እግዚአብሔር አስገረመን

በእንዳልካቸው ኪዳነ ወልድ

የካቲት 13፣ 1962 ዓ.ም. ነው። በጎሬ ኢሉባቦር አዳሪ ትምህርት ቤት አርብ አርብ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ ለተማሪዎች የመዝናኛ ክፍለ ጊዜ ይዘጋጅ ነበር። ሁላችንም አርብ ምሽትን በናፍቆት ነበር የምንጠብቀው። እኔም በበኩሌ ጨዋታ በጣም እወድ ነበር።

የዛሬው አርብ ምሽት ግን ከሌላው ሁሉ ለየት ያለ ነበር። እንደ ወትሮ ጨዋታ አላማረኝም ነበር። ትዝ ከሚለኝ አንዱ ወንጌላዊ የነበረው የአሁኑ ቄስ ኢተፋ ጎበና ከጨዋታው በፊት ለአንድ አፍታ ጸልየን እንመለሳለን ብሎን ወደ ጸሎት ቤት መሄዳችንን ነው። ይህ አይነቱ ጸሎት ቀድሞ አይታወቅም ነበር። እርግጥ ጠዋት ጠዋት ለሠላሳ ደቂቃ የመጽሐፍ ቅዱስና የጸሎት ጊዜ ይኖረን ነበር።

በዚህ ምሽት ግን በፈቃደኛነት ጥቂቶቻችን ተሰባስበን ሳለ ወንጌላዊው እንግዳ የሆነ ነገር አሰማን፦ “አንዲት ልጅ በመቱ ከተማ አካባቢ እንደ ራእይ ያለ ነገር ይታየኛል ትላለች፤ ምን እንደ ሆነ አይታወቅምና እንጸልይላት ብዬ ነው የጠራኋችሁ” አለን።

ይህ የሰማነው ነገር ግን ግራ አጋባን። ለማንኛውም ወንጌላዊ ኢተፋ ጸሎት አደረገና ተበታተንን።

እኔ ግን በዚያች አጭር የጸሎት ጊዜ መንፈሴ ተለወጠብኝ። ጸሎቱን ማቋረጥ አልፈለግሁም፤ ቀጥዬ መጸለይ ፈለግሁ። ብቻዬን ግን እንዴት መጸለይ እንዳለብኝ ገና አላውቅም ነበርና ከሌሎች ጓደኞቼ ጋር መጫወት ቀጠልሁ። ሆኖም ከልቤ ሆኜ መጫወት አልቻልኩም።

በውስጤ መቼ ጨዋታው አብቅቶ ጸሎት ቤት እንደገና ከወንጌላዊው ጋር ሄጄ እጸልያለሁ እል ነበር። ጨዋታው እንዳበቃ ወዲያው ወንጌላዊ ኢተፋን፦ “እባክህ ጸልይልኝ፣ መጸለይ እፈልጋለሁ አልኩት።”

እግዚአብሔር ሊሆን ላለው እያዘጋጀን እንደሆነ የገባን ኋላ ነበር።

ከዚያ በፊት ለተከታታይ ሳምንታት ጠዋት ጠዋት ከሐዲስ ኪዳን ውስጥ የሐዋርያት ሥራን መጽሐፍ እንማር ነበር። መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያትና አብረዋቸው በነበሩት ላይ ስለ መውረዱ፣ በልሳን ስለመናገር፣ ስለ ፈውስ እንማር ነበር። አንድ የማስታውሰው ጥያቄ፦ “በዚህ በእኛ ዘመን እንዲህ አይነት ነገር ይሆናል ወይ? እግዚአብሔር አሁንም እንዲህ ያደርጋል ወይ?” የሚል ነበር። ያስተምሩን የነበሩትም ሰው፦ “አዎን አንዳንድ ሰዎች የዚህ አይነት ልምምድ እንዳላቸው አውቃለሁ” ሲሉ አስገረሙን። ይህም አባባላቸው አእምሮዬ ውስጥ ቀረ።

ወንጌላዊ ኢተፋም፦ “እሺ እንሂድና እንጸልይ” በማለት ወደ ጸሎት ቤት ይዞን ገባ። ወንድም መርሻ ስዩም እንዴት አብሮን እንደመጣ ባላስታውስም አንድ ሌላ ሰው እንደዚሁ ከእኛ ጋር እንደ ነበረ አስታውሳለሁ።

ወንጌላዊውና እኔም ለመጸለይ ተንበረከክን። በግንባራችንም ተደፍተን መጸለይ ጀመርን። እግዚአብሔር መንፈሱን እንዲሰጠን ይመስለኛል የጸለይነው። እንደዚህ አይነቱ ጸሎት አልተለመደም ነበር፣ ሰምተንም አይተንም አናውቅም። ከተንበረከክን በኋላ የሆነው ግን ከአእምሮአችን በላይ ሆነብን።

በእንባ እንጸልይ ነበር፤ ንስሃ እንገባ ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ እጆቼ ተዘርግተው በአዲስ በማላውቀው ቋንቋ መጸለይ ጀመርኩ (የሐዋርያት ሥራ 2 ይመልከቱ)። አሁን ሳስታውሰው ሦስት ወይም አራት የማልገነዘባቸውን ቃላት ነበር እየደጋገምኩ የምለው። ትርጉማቸውን ግን አላውቅም ነበር። ይኸ ሲሆን ይሰማኝ የነበረው ሰማያዊ፣ መንፈሳዊና ልዩ የሆነ የእግዚአብሔር ክብር በዚያ ሥፍራ መኖሩ ነበር። እነ ወንድም መርሻ ምን እየሆኑ እንደነበር ባላስታውስም ታላቅ የእግዚአብሔር መገኘት ክብር ውስጥ ስለ ነበርን ሁላችንም እያነባን እንጸልይ እንደ ነበር አስታውሳለሁ።

ብዙም ሳይቆይ፣ ይህን ብርቱ ድምጽ ሰምተው ኖሮ የአዳሪ ቤቱ ተማሪዎች በመደናገጥ ጭምር ወደ ጸሎቱ ቤት ተሰበሰበው መጡ። የመጡትም ሁሉ ወድቀው ንስሃ መግባት ጀመሩ። በዚሁ እንዳለ ጊዜው በጣም መሽቶ ነበርና ወደየመኝታ ቤታችን እንድንሄድ ተነገረን። የጸሎቱና የእንባ ንስሃው እዚያም እንኳን አላቆመም። ሌሊቱን ሁሉ ሲጸልዩ ያደሩም ነበሩ።

ቀጣዩ ቀን ቅዳሜ ነበር። ቅዳሜ ምሽት ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች የጸሎት ጊዜአቸው ነበር። አንዳንዶቻችን በዚህ ጸሎት ላይ ተገኝተን መሳተፍ ጀምረን ነበር። እንደገባኝ ከሆነ ቀደም ባሉት ወራት የመሪዎች ስብሰባ ተደርጐ፦ “ጎሬ ላይ ብዙ ገንዘብና ጉልበት ቢፈስስም፣ ወንጌል ግን ሊስፋፋ ቀርቶ ከትምህርት ቤቱ ግቢ እንኳ ፈቀቅ ሊል አልቻለም። አገሩ ድንጋይ የሕዝቡም ልብ ድንጋይ ነው። ማእከሉን ለትምህርት ሚኒስቴር አስረክበን በትምህርት ዓመቱ መጨረሻ ላይ እንለቃለን” የሚል ውሳኔ ላይ ተደርሶ ነበር። እውነትም ከሃምሳ አመት ድካም በኋላ ባልሳሳት ለክርስቶስ የተሰጠ ሕይወት የሚታይባቸው አባላት ቁጥር አስራ አምስት ቢሆን ነው።  

እንግዲህ የቅዳሜ ምሽት የሽማግሌዎች ጸሎት የተጀመረው ለትምህርት ሚኒስቴር እናስረክብ ከሚለው ውሳኔ በኋላ ነበር። ታሪኩ ይህ ሆኖ በዚያች ቅዳሜ የካቲት አስራ አራት ምሽት አብዛኛው ተማሪዎች በጸሎቱ ስብሰባ ላይ ተገኙ። እንደማስታውሰው “ስብሐት ለአምላክ” ከምትለው የመዝሙር መጽሐፍ ላይ መዝሙር ተዘመረ። ከስብከቱ በፊት ጸሎት እንደ ተደረገ ታላቅ የእግዚአብሔር መገኘትና ክብር እንደገና መጥቶ ሥፍራውን ሞላው። የነበሩትም ሁሉ በንስሃ መንፈስ ለቅሶና ጸሎታቸውን ቀጠሉ። በአዲስ ልሳንም መናገር ጀመሩ፤ ትንቢት ተናገሩ፤ ራእይም ይታያቸው ጀመር። በዚያን ሰአት የሚነገረው ትንቢት፣ ራእዩም ክርስቶስን ስለማያውቁት ስለ ጠፉ ነፍሳት ነበር። እኛም ወንጌልን ለሰዎች የማድረስ ታላቅ ጉጉት አደረብን።

የዚያን ምሽት ጸሎት፣ ጩኸትና ለቅሶ ከተማው ድረስ ተሰምቶ ስለ ነበር ሕዝቡ ሰው ሞቶ ነው ወይስ ምን ተፈጥሮ ነው እያለ ወደ ጸሎቱ ቤት ጎረፈ። ትዝ እንደሚለኝ ወደ ጸሎቱ ቤት ውስጥ የገቡ በአብዛኛው የእግዚአብሔር መንፈስ ስለ ነካቸው በንስሃ በእግዚአብሔር ፊት ወድቀው ያለቅሱ ጀመር። ይህ ለኔ አስገራሚ ነገር ሆነብኝ። ይኸውም፣ ስብከት ሳይኖር እንዴት ሰው ንስሃ ይገባል? እያልኩ ነበር። ይህ ግን እግዚአብሔር ያደረገው ነገር ነበር። ሌሎችም በመስኮት በኩል እየተጨናነቁ የሚሆነውን ለማየት ይገፋፉ ነበር።

አንድ ታሪክ እዚህ ላይ ባክል መልካም ይመስለኛል። በዚህች ምሽት ከቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች አንደኛቸው ወደ ጸሎቱ መምጣት አልቻሉም ነበር። በኋላ ሲናገሩ “ብራዚል” ጠጅ ቤት እንደ ነበሩ ነገሩን። ጩኸት በአዳሪ ትምህርት ቤቱ ግቢ ሲሰማና ሕዝቡ ሲሯሯጥ ሰምተው እርሳቸውም ሕዝቡን ተከትለው ይመጣሉ። ጸሎቱ ቤት ሲደርሱ እርሳቸውንም ምሕረቱ የማያልቅበት ጌታ በሰማዩ ጸጋና መንፈስ ነካቸው። ተንበርክከው፦ “እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ” እያሉ እንባቸውን ያፈስሱ ጀመር። ሲመሰክሩ የማስታውሰው ተመልሰው ወደ ቤታቸው እየሄዱ ሳለ እንኳ በከተማው ድንጋያማ መንገድ ላይ ደጋግመው ተንበርክከው መጸለያቸውን ነው።

እውነትም የሰውን ድንጋይ ልብ መለወጥ የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው። ያች ቅዳሜ የዛሬይቱ የኢሉባቦር ሲኖዶስ የተፈጠረችበት ዕለት ነው እላለሁ።

ከዚያች ቀን በኋላ ወንጌል እግር አወጣ። በየእሑዱ ተማሪዎች ቡድን በቡድን በየአቅጣጫው ወንጌል ለማዳረስ እንሰማራ ጀመር። በየአውጫጭኙ እና በየዕድር ስብሰባ ላይ እያስፈቀድን መመስከርና መስበክ ጀመርን። ብዙዎችም በጥሞና ይሰሙን ነበር። በመጠጥ ቤቱ፣ በከተማውና በገጠሩ ስለ ጌታ ኢየሱስ አዳኝነት በብዙ ድፍረትና ጸጋ መናገር ቀጠልን። ተማሪ ቤት ሲዘጋ ደግሞ በመንፈስ የተቀጣጠለው ተማሪ ሁሉ ወደ መጣበት ተመልሶ ወንጌልን ማዳረስ ዋና ተግባሩ ሆነ። ወንጌል በጎሬ ከተማ፣ በመቱ፣ በሁሩሙ፣ በያዮ፣ በቡሬ፣ በጨራ በየገጠሩ፣ በሞቻ አውራጃ በበደሌ አውራጃ በየአቅጣጫው ይሰራጭ ነበር። መሠረታዊ የሆነ የወንጌል ቃል እውቀት እንዲኖረን የሚያስተምሩን መምህራን መኖራቸው በዚያን ዘመን በጣም ጠቅሞ ነበር።

ከዚያ ሌላ አሁን ወደ ኋላ ተመልሼ ሳስበው የሚገርመኝ በጎሬ ጸሎት ቤት ከትምህርት ቤት መልስ ለተከታታይ አመታት በየቀኑ ይደረግ የነበረው ኮንፈረንስ የሚመስል መንፈሳዊ ስብሰባ ነበር። የቃሉ ብርሃን ተገልጦልን መንፈሳዊ መረዳት አግኝተን በጌታ ማደግ መቻላችን የእግዚአብሔር ቅዱስ ጸጋ እንጂ የሰው ብልሃት እንዳልነበረ ተረድቼአለሁ፤ ይህንንም እመሰክራለሁ።

አቤቱ፣ በዓመታት መካከል ሥራህን ፈጽም፣ በዓመታት መካከል ትታወቅ፣ በመዓት ጊዜ ምሕረትን አስብ። (ትንቢተ ዕንባቆም 3፡2) 

ወንድም እንዳልካቸው ኪዳነ ወልድና ባለቤቱ እህት መሠረት ጽጌ፣ “የአዲስ ኪዳን በግ ቅዱስ ካህን/የጽድቅ ንጉሥ ያለም መድኅን/የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ/ቅዱስ ካህን አለን በላይ በሰማይ” እና “የጽዮን ግርማዋ የሱስ ክርስቶስ ነው/ባባቱ ቀኝ ያለው በላይ ያለው/ የንጋቱ ኰከብ ደምቆ የሚታየው/እኛ የምናመልከው ጌታችን እርሱ ታላቅ ነው” የተሰኙ ውድ መዝሙራትን የዘመሩ ናቸው። ይህን ምስክነታቸውን ከሦስት ዓመት በፊት በዚሁ ድረ ገጽ ላይ አትመነው ነበር።

ቄስ ኢተፋ ጎበና በወንጌል ምክንያት በደርግ ዘመን ታሥረው ብዙ ከማቀቁት መካከል አንደኛው ሲሆኑ የወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ፕሬዚደነት የነበሩና ዛሬም ጌታን እያገለገሉት ያሉ የቤተ ክርስቲያን መሪ ናቸው።                                   2/15/2010