treefikrepoem

ይ ቺ  ና ት  የ ኔ  ም ድ ር
  ፍ ቅ ሬ  ቶ ሎ ሳ
....................................................................
ግን እኮ እዚህም ኢዮሄ! እልልሻለሁ፤ አለቅሥልሻለሁ ለብቻዬ
ከመላው ምድረገጽ ለሥቃይ፣ ለርሀብ፣ ለምን? ለምን? ተመረጠች ኢትዮጵያዬ!

በኃጢዓትዋ ነው ይሉኛል ቄሱ፤ መልሳቸው አንጀቴን ላያረካ
ኃጢዓትሽ ይብስ ይሆን ከአውሮፓና ከአሜሪካ?
እግዜር ስለሚያፈቅራት ነው የሚቀጣት ይላሉ ቄሱ
አባትም የሚቀጣው የገዛ ልጁን ብቻ ነው የሚወደውን እንደራሱ
ሌሎቹን የማይቀጣቸው ስላይደሉ ነው የሱ።
እሥራኤል እግዜር የመረጠው ሕዝቡ ሆኖት
ባምላኩ ላይ ስላመፀ፣ በርሀብ፣ በቸነፈር፣ በጦርነት ቀጥቶት፣ በመላው ዓለም በታትኖት
ኋላ ግን ሕዝበ እሥራኤል ቢፀፀት ጥፋተኛነቱን ተቀብሎ
እንደገና ሠብሥቦ ነፍሥ ዘራበት፣ እንደሌላው አልጣለውም ጥሎ
ኢትዮጵያም እግዚኦ ካለች፣ ይታረቃታል በቃሽ ብሎ።

ፖለቲከኛውንም ስጠይቀው የራሱን መልሥ ይሠጠኛል
በመንግሥት፣ በተፈጥሮና በአስተራረስ ጥፋት ነው ይለኛል።
ባለታሪኩንም ባናግረው “ካክሱም በፊት ያለውንኳ ብንተወው ተነግሮ ስለማይጨረስ
ካክሱም መመሥረት አንሥቶ እስከጣሊያን ወረራ ድረሥ
የኢትዮጵያን ታሪክ ብንመረምረው ባለፈው ሃምሣ ዓመት ብቻ *
ከውጭ ወራሪ ጋር መተላለቅ፣ ርሥበርሥ መተራረድ ነው ባለም የሌለው አቻ
የደም መፍሠሥ ታሪክ ነው ታሪክዋ የኢትዮጵያ
ታዲያ መቸ ሠላም አግኝታ ትሻሻል? ይለኛል የታሪኩ ባለሞያ።
መንሥኤው ሰው-ሠራሽ ይሁን የእግዜር ቊጣ፣ ወይም የተፈጥሮ
ሐቊ ተርበሻል፣ ተራቊተሻል፣ ደምተሻል ኢትዮጵያዬ
ምክንያት ቢደረደር አይበጅም ዘንድሮ።
እኔ ልጅሽ ግን አምናለሁ፣ ይኸ ቀውጢ ቀንሽ ተሽሮ
በጥጋብ፣ በብልጽግና፣ በፍቅር፣ በሠላም ተቀይሮ
ዛሬ ለርሀብና ለጦርነት ተጋልጠሽ እንደተዋረድሽ፣ ነገ አንቺነትሽ ተከብሮ
አንቺ ለመላው ዓለም የብልጽግና፣ የሠላምና የፍቅር ምሣሌ ሆነሽ
ትቢያውን ከላይሽ ላይ በትነሽ፣ ሞተሽ ከተቀበርሺበት እንደምትነሽ!

* ግጥሙ የተጻፈው በሺ ዘጠኝ መቶ ሰባ ዘጠኝ ዓ.ም. ነው። የታተመው በአሜሪካ 2006፤ ገጽ 27-28።
“ይቺ ናት የኔ ምድር” አገራችን የገባችበትን መከራ ከመግለጥ አልፎ ተስፋ ሰጭ ስለሆነ ለዚህ ገጽ በሚሆን መልኲ አትመነዋል።
ሙሉውን መጽሐፍ እዚህ ያንብቡ | Picture credit: Wikimedia Commons