ፖ ዬ፣  እ ግ ዜ ር  ይ ይ ል ህ!

ፍቅር ፈቀደ

dog2

ድሮ ልጅ ሆነን እኮ ነው። በተለምዶ “ውሻው ጋ” የምንለው አንድ የቤታችን ጥግ ነበር። የቦታው በዚህ ሥም መጠራት ምክንያቱ፣ ጎሮቤታችን ጋሽ ከቤ ውሻቸውን የሚያስሩበት ቦታ በመሆኑ ነው። እንኳን ቦታውን ረግጣችሁ ይቅርና፣ ለመሄድ ስታስቡ ነው መጮህ የሚጀምረው። ለበዓል የተሠጠኝን የሃገር ባህል ልብስ፣ በዓሉ ከመድረሱ በፊት ቦጭቆ ያስለቀሰኝን ግፉን እስካሁንም አልረሳለትም። አበብ ምስክር ነሽ።

የሚያስገርመው ነገር፣ ይህ ውሻ አጠገብ ታዲያ ሳንቲሞች ያለመጥፋታቸው ነገር ነው። ዛሬ አስር ሣንቲም ካገኛችሁ ነገ ሥሙኒ ይጠብቃችኋል። ከነገ ወዲያ ደግሞ ብዙ ዝርዝር ሣንቲሞች (የማወራው ስለእኛ ዘመን ሣንቲም ነው)… ቢሆንም፣ ያንን ዘንጣይ ጥርሱንና ሬሳ ቀስቅስ ድምጹን አልፋችሁ ጒዳይዋን ማንሳታችሁ የማይቀር ነው።ችግሩ፣ ካነሳችሁት በኋላ የምትወስዱት እርምጃ ነው የዚህ ጽሑፍ ርዕሰ ነገር የሚያስደርጋችሁ።

እሮጠን ፖዬ ጋ የሚወስደን ጒድ ግን ምን ነበር?! ሣንቲም ማግኘታችንን አስተናግር እንደቀመሰ ሰው እየተቅለበለብን እንነግረዋለን። የእርሱ ጥያቄ ሁለት ነው። “ያገኛችሁት ሳንቲም ከፊት የሰው ቅርጽ አለበት?” የእኛ መልስ “አዎ” የሚል ነው። ሁለተኛውን ደግሞ ይቀጥላል። “የያዛችሁት ሳንቲም ከኹዋላ አንበሳ አለው?” የሣንቲሙን ከመሬት መገኘት እንዲያረጋግጥልን ስለምንፈልግ በጋራ “አዎን” እንላለን። ኮስተር ያለ መደምደሚያ ይከተላል። “ሣንቲሙ የእኔ ነው!” እኛን ነበር ማየት! እጃችንን አንከርፈን ያገኘነውን እናስረክበዋለን። ከራራልን በጊዜው እጅ ላይ የምትለጠፍ ምስል ያላት “ድመት ማስቲካ” በ15 ሣንቲም ገዝቶልን ሌላውን የት እንደሚያደርሰው እንጃ!

ልጅነት ጥሩ ነው። ታላቅን የማመን ሰብዕናን ይቸራል። መግዛትና መለወጥ የሚችል ነገር ሲቀሙ ዝም ብሎ ማስረከብ ያለማወቅ ወይም የመፍራት ውጤት ነው (ብትከራከሩ የታላቅ ጡጫ አይቻልማ!) ብቻ የተሰጣችሁን ይዛችሁ ማለቃቀስ ነው። ፖዬ እግዜር ይይልህ …

ምን ለመጠየቅ ነው? ቤት ለመግዛት ያጠራቀምኩት ብር የቱ ፖዬ ገጥሞት ነው ዳቦ ወደመግዛት ያነሰው?

© 2020 by Fikir Fekede