የፀደይ ወቅት እንቅልፍ
በፀደይ ተኝቼ ሳላውቀው ጎህ ቀዶ
ጭልጥ አርጎ ወስዶኝ እንቅልፌ አልጋ ወዶ
ወፎች ሲዘምሩ በየመስኩ ማዶ
ሰማሁና ነቃሁ ቀኑ ሞቆ ማልዶ
ለካስ በዚያ ሌሊት ዶፍ ያዘለ ዝናም
ካውሎ ነፋስ ጋራ ዘንቦ ኖሮ በጣም
ሌሊት የወረደው የዝናብ ማዕበል
መብረቅ ወይ ነጎድጓድ ይህ ነው የማይባል
ስንቱን ጽጌያት ነው የፀደይ ቀዘባ
ጠራርጎ ያጨደው ያረደው አበባ
መርገፋቸው እንጂ እንዲያው በድምሩ
ቊጥራቸውን ማን ያውቃል ስንት እንደ ነበሩ
~ ገሞራው (ኃይሉ ገብረ ዮሐንስ)
ለንደን (በአውሮጳ 1979)