የስኳር በሽታ በተለይም ለኢትዮጵያውያን

በወርቁ አበበ

DrWorkuበየአመቱ ህዳር 5 (ኖቬምበር 14) የአለም የስኳር በሽታ መታሰቢያ ቀን ተብሎ በአለም የጤና ጥበቃ ድርጅትና በአለም የስኳር በሽታ ማህበር ከተወሰነ ስንብቷል። ዋና አላማው የበሸታውን በአሳሳቢ ደረጃ መስፋፋትና አሰከፊነት ለህዝብ በማሳወቅ ወይም በማስታወሰ የመከላከያ እርምጃ እንዲወሰድ ለማበረታታት ነው። ይህ ጽሁፍ ለዚህ አላማ አሰተዋጽዎ ለማድረግ ተብሎ ቀደም ብሎ ለአገር ተቆርቋሪ ለሆነ የሬድዮ ጣቢያ ለስርጭት የቀረበ ነው።

በአለም ዙሪያ ባሳሳቢ ሁኔታ በመጨመር ላይ ካሉ በሽታዎች መካከል አንዱ የስኳር በሽታ መሆኑ ተመዝግቧል። ለምሳሌ ያህል የአለም የጤና ጥበቃ ድርጅት በአለም ደረጃ የዚህ በሽታ ሰለባዎች እ.አ.አ በ1985 ዓ.ም 30 ሚሊዮን መሆናቸውን በመግለፅ በ1995 ዓ.ም 135 ሚሊዮን ፤ በ2000 ዓ. ም ደግሞ 171 ሚሊዮን መድረሳቸውን አሳውቋል። በመጪው 2030 ዓ.ም ይህ ቁጥር እጥፍ ሊደርስ  እንደሚችልም ተተንብዮአል። በአለም ደረጃ የበሽታው መጠን ባጭሩ ይህንን የመሰለ ሲሆን ፤ ችግሩን በዝርዝር ስናይ የበሽተኞቹ ቁጥር ከቦታ ቦታ እንደሚለያይ መገንዘብ ይቻላል።  ሆኖም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ በአገር ደረጃ ምን ያህል የስኳር በሽተኞች እንዳሉ በውል አይታወቅም። ነገር ግን በአንዳንድ በተወሰኑ ቦታዎች በተካሄዱ አነስተኛ ጥናቶችና በሀኪም ቤት የምዝገባ ሰነዶች መሠረት ከአስር ዓመታት በፊት ገደማ ጀምሮ ከመቶ ዘጠኝ እጅ (9%) ሊደርሱ የሚችሉ የስኳር በሽተኞች እንደነበሩ ተገልጿል። በየሀኪም ቤቱ በየቀኑ ከሚመረመሩ በሽተኞች አኳያ ሲታይ በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ከዚህ ቁጥር የሚበልጡ እንጂ ያላነሱ በሽተኞች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገመታል። ከኢትዮጵያም ውጭ ቢሆን በቅርቡ በእስራኤል አገር የቤተ እስራኤል ወገኖቻችንን አስመልክቶ የተደረገው ጥናት ይህን የበሽተኞች ቁጥር ብዛት የሚያጠናክር ነው። ስለዚህ ይህንን አሳሳቢ የሰኳር በሽታ ሁኔታ ተገንዝቦ በሌሎች በብዙ አገሮች እንደሚደረገው በሽታውን በኢትዮጵያም ውስጥ በተቻለ መጠን ለመቆጣጠር አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን መውሰድ የግድ ይላል።

ለመሆኑ የስኳር በሽታ ምንድን ነው ?

ይህ በሽታ ስኳር ወይም ጉሉኮስ በደም ውስጥ ከመጠን በላይ ሆኖ ሲገኝ የሚከሰት ነው። የዚህ ችግር መንስሄው ከቆሽት የሚመነጨው ኢንሱሊን የተባለው ሆርሞን (ንጥረ ነገር) ጭራሽ መጥፋቱ ወይም መጠኑ መቀነሱ፤ ወይም ደግሞ የሚያከናውነው ሥራ ሲሰናከል ነው። ጉሉኮስ ከደም ወደ የአካላት ሕዋሳት ውስጥ በመግባት ቢያንስ እንደ ነዳጅ ሆኖ ለሰውነት የሚያገለግል ንጥረ ነገር ወይም የምግብ አይነት ሲሆን፤ ይህንን ለማድረግ የኢንሱሊን መኖር ወይም ኢንሱሊኑ ሥራውን በሚገባ ማካሄድ አለበት። ጉሉኮስ ከተለያዩ የምግብ ዓይነቶች (ለምሳሌ ያህል እንደ ስንዴ ዳቦ፤ እንጀራ፤ ድንች፤ ስኳርነት ያላቸው መጠጦች የመሣሠሉ) ሊገኝ የሚችል አስፈላጊ የሆነ የምግብ ክፍል ነው። መጠኑ በደም ውስጥ ከልክ በላይ እስካልሆነ ድረስ ጎጂነት የለውም። ምግብ ከተወሰደ በኋላ ጉሉኮስ በደም ውስጥ በርከት ብሎ በመገኘት ቆሽት ኢንሱሊንን እንዲያመነጭ አድርጎ ጉሉኮሱ ከጥቅም ላይ እንዲውል ያደርጋል። ሆኖም በኢንሱሊን እጥረት ወይም የሥራ መሰናከል የተነሳ ጉሉኮስ በደም ውስጥ በብዛት ከተገኘ በሰውነት ላይ የተለያዩ ጉዳቶችን በማምጣት መታመምን ያስከትላል። ስለሆነም የጉሉኮስን የደም መጠን ማስተካከሉ ሕመምን የሚቀንስ ብቻ ሳይሆን በሕይወትም ለመቆየት የሚረዳ ነው።

የተለያዩ የስኳር በሽታ አይነቶች አሉ?

መነሻቸውን አስመልክቶ የተለያዩ የስኳር በሽታዎች መኖራቸው የተመዘገበ ሲሆን፤ ዋናዎቹ ሦስት ናቸው። እነሱም አይነት አንድ፤ አይነት ሁለት እና በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የስኳር በሽታዎች ናቸው።

አይነት አንድ፡ የስኳር በሽታ በቆሽት መጎዳት የተነሳ ኢንሱሊን በሰውነት ውስጥ እንደሚገባው መኖር ባለመቻሉ የሚከሰት ሲሆን ብዙውን ጊዜ ከልጅነት ጀምሮ የሚኖር በሽታ ነው። ከመቶ ውስጥ ከ5 እስከ 10 እጅ የሆኑ የስኳር በሽተኞች በዚህ አይነቱ ሕመም የሚሰቃዩ ናቸው። እርግጠኛም ባይኮንም ይህ የስኳር በሽታ በዘር ሊተላለፍ የሚችል ለመሆኑ አንዳንድ ፍንጮች አሉ። የስኳር በሽታ አይነት ሁለት ከጊዜ በኋላ የሚከሰት ሆኖ ሣለ ከቆሽት የሚመነጨው ኢንሱሊን ሥራውን እንደሚገባ ሊሠራ ባለመቻሉና ቀጥሎም መጠኑ በማነሱ ጭምር የሚመጣ ሕመም ነው። ከመቶ ውስጥ ከ90 እስከ 95 እጅ የሆኑ የስኳር ሕሙማን በዚህ አይነቱ የስኳር በሽታ የተያዙ ናቸው። ይህም የስኳር በሽታ በዘር የመተላለፍ ፀባይ አለው። በእርግዝና ወቅት የሚከሰተው የስኳር በሽታ ደግሞ እስከ 7 እጅ (7%) የሆኑ ነፍሰጡሮችን የሚያጋጥም ነው። ይህ ሕመም በእርግዝና ጊዜ ተደጋግሞ የመታየት ፀባይ ሲኖረው በዘር ስለመተላለፉ ጉዳይ በውል የታወቀ አይደለም። ሆኖም ሕመሙ በእርግዝና ወቅት ያጋጠማቸው ነብሰጡሮች ከወለዱ በኋላ አይነት ሁለት የስኳር በሽታ ሊይዛቸው እንደሚችል መረጃዎች ያመለክታሉ።

የስኳር በሽታ ምልክቶች ምንድን ናቸው?

ሁሉም የስኳር በሽታ አይነቶች ተወራራሽ የሆኑ ጸባዮችን የሚያሳዩ ቢሆንም እያንዳንዳቸው የራሳቸው የሆኑ ልዩ የመለያ ምልክቶች አሏቸው። ከዚህም ሌላ የእያንዳንዱ የሕመም ምልክቶች እንደ በሽተኛው ሁኔታ ሊለያዩ ይችላሉ። ዋናዎቹ የአይነት አንድ የስኳር በሽታ ምልክቶች የሚቀጥሉት ናቸው ።  

  • አዘውትሮ መሽናት
  • በብዛት ውሃ መጠጣት
  • የአፍ መድረቅ
  • በብዛት መራብ
  • በብዛት ክብደት መቀነስ (መክሳት)
  • አዘውትሮ በሆነው ባልሆነው መበሳጨት
  • የድካም ስሜት
  • የአይን ግርዶሽ

እነዚህ ምልክቶች በድንገት ወይም ጊዜ ሳይወስዱ ሊከሰቱ የሚችሉ ይሆናሉ። ቀጥሎ የሰፈሩት የአይነት ሁለት የስኳር በሽታ ዋነኛ ምልክቶች ናቸው። ከላይ የሰፈሩት የአይነት አንድ ምልክቶች ሁሉም ወይም በከፊል  ለዚህም አይነት የሚያገለግሉ ናቸው። ሆኖም ግን በአይነት ሁለት በሽታ እነዚህ ምልክቶች የሚታዩት መለስ ባለ ሁኔታ ነው።

  • በተደጋጋሚ ተላላፊ በሆኑ የበሽታ አይነቶች መያዝ
  • ከቁስል በቶሎ ለመዳን አለመቻል
  • እግርና እጅ ከሚያቃጠልና ከሚያደንዘዝ ስሜት መሰቃየት
  • በተደጋጋሚ በቆዳ፤ በአፍ (ወይም በጥርስ) እና በኩላሊት በሽታዎች መያዝ

ሌላ መጠቀስ ያለበት ጉዳይ ብዙ የሆኑ የአይነት ሁለት የስኳር በሽተኞች ከላይ የተጠቀሱትን ምልክቶች በግልጽ ሳያሳዩ ለረጅም ጊዜ ሊቆዩ እንደሚችሉ ነው። የደማቸው የስኳር መጠን ከፍ ያለ ቢሆንም እነዚህ በሽተኞች መያዛቸውን ሳያውቁ በበሽታው ሊጎዱ የሚችሉ ናቸው።

በእርግዝና ወቅት የሚፈጠረው የስኳር ሕመም ብዙውን ጊዜ ከሁለተኛው አይነት የስኳር በሽታ ጋር ተቀራራቢ የሆኑ ምልክቶችን የሚያሳይ ነው። ከዚህ ጋር በመገናዘብ በሽተኞቹ በብዛት መጠማትን፤ ሽንት መሽናትንና መራብን የመሳሰሉ ምልክቶችን ያሳያሉ።  ይህ ሕመም በትክክል መኖሩ የሚታወቀው ግን የደምና የሽንት ስኳር (የጉሉኮስ) መጠን ምርመራ በሚደረግበት ጊዜ ነው።

የስኳር በሽታ ጥንቃቄ ሳይደረግለት እንዲቀጥል ከተደረገ ምን ችግሮችን ያስከትላል?

ይህ ሁኔታ እንዲቀጥል ከተደረገ በሽታው በተለያዩ የሰውነት አካላት ላይ የተለያዩ ጉዳቶችን በማምጣት ከፍተኛ የጤንነት መጓደልን ያስከትላል። የረጅም ጊዜ ዋነኛ ችግሮች ተብለው የተመደቡት ቀጥሎ የተዘረዘሩት ናቸው።

የደም መዘዋወሪያ ቧንቧን በመጉዳት የደም ብዛት ወይም ግፊት የመጨመር በሽታን ማምጣት

  • የልብ በሽታ መከሰት
  • የአይን በሽታን ብሎም መታወርን ማስከተል
  • የኩላሊት በሽታን ማምጣት ወይም ማባባሰ
  • የስራስር (ነርቭ) በሽታና ከዚህ ጋር የተያያዙ ችግሮች ማስከተል
  • የደም መዘዋወርን ችግር በእግርና በሌሎች አካላት ውስጥ ፈጥሮ የተያያዙ ጉዳቶችን ማስከተል፤ በተለይም  

ደግሞ ለእግር መታመምና መቆረጥ ምክንያት መሆን

  • ከመድረቅ አንስቶ የተለያዩ የቆዳ ህመሞችን መፍጠር
  • በአንጎል ውስጥ ደም የመፍሰስ ወይም የመርጋት ችግር መፍጠር

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት የረጅም ጊዜ ችግሮች በተለይ ሊኖሩ የሚችሉት አይነት አንድና ሁለት የስኳር በሽታ ባላቸው ሕመምተኞች ላይ ነው። ሆኖም ግን ችግሮቹ በሁሉም በሽተኞች በአንድ ጊዜ በእኩል ደረጃ ላይታዩ ይችላሉ። በነዚህ ሕመሞች የተነሳ የስኳር በሽተኞች ከጤነኞች ሰዎች ጋር ሲነጻጸሩ የመሞት እድላቸው ቢያንስ እጥፍ እንደሚሆን ተመዝግቧል።

በእርግዝና ጊዜ የሚፈጠረው የስኳር ሕመም ጥንቃቄ ሳይወሰድ እንዲቀጥል ከተደረገ ማሕፀን ውስጥ ያለው ልጅ ከመጠን በላይ የመወፈር/የማደግ እድል ይኖረዋል። በዚህም ምክንያት በወሊድ ወቅት ህጻኑ ትልቅ በመሆኑ ከማሕፀን የመውጣት ችግር ያጋጥማል። ብልሃት ሳይታከልበት በግድ እንዲወለድ ከተደረገ በህጻኑ ሰውነትና በእናቱም ማሕፀን ላይ ጉዳት ሊደርስ ይችላል። የዚህ ዓይነቱን ችግር ለማቃለል በሆስፒታል አካባቢ ብዙውን ጊዜ ልጆች በቀዶ ጥገና እንዲወለዱ ይደረጋሉ። ለወደፊቱም ቢሆን የዚህ አይነቱ ችግር ያላቸው እናቶችም ሆኑ ልጆች (ሁሉም ባይሆኑ) ቢያንስ በአይነት ሁለት የስኳር በሽታ ሊታመሙ ይችላሉ።

ለስኳር በሽታ መከሰት ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ጠንቆች አሉ?

አይነት አንድን በተመለከተ የተረጋገጠ ቀጥተኛ የሆነ ጠቋሚ ምክንያት የለም። ነገር ግን በተዘዋዋሪ ከዚህ ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ ጥቂት አመልካች ነገሮች አሉ።  እነርሱም፦

  • በቤተሰብ ውስጥ ሕመሙ ቀደም ብሎ መታየቱ
  • ለአንዳንድ የጀርም አይነቶች (ቫይረስ) መጋለጥ
  • በትውልድ ጊዜ ልጆች ለአንዳንድ የበሽታ አይነቶች መጋለጥ ናቸው ።

አይነት ሁለትን አስመልክቶ የአንዳንድ ሰዎች በበሽታው የመያዝ ወይም ያለመያዝ ምክንያቶች በግልፅ የታወቁ ባይሆኑም፤ ቀጥሎ የሰፈሩት ጉዳዮች ብዙ ሰዎች በሽታውን በግልፅ ለማሳየታቸው በምክንያትነት ሊቀርቡ የሚችሉ ናቸው።

  • ሕመሙ በቤተሰብ ውስጥ መኖር
  • የሰውነት እንቅስቃሴ (ስፖርት) አለማድረግ
  • ውፋሬ ወይም ክብደት ከሚገባ በላይ መጨመር     
  • በእድሜ መግፋት
  • የደም ስኳር (ጉሉኮስ)፤ የመጥፎ ኮሌስትሮልና የሌላ የመጥፎ ቅባት አይነት መጠን መጨመር
  • በርግዝና ወቅት በስኳር በሽታ መታመም
  • ክብደቱ ከፍተኛ (ከ4 ኪሎ በላይ) የሆነ ልጅ መውለድ
  • የደም ብዛት ወይም ግፊት ከመጠን በላይ ሆኖ መገኘት
  • የልብ በሽታ መኖር

በእርግዝና ጊዜ የሚታየው የስኳር በሸታ ብዙውን ጊዜ ከታች ከተገለፁት ጠቋሚ ሁኔታዎች ጋር የተያያዘ ለመሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ።

  • ነፍሰጡሯ ከ25 ዓመት በላይ እድሜ ያላት
  • በቤተሰብ ውስጥ አይነት ሁለት የስኳር በሽታ መኖሩ ወይም ወደዚያ የሚያመራ ሁኔታ መፈጠሩ
  • ቀደም ብሎ በእርግዝና ወቅት ለተመሳሳይ ችግር መጋለጥ
  • ከፍተኛ የሆነ የሰውነት ውፋሬ ወይም ክብደት መኖር

የስኳር በሽታንና ጠንቆቹን እንዴት ለመከላከል ወይም እንዳይባባሱ ማድረግ ይቻላል?

የትኛውም አይነት የስኳር በሽታ ቢሆን የሕመሙ ምልክቶች ከታዩ ወዲያውኑ የሕክምና አዋቂን ማየት አስፈላጊ ነው። ስለዚህ ምልክቶቹን ማስተዋሉ ጠቃሚ ነው። ነገር ግን ምልክቶቹ በግልፅ ሳይታዩ፤ በተለይ አይነት ሁለትን የስኳር በሽታ አስመልክቶ፤ ለረጅም ጊዜ ህመሙ ሊኖር ስለሚችል አልፎ አልፎ የጥንቃቄ ምርመራ ማድረግ መለመድ ያለበት ጉዳይ ነው። ይሄ እርምጃ በተለይ አሰፈላጊነቱ ቀደም ብሎ የተጠቀሱት ጠቋሚ ነገሮች በሚኖርበት ወቅት ነው። እነዚህ ጥንቃቄዎች በጊዜ ከተወሰዱ እንደ በሽታው አይነት ሕመሙን ለመከላከል፤ ለማዘግየት ወይም ደግሞ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የሚቻል ነው። ይህ ከተደረገ ሕመምተኛውን መርዳት ብቻ ሳይሆን በበሽታው ጠንቅ ለሕክምና ተብሎ ሊወጣ የሚችለውን ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ለመቀነስ ያስችላል።

አንዳንድ የምርምር ጥረቶች እየተካሄዱ እንዳሉ ቢታወቅም አይነት አንድን የስኳር በሽታ ለመከላከል እስካሁን የሚቻል አልሆነም። ሆኖም በመድኃኒትና (ኢንሱሊን) ሌሎች ለጤንነት የሚበጁ እርምጃዎችን በመውሰድ በሽታው የሚያስከትለውን የአካል ጉዳት መቀነስና እድሜን ማራዘም ይቻላል። በአንፃሩ አይነት ሁለት በሽታን በጊዜ አስፈላጊ የሆኑ ለጤና ጠቀሜታ ያላቸውን እርምጃዎች በመውሰድ በሽታውን መከላከል ወይም ማዘግየት ይቻላል ። ነገር ግን እነዚህ እርምጃዎች የሚጠበቀውን ውጤት ለመስጠት ብቁ ሆነው ካልተገኙ በሽተኛው በመድኃኒቶችም ጭምር ሊታገዝ ይገባዋል። በእርግዝና ወቅት የሚከሰተውን የስኳር በሽታ መከላከል የሚቻል ቢመስልም የዚህ እርምጃ አስተማማኝነት አጠራጣሪ ነው። ስለሆነም ብዙውን ጊዜ መድኃኒቶችና ሌሎች ለጤና ጠቃሚ የሆኑ ነገሮች አብረው መወሰድ ይኖርባቸዋል።

ቀጥሎ የተመለከቱት ለሶስቱም የስኳር በሽታ አይነቶች መደረግ ያለባቸው መሠረታዊ ጠቃሚ ነገሮች ናቸው።

  • የደምን የስኳር መጠን መከታተል። ይህ የበሽታውን ሁኔታ ለማወቅ የሚረዳ መሠረታዊ መረጃ ሰጪ ተግባር ነው ። ቀጥሎ ሊወሰድ የሚገባውን እርምጃ ጠቋሚ ሊሆን ይችላል።
  • ጤነኛ የሆነ ምግብ መመገብ። ይህ ምግብ አትክልትና ፍራፍሬ በብዛት የያዘ ሆኖ ፤ ስኳርነትና ቅባት ነክ የሆኑ ነገሮች ያልበዛበት ቢሆን ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነው። ሆኖም እንደ አሣ ዘይት፤ ተልባ፤ የወይራ ዘይት የመሳሰሉት በዚህ የሚጠቃለሉ እንዳልሆኑ መጠቀሰ አለበት።  ተጣርተው ከተፈጩ የእህል ዘሮች ይልቅ ገለባማ የሆኑት ለምግብነት ይመረጣሉ። በማዕድ ወቅት ምግብም ሲወሰድ በአንዴ ብዙ ከመመገብ ይልቅ ከፋፍሎ በየጊዜው መመገቡ የተሻለ ውጤት አለው።
  • ተገቢ በሆነ የሰውነት ክብደት ወይም ውፋሬ ላይ መገኘት
  • አዘውትሮ የሰውነት እንቅስቃሴ (ስፖርት) መሥራት። ለምሳሌ ያህል በየቀኑ ግማሽ ስዓት በመውሰድ በሳምንት ውስጥ ለአምስት ቀናት ያህል መሮጥ
  • ሲጋራ ወይም ትንባሆ ነክ የሆኑ ነገሮችን አለመጠቀም
  • አልኮል መጠጦችን መጠጣት ማቆም ወይም መቀነስ
  • ለተላላፊ በሽታ መከላከያ ተብለው የተሰጡትን ክትባቶች መውሰድ
  • ጨው በብዛት አለመጠቀም
  • በሰውነት ላይ ጭንቀት የሚያመጡ ነገሮችን በተቻለ መጠን መቀነስ ወይም ማስወገድ፤ በቂ የሆነ እቅልፍ ማግኘት
  • የእግርና የጥርስን ጤንነት መንከባከብ
  • ከሁሉም በላይ ስለ ጤንነት ሁኔታ አጠቃላይ ግንዛቤ ለማግኘት በየጊዜው በሕክምና አዋቂ መመርመር። ከላይ እንደተባለው ይህ ድርጊት ቀደም ብሎ አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን ለመውሰድ ይጠቅማል። ምርምር የሚደረግባቸው ነገሮች ብዛትና አይነት እንደ በሽታውና በሽተኛው ሁኔታ የሚለያዩ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ የደምን ስኳር (ጉሉኮስን)፤ የኮሌስትሮልን፤ የደም ብዛት (ግፊት) መጠንና የአይንን ጤንነት፤ የልብን አሰራር፤ የኩላሊትን ጤንነትና የእግርን ደህንነት የሚመለከት ሊሆን የሚችል ነው።

የስኳር በሽታን በምግብ፤ በሰውነት እንቅስቃሴ (ስፖርት) እና በሌሎች ለጤንነት ጠቃሚ በሆኑ ነገሮች ለመቆጣጠር ካልተቻለ ሕመምተኛው መድኅኒት መውሰድ አለበት። የሚወሰደው መድኅኒት መጠንና አይነት እንደ በሽታውና በሽተኛው ሁኔታ የሚለያዩ ሲሆን ቢያንስ ቀጥሎ የተጠቀሱት መድኅኒቶች መሠረታዊ ናቸው። 

  • ለአይነት አንድና ለነፍሰጡር የስኳር በሽታ በመርፌ መልክ የሚወሰዱ የተለያዩ የኢንሱሊን ዝግጅቶች
  • ለአይነት ሁለት የስኳር በሽታ በአፍ የሚወሰዱ የተለያዩ መድኅኒቶች ለብቻቸው ወይም ከኢንሱሊን ጋር የሚወሰዱ ናቸው።

እነዚህ መድኅኒቶች የበሽተኛውን የደም ስኳር (ጉሉኮስ) መጠን ለማስተካከል ተብለው የሚወሰዱ ናቸው። ህመምተኛው ሌሎች ተጓዳኝ በሽታዎች ካሉት (ለምሳሌ እንደ ደም ብዛት/ ግፊት፤ የኩላሊት ሕመም ፤ የልብ ሕመም፤ የኮሌስትሮል መብዛት የመሳሰሉ) ለነዚህም የሚሆኑ ተጨማሪ መድኅኒቶች እንዲወስዱ ይታዘዛል። ብዙውን ጊዜ አንዳንዶቹ መድኅኒቶች ተጓዳኝ የሆኑ ሕመሞች ከመታየታቸው በፊት ለመከላከል ተብለው የሚወሰዱ ናቸው። መድኅኒቶችን ከመጠቀም ውጭ እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎች የሕክምና አገልግሎቶችም ለስኳር ሕመምተኛው የሚሰጡበት ጊዜ አለ።

የደም ስኳር (ጉሉኮስ) መጠንን ለመቀነስ (ለማስተካከል) ተብለው በሐኪም የሚታዘዙ መድኅኒቶች አንዳንዴ ስኳሩን ከሚፈለገው በላይ ሊቀበሉ ይችላሉ። ብዙውን ጊዜ ይህ የሚሆነው መድኅኒቶቹ ከመጠን በላይ ከተወሰዱ፤ ምግብ ሳይበላ ሆድ ባዶ ከሆነና በፍጥነት የሰውነት እንቅስቃሴ (ስፖርት) በሚሰራበት ወቅት ነው። በዚህ ጊዜ ሕመምተኛው ያልበዋል፤ ይርበዋል፤ ይንቀጠቀጣል፤ ይደክመዋል፤ ያዞረዋል፤ ልቡ በብዛት ይመታል፤ ራስምታት ይይዘዋል ፤ አይኑን ይጋርደዋል ፤ ያበሳጨዋል፤ ንግግሩን ይይዘዋል፤ አዙሮት ሊወድቅ ይችላል። የዚህ አይነት ስሜቶች ሲጀምሩ ቶሎ ብሎ ስኳርነት ያላቸው ለስላሳ መጠጦች (ምሳሌ፤ ስኳርነት ያላቸው የአትክልት ጭማቂዎች፤ ኮካ ኮላ የመሳሰሉ) ወይም የሚበሉ ነገሮች (እንደ ከረሜላና ስኳር ራሱን የመሳሰሉ) መውሰድ አለባቸው። ለዚህ አይነቱ ችግር መጠባበቂያ እነዚህን ነገሮች በቅርብ ማስቀመጡ ጠቃሚ ነው።

በተቃራኒው የስኳር በሽታ ያላቸው ሰዎች የሚገባውን መድኅኒት ሳይወስዱ ስኳርነት ያለው ምግብ/መጠጥ በብዛት ከወሰዱ ወይንም ደግሞ ለአንዳንድ ለተለዩ የበሽታ አይነቶች ከተጋለጡ የሰውነታቸው የስኳር (ጉሉኮስ) መጠን በጣም ክፍ ሊል ይችላል። በዚህን ጊዜ፤ ሕመምተኞቹ የማቅለሽለሽ፤ የመበሳጨት፤ የመራብ፤ አዘውትሮ የመሽናት፤ የመጠማት፤ የመድከም፤ ያለማተኮር፤ የአይን ግርዶሽና የአፍ መድረቅ ስሜት ወይም ችግር ይኖራቸዋል። ለዚህ ችግር መፍትሄ ሊሆን የሚችለው ሳይዘገዩ አስፈላጊውን መድኅኒት መውሰድና ምግብን/መጠንን ማስተካከል ነው።

አንዳንድ የስኳር በሽታ ሕመምተኞች፤ በተለይ አይነት አንድ በሽታ ያለባቸው፤ በሰውነታቸው ውስጥ በኢንሱሊን እጥረት ወይም እጦት ምክንያት ጉሉኮስን ከመጠቀም ይልቅ ሰውነታቸው ሞራ (ፋት) ነክ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን ለመጠቀም ይገደዳል። ይህ ሁኔታ ለሰውነት ጉጂ ሊሆኑ የሚችሉ ኬሚካሎች (ማለት፡ “ኬቶንስ” የተባሉ) በብዛት እንዲፈጠሩ በማድረግ የሚከተሉትን የጤንነት ችግሮች ሊያስከትል ይችላል።

  • የሆድ ህመም
  • ማቅለሽለሽና ብሎም ማስታወክ
  • ክብደት መቀነስ ወይም መክሳት
  • ድካም
  • ትኩሳት
  • ትንፋሽ ወደ ሽቶ መሳይ ነገር መቀየር

በኬቶንስ ከመጠን በላይ በሰውነት ውሰጥ መከማቸት የተነሳ እነዚህ ችግሮች እየጨመሩ ከመጡ በአፋጣኝ የሕክምና አዋቂን ማየት አሰፈላጊ ነው።

ማጠቃለያ:- እስካሁን እንደተገለፀው የስኳር በሽታ የብዙ ሰዎች ችግር እየሆነ እንደ መጣ ታምኗል። የዚህ በሽታ ሕመምተኛ ሆኖ መኖር ቀላል አይደለም፤ በተለይም አይነት አንድ የሰኳር በሽታ ላለባቸው። ከማንም በላይ በሽታው የሚመለከተው ሕመምተኛውን እራሱን መሆኑ ታውቆ ሃላፊነቱን በመውሰድ በተቻለ መጠን በተሻለ ጤንነት ለመኖር የሚቻለውን ነገር ሁሉ ማድረግ አለበት። በዚህ የጽሑፍ ዝግጅት ለዚህ ሃላፊነት የሚረዱ ዋና ዋና መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች ተገልፀዋል። ሕመምተኛውም ሆነ የሚያክመው የሕክምና አዋቂ ከሚያደርጉት ጥረቶች በተጨማሪ ችግሩ በዚህ ብቻ ውሱን ሰላልሆነ የሌሎችም ትብብርና ድጋፍ የሚያስፈልገው ነው። ከሌሎች አገሮች ልምድ ለማወቅ እንደሚቻለው በዚህ ተግባር ላይ ያተኮሩ የድጋፍ ወይም የመረዳጃ ድርጅቶች ቢቋቋሙ በተቀናጀና ጠቀም ባለ መልክ ለሕመምተኞች ጠቃሚ አገልግሎት ለመስጠት ይቻላል ። ጉዳዩ ሰፋ ተደርጎ ሲታይ የስኳር በሽታ የግለሰቦች የጤንነት ቀውስ ብቻ ሳይሆን ብዙዎችን ሊነካ የሚችል የማህበራዊና የኢኮኖሚም ችግር ጭምር መሆኑ መታወስ ይኖርበታል። በዚህ መሰረት ሰፊው የሕብረተሰብ ክፍል የስኳር በሽታን ችግር ለመቆጣጠር ድርሻ ሊኖረው እንደሚገባና እንደሚችልም መጠቆም አለበት።

ዶክተር ወርቁ አበበ የፋርማሲና የፋርማኮሎጂ ባለሞያና ፕሮፌሰር ሲሆኑ በስኳር በሽታ፤ በደም ብዛት፤ በጥርስ በሽታና በባህል መድኅኒቶች ላይ መሰረታዊ ምርምሮችንና በርከት ያሉ ሳይንሳዊ ጽሑፎችን ያሳተሙ ምሁር ናቸዉ። ለወገኖቻቸው ይጠቅማል ብለው ይህን ጠቃሚ ጽሑፍ አዘጋጅተው እንድናትም ስለ ፈቀዱልን በአንባቢዎቻችን ስም እግዚአብሔር ይባርክዎት እንላለን። (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)