mez22

መ ል እ ክ ት  ከ አ እ ዋ ፋ ት  መ ን ደ ር

በሰላም እጦት ሰዎች ሲቸገሩ እኔ እርግብ እያየሁ፥
ጥሩ ነገር ሁሉ ከምድሪቱ ሲርቅ እያስተዋልሁ፥
ጥንት የሕይወት ተስፋ’ሚሆን ቅጠል በጥሼ ለኖህ እንደሰጠሁ፥
ዛሬ ደግሞ የሰላም ተስፋ’ሚሆን ቅጠል በጥሼ ምሰጠው ሰው ባገኘሁ፥
እያልኩ በስሜታዊ ጉጉት ተጠመድሁ።
ከአእዋፍ መካከል እኔ ተመርጬ - መንፈስ ቅዱስ ያደረብኝ፥
የሰላም ምልክት መሆኔ ትዝ - ትዝ እያለኝ፥
የምድር ሰላም እጦት እጅጉን አሰጋኝ።

የሰላሙ ንጉሥ (ኢየሱስ ክርስቶስ) ተከታዮች፥
ሰላምን ሲሰብኩ ሁለት ሺህ ዓመታት አለፋቸው፤
እኔን የገረመኝ - ምንድርነው ሰዎች ያልገባቸው?
አሁንም አልቀረም ጭቅጭቅ - ጦርነት ሁኗል ሰላማቸው።

ታዲያ፥ እኔ ለማን - ምን ብዬ - ምን እውነት ልናገር?
ምን ብዬስ ልመስክር?
ምን አለና ያልተነገረ ያልተወራ ነገር።
ከኖህ መርከብ እስከ መስቀሉ፥
ምህረት ተሰጥቶ ለሰው ልጅ ሁሉ፥
ሰውም ካልተዛዘነ እርስ በርሱ፥
ዝም አይሉም ነፍስ ያላቸውስ ሁሉ፥
ይንቀሳቀሳሉ ለህልውናቸው ሲሉ።
በጥሞና ለሚያዳምጡን፥
በዝማሬዎቻችን ይገለጣሉ ስሜቶቻችን - ደስታ ሃዘናችን፥ ለቅሶና ዋይታችን።
ሃያል ነው የተፈጥሮ አቤቱታ፥
አይተነዋል እኮ! አጥፊውን ለማጥፋት ሲሰጠው ችሎታ።
ለዚህ እንደ ማስረጃ - ምስክር የሚሆን ፍንጭ ፍለጋ፥
ከኢትዮጵያ የሰሜን ተራሮች ተነስቼ - ወደ ሰሜን ምሥራቅ በረራ፥
ለሽርሽር ሳይሆን ለሥራ፤
እግረ መንገዴን ያየሁትን የሰው ልጅ መከራ - ተቆጥቤ ሳላወራ፥
በርሬ - በርሬ ደረስኩ ከአንድ ሥፍራ።

ክንፎቼ እስኪዝሉ ብከንፍ - ብዞር ካለ እረፍት፥ ምናለ ብለፋ፥
ሰውን የሚያሳምን ካገኘሁኝ ተስፋ።
ከሩቅም ከቅርብም ሳስተውል፥
ከተራራው ተቀርጾ ልክ እንደ ስዕል፥
ታየኝ የመርከብ ምስል።
አዎ! እርሷው ነች፤
ተሰብራ፥ ተሰባብራ፥ ህልውናዋ ጠፍቶ፥
መላው አከላቷ ወደ አፈርነት ተለውጦ፥
አዎ! እርሷው ነች - በእርግብ አይን እይታ የታየች፤
ጊዜ ጠብቃ የተከሰተች፤
ለሰው ልጅ ደግ እንዳልሰራች፥
ዘመን አሻግራ ለወሬ ነጋሪ በትንሹ የተረፈች፤
ከአንድ አጣብቂኝ ሥፍራ ተወስና የቀረች።
አዎ! እርሷው ነች - ሰውም እንስሳም እንዳይጠፋ፥
ሁሉንም በጉያዋ ታቅፋ፥
መጥፎውን ዘመን አሳልፋ፥
ለሰው ልጅ የሆነችው ተስፋ።

ያ የጥንቱ ሰው ከመርከቢቱ ጉያ ወጥቶ፥
ወደ ሜዳው ዘልቆ ሲኖር ተንሰራፍቶ፥
እህል ዘርቶ ያመረተውንም በልቶ፥
ከመደሰቱ እና ከመባዛቱ፥
እጅግ ተበራከተ ኃጢአቱ።

ከሰው ጋር እንስሳት፥ ከአእዋፋት ጋርም እጽዋት፥
ሁሉም እንዲጠበቅ - እንዲኖር በህብረት፥
ከሰማይ አካላት ሰላም በምድሪቱ፥
ላመነበት ተስፋ ተሰጥቶታል - በቀስተ ደመናው ምልክቱ።
ታዲያ፥ ስለ እውነት መስካሪ ካልጠፋ - መልካም መንፈስ እንደ እርግቢቱ፥
ምነው የሰው ልጅ አልገባ አለው ትምህርቱ?
ሲጨነቅ፥ ሲደናገር - መጥፎውን እያሰበ በራሱ ለራሱ፥
ጦርነት፥ ስደት፥ ረሃብና ጥማት፥ በሽታ እና ሕመም ሲፈራረቅበት በገዛ ክፋቱ፥
ለምን አይማርም ከስህተቱ?
የሰው ልጅ በውሃ ካልጠፋ፥ እኔ በእሳት ላጥፋው ብሎ መነሳቱ፤
የአዝማሚያው አስጊ መሆን በዛሬ እና በነገ ሂደቱ፥
በየአገሩ፥ በየክልሉ፥ በየመንደሩ፥ ለሰው ልጅ ራሱ ሰው ሲሆን ጠላቱ፥
በዚሁ ከቀጠለ - በመጥፎው ድርጊቱ፥
እጅጉን ያሰጋል - ተሰባብሮ እንዳይቀር እንደ መርከቢቱ።

የቀስተ ደመናው ተስፋ ከሰማዩ አልጠፋም፤
ያውና በአለም ዙሪያ - ይታያል መስቀሉም፤
መጥፎ ጊዜ ቢመጣ፥ ዘመኑ እጅግ አስከፊ ቢሆንም፥
በሰላሙ ንጉሥ (ኢየሱስ ክርስቶስ) የተሰጠውን ሰላም፥
በእምነት ከተቀበልን ሁላችንም፥
እንኖራለን እንጂ፥ አንጠፋም።

©መዝ ኃይሌ፣ 2014 | 2022