ቼ በለው
ሕይወት ጎዳናው ገፁ ሲለወጥ
በጭነት ታክቶ ጀርባው ሲመለጥ
የእንቅፋት አፅሙ ቋጥኙ ሲገጥ
ሸክም ዘንቦበት ትቢያው ሲላቊጥ
ሲሆን ድጥ በድጥ
ሾህ ጭቃ ቅይጥ
ልብህ አይደንግጥ።
በምኞት ቅዠት በሥጋት ርዶ
አይፍረስ ግንቡ ወኔህ ተንዶ
ከቆመው ቆመህ ከንፈር ከመምጠጥ
በተስፋ ፈረስ በልጓም ሸምጥጥ።
አያረጅ የለም አይለዋወጥ
ነገን ተማምነህ በመጓዝ ቁረጥ...
ከሩቅ አልመህ ቅርብ አትርመጥመጥ
ሠግተህ ከምትቆም ስትጋልብ ፍረጥ።
~ ሰዓሊና ቀራጺ በቀለ መኮንን
ምንጭ፦ አዲስ አድማስ (2014 ዓ.ም.)
photo credit: Yves-Marie Stranger