እውነተኛ ክርስቲያን ማን ነው?
በመጋቢ ገ/እግዚአብሔር ካሕሳይ

ይህንም በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተነካ፥ ጴጥሮስንና ሌሎችንም ሐዋርያት:- ወንድሞች ሆይ፥ ምን እናድርግ? አሉአቸው። ጴጥሮስም:- ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ። የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነውና አላቸው። በብዙ ሌላ ቃልም መሰከረና:- ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ ብሎ መከራቸው። በሐዋርያትም ትምህርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቍረስ በየጸሎቱም ይተጉ ነበር። ነገር ግን በሰው ሁሉ ፍርሀት ሆነ፤ በሐዋርያትም እጅ ብዙ ድንቅና ምልክት ተደረገ። ያመኑትም ሁሉ አብረው ነበሩ፤ ያላቸውንም ሁሉ አንድነት አደረጉ። መሬታቸውንና ጥሪታቸውንም እየሸጡ፥ ማንኛውም እንደሚፈልግ ለሁሉ ያካፍሉት ነበር። በየቀኑም በአንድ ልብ ሆነው በመቅደስ እየተጉ በቤታቸውም እንጀራ እየቈረሱ፥ በደስታና በጥሩ ልብ ምግባቸውን ይመገቡ ነበር፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ በሕዝብ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው። ጌታም የሚድኑትን ዕለት ዕለት በእነርሱ ላይ ይጨምር ነበር [የሐዋርያት ሥራ 2፡37-47]::

ናፖሊዮን ቦናፓርቴ የሚባል ጀግና የጦር መሪ አንድ ቀን ወደ ጦርነት ከመዝመቱ በፊት ሌላ ሰው መስሎ ወታደሮቹን እየዞረ ይጐበኝ ነበር። በፍርሃት የሚንቀጠቀጥ አንድ ወታደር ያገኝና፦ "ምን ሆነህ ነው የምትንቀጠቀጠው?” ብሎ ይጠይቀዋል። ወታደሩም ሌላ ተራ ወታደር የሚጠይቀው መስሎት፦ “የምንቀጠቀጠውማ የነገውን ጦርነት እያሰብኩ ነው” ይለዋል።

"ስምህ ማን ነው?"

"ስሜ ናፖሊዮን ነው"

ናፖሊዮን ቦናፓርቴም፦ "ወይ ስምህን ወይ ባህሪህን ቀይር" አለው ይባላል።

በዚህም ዘመን፣ "ወይ ስምህን ወይ ባህሪህን ቀይር" መባል የሚገባቸው ብዙ ሰዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል የክርስቲያን ባህርይ ሳይኖራቸው ክርስቲያን ነን የሚሉ ይገኛሉ። እውነተኛ ክርስቲያን ማን ነው? ለሚለው ጥያቄ የተለያዩ መልሶች እንደሚሰጡ የታወቀ ነው። በዚች አጭር ጽሑፍ ከሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2 ቁጥር 38-47 ሦስት የእውነተኛ ክርስቲያን ባህሪያትን እንመለከታለን።

1. እውነተኛ ክርስቲያን የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቶ ተገቢውን ምላሽ የሰጠ ሰው ነው [የሐዋ. ሥራ 2:37-41]። የጌታ ደቀ መዛሙርት በመጀመርያ ሲያደርጉ የምናየው በአንድ ልብ ሆነው ሲጸልዩ ነው [የሐዋ. ሥራ 2፡1]። ከጸለዩም በኋላ መንፈስ ቅዱስ በላያቸው ወርዶ ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው፣ ሰዎች ሊሰሙት በሚችሉት ልሳኖች  /ቋንቋዎች/ የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ መናገር ጀመሩ [የሐዋ. ሥራ 2፡5-12]።

በዚያን ዕለት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የእግዚአብሔር ታላቅ ሥራ ሲሰበክ ሰምተው ንስሃ ገብተው የተጠመቁና ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የተጨመሩ ሰዎች ሶስት ሺህ ያህሉ ነበር። “ይህንም በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተነካ” ሲል፣ የሰሙት ምንድነው? ብለን መጠየቅ ተገቢ ነው። እነዚህ ሰዎች የአይሁድ ሃይማኖት ተከታዮች ነበሩ። በአጭሩ የተነገራቸው፣ ኢየሱስ ጌታና መሲሕ መሆኑን ነበር። ነቢያት የተናገሩለት የዓለም መድኃኒት እርሱ እንደ ሆነና ከኃጢአት አንጽቶ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቅ መሆኑን ነበር። ይህንን ሲሰሙ ልባቸው ተነካ ይላል። ስለ ሰሙትም ነገር፦ "ወንድሞች ሆይ፣ ምን እናድርግ?" ብለው ጠየቁ። የተነገራቸውንም ታዝዘው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ተጨመሩ።

እውነተኛ ክርስቲያን ስለ ጌታ ኢየሱስ ማንነትና ስለ እጁ ሥራ እውነተኛውን ወንጌል የሰማ፣ መንፈስ ቅዱስ ልቡን የነካውና ለመንፈስ ቅዱስ መልእክት ተገቢ ምላሽ የሰጠ ሰው ነው። ሰዎች ክርስቲያኖች እንዲሆኑ ወንጌል በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መሰበክ አለበት። ወንጌል ሲባል ደግሞ ሰው የሚፈልገውን እየመረጠ ሳይሆን ተገቢ ምላሽ በሚጠይቅ መንገድ ክርስቶስ ማን እንደሆነና ምን እንደሠራ መሰበክ አለበት ማለት ነው።

ሰዎች ወንጌል መስማት አለባቸው። "ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልምና … እምነት ደግሞ የሚመጣው ከመስማት ነው፤ መስማትም ከእግዚአብሔር ቃል ነው።" (ዕብራውያን 11፡ 2፤ ሮሜ 10፡14-17)። በዚህ ዘመን የእግዚአብሔር ታላቅ ሥራ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሳይሰበክ፤ የሰሚው ልብ ሳይነካ፤ የጌታ ኢየሱስ ማንነትና ሥራው በሚገባ ሳይታወቅ፤ ከኃጢአትም ንስሓ ሳይገባ፤ እውነተኛ ክርስቲያን ነኝ ማለት እየበዛ መጥቷል።

እውነተኞች የጌታ ኢየሱስ ደቀ መዝሙር ለመሆንና ሌሎችን እውነተኞች የጌታ ደቀ መዛሙርት ለማፍራት ራሳችን በቅድሚያ እውነተኞች ክርስቲያኖች ልንሆን ያስፈልጋል። የእግዚአብሔር ታላቅ ሥራ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሲሰበክ ሰምተናል ወይ? ሰምተንስ ተገቢውን ምላሽ ሰጥተናል? ሰዎች እውነተኛ የጌታ ደቀመዛሙርት እንዲሆኑስ የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እየሰበክን ነው? ወይስ ሰው የሚፈልገውን እየመረጥን እንሰብካለን? እውነተኛ ክርስቲያን የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቶ ተገቢ ምላሽ የሰጠ ሰው ነው።

2. እውነተኛ ክርስቲያን የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቶ የሚታዘዝ ሰው ነው (የሐዋ.ሥራ 2:42-47)። በዚህ ምድብ የምናገኛቸው እውነተኞች ክርስቲያኖች ወንጌል በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሲሰበክ ሰምተው ተገቢ ምላሽ የሰጡ ብቻ ሳይሆኑ፣ ምላሽ ከሰጡ በኋላ የእግዚአብሔርን ቃል በመማርና ቃሉን በመታዘዝ የሚተጉ ሰዎች እንደነበሩ እንገነዘባለን። ስለዚህ እውነተኛ ክርስቲያን ቃሉን ሰምቶ ምላሽ የሰጠ ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ የእግዚአብሔርን ቃል የሚማርና ተምሮ ደግሞ በተማረው መሠረት የሚመላለስ ሰው ነው።

በብሉይ ኪዳን ሆነ በሐዲስ የምናገኛቸው የእግዚአብሔር ሰዎች ሁሉ ቃሉን ለመማርና ለመታዘዝ የሚተጉ ሰዎች ነበሩ። ለምሳሌ፣ ዕዝራ የእግዚአብሔርን ቃል ለመማር ለመታዘዝና ለማስተማር ልቡን አዘጋጅቶ ነበርና ጌታም ባርኮ ለበረከት አደረገው ይላል። (ዕዝራ 7፡10)። ሥርዓት ባለው መንገድ የእግዚአብሔርን ቃል የምናጠናበት ጊዜና መንገድ አለን ወይ?  ጌታ ያስተማረንንስ እንታዘዛለን ወይ? ተምሮ መታዘዝ በረከት ነው። ተምሮ አለመታዘዝ ግን መርገም ነው። እውነተኛ ክርስቲያን ወንጌል ሰምቶ ምላሽ ከሰጠ በኋላ የእግዚአብሔርን ቃል በትጋት እየተማረ የሚታዘዝ ሰው ነው።

3. እውነተኛ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር ሆኖ ጌታን የሚያገለግል ሰው ነው። (የሐዋ. ሥራ 2:42-47)። እውነተኞች ክርስቲያኖች ለሰሙት ወንጌል ተገቢ ምላሽ መስጠት ብቻ ሳይሆን፣ የእግዚአብሔርን ቃል በትጋት ይማሩና ይኖሩበት ነበር። በሕብረት ሆነው ደግሞ ጌታን ያገለግሉት ነበር። ከዚህ የምንረዳው ወንጌልን ሰምቶ ተገቢ ምላሽ የሰጠ፣ የእግዚአብሔርን ቃል በትጋት የሚያጠናና የሚታዘዝ እውነተኛ ክርስቲያን ከሌሎች እውነተኞች ክርስቲያኖች ጋር ሆኖ ጌታን ያገለግለዋል።

እውነተኛ ክርስቲያን ከሌሎች እውነተኞች ክርስቲያኖች ጋር ቃሉን በማጥናት፤ እንጀራ በመቁረስ፤ በጸሎት፤ ያለውን በማካፈል፤ በቤትና በእግዚአብሔር ቤት በኅብረት ጌታን በምስጋና የሚያገለግል ሰው ነው። እውነተኛ ክርስቲያን በጌታና በሰዎች ፊት ከሚኖረው ኑሮና ከሚያሳየው ድርጊታዊ ፍቅር የተነሳ ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚስብ ሕይወት ያለው ሰው ነው። ሕይወታችን ሰዎችን ወደ ጌታ የሚስብ ነው ወይስ ሰዎችን ከጌታ የሚያርቅ? እውነተኛ ክርስቲያን የጌታን ታላቅ ሥራ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሲሰበክ ሰምቶ ተገቢ ምላሽ የሰጠ፤ ቃሉን ለመማርና ለመታዘዝ የሚተጋና በኑሮውና በንግግሩ ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚስብ ሕይወት ያለው ሰው ነው።

ሕይወታችን ከላይ ባየናቸው ሦስት የእውነተኛ ክርስቲያን ባህሪያት ሲመዘን ምን ይመስል ይሆን? የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሲሰበክ አልሰማን ከሆነ የእግዚአብሔር ታላቅ ሥራ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ወደሚሰበክበት ቤተ ክርስቲያን ሄደን ልንሰማ ያስፈልጋል። ወንጌል ሰምተን ከሆነ ደግሞ ለሰማነው ወንጌል ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ንስሓ እንግባ። ተገቢውን ምላሽ ሰጥተን ከሆነ ደግሞ ሥርዓት ባለው መንገድ ቃሉን በመማርና በመታዘዝ እንትጋ።  ይህን ካደረግን ጌታን የሚያከብርና ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚስብ ሕይወት ይኖረናል፤ እውነተኞች ክርስቲያኖችም እንሆናለን። ጌታ እውነተኞች ክርስቲያኖች የመሆን ጥማትና ጉልበት ይስጠን። አሜን።