እ ኔ ም  ለ ዚ ህ  መ ጣ ሁ

መንገድ ተሰናክሎ፥ ውሉ ጠፍቶ ሰንደቅ
ህሊና ጠርንፎ፥ የበደል እግረ ሙቅ
ደመ ነፍስ ሲራኮት፥ በመግደል ለመፅደቅ

ንጉሥ እንዲገረፍ፥ የበርባን ማቅ ሲወልቅ
ለሃጢእ ሠላም ወርዶ፥ እንዲኮነን ፃዲቅ
እጅ በውሃ ነፅቶ፥ በደም እንዲጠመቅ

አመዛኙ ስሁት፥ ልሂቅ እስከ ደቂቅ
ስቀል ብሎ ጩኸት፥ ሞትን ሞቶ መራቅ
እውነት አስደንብሮት፥ ሽሽት እመቀመቅ

እኔም ለዚህ መጣሁ፥ እውነት አይደበቅ
ካራ እንዳነሣ፥ መንግሥት ለመሰንጠቅ
ሲዖል ተሽመድምዶ፥ ዲያብሎስ እንዲደቅ

እውነት እልሃለሁ፥ እውነትን ለማታውቅ
አፍህ ተቀኝቶ፥ ፈሪው ልብህ አይውደቅ
ለሙታን አድልተህ፥ እውነትን አትልቀቅ!

~ ሲሞን ሄሊሶ
ሕማማት 2013 ዓ.ም.