የሚቀጥለው እርምጃ ምን ሸሽጓል?

ኮሮና ሁልህም ባለህበት እርጋ ብሎናል። ተሰድዶ መሄድ አይቻል። ከበረሓ ከረሓብ?

ሩቅ ነው ያልነው የዓለም ዳርቻ ለካ ሩቅ አይደለም። ብርቱ የመሰሉን ለካ ብርቱ አይደሉም። ጠቢባንን ጥበብ ከዳቻቸው። ሞት በሚቀጥለው እርምጃ ውስጥ ተሸሽጓል። አዳልጦት የወደቀው፦ ልወድቅ ነው፤ እየወደቅሁ ነው፤ አሁን ወደቅሁ አይልም። ራሱን ወድቆ ያገኘዋል፤ ከተጋደመበት ሆኖ ምን ነካኝ፤ ሰው አየኝ አላየኝ? ይላል። ለዚያውም ካቀለለት ነው እንጂ ወድቆ አለመነሳትም አለ!!

ይህ ዘመን ከኮሮና በፊትና ከኮሮና በኋላ ተብሎ ወደፊት ይታሰባል። ሰማንያ አንድ ዓ.ም. ከቀዝቃዛው ጦርነት በፊትና በኋላ እንደተባለ ሁሉ፤ የኖረው የኃይል አሠላለፍ ከበርሊን ግንብ ጋር አብሮ መደርመሱ። ዘጠና ሦስትን ከአሜሪካ ፍንዳታ በፊትና በኋላ እንደምንል ሁሉ፤ በአናሳነታቸው ሲጠቊ የኖሩ ግዙፉን በተራቸው ማንበርከካቸው።

የአሁኑን ልዩ የሚያደርገው ማንም ሸሽቶ ማምለጫ አለማግኘቱ ነው። ከሽብርተኛ የፈጠነ ስውር ጠላት መምጣቱ ነው። የዘጠና ሦስቱ አደጋ ያነጣጠረው በኃያሏ አሜሪካ የጦርና የኤኮኖሚ አውታር ላይ ነበር። ምንም አይነካንም ሲሉ እንዳልነበር ትምክሕታቸው ከንቱ ሆነ። በሰባተኛ ዓመቱ የዓለም ኤኮኖሚ ከመሠረቱ ተናጋ። የግፍ ግፍ፣ ለመናጋቱ ምክንያት የሆኑት ባለሃብቶች ዳግመኛ ተካሱ! በአስራ ሁለተኛ ዓመቱ የሶሻል፣ የኤኮኖሚ፣ የስነ ልቦና፣ የጦር ኃይል አውታር በሽባነት ተመታ።

የአምልኮ ማእከሎች መዘጋት ኮሮናን ዓይነተኛ አድርጎታል። የዘመን ፍጻሜ ምልክቶች ከዚህ ቀደም ካየናቸው በተለየ መልካቸው እየታዩ ነው። ነገሮች ድንገት ይለወጣሉ፤ ማንም ምንም ማድረግ የማይችልበት ሰዓት መኖሩን ይገልጣሉ። የሥጋ ለባሽን አቅምና የእግዚአብሔር ኃያልነት ያነጻጽራሉ።

አንተ ግን እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ ቃሉን ዝጋ፥ መጽሐፉንም አትም፤ ብዙ ሰዎች ይመረምራሉ፥ እውቀትም ይበዛል። (ዳንኤል 12:4) | ...በምድር ላይም አሕዛብ ከባሕሩና ከሞገዱም ድምፅ የተነሣ እያመነቱ ይጨነቃሉ፤ ሰዎችም ከፍርሃትና በዓለም የሚመጣበትን ከመጠበቅ የተነሣ ይደክማሉ... (ሉቃስ 21:25-26) | በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። (2ጢሞቴዎስ 3:1) | ራስዋን እንደ አከበረችና እንደ ተቀማጠለች ልክ ሥቃይና ኀዘን ስጡአት። በልብዋ። ንግሥት ሆኜ እቀመጣለሁ ባልቴትም አልሆንም ኀዘንም ከቶ አላይም ስላለች፥ ስለዚህ በአንድ ቀን ሞትና ኀዘን ራብም የሆኑ መቅሰፍቶችዋ ይመጣሉ፥ በእሳትም ትቃጠላለች፤ የሚፈርድባት እግዚአብሔር ብርቱ ነውና። እነዚህን የነገዱ በእርስዋም ባለ ጠጋዎች የሆኑት እያለቀሱና እያዘኑ። በቀጭን ተልባ እግርና በቀይ ሐምራዊም ልብስ ለተጐናጸፈች በወርቅና በከበረ ድንጋይም በዕንቊም ለተሸለመች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት፥ ወዮላት፥ ይህን የሚያህል ታላቅ ባለ ጠግነት በአንድ ሰዓት ጠፍቶአልና እያሉ ስቃይዋን ከመፍራት የተነሣ በሩቅ ይቆማሉ። (ራእይ - ምዕራፍ 18፡7-8፣ 17)

የምድራዊ ኑሮ መቊረጫ እንደ ሸማኔ መወርወሪያ ነው። እንደ ቀላል የወሰድናቸው መብቶቻችን በቀላሉ ሊወሰዱ እንደሚችሉ እያየን ነው። የወዳጅ መጨባበጥ። አብሮ መብላት፣ ቡና መጠጣት። ኳስ ሜዳ መተያየት። አብሮ መጸለይ። የሚያስተማምኑ የመሰሉ እንደማያስተማምኑ።

ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ … ነገር ግን ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች፥ እያሳቱና እየሳቱ፥ በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ። (2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡2-5፣ 13)

ሰዓቲቱን የሚያውቅ እግዚአብሔር ብቻ ነው። የአንዳንዶችን የፍጻሜ ቀመር ባንከተለም፣ በማስተዋል እንድንኖር ይጠበቅብናል። ዓለምን ብንቃኛት ምን እንታዘባለን? የክፋት መጠኑ እየባሰ መጥቷል፤ ይህን ያልተገነዘቡ ታሪክን የዘነጉ ናቸው! ቀኝ ዘመም አክራሪያን በየአህጉራቱ ተጠናክረዋል፦ በብራዚል (ጃኢር ቦልሶናሮ)፤ በሃንጋሪ (ቪክቶር ኦርባን)፤ በእንግሊዝ (ቦሪስ ጆንሰን)፤ በህንድ (ናሬንድራ ሞዲ)፤ በአሜሪካ (ዶናልድ ትረምፕ)፤ በእስራኤል (ቤንጃሚን ነታንያሁ)፤ በጣልያን (ማቴዎ ሳልቪኒ)፤ በኦስትሪያ (ኖርበርት ኦፈር)፣ በቡልጋሪያ (ቬዜሊን ማሬሽኪ)፤ በጃፓን (ሺንዞ አቤ)፤ ወዘተ። የሚያመሳስላቸው ምንድነው? ዓለም አቀፋዊ ውክልናቸው። በጥቂቶችና በብዙኃን መሓል ትልቅ የኑሮ ደረጃ ክፍተት መፍጠራቸው። ቊጣና ፍርኃት ዘርተው ሥልጣን መያዛቸው። ቋሚ መረጃን በዘፈቀደ መረጃ መተካታቸው። ባእድ/ስደተኛውን ማስጠላትና ማሳደዳቸው። ዲሞክራሲያዊ መብትን፣ ተጠሪነትና ግልጽነትን ማፋለሳቸው።

የአፍሪካ መሪዎች ጥገኛና የገደል ማሚቶ ስለሆኑ እዚህ አንጨምራቸውም። ለምሳሌ፣ መንግሥቱ ኃይለማርያም እና የያኔው አብዮተኞች (ከ1966—1983 ዓ.ም.) እንደ ሶቪየቶች፣ “ማርክስ፣ ኤንግልስ፣ ሌኒን” ወይም “ቀይ ሽብር፣ ነጭ ሽብር” ሲሉ መነበራቸው። መለስ ዜናዊ (ከ1983—2004 ዓ.ም.) አንዴ እንደ ቢል ክሊንተን “ኒው ዲሞክራትስ” እንደ ጆርጅ ቡሽ “ፀረ ቴረሪዝም” እንደ ኦባማ “ብሩህ ተስፋ” ማለታቸው። ዶ/ር ዐቢይ አሕመድም ያላየነውን “የጥንቱን ታላቅነት” (ኤርትራና የአፍሪቃን ቀንድ ጨምሮ) እያስናፈቁን ይገኛሉ። በአፄ ኃይለሥላሴ፣ ሰሎሞናዊ የዘር ሐረግ ነበር። በመንግሥቱ ኃይለማርያም፣ መደብ አልባ ሶሻሊስታዊ ሥርዓት። መለስ ስለ ኢትዮጵያ ትንሣኤ አንስተውልን ነበር (አንዳንዶች ትግራይን ማለታቸው ነው ብለውናል)። ዐቢይም “ብልጽግና፣ ብልጽግና”። ሁላቸውም በ “ታላቅነት” መረቅ አስቋምጠውናል። እነርሱ ካልመሩን የተስፋዪቱን ጎዳና እንደማንረማመዳት ሰባብከውናል። የገቡልንን ተስፋ ስንጠባበቅ ብዙዎቻችንን ሞት አሰናበተን፣ የተረፍነው እስከ ዛሬ ምንም አላየን! እኛም ተጃጅለን፣ እጅ አጣምረን ጠበቅናቸው! ታሪኩን የረሳን አዲሱን ትውልድ፤ ባረጀ ብልጠት እንደ አዲስ አሞኙት!

ፖለቲከኛ አይዋሽም አይባልም። በአሜሪካ መዋሸት ቋሚ ፖሊሲ ሆኗል፤ በሶቭየት ኅብረት ሲላከክ የኖረው ዛሬ ዓይነተኛ የፖለቲካ ስልት ተደርጓል። በአሳብ የማይስማማውን በአደባባይ ማዋረድ፤ ረብሻና ግድያ መፈጸም ቀሏል። የስታሊን የማኦ እና የሂትለር አባባሎች ይደመጣሉ። ለምሳሌ፣ “ነጻ ፕሬስ የሕዝብ ጠላት ነው” ይሉ የነበሩት ስታሊንና ማኦ ናቸው። የሰሜን አውሮጳን ነጭ ደም ጥራት ያወጀው ሂትለር ነው። የበርሊን ግድግዳ በፈረሰ በሠላሳ ዓመቱ በአሜሪካና በሜክሲኮ ድንበር ላይ እየተገነባ ነው። መነሻ አሳቡ ፍርኃትን ቀስቅሶ የሕዝብን ድጋፍ ማግኚያ ነው። ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም ኃያልም በኃይሉ ብዛት አያመልጥም። ፈረስም ከንቱ ነው፥ አያድንም፤ በኃይሉም ብዛት አያመልጥም። (መዝሙር 33፡16-17) እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ ጠባቂ በከንቱ ይተጋል። (መዝሙር 127፡1)

wall2

“ታላቅነት” የሚሉት የቱና ምኑን እንደሆነ የሚያውቅ የለም፤ ሁሉም ምኞቱን የሚቃርምበትን ቀልቀሎ አንጠልጥሎ ቀፈፋ ወጥቷል! ታሪኩን በማጋነን ኢትዮጵያውያንን የሚተካከል የለም። ታሪኩን በመርሳት አሜሪካኖችን የሚተካከል የለም። “ሜክ አሜሪካ ግሬት አጌን” አሜሪካን ወደ ቀድሞ ታላቅነቷ እንመልሳታለን ነው! ውስጠ ዘ ነው! የነጭ የበላይነትና የጥቊሮች ባርነት ወደ ነበረበት ማለት ነው።

የጥላቻና የሃሰት ቧንቧው የተፈታ ይመስላል። የተቀደሰው ረክሶ፣ የረከሰው ገንኗል። የአሜሪካ ወንጌላውያን (እነ ፖላ ኋይት፣ እና ተከታዮቻቸው፤ ሁላቸውም ነጮች ወዘተ) ፕው ባካሄደው የሕዝብ አስተያየት ፍተሻ፣ ሁለት ሲሦአቸው ትረምፕን “ቅን፣ መልካም ስነ ምግባር የተላበሱ” ብለዋቸዋል! አባባላቸው ብዙዎችን ግራ አጋብቷል። እግዚአብሔር ቀብቶአቸዋል ይሉናል፤ ትንቢት ቢጤም ነስንሰውላቸዋል! አንደኛቸው “ትረምፕ እንደ እስራኤል ንጉሥ ናቸው፤ እንደ እግዚአብሔር ምጽዓት ናቸው” ብሏል፤ ፕሬዚደንቱም በቲዊተራቸው አባባሉን አጽንተውታል። እነ ፍራንክሊን ግራሃም፣ ይህ በእግዚአብሔር ላይ ድፍረት ነው ብለው አልተቃወሙም! እውነትን ከሃሰት ይለያሉ የተባሉት ብሰው ተገኙ! ትውልደ ኢትዮጵያ አሜሪካውያን ወንጌላውያን ውሸትን መንፈሳዊ በማስመሰል ከነጮቹ ብዙ ይለዩ ይሆን?

ጥላቻ በሚቀጥለው እርምጃ ውስጥ ተሰውሯል። ስደተኛን መጠርጠር፣ መጥላትና ማግለል ተባብሷል። ነገሮች በፍጥነት ይለዋወጣሉ። አሜሪካ ስደተኛ የሚጠለልባት፣ በተለይም ጥቊሮች የገነቧት አገር ነች። የጥቊሮችን ቊጥር ለመቀነስ፣ የመቋቋሚያ ድጎማ መከልከል፤ ቤተሰብ እንዳያስመጡ ማገድ፤ ልጅን ከወላጅ ሚስትን ከባል ነጥሎ ማንገላታት፣ በሰበብ አስባብ ወደ መጡበት መመለስ፣ በቆየ ህመም ሳቢያ ኢንሹራስ መንፈግና ክፍያ መጨመር፤ የሚሉ ህጎች ረቀው በይደር ተይዘዋል። በ2020ው ምርጫ መራጭ በነቂስ ወጥቶ ራሱን ካላስጣለ በተቀር መበላቱ ነው። ለኢትዮጵያውያን የዓባይ ውሃ አጠቃቀም ድርድር መጨናገፉ ሌላ ፍዳ ይዞ ይጠብቀናል።

 

ማንም ምንም ማድረግ የማይችልበት ሰዓት መኖሩን ከእንግዲህ ወዲያ መጠራጠር ሆነ መከራከር አንችልም። እግዚአብሔር በዘጠና ሦስት ነግሮናል፤ በሁለት ሺህም ነግሮናል፤ ሰምተን ችላ እንዳንል በሁለት ሺህ አስራ ሁለት ደግሞልናል። ላለፉት ትውልዶች ለነኖኅ፣ ለነሎጥ ይህንኑ አድርጎላቸዋል! እግዚአብሔር በሥራው ሁሉ ጻድቅ ነው።

የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጕብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ፤ ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ፤ (መክብብ 12:1) እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፥ ቀርቦም ሳለ ጥሩት፤ ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም አሳቡን ይተው፤ ወደ እግዚአብሔርም ይመለስ እርሱም ይምረዋል፥ ይቅርታውም ብዙ ነውና ወደ አምላካችን ይመለስ። (ኢሳይያስ 55:6-7) እግዚአብሔር ርኅሩኅና መሓሪ ነው፥ ከቍጣ የራቀ፥ ምሕረቱም ብዙ ነው፤ (መዝሙር 145:8) ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል። የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፥ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣል፥ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል። ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፥ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ፥ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል? ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይፈታል፤ ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን። ስለዚህ፥ ወዳጆች ሆይ፥ ይህን እየጠበቃችሁ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም በእርሱ እንድትገኙ ትጉ፥ (2ኛ ጴጥሮስ 3:9-14)

ምትኩ አዲሱ

ሚያዝያ 16/2012 ዓ.ም.

pic credit: googleImages