ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው - ክፍል2
በመጋቢ ገ/እግዚአብሄር ካሕሳይ

ባለፈው ጊዜ ደቀ መዛሙርት ለማፍራት 1. የጌታ ትእዛዝ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል 2. ራሳችን የጌታ ደቀ መዛሙርት ልንሆን ያስፈልጋል 3. ወደ አሕዛብ ሁሉ መሄድ ያስፈልጋል ብለናል። ቀሪውን ዛሬ እንመለከታለን፦

4. ደቀ መዛሙርት ለማፍራት ያመኑትን በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ማጥመቅ ያስፈልጋል። “በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋችሁ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” (ማቴዎስ 28፡ 19-20) በአሁኑ ዘመን ስለ ጥምቀት በተለያዩ የእምነት ክፍሎች የተለያየ መረዳት ቢኖርም ጥምቀት ከጌታ ትእዛዞች አንዱ ነው። በሌላ ሥፍራም ጌታ “ያመነ የተጠመቀም ይድናል፣ ያላመነ ግን ይፈረድበታል” ሲል አስተምሯል። (ማርቆስ 16፡ 16)

የአዲስ ኪዳን አብያተ ክርስቲያናትም ጌታ ባዘዘው መሠረት ያመኑትን ያጠምቁ ነበር (የሐዋርያት ሥራ 2፡ 41)። ዛሬም ቢሆን ያመኑት ጌታ ባዘዘው መሠረት በአብና በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቅ አለባቸው፣ ምክንያቱም ጥምቀት ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር የተሰጠው የኢየሱስ ክርስቶስ ትእዛዝ ነውና።

5. ደቀ መዛሙርት ለማፍራት ጌታ ያዘዘውን ሁሉ ማስተማር ያስፈልጋል። “ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” (ማቴዎስ 18፡ 19-20) ደቀ መዛሙርት ለማፍራት መሄድ፣ መስበክ፣ ማመን፣ ማጥመቅ ብቻ በቂ አይደለም። አንድ ሰው ወንጌልን ሰምቶ ንስሓ ከገባና በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምኖ ከተጠመቀ በኋላ ጌታ ያዘዘውን ሁሉ እንዲጠብቅ መማር አለበት።

በዘመናችን ወንጌል በመስበክ የተሰማሩ ብዙ ወገኖች አሉ፤ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ዋና ተግባራቸውን ወንጌልን መስበክ ብቻ አድርገዋል። በስብከት የሚያገለግሉ አገልጋዮች አሏቸው። በማስተማር የሚያገለግሉ አስተማሪዎች ግን የሏቸውም፤ ቢኖሯቸውም የታወቀ አይደለም። በሥርዓትና በተያያዘ መልኩ አያስተምሩም፤ በተገኘው ቀዳዳ ከስብከት ያልተለየ ትምህርት ብቻ መስጠት ነው የሚችሉ። ጌታ ግን ያዘዝኋችሁን በከፊል ሳይሆን ሁሉን እንዲያውቁ፣ አውቀው እንዲጠብቁ፣ እንዲታዘዙና ሥራ ላይ እንዲያውሉት አስተምሯቸው  ነው ያለው።

ጌታ ያዘዘውን ሁሉ አውቆ ማስተማር ቀላል አይደለም። መጀመሪያ ራሳችን ተማሪዎች ሆነን በጌታ እግር ሥር ሆነን ጌታ ያዘዘውን መማርና በተግባር ማዋል ይጠበቅብናል። ይህን ስንል ሁላችንም ሥራችንን ትተን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት መግባት አለብን ማለት አይደለም። ጌታ የሰጠንን ሥራችንን እየሠራንም ቢሆን ለጌታ ጊዜ መስጠት አለብን ማለት እንጂ።

ሰውን እንዲያውቅ ማስተማር በራሱ ቀላል ተግባር አይደለም። ጌታ ግን ያዘዘን እንዲያውቁ ብቻ ማስተማር ሳይሆን አውቀው እንዲታዘዙ አስተምሩ ብሎ ነው። ማወቅ ብቻ በቂ አይደለም ማለት ነው። ሰው አውቆ ሲታዘዝ ነው ደቀ መዝሙር የሚሆነው። አውቆ አለመታዘዝ ከአለማወቅ የባሰ ነው። በዚህ ዘመን በአንዳንድ ሥፍራ መታዘዝ የጐደለው ዕውቀት ሲበዛ፣ በሌላ ሥፍራ ደግሞ ዕውቀት የሌለው መታዘዝ በዝቶ ይታያል። ጌታ ያዘዘው ግን ትዕዛዛቱን ሁሉ መሠረት ያደረገ መታዘዝን ነው። የጌታ ደቀ መዛሙርት ለማፍራት ጌታ ያዘዘውን ሁሉ እንዲታዘዙና እንዲጠብቁ ማስተማር ያስፈልጋል።

6. ደቀ መዛሙርት ለማድረግ ስንሰማራ ጌታ ሁልጊዜ ከእኛ ጋር እንደ ሆነ ማወቅ ያስፈልጋል። “እነሆ እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴዎስ 28፡ 20) የጌታ እውነተኛ ደቀ መዝሙር መሆን ቀላል ነገር አይደለም። በእርኩሰት በተሞላች ዓለም፣ ደካማ የሆነ ሥጋ ተሸክሞ የጌታ ኢየሱስ እውነተኛ ደቀ መዝሙር መሆን ከባድ ነው። የጌታ ደቀ መዝሙር ከመሆን አልፎ እውነተኛ የጌታ ደቀ መዛሙርት ማፍራት እጅግ በጣም ከባድ ነው። ታላቅ መስዋእትነት ብዙ ፍቅርና ትዕግስት የሚጠይቅ ኃላፊነት ነው። ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ መስበክ፣ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ማጥመቅ ጌታ ያዘዘውን ሁሉ እንዲታዘዙና እንዲጠብቁ ማስተማር ቀላል ኃላፊነት አይደለም።

ጌታም የሰጠንን ኃላፊነት ክብደት ስላወቀና በራሳችንም ልንወጣው እንደማንችል ስለ ተገነዘበ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ በማለት ታላቅ ተስፋ ሰጥቶናል። ጌታ ሊረዳን፣ ሊመራንና ሊያስችለን ሁልጊዜ ከእኛ ጋር ነው። በእርሱ ታምነን፣ እርሱን ሰምተን፣ እርሱን ታዝዘን የምንወጣና የምንገባ ከሆንን ያዘዘንን ለመፈጸም ያስችለናል። የእርሱ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት እንሆናለን። በእውነት የእርሱ ደቀ መዛሙርት የሆኑትን እናፈራለ። በዚህም ትርጉም ያለው ሕይወት ይታይብናል።

መደምደሚያ

ደቀ መዛሙርት ማፍራት ከጌታ የተሰጠን ትእዛዝ መሆኑንና ደቀ መዛሙርት ለማፍራት ምን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ከተመለከትን በኋላ ጸሎታችን ምን ሊሆን ይገባል? ጥያቄአችንስ ምን ሊሆን ይገባል? ጌታ በልባችን ያስቀመጠውን ጸሎት ከልባችን ወደ ለእርሱ እናቅርብ። ጌታ ይህችን አጭር ጽሑፍ እንዲጠቀምበት ጸሎቴ ነው።   

የውይይት ጥያቄ

1.  ሰባኪና አስተማሪን ምን ይለያቸዋል?

2.  ባለንበት ቤተ/ክ የማስተማር ጸጋ የተሰጣቸው አሉ? ይህንስ ጸጋ አክብረው ይጠቀማሉ?

3. በማስተማር የሚያገለግሉ ጥቂት መሆናቸው ማስተማር የሚጠይቀውን ትዕግስትና ኃላፊነት ለመቀበል ካለመፍቀድ የተነሳ ይሆን? አኗኗራችን የሩጫ በመሆኑ ይሆን? የማንበብና የማጥናት ልምድ ከማጣት ይሆን? ከምንገኝበት ሁኔታ ጋር ለማገናዘብ ካለመቻል የተነሳ ይሆን?

4.  “እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ፣ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” ሲል ምን ማለቱ ነው? (ዮሐንስ 8፡ 31-32)