tukul

ፍ  ቅ  ር   በ  ሦ  ስ  ት   መ  ቶ

ፍቅር ፈቀደ

ወደ ስድሳዎቹ አጋማሽ መሠሉኝ። እርሳቸው ሲያስተምሩ ሁሉ ነገሬ ወደጆሮነት ነው የሚቀየረው። በዘመናዊ እውቀትም ሆነ በተፈጥሯዊ ገጠመኝ የተባረኩ ሰው ናቸው። ቋንቋችን አማርኛማ! እንደእርሳቸው ፊት የሰጠችው ሰው ያለ አይመስለኝም። እስከዛሬ ያልገባኝ፣ ሲያስተምሩ፣ ጓደኛዬን ዕፅገነትን ብቻ እየሾፉ የነበረበት ሚሥጢር ነው። የምር ምራቋን የምትውጥበት ጊዜ እንኳን አይሰጧትም ነበር። ዐይናቸው ገጿ ላይ እንደተሠፋ...

ለቀናት ካስተማሩ በኋላ “ፍቅር የቷ ናት?” ብለው ጠየቁና ወደቢሯቸው አስጠሩኝ። ትልቅ መጽሐፍ ሰጡኝና “አንቺም የቀሩትም ኮፒ እያደረጋችሁ አንብባችሁ...”

በእርሳቸው መጠራት የምር የሆነ ደስ የሚል ነገር አለው። ስሜ አፋቸው ላይ እንዴት አንደሚጣፍጥ፤

“ከእንግዲህ በኋላ ጓደኞች ነን!” ያሉኝ ቀን “እሺ! በደስታ!” ያልኹዋቸው ገና የመጨረሻው ቃል ሙሉ ለሙሉ ከአንደበታቸው ተጠናቆ ሳያልቅ ነበር። (እኔ እኮ ጥሩ ጓደኛ ነኝ...)

ቀስ እያለ ሕይወታቸውን እያጫወቱኝ (በተለይ የኢሕአፓዊ ትግላቸውን)፣ እየመከሩኝ፣ ስለእራሴም እየጠየቁኝ አብሮነታችን ጠነከረ። የሆነ ቀን ቢሯቸው ጠርተው የተወከልኩበትን ጒዳይ ከነገሩኝ በኋላ፣ እጃቸውን ወደሹራብ ኪሴ ሰደዱ (አንዳንዶቻችሁ ሌላ ነገር መስሏችሁ? ...)፤ ለመከላከል ብሞክር ቆጣ አሉ (እኔ እኮ ትልቅ ሰው አከብራለሁ)፤ እና ዝም ብዬ ቢሯቸውን ለቅቄ እደጅ ወደሚጠብቁኝ ጓደኞቼ ኃይልሽና ጸጊ አመራሁ።

በመንገድ ኪሴ ስገባ የሚንቋቋ ነገር በዛ። ሦስት መቶ ጥሬ ብሮች፤ አቤት አዲስነታቸው! ለጓዶቼ ነገርኋቸው። በኃይልሽ ወትዋችነት በብሩ ዘና ፈታ አልንበት (ያኔ ብዙ ብር ነበር ወገኖቼ!)። እኔ ግን ለምን እንደዚህ ስዝን አድርጌ፣ አንጀታቸውን በልቼ፣ እጃቸውን እንዳረጠቡብኝ አልገባኝም ነበር። ዝናብ ሲዘንብ እያስታወሱ ሲረፍድብኝም ጭምር የዩኒቨርሲቲውን መኪና በግል እያዘዙልኝ በምቾት አሠቃይተውኝ ነበር። (ገለታ ይግባቸው!)

ታዲያ አንድ ቀን ሉሲ ጋዜቦ ቀጠሩኝ። “ፍቅር ይኸውልሽ! ዕውቀትን የምትደግፍ ሴት ደስ ትለኛለች። ብዙ አልገጠመኝም።” (ጒራ ሊጀማምረኝ ነበር፤) ቀጠሉ፦ “እኔ እንኳ ብዙ ለእንደዚህ ዓይነት ጉዳይ ትኲረት አልሰጥም ነበር። ግን ምን መሰለሽ፣ የቤተሰብ ግፊትም እያየለ መጣ” (ታድለው፣ ስድሳዎቹ አጋማሽም ሆነው መገፋት ባለባቸው ዕድሜ እንኳ የሚገፋቸው ቤተሰብ አላቸው፤) “እና ምን መሠለሽ! እንድንጋባ እፈልጋለሁ፣” ጌታ ሆይ! እንዴት እንደተጠቀለልኩ፤ ረጅምነቴን እንደጠላሁት እና ክርፍፍ እንዳልኩኝ፤ እንዴት መደበቂያ ቦታ እንደጠፋኝ... ከዚያ በኋላ ምንም አልተናገርኩም። እርሳቸውን የሚያንቋሽሽም ሆነ እኛ ሴቶች እንደምንለው “ልክ ልካቸውን” የመናገር አቅሙ አልነበረኝም። ዝም እንዳልኩ ቀረሁ። እርሳቸውም በግሬድ አልተበቀሉኝም። እንደዚያ ኃይልሽ በአብዛኛው እየተጋበዘ የጨረሳትን ብር ከኪሴ አስልቼ፣ በኮርሱ ማለቂያ ላይ በቢሯቸው ቀዳዳ በኩል ላክሁላቸው። (ግን ቤተሰብ ባይገፋቸውስ ኖሮ?)

እኔም፣ እኲያቸው የነበረው አባቢ ሳይገፋኝ በፊት፣ ያኔ የጀመረኝ ሽበት የምር ሆኖ መግፊያ ላይ ሳያደርሰኝ በፊት፣ አንዱ ሸበላ ላይ የዛሬ ዘጠኝ ዓመት እንደመድሃኒት ቤት እባብ ተጠምጥሜበት ቅርት አልኩ እላችኋለሁ ...

© 2021 by Fikir Fekede