አይሆንላቸውም፤ በተለይ ህወሓት/ኢሕአዴግ (ዶ/ር አረጋዊ በርሀ እንደ ገለጹት፣ ገጽ 300—304) ከዚህ ቀደም ባልታየ ስልት ቤተ እምነቶችን በሥልጣን ለመቆያ በመቆጣጠሩ አገርና ማኅበረ ምዕመን በዘር ፖለቲካ ለመታመሳቸው ምክንያት ሆኗል።
ባስልዮስ ገዳም የገቡት በቃል አለመታመን ከአንድ አባት ስለማይጠበቅ ነው። የጃንሆይ እርቅ መጠየቅ ለእግዚአብሔር አክብሮት ብቻ ሳይሆን ቤተ ክህነትም ሥልጣን እንዳላት የሚያሳይ ነው። አቡነ ቴዎፍሎስና አቡነ ተክለ ሃይማኖት በደርግ፤ አቡነ መቆሬዎስ በህወሓት/ኢሕአዴግ ዘመን ይህ ለምን ሆነ? ብለው መጠየቃቸው ይህንን ሥልጣን መጠቀማቸው ነው። ፓትርያርክ ጳውሎስን ከቤተ መንግሥት ጋር ባላቸው ቅርርብ አንዳንዶች በጽኑ ተችተዋቸዋል፤ ቅርርቡ ሌሎች ካደረጉት የተለየበትን እነዚሁ አይገልጹም! ስድስተኛው ማትያስ ቤተ ክህነትን ወዴት አቅጣጫ እንደሚመሩ እየተጠበቀ ነው።
የመጨረሻው ግብጻዊ ፓትርያርክ ቄርሎስ በአርባ ሁለት ዓ.ም. ከሞቱ በኋላ ስድስት ኢትዮጵያዊ ፓትርያርኮች ተሹመዋል። አቡነ ባስልዮስ [ትውልድ ሸዋ] በሃምሳ አንድ ዓ.ም. ነገሡ፤ ታመው ከረሙና ጥቅምት 3/1963 ሞቱ። ምክትላቸው አቡነ ቴዎፍሎስ [ትውልድ ጎጃም] ግንቦት 1/1963 በቤተ ክህነት ሥርዓትና ደንብ ተተኩ። ከሦስት ዓመት በኋላ የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ዐመጽ ስድሳ የአገር መሪዎችን በመግደልና እግዚአብሔር-የለሽ ሥርዓት በማራመድ የ17 ዓመት ግርግር ጀመረ። ዐመጽ ተበራክቶ ነሐሴ 21/1967 አፄ ኃይለ ሥላሴ ተገደሉ። በወቅቱ የነበሩት አቡነ ቴዎፍሎስ በሦስት ጉዳዮች ላይ የወሰዱት አቋም ከቤተ መንግሥት መሪዎች ጋር ከጅምሩ አነካክሶ ለምድራዊ ሕይወታቸው ፍጻሜ መነሻ ሆነ፦ ስለ ሞቱት መሪዎች ተቃውሞ ማሰማታቸው፣ ለአፄ ኃይለ ሥላሴ ፍትሃት ማድረጋቸውና ለቤተ መንግሥት ሳያስታውቁ አምስት ጳጳሳትን መሾማቸው ደርግን አስቆጣ፤ ባለፈው ዓመት የሞቱት አምስተኛው ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ አንደኛው ተሿሚ ነበሩ። ቴዎፍሎስ በስድሳ ስምንት ዓ.ም. ተያዙ፤ በዓመቱ ተገደሉ። ልብ እንበል። አፄ ኃይለ ሥላሴ ቀድመው ሞቱ፤ ቴዎፍሎስ ተከተሉ።
አቡነ ተክለ ሃይማኖትን [ትውልድ ጎጃም] ነሐሴ 23/1968 ቤተ መንግሥት ሾማቸው። ተክለ ሃይማኖት ባሕታዊ በመነበራቸው ለነፍሳቸው ያደሩና የማያስቸግሩ ይሆናሉ ብሎ ደርግ ገምቶ ነበር። ተክለ ሃይማኖት ብዙ ሳይቆዩ በድርጊታቸው መናገር ጀመሩ። ጫማ አላጠልቅም አሉ፣ አልጋ ትተው መሬት አነጠፉ፤ የባሕታዊና የመከራ [ቢጫ] ቀሚስ እንጂ ለሥልጣናት የተመደበውን ጥቊር አላጠልቅም አሉ። ጾምና ጸሎት ያዙ፣ ጥሬና ውሃ እንጂ አልቀምስ አሉ። የተመደበላቸውን ደመወዝ ለደሃ ልጆች ማሳደጊያና ማስተማርያ መደቡ። ይህ ሳያንስ በሰሜኑ ወታደራዊ ዘመቻ ሳቢያ መንግሥት የሚጥለው ቦንብ በሕዝብ ላይ ያስከተለውን ጉዳት ተቃወሙ። ግንቦት 1980 ወደ ቀድሞ ሰበካቸው ወደ ወላይታ አመሩ፤ ለአዲስ ቤተ ክርስቲያን ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ከመረቁ በኋላ ታምመው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ፤ ሆስፒታል ገብተው ግንቦት 30/1980 ሞቱ። አቡነ መርቆሬዎስ [ትውልድ በጌምድር] ከሰማንያ እስከ ሰማንያ ሦስት ተተኩ። ልብ እንበል። ሊቀ መንበር መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ግንቦት 13/1983 ከአገር ወጡ። አቡነ መርቆሬዎስም በዚያው ዓመት ተከትለው ወጡ።
በጠ/ሚ መለስ ዜናዊ የሚመራ አዲስ መንግሥት [ህወሓት/ኢሕአዴግ] ሥልጣን ጨበጠ፤ አቡነ ጳውሎስን [ትውልድ ትግራይ] ከአሜሪካ ጠርቶ ሾመ። ጳውሎስ ሃያ ዓመት ነገሡ። በትምህርትና ሥልጠና፣ በቤተ ክርስቲያን ግንባታ በቅርሶች አያያዝ ላይ የሚታይ ሥራ ሠሩ። ቤተ ክህነት ግን ተከፋፈለች፤ ሊያስማሙ አልቻሉም። ሊያስማማ የሚችል ጠፋ። ቤተ ክህነትም እንደ ቤተ መንግሥት በሙስና ታመሠች። ለአቡነ ጳውሎስ አልባሳትና መኪና መግዣ የወጣው ከፍተኛ ወጪ ቅሬታ አስነሳ። ከአራት መቶ ሺህ ብር በላይ የፈጀ ምስላቸው መድኃኒዓለም ደጅ ሲተከልላቸው አለማስቆማቸው ቅሬታ አስከተለ። የሃያኛ ዓመት ሲመታቸውን በቤተ ክህነት አዳራሽ ሐምሌ 5/2004። ደግመው በሸራተን ሆቴል በናጠጠ ድግስ አከበሩ፤ ብዙዎች ባላደረጉት ይሻል ነበር አሉ። ነሐሴ 10/2004 ታመው ሆስፒታል ገቡ፤ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሞቱ። ልብ እንበል። መለስ በ2004 ሐምሌ አጋማሽ ላይ ቤልጀም ሆስፒታል በሕክምና ላይ እያሉ አረፉ፤ በወሩ አቡነ ጳውሎስ ተከተሉ።
ሁለት በሁለት። ኃይለ ሥላሴ ሞቱ፤ ቴዎፍሎስ ተከተሉ። መንግሥቱ ኃይለማርያም አገር ጥለው ወጡ፤ መርቆሬዎስ ተከተሉ። መለስ ሞቱ፤ ጳውሎስ ተከተሉ። [1] ቤተ ክህነትና ቤተ መንግሥት በሞትና በሕይወት እስከ ዛሬ አልተነጣጠሉም። የአፄው መንግሥት ባስልዮስንና ቴዎፍሎስን ሾመ፣ አብዮታዊ ሶሻሊስቱ፣ ተክለ ሃይማኖትንና መርቆሬዎስን፣ አብዮታዊ ዲሞክራሲው [ህወሓት/ኢሕአዴግ]፣ ጳውሎስና ማትያስን ሾሙ።
ኃይለማርያም ደሳለኝ መስከረም 11/2005 መለስ ሲመሩት የነበረውን ፓርቲ ተረከቡ፤ የራሳቸው ራእይ እንደሌላቸው፣ የመለስን ብቻ ራእይ እንደሚያራምዱ አብዝተው ተናገሩ። ህወሓት/ኢሕአዴግ ማትያስን [ትውልድ ትግራይ] ከኢየሩሳሌም ጠርቶ የካቲት 24/2005 ሾመ። ብጹእነታቸውና ኃይለማርያም በምድራዊ ሕይወታቸው ፍጻሜ ሰሞን ምን ሲሠሩ ይገኙ ይሆን? የሚያልፉትስ እንዴትና በምን አኳኋን ይሆን?
+ + +
በ 2008 ዓ.ም. በመለስ ራእይ ላይ ሕዝባዊ ተቃውሞ ተቀጣጠለ። ኃይለማርያም መለስን በተኩ በስድስተኛ ዓመት ሐሙስ የካቲት 8/2010 ዓ.ም. ወርደው፣ ዐቢይ አሕመድ መጋቢት 24/2010 ዓ.ም. ሥልጣን ያዙ።
ጠ/ሚ ዐቢይ፣ ወታደራዊ ደርግ እና ህወሓት/ኢሕአዴግ የሾሟቸውን፣ በቅደም ተከተል፣ መርቆሬዎስ እና ማትያስን አስማሙ፤ የተከፋፈሉትን ማኅበረ ምእመን አንድ አደረጉ። ለ30 ዓመታት ያህል ከተሰደዱበት ከአሜሪካ ማትያስ ደርግን፣ መርቆሬዎስ ህወሓት/ኢሕአዴግን ሲያወግዙ ቆዩ። በዐቢይ ዘመን ለሁለቱ አባቶች፣ ሁለት መንበር ተዘጋጀ። መርቆሬዎስ እግራቸው ስለማይረግጥላቸው በጸሎት እንዲመሩ፣ ማትያስ በአስተዳደር እንዲመሩ ተወሰነ፤ በዚህም የቤተ ክህነት የሞራል ድህነትና ጥገኝነት ተገለጠ። እውነት ነው፣ የክርስቶስ መንበር ዘር አይለይም፤ የዘመኑ መንፈስ ግን ዘር ለይቶ፣ ልብሰ ተክህኖ የሸሸገውን ገልጦ "አማራና ትግሬን" አነገሠ። በዚህም የዘመኑን አስተሳሰብ መሰከረ፦ ዘመኑ ማንንም ሳያስቀይም (ሁሉን ወገን ለማስደሰት) መሠረታዊውን ችግር አድበስብሶ ያልፋል፤ የሚያቀርበው ጊዜአዊ መፍትሔ የባሰ ችግር ቋጥሯል!
አፄ ኃይለሥላሴ፣ ወታደራዊ ደርግ፣ እና ህወሓት/ኢሕአዴግ ሁለት ሁለት ፓትርያርክ ሾሙ። በዐቢይ ዘመን የሁለት ፓትርያርኮች ጥምረት ተጀመረ፤ ሁለት እራስ!! ሁለት እረኛ አንድ መንጋ ፍቺው ምን ይሆን? መጽሐፍ ግን “አንድ መንጋ ይሆናሉ፣ እረኛውም አንድ” ብሏል (የዮሐንስ ወንጌል 10፡16)። ሞት ለማንም አይቀርምና ከሁለቱ አባቶች አንደኛቸው ወይም ሁለቱ ተከታትለው ቢሞቱስ? የዐቢይ ዕጣ ምን ይሆን?
+ + +
[1] ማስታወሻ፦ የመለስ ሞት ዜና የተምታታ እንደነበረ አንርሳ! photo credit: addisababa.eotc.org.et
ፓትርያርክ በዕጣ ይጫኑ።