"እንደ ቤርያ ሰዎች"

ቃለ ምልልስ ከወንድም ሚካኤል አለሙ ጋር

berea

ስለ ቤርያ ሰዎች ልበ ሰፊነትና ቃሉን መርምሮ ስለ መቀበል ብዙዎቻችን አንብበናል (የሐዋ ሥራ 17፡11)። በዚሁ መንፈስ ስለ ተነሳሱት ስለ “ቤርያ ሚኒስትሪ” እንዲነግረን ወንድም ሚካኤል አለሙን አነጋግረናል፦

ኢትዮፕያንቸርች። ከ “ቤርያ ሚኒስትሪ” ጋር ያለህ ግንኙነት ምንድነው? የአገልግሎቱ መነሻ ዓላማ ምንድነው?

ሚካኤል። አገልግሎቱን ከመመሥረት ጀምሮ በአመራር ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር በመሆን አገለግላለሁ። አገልግሎቱ በፈረንጆች 2006 መጨረሻ አካባቢ ነው የተጀመረው። ቴሌኮንፈረንስ ቴክኖሎጂ ሲጀመር፣ ሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ሃበሾች የሚገናኙበት አንድ ኮንፈረንስ ቁጥር ነበር። ወደ ቁጥሩ ስልክ ደውለህ ማንኛውንም ሁለት ዲጂት “ፓስ ኮድ” ስታስገባ ከአምስት እስከ ስምንት የሚሆኑ ሃበሾች ልዩ ልዩ ወሬ ወደሚያወሩበት ክፍል ያስገባ ነበር። ክርስቲያኖችም ገብተው በጥበብ ወንጌልን ይመሰክሩ ነበር። በዚያው ቀጥለን ማታ ማታ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመርን። ማታ ብቻ የነበረው ሌሊቱን፣ ከዚያም ቀኑን እያለ በ2010 የሃያ አራት ሰዓት አገልግሎት ጀመርን። ቀደም ብለን ፕሮግራሙን ስንመራ የነበርን ወንድሞች ተሰባስበን መሪዎችን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን እና የአገልግሎት ዘርፎችን አዋቅረን ሃያ አራቱን ሰዓት በሦስት በመክፈል ፕሮግራሞችን ነድፈን አገልግሎቱን ቀጠልን። የተገልጋዩ ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ በአካል መገናኘት ይጠቅማል በሚል በ2012 ዴንቨር ኮሎራዶ የመጀመርያውን ኮንፈረንስ አደረግን። ከኮንፈረንሱ የተረፈንን አስር ሺህ ዶላር ይዘን በ2013 ከታላቁ ተልኮ ኢትዮጵያ ጋር በመሆን ወንጌል ባልደረሰባቸው የሰሜን እና ምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች የወንጌል መልእክተኞችን ለማሠማራት ተስማማን። በ2013 ላስቬጋስ በነበረን ኮንፈረንስ ለተሳታፊዎቻችን ራዕይችንን አስተዋወቅን። በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በኤርትራም ያለችውን ቤ/ክ ለማገዝ ተስማማን። በዚህ መሠረት እስከ ሁለት መቶ የወንጌል መልእክተኞችን በማሠማራት ወንጌልን አብረን አገልግለናል። በኤርትራ ያለችውን ቤ/ክ በየዓመቱ እንደግፋለን። አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ መቶ ሠላሳ አምስት የወንጌል መልእክተኞች አሉን።

ኢትዮፕያንቸርች። የየትኛው አጥቢያ ቤተ/ክ አባል ነህ?
ሚካኤል። አባልነቴ በ ህይወት ቃል ሳክራሜንቶ ህብረት ነው፤

ኢትዮፕያንቸርች። ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የወንጌላውያን አብያተክርስቲያናትን እንቅስቃሴ እንዴት ትገልጸዋለህ?

ሚካኤል። ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የብዙ ነፍሳት ወደ እግዚአብሔር ቤት መጨመር ጥሩ ነገር ነው። ይሁን እንጂ በትክክል ደቀ መዝሙር በመሆን ማደግ ላይ ችግር አለ። ይህ ብቻ ሳይሆን ቤ/ክ በስሕተት ትምህርት እየተናጠች ነው። በአጠቃላይ ዓለማዊነት የስሕተት ትምህርት እና በክርስቶስ ትምህርት ሥር ሰዶ ማደግ ላይ ትልቅ ችግሮች ይታያሉ።

ኢትዮፕያንቸርች። “ቤርያ ሚኒስትሪ”፣ ቤተክርስቲያን ልትሰጠው ያልቻለችውን ምን የተለየ አገልግሎት ይሰጣል?

ሚካኤል። ቤርያ ሌትና ቀን (በተለያዩ አህጉሮችና የሰዓታት ክልል ለሚገኙ) ሳያቋርጥ የሚሰጥ አገልግሎት ነው። ቤርያን በሳምንት ሁለት እና ሦስት ሰዓት አገልግሎት ከሚሰጡ ቤ/ክርስቲያኖች ጋር ማወዳደር አትችልም። በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ ከአራት ያላነሰ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ትምህርት፣ ስብከት፣ ጸሎት፣ በቡድን ውይይት፣ ጥያቄና መልስ፣ ስለ ልጆች አስተዳደግ፣ ስለ ትዳር፣ ሁለንተናዊ አገልግሎት፣ ሥነ ፅሁፍ፣ ሌሎቹም አገልግሎቶች ይሰጣሉ። ነፍሳት ይድናሉ፤ ለዳኑት መሠረታዊ ትምህርት ይሰጣቸዋል። በህይወት የደከሙ በርትተዋል፤ ብዙዎቻችን አድገንበታል። ጥቅሙ እጅግ ብዙ ነው። ይህንን ጥያቄ ከኔ ይልቅ የተገለገሉ ሰዎችን ብትጠይቅ በቂ መልስ ታገኛለህ። ምናልባት እኔ ብዙ ባወራ አያምርም።

ኢትዮፕያንቸርች። ከሦስት መቶ የሚበልጡ “የግል ሚኒስትሪዎች” እንዳሉ ይነገራል። እነዚህ አገልግሎቶች በቤተክርስቲያን ላይ ምን ዓይነት ተጽእኖ አድርገዋል ትላለህ?

ሚካኤል። ስለ ሌሎቹ አገልግሎቶች ብዙ ስለማላውቅ መናገር ይከብደኛል። ቤርያ ግን በጌታ ኃይልና ችሎት በወንጌል ሥራ ብዙ እየሠራ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ከአንድ መቶ ሰማንያ አምስት በላይ አጥቢያ ቤ/ክርስቲያናት ተክሎአል። በእስር ላሉ ኤርትራ ወገኖቻችን በያመቱ ድጋፍ ይሰጣል። በዓለም ዙርያ የእግዚአብሔርን ቃል ያስተምራል። ወደ ቴሌኮንፈረንሳችን በስልክ ብቻ ሳይሆን በድረገጽ መግባት ስለሚቻል ሰዎች ከኢትዮጵያ፣ ከአፍሪካ፣ ከአውሮፖ በነፃ በኢንተርኔት መግባት ይችላሉ። ድረገጻችንም bereaministry.org ነው።

ኢትዮፕያንቸርች። ውይይታችንን ሌላ ጊዜ እንቀጥላለን። እስከዚያው እግዚአብሔር አንተን፣ አብረውህ የሚያገለግሉትን እና ቤርያን ይባርክ።

ሚያዝያ 28/2012 ዓ.ም.

እንዳለፈ ውሃ - የእህት አስቴር ተፈራ ቁ.3 መዝሙር ግምገማ

photo credit: bereaministry.org