ababaTesfaye

ልጆች ዛሬ አንድ ተረት ይዤላችሁ ቀርቤአለሁ ...

ተረት ተረት፤ “የመሠረት” አላችሁ፤ በአንድ ሰፊ ደን ውስጥ አንበሳ፣ ጥንቸልና አሳማ ይኖሩ ነበር። ከዕለታት በአንደኛው ቀን አንበሳው በጣም ስለራበው ምግብ ፍለጋ ከዋሻዋ ሲወጣ “እግዚአብሔር ሆይ ዛሬ በጣም ስለራበኝ እባክህን ምግብ ስጠኝ?” ብሎ ጸለየ። ጸሎቱን እንደጨረሰ ከፊት ለፊቱ ጥንቸልን ተመለከታት አንበሳውም “አምላኬ ሆይ ጸሎቴን ሰምተህ ምግብ እንድትሆነኝ ጥንቸልን ስላዘጋጀህልኝ አመሰግንሃለሁ” ብሎ አፉን ከፍቶ ዐይኑን አፍጥጦ ቆመ … ጥንቸልም አንበሳውን ስታይ በጣም ደነገጠችና “ወይኔ አምላኬ ይኼ አንበሳ በጣም ያስፈራል፣ እባክህን የዛሬን ብቻ ከዚህ አንበሳ አፍ አውጣኝ” ብላ ጸለየች።

አንበሳው፦ “እግዚአብሔር ሆይ አብላኝ” በማለት እየ ጸለየ ጥንቸሏም “እግዚአብሔር ሆይ ከዚህ አንበሳ አድነኝ” እያለች እየጸለየች ሁለቱም መሮጥ ጀመሩ። አንበሳው ከኋላ ሲያባርራት ጥንቸሏም ስትሮጥ አንድ ወንዝ አገኘች። ወንዙን ዘላ ስትሔድ ከወንዙ አጠገብ አንድ አሳማ በልቶ ጠጥቶ ጸሎት ሳያደርግ ተኝቶ ነበር። አንበሳውም ዞር ሲል የተኛ አሳማ ተመለከተ ወዲያው አንበሳው የተኛ አሳማ ከአጠገቤ እያለ ከጥንቸል ጋር ምን አሯሯጠኝ አለና ጥንቸሏን ትቶ አሳማውን በላ። ከዚያ በኋላ የጥንቸሏን መዳን የአንበሳውን መብላት የአሳማውን መበላት ያዩ አንድ ሽማግሌ፣ “ልብላም ያለ በላ፤ ልውጣም ያለ ወጣ ከመሐል የተኛ አሳማ ተበላ” ብለው ግጥም ገጠሙ ይባላል።

“አባባ ተስፋዬ” በ94 ዓመታቸው ሐምሌ 24/2009 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። እግዚአብሔር ያዘኑትን ሁሉ ያጽናና። 

image credit: googleimages