menelikornis

ምንሊክ-ዖርኒስ ሩስፖሊ እባላለሁ። ደስ አልልም? ስሜ ደስ አይልም? እስቲ ምንሊክ-ዖርኒስ በልና አንዴ ልስማህ። ያንተ ስም ማነው? እውነተኛ ስሜ ጒጒኬ ነው። ጒጒኬ ግን በፌስቡክ ስኬት ዘመን ለክብሬ አይመጥንም ብዬ ንቄዋለሁ። የምታየውን ፎቶዬን የተነሳሁት ነገሌ ቦረና ነው። ቱሪስት አንስቶ ሳይበር ቴክስት አርጎልኝ። አላምርም? ባንዲራ ቀለሜስ? አትታዘበኝና ሰሞኑን ኢትዮፕያን አይዶል ለወፎች ለምን አይደረግም ስል ነበር።

የሆነውን ላስረዳህ፦ ሩስፖሊ የሚባል የጣልያን መስፍን ነበረ፤ በ1858 ዓ.ም. የተወለደ፤ ከቤተ ቦናፓርቴ የተጋመደ። አባቴ ግን እርሱ አይደለም። ወፍ ምን አባት አለው! ወፍ ወፍ ነው፤ ተወልዶ መብረር፣ በርሮ በርሮ መፍረስ ነው።

ልዑል ሩስፖሊ ሕይወት ስትሰለቸው እስቲ ወጣ ብዬ ከአእዋፍ ልማረው ብሎ በብርበራ አድርጎ ውጋ ዴን ከውጋዴን ሸበሌ ሠፈራችን መጣ፤ እንደ እኛ እንደ ወፎቹ ቪዛ ሳያስፈልገው በጓሮ በር ከች አለ። ይህን ተባራሪ ወሬ ሰምቼ እንጂ እርግጠኛ አይደለሁም። የወፍ ጭንቅላት ብዙ ነገር መሸከም አይችልም እኮ። የኢትዮጵያ ውትብትብ እንኳን ለወፍ ለሰውም አልጨበጥ ብሏል። ስለ ጎጆ አሠራር ጠይቀኝ፤ ስለ ሩጫ ጠይቀኝ፤ ስለ ማህበራዊ ኑሮ ጠይቀኝ፣ አስረዳሃለሁ። ሩስፖሊ ሲመጣ የቅድመ አያቴ ቅድመ አያት በሕይወት እንደ ነበሩ ሰምቻለሁ። የመጣው ከአድዋ ጦርነት አምስት ዓመት አስቀድሞ ነው። ያኔ ምንሊክ የሚባሉ ነበሩ። ሩስፖሊ እስከ ቦረና ዘመተ። የአገሬው ሰው እየመራ ጓዳ ጎድጓዳውን አሳየው። እየዘረፈ፤ መንደርተኛ እያረገፈ አለፈ። መቶ ሰማንያ ሦስት ልዩ ልዩ አእዋፍ ረፍርፎ፣ ምን እንደሚያደርግለት እንጃ ሥጋቸውን አድርቆ፣ አፈራችንን ጭምር ዘግኖ አገሩ ገባ። ሽብር ሲበራከት፣ ጮኸን ጮኸን ሰሚ ስናጣ፣ ምን እናድርግ እኛም በርረን ከነቤተሰባችን ወደ እንግሊዞች ኬንያ ሸሸን።

ስሜን ለምን ምንሊክ-ዖርኒስ እንዳለ ገብቶሃል? በርሱ ቤት በምንሊክ ስም አስታኮ እራሱን የምንሊክ አባት ማድረጉ ነው። ብልሃቱን ያዝክልኝ? ሕይወት የሰለቸችው ሩስፖሊ አላገባም፤ ዘር አልተካም። ስሜን ቀይሮ ባቋራጭ የኔና የምንሊክ አባት ሆኖ ቊጭ። የአድዋ ጦርነት ሊጀመር ሦስት ዓመት ሲቀረው ቡርጂ ሶማሌ ግዛት ገናሌ ወንዝ ዳርቻ ዝኆን አይቶ፣ አብረውት ያሉትን በምልክት ዝም ካሰኘ በኋላ ካርባይኑን ደግኖ ለቀቀበት። አጅሬ ዝኆን ቀድሞ አይቶታል። እንደ አውራቂስ ከንፎ በኲንቢው መሓል ልዑሉን ሩስፖሊን ቀስፎ ያዘው፤ ፓድሬ ኖስትሮ ለማለት እንኳ ፋታ አልሰጠው፤ ይዞ ወደ ሰማይ አወጣው ደግሞ ወደ ምድር አውርዶ ፈጠፈጠው፤ ረጋግጦ ለቀብር እንዳይሆን አድርጎ አጨማለቀው። እግዚዖ መሃረነ ክርስቶስ። ነፍስ ይማር። ነፍስ ይማር። ከዝኆን የተራረፈውን ለነፍሱ ያደረ የቦረን ሰው ለቃቅሞ ከዚያው ቀበረው። ሩስፖሊ ዕድሜው ገና ሃያ ሰባት ዓመት ነበር።

ኢትዮጵያ የሚወጋትን አትምርም፤ በተወጋው አትጨክንም። ያንተን አላውቅም፤ እኔም እንኳ በወፍ አቅም ይህን ያህል ተረዳሁ እልሃለሁ። የሚክሰኝ አስመስሎ ወስዶ ከንጉሥ ቤተሰብ ከጣልያኑ ከፈረንሳዩ መሓል ጨመረኝ እልሃለሁ! እኔ ግን ከወገን ሊነጥለኝ እንደ ሆነ ነቅቼበት ክብሩ ይቅርብኝ ብያለሁ።

ቆይኮ! ይኸ ነገር አልመስልህ አለኝ። ሩስፖሊ በሃያ ሰባት ዓመቱ ሞተ ካልሽ፣ ከሙታን ተነሥቶ ነው ስም ያወጣልሽ?

ጥሩ ጥያቄ ነው። ስም ያወጣልኝ እርሱ ሳይሆን፣ ሳልቫዶሪ የተሰኘ ወዳጁ ነው፤ ሩስፖሊ ዘር ሳይተካ እንደ ወጣ መቅረቱ ከንክኖት የአድዋ ድል ማግሥት፣ ምንሊክ-ዖርኒስ ሩስፖሊ ብሎ ስም አወጣልኝ። ነገሌ ቦረና የተነሳሁትን ፎቶዬን እንደ ገና ልብ ብለክ ተመልከት። ሰለሞንን አያስታውስህም?

የትኛውን ሰለሞን?

ስንት ሰለሞን አለና ነው? ሰለሞን ባረጋ ነዋ! ኢትዮጵያን ላያስነካ ተፋላሚውን ሁላ በአሥር ሺህ ገመድ ጠልፎ የጣለው። ከእንግሊዝ ሱማሌ ከ ሞ ፋራ መንጋጋ ወርቅ መንጭቆ ያወጣው! የሰለሞንን የጠጒር ቊርጥ ልብ ብለካል? ከማን የቀዳ መሰለህ? ያሸነፈው እንዴት መሰለክ?

አንዳንዴ ሕይወት ስትሰለቸኝ፣ ስሜን ምንሊክ-ዖርኒስ ባረጋ ልበል ወይ እላለሁ! ምን ይመስልሃል?

selemon barega

ሰለሞን  ባረጋ | picture credit: googleImages

ምትኩ አዲሱ