~ ኡኡታ
የሰው የሃሳቡና የባህሬው ምንጭ
እሷና እሷ፥ እንዲሁም እሱና እሱ፥ እንዲህ ሲነጋገሩ፥
“እኔነቴ ጠፋብኝ! እንጃ ማንነቴንም አላወቅሁት -
ጎኔና ጎኔ ሲከራከሩ…”
እያሉ በሃሳብ ሲወጠሩ፥
ምንድነው ይህ የሰው የሃሳቡ አጫፋሪ -
የሁለትነት ምሥጢሩ።
ከመብላት ጋር ረሃብ፥ ጠጥቶም ጥማት፥
ከደስታ ጋር ሃዘን፥ ከዚህ ከዛም ቤት፤
ዝምታ ሲሰፍን እልል ባሉበት፥
ክፉውና ደጉ ቦታ ሲለዋወጥ፥
በማይረጋ ስሜት፥ በሃሳብ መናወጥ።
በሁለት ተቃራኒ ሃሳቦች መጠመድ የሆነ ከፍጥረቱ፥
በሁለትነቱ ኃጢአትን እየሠራ መቆየቱ፤
ሰው ሲባል እንዲሁ ነው (?)፥ በከፊልም ሆነ በምልአቱ።
ታዲያ ምንድነው ይህ ሰውን የከፈለ በሁለት?
የተፈጥሮ ባህሪይ ከአንስት እስከ አቢይት፤
የመረረ፥ የከረረ ቅራኔ፥ የሰው ሃሳቡና ባህሬው፥
እንቅልፍ የሚያሳጣ፥ እሱ ለሱው ጠላት የሆነው፥
በነማን ላይ ነው እንዲህ አይነት ቅራኔ የነገሠው?
ወይንስ በሁሉም ዘንድ ነው ያለው።
ማሰብማ ምን ይጠቅማል፥
ሰው በገዛ ሃሳቡ ይጎዳል።
ሰው ከራሱ ወጥቶ ቢመለከት እራሱን፥
እርሱም እንደ ዳኛ ፈራጅ ቢሆን፥
ማየት ቢችል፥
አጥፊውን፥ አልሚውን፥
ለየትኛው ጎኑ ይፈርድ ይሆን?
ወይም መርጠህ ውሰድ ቢባል፥ ከሁለቱ አንዱን፥
የትኛውን ጎኑን መርጦ ይውሰድ?
የትኛውን ጎኑን (የትኛውን እርሱን፥ እርሱነቱን) ይጥላ፥
የትኛውን ጎኑን (የትኛውን እርሱን፥ እርሱነቱን) ይውደድ።
ታዲያ፥ ይህ ከሆነ፥ በሁለትነት መፈጠር፥ መነሻው የባህሬአችን፥
ሰው እንዴት ሊያውቅ ይችላል፥ ከራሱ ወጥቶ ስለራሱ - የራሱን?
በሰው ሁሉ ነው ቅራኔዎች ቤት የሠሩት፥
ፍጥረትና ቅራኔ፥ ቅራኔና ፍጥረት፥
በአንድነት ሁለትነት፥ በሁለትነት አንድነት፥
የመሆን፥ ያልመሆን ትግል ይካሄዳል በያለበት፥
ጥንት እንደነበረ፥ አሁንም መቀጠል አለበት።
© 2011 ዓ.ም. | መዝ፣ ቅጽ 2፣ ምዕራፍ 10፣ ገጽ 165-166