ሰ ዉ ሲ ሽ ኮ ረ መ ም ጨ ረ ቃ ት ና ገ ር
በኢትዮጵያችንም ስለ ጦርነት ብዙ ወሬ ይሰማል፤
የኢትዮጵያኖችን የልብ ትርታ ማን ያዳምጣል?
ጀግናውም - ፖለቲከኛውም - አዋቂ ነኝ ባዩም ብዙ ያወራል፤
የዛን ሰው - የልቡን ማን ይረዳዋል?
ኃይሉን ከሕዝቦች ተቀብሎ እንደ ራሱ ኃይል ይወስናል፤
እንደ ራሱም ኃይል ይፈርዳል።
በእርግጥ የኢትዮጵያችንን (የአገሪቷን) መንፈስ ማን ይገነዘባል?
የአገራችን መንፈስ ከግለሰብ መንፈስ በላይ፥
የኢትዮጵያችን መሬት ሁሉ የኢትዮጵያችን ሁሉ መሆኑን፥
ይህንን ጉዳይ ማን አስተውሎታል?
ግን - እነርሱ (መሪዎቹ እንዲሁም አንዳንዶች ከሊቅ እስከ ደቂቅ)፥
ክማንነታቸው ባሻገር፤
ነፍስ-ወስጋ ኢትዮጵያችንን በገመድ (ዘር) እየጎተቱ.....፥
አዳምና ሔዋን የሰው ልጅ መገኛው መሬት በፍጥረቱ፤
ሁሉም የርሱ (የሰው) ናት እኮ! ብናስተውል በጥልቀቱ።
ተረሳ እንዴ?
ያ ሰው - ተተካ እንዴ በዶላር?
የሥልጣን ጥም፥ ግለኝነት፥
ውዳሴ ከንቱ - ማጋጌጥ በምድራዊነት፤
እንግዲያውስ ስሙ፤ ከሁላችንም በላይ ከሰማዩ፥
ሁላችንንም ከምታይ ከአንዲት (አንዲት?) አነስተኛ ፍጥረት፥
ሰውና መሬቱን እየታዘበች ከቆየች ውቢት፥
እርሷ ባትሆንም እንኳን አፍ አውጥታ ትናገራለች የምላት፥
እስቲ የእውነት እውነትነቱን ብቻ አስተውሉት።
እኔም እናንተም አብረን እንስማ ከደማቋ ጨረቃ (ቃ!.... ድምቡለቃ....)፤
“ሂድ ውጣ አገርህ ሌላ ነው....” የሚል ሲመጣ፥
“አይ! እኔ እንኳን አይደለሁም ከራያ ወይንም ካላማጣ፥
የማንነቴ ምሥክር እትብቴ ከመሬት ተቆፍሮ ሳይወጣ፥
ተፈረደብኝ እኮ! አማራ በመባሌ ብቻ!
ከገዛ አገሬ ተነቅዬ እንድወጣ።
ያ ቀዬ - ያ መንደር - ያ ከተማ - መሬቱ - ቢዬን ኪያ/ቢዬን ኬኛ፤
ቋንቋዬም አማርኛ እንዲሁም ኦሮምኛ፥
"ኤኙ አዳን ኑባሴ - ማነው የለያየን" እያልኩ፥
እየተማረርኩ በጠላት ፖለቲከኛ፥
"የተወለድኩበት ሥፍራ አገሬ ነው፥
ከገዛ አገሬ ተሰድጄ ወዴት ነው የምሄደው...?”
እያልኩ ሃዘኔን - ብሶቴን ሁሉ ተናግሬ ሳላበቃ፥
ድብልቅልቅ ያለ ስሜት - ደስታም ድንገት ተሰማኝ፤
አዎንታዊና ሁለንታዊ እውነት መኖሩ ታወቀኝ።
ጨረቃዬ ደማቅ ብርሃኗን ረጨችብኝ፤
በደማቅ ቀለሟ እውነታዎቿን አፈሰሰችብኝ፤
ከእንግዲህስ እንዳልፈራ በምስጢር አወራችኝ፤
በድምጽ አልባ ንግግሯም አጽናናችኝ፤
“ጨረቃዬ ያጭር ጊዜውን ወደፊት አውቀዋለሁና አትንገሪኝ...”
እያልኩ የልቤን - ጭንቀቶቼን ሁሉ ሳዋያት፥
ጨረቃዬ የምወዳት (የልቤ እውነት - ምሥጢሬ) እንዲህ አለቺኝ፦
"ይህ በምሥራቅ አፍሪቃ የሚካሄድ ጦርነት
የኢትዮጵያ መሬት ሁሉ
ለኢትዮጵያውያን ሁሉ
መሆኑ እስኪረጋገጥ ድረስ
ፍጻሜ አይኖረውም።"
© 2021 መ. ኃ/መ