birdie3 

ከ የ ት  ተ ገ ኘ ሽ  ሳ ል ል

ከየት መጣች ሳልል —

“አግድም በረራ ላሳይክ?” አለች

አግድም በረራ ምንድነው ልል፣

“ጎንዮሽ በረራስ?” አለች

ይልቅ ስትቀብጪ ወድቀሽ

የዘነጋሁት ሳቅ አፈትልኮ እንዳይድጥሽ! ...

“ክናፍ አል አክናፍ ይሻልካል?” አለች

“አስራምስትዮሽስ?”

አጣደፈቺኝ —

አል አክናፍ ደግሞ ምንድነው?

ምን ፍጥረት ነች?

ድንገት ሳላስበው አየሩን ገመሰች

ቀኝ ጎኗን እንደ አኮርዲዮን ተረተረች

በሞገድ ሠገረች ዋኘች

ተጋርተን የምንተነፍሰውን አራገበች ቀዘፈች

የባከኑ ውሃ ያቀረሩ ዐይኖቼን አስፈገገች

ኧረ ምን ፍጥረት ነች፣

የነፋስ ሚስት ነች?

ቀጥ ብላ ቆመች፣ ያለ ምርኲዝ

ሽቅብ አጋደለች

ተንሳፈፈች፣ ይኸው በፎቶ እንደ ታየች፤

ወፌ ቆመች! ወፌ ቆመች!

ምርኮ አግኝታ አሁንማ ተርገበገበች፣ ፈነጠዘች።

እኔማ የቆምኩባት ምድር አድክማኝ አለች።

ከየት ተገኘሽ ሳልል

ጎንዮሽ ሸብለል ከብለል

አግድምዮሽ ፎለል ፎለል

ሽቅብ ዘለል ቀለል

እያየኋት ፈንጠር፣ በረር

ካይኔ ፊት ተሠወረች፤

እጄ ገባች ያልኳት፣ አየኋት ያዝኋት፣

ከመ—ቅጽበት አጣኋት፣

~ ምትኩ አዲሱ

© 2012 ዓ.ም | 2019