ከአንበሳ ከጣዎስ

peacockLion

ማህበረሰብ የሚጋራቸው፣ የሚዋዋሳቸው፣ ከትውልድ ትውልድ የሚቀባበላቸው ምልክቶች አሉት። (ሞዓ) አንበሳ ከአይሁድ (ከግሪክ፣ ከግብጽ፣ ከፐርሽያ) የተወረሰ ነው። ኢትዮጵያውያን አንድ ጒብዝናችን ከሌላ የተዋስነውን ራሳችን እንዳመነጨነው አድርገን መከራከርና ራሳችንን ማሳመን መቻላችን ነው። ለምሳሌ ክርስትናን። ከመቶ ዓመት በኋላ የዛሬዋ ጣዎስ ህንዳዊት ሳትሆን ንጹሕ ኢትዮጵያዊት ነች ብለን እንጋደልባታለን!!

ማህበረሰብ በምልክቶቹ እርስበርስ ይያያዛል፣ ከሌሎች ሕዝቦች ራሱን ይለይበታል፤ ምኞቱን፣ ነጻነቱንና ክብሩን ይገልጽበታል። ሲያስፈልግም ይጋደል(ላ)(ባ)ቸዋል። ሰንደቅ ዓላማ ለምሳሌ። ሐውልቶች። ብሔራዊ መዝሙር። የኃይማኖት ምስሎች። ሳንቲሞች። ጅረቶች። ዕፀዋት። አእዋፍ። ጀግኖች አባቶችና እናቶች፤ ወዘተ። አረንጓዴ-ቢጫ-ቀይ ባንዲራ፤ ዓባይ፤ አክሱም ሐውልት፤ ገዳማት። የሐረር ግንብ፤ ወርካ ዛፍ። የፋሲል ቤተመንግሥት፤ ቡና፤ ዋልያ፤ ወዘተ። ሌሎች ምልክቶች ወይ ይጨመራሉ ወይም ተቀባይነት በማጣት ይረሳሉ።

አንበሳ ከትውፊቶቻችን መሓል ትልቅ ሥፍራ የያዘ ብሔራዊ ምልክት ነው። ሰሞኑን ግን የተኛው አንበሳ ተቀስቅሶ በብልጭልጭ ወፍ ትመነዝሩኝ ብሎ አጓርቷል አሉ! የክርክሩ መነሻ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ በቤተመንግሥቱ መግቢያ በር ላይ አንበሳን በፒኮክ/ጣዎስ (ወይስ ጣኦት) መተካታቸው ነው። ፒኮክ ላዲሳበቤዎች ከፒኮክ ቡና ቤትና ከፒኮክ ፓርክ አልፎ አያውቅም! ሁለት ነገሮችን አንርሳ፦ ሀ/ በሌሎች ሥፍራዎች ያሉ አንበሶች አልተነኩም! ለ/ ፒኮኳ ከ"አንድነት ፓርክ" ግንባታ ጋር የተፈጠረች ነች። ለመንቀፍ ላሰፈሰፉ ግን ከበቂ በላይ ሰበብ ፈጥሮላቸዋል። (ሳተናው የዚህና የተመሳሳይ ንቅናቄ ማእከል መሆኑ ግልጽ ነው!)

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ “መደመር” የተሰኘ የፖለቲካ ስልታቸውን እንድታቀልምላቸው ወፊቱን ፈልገዋል። አፈ ታሪካችን ከ ‘ድር ቢያብር አንበሳን ያስር’ ወደ ‘ድር ቢያብር ወፍ ያስፈንጥር’ መሸጋገሩ እንዳይሆን!

የጠ/ሚሩን ውሳኔ እንደ አገር ክህደት የወሰዱ አሉ። ለምሳሌ፣ መስቀሉ አየለ፣ “ጥቊር አንበሳው ከትናንት እስከ ዛሬ” በሚል ርእስ፣ ብሔራዊ ቲያትር አጠገብ የተተከለውን አንበሳ ብሶት፣ ፈረንሳዊ መሀንዲስ እንደገነባውና የሚገባውን ከበሬታ ሳያገኝ መቅረቱን በቊጭት አግስቷል። (ሳተናው፣ ኤፕሪል 26/2020)

ባልደራስ “አስገራሚ መረጃ፣ አዲስ አበባን የመጠቅለል አባዜ” ሲል ይጀምራል። “የጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ብልጽግና ከለሊት ወፍ ፒኮክ ተከላ እስከ ሐውልት ነቀላ የሥርዓቱ ድፍረት ማቆሚያ አጥቷል። ብሔራዊ ቲያትር አጠገብ የቆመው ሞዓ አንበሳ ሐውልት ሊፈርስ የመታቀዱን ምሥጢር ደርሰንበታል፤” ይለናል። መረጃ ግን የለውም። “ባልደራስ (የእነ እስክንድር ድርጅት) ጒዳዩን እየተከታተለው" ነው። (ሳተናው፣ ኤፕሪል 24/2020)። ባልደራስ ፒኮኳን ለማጣጣል “የለሊት ወፍ” ብሏታል፤ አንበሳውን ለማግዘፍ “ሞዓ” ን ቀጥሎለታል። “ሞዓ” በኦሮምኛ አሸናፊ፣ ድል አድራጊ ነው!

ገለታው ዘለቀ፣ በምሬት “ጠቅላይ ሚ/ር አብይ አህመድ ለምን ከቤተ መንግሥቱ ላይ አንበሳውን አነሱት? ያንብቡት ሼር ያድርጉት” ብሎ ይጀምርና፤ “የዶክተር አብይ ፒኮክና የይሁዳ አንበሳ” በሚል ንኡስ ርእስ ክርክሩን ይቀጥላል። ፒኮክ መምረጣቸው እንደ አንድ ሕዝብ እንዳሳነሰን ለማስረዳት የአራዊቱን ባህርይ ከ "ሳይንቲፊክ አሜሪካ" መጽሔት መረጃ ጠቃቅሶ፤ ሃገራት እንስሳትን ብሔራዊ ምልክት አድርገው ይጠቀማሉ፤ የእኛ አንበሳ ሆኖ ኖሯል፣ ዶ/ር አብይ ሕዝብ ያልመረጣቸው ሆነው ሳለ፣ ሊታገሱ እንኳ እንዴት አልቻሉም ይለናል። “ትውፊታችን አንበሳ ነው፤ ፒኮክን ሕዝባችን ምን እንደሆነች እንኳ አያውቃትም። ጠ/ሚሩ እሴትን የመሥበር መሠሪ ጥረት ይዘዋል። ክብር ለትውፊታችንና ለእሴቶቻችን። እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ” ሲል ይደመድማል። (ሳተናው፣ ኤፕሪል 23/2020)

አስቻለው ከበደ አበበ ደግሞ በ “መልክአ ጣዎስ (ታዎስ)” መልእክቱ (ሳተናው፣ ኤፕሪል 29/2020)፣ ኮሚኒስቶች እንዴት ቀጥቅጠው እንደ ገዙን፤ ጸሎትና ትግል ከህወሓት/ኢሕአዴግ እንደ ገላገለን፤ እግዚአብሔርን የሚፈራ መሪ በጠ/ሚ ዐቢይ እንደ ተተካልን ገልጾ፤ እኝሁ ሰው ስለ ሠሩት “አንድነት ፓርክ” አመስግኖአቸዋል። የተለያዩ የእምነት ክፍሎች ስለ ጣዎሲት ያላቸውን አተረጓጎም ከአዋልድ መጻሕፍትና ከአፈ ታሪክ ጠቃቅሶ፤ ለጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ሁለት ጥያቄዎችን አቅርቦላቸዋል፦ አንደኛ፣ ሐውልት የተሠራላቸው ሁለቱ ‘ባእዳን’ ጣዎሶች ምን የሚሉት እምነት መገለጫ ናቸው? ሁለተኛ፣ እርስዎ የሚመሩት ብልጽግና ፓርቲ አርማ ላይ የምትታየው ጣዎሲት ነች ወይስ ዐይኔ ነው? የሚል ነው። ከጠ/ሚሩ ወይም ከረዳቶቻቸው መልስ ያገኛል ብለን እንለፈው።

ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ፣ “የራስን ጥሎ የሰው አንጠልጥሎ” ሆነብን እሳ ነገሩ ሁላ” ካለ በኋላ፣ ለመሆኑ “እነ ቀይ ቀበሮ፣ ዋልያ፣ አይቤክስና ጭላዳ ዝንጀሮ ... ብቊ አልሆን ብለው ይሆን ወይስ እነሱም በአማራ ክልል ስለሚገኙ?” ብሎ ይደመድማል። (ሳተናው፣ ኤፕሪል 25/2020)

ከሁሉ ከረር ያለ ትችት የሠነዘረው ርዕዮት “ቶክሾው አዘጋጅ ቴዎድሮስ ፀጋዬ ነው። “የፒኮክ ፖለቲካ እና የአፈቄሳር ዳንኤል ክብረት ነገር” ብሎ አንድ ሰዓት የፈጀ ፕሮግራሙን ይጀምራል (ሳተናው፣ ኤፕሪል 26/2020)። ቴዎድሮስ ለጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ያለውን ጥላቻ መደበቅ አልቻለም። ስለ "ፒኮክ ፖለቲካ" እና ስለ አንበሳ ታሪካዊነት ጥሩ ማብራሪያ ከሰጠ በኋላ ወደ ዋናው ጉዳዩ ተሸጋግሮ፣ ዐቢይ የህወሓት/ኢሕአዴግ አባል መነበራቸውን፣ ህወሓት ለፈጸማቸው በደሎች ሁሉ ተጠያቂ ናቸው ብሎ ሊያሳምነን ሞክሯል። ለሠነዘራቸው ክሶች አሳማኝ መረጃ አላቀረበም፤ ለምሳሌ ዐቢይ የስለላ ድርጅት ውስጥ ሲሠሩ በነበረ ወቅት የፈጸሙትን ወንጀል መረጃውን ከየትና እንዴት እንዳገኘ አልነገረንም።

ታየ ደንድአ፣ “ፒኮክ (ጣዖስ) ዙሪያ የተጧጧፈው ውዝግብ” በሚል ርእስ ከላይ ለተነሡት አስተያየቶችና ተቃውሞዎች ምላሽ ሰጥቶአል። (ሳተናው፣ ኤፕሪል 23/2020) ታየ የብልጽግና ፓርቲ ባለ ሥልጣን ነው፤ እዚህ ያቀረበው መልስ የግሉ ይሁን የፓርቲው ግልጽ አይደለም። ለማንኛውም፣ “ሥራ መፍታት፣ አገር በመገንባት ከመሳተፍ ይልቅ ለማሰናከል ይጣደፋል” ሲል ይጀምራል። ቀጥሎ፣ አንበሳ፣ ግመል፣ ወዘተ፣ ሁላቸውም ነቀፌታ ከማስነሳት በተቀር የፒኮክን ያህል የማስተባበር ብቃት የላቸውም ይለናል፤ የወፊትን ባህርይ ይዘረዝራል። ፒኮክ ብርሃን ሲያርፍባት ህብረቀለማት ታመነጫለች፣ የተለያዩ ድምጾችን ታወጣለች፤ በፍቅር፣ ካልሆነም በጠብ አትቻልም፤ ብሔር ብሔረሰባዊነትንና ዓለም አቀፋዊነትን ትወክላለች! አንበሳ ስብረው ነው! “ፈጣሪ ኢትዮጵያንና የጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዓቢይን የሥልጣን ዘመን ይባርክ። ሀገርና ህዝብ (አትራፊ) ናቸውና!” ሲል ይደመድማል።

lion2

ከላይ በተነሳው ክርክር ላይ እንድጽፍ ያነሳሳኝ በፈረንጆች አቆጣጠር፣ ማርች 2006 “The Future Of Our Legacies” (Tecolahagos.com) በሚል ርእስ ያስነበብኩትን ስላስታወሰኝ ነው። በወቅቱ አነጋጋሪ የነበረው ጒዳይ ህወሓት የአንበሳን ምስል ከኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ ሊያነሳ ነው መባሉ ነበር። ወቅቱ “አንበሳ” አውቶቡስ ወደ ጎን ተደርጎ “ሰላም” አውቶቡስ የገነነበት ወቅት ነበር። እኔም፣ አንበሳ በኢትዮጵያና በዜጎቿ ማንነት ምን ያህል ቊርኝት እንዳለውና ይህን ቅርስ ማስጣል አስፈላጊም ቀላልም እንዳይደለ፣ የምልክቱን ታሪካዊነትና ሂደት በመጠቃቀስ ለማስረዳት ሞክሬ ነበር። በአንጻሩ፣ ዛሬ "ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ" እንጂ የሚሉትን ታሪክ፣ ኃይማኖትና (መጽሐፈ ራእይ 5፡5) የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ አይደግፋቸውም። የአንበሳን ውበትና ግርማ በምናብ ማየት ብቻ ይበቃል ባይ ነኝ። ጉዳዬ፣ በዋናነት የጣዎስ መደመር ሳይሆን የአንበሳ መቀነስ ነው! የጣዎስ ጥንታዊት አለመሆን ሳይሆን፣ በዘፈቀደ መደመሯ ነው።

ላሁኑ፣ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ በብዕር ስም “እርካብና መንበር” (2009 ዓ.ም፣ 173 ገጽ) መጽሐፋቸው፣ “ኃይልና ሥልጣን በኢትዮጵያ” (ም. 4፣ ገጽ 47—73) ላይ ስለ አንበሳ ያሠፈሩትን በማጣቀስ አስተያየቴን ልስጥ።

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ፣ በኢትዮጵያ የምናየው የኃይልና ሥልጣን አደረጃጀት ጦረኛነትን፣ ኃይማኖተኛነትን፤ ጭካኔና ጋብቻን አካትቶ ነው ሲሉ በትክክል አስቀምጠዋል። ባጭሩ፣ አንበሳ “ጀብዳዊ ጭካኔ”ን ስለሚወክል ይቀየር ነው የሚሉት። የፒኮክ ብቅ ማለት ከዚህ ጋር ይያያዛል።

ጠ/ሚሩ በመጽሐፋቸው ውስጥ ያላገናዘቡት ጉዳይ ያለ ይመስላል። አንደኛ፣ የኢትዮጵያ መሪዎች የተገኙበትን ዘመን፣ ሥልጣን ለመያዝና ለማደራጀት የነበራቸውን አማራጮች፣ ከውስጥና ከውጭ የገጠማቸውን እንቅፋት፣ የገዙትን ሕዝብ የኑሮና የእውቀት ደረጃ ያማከለ አይመስልም። በዘውዳዊ አገዛዝ ዘመን ቀርቶ ዛሬም እንኳ "በምርጫና በሕዝብ ፍላጎት" የቆመ መንግሥት የለም!! አፄ ኃይለሥላሴ በየሥፍራው ቤተመንግሥት ማሠራታቸው ለምን እንደ ስሕተት ታየ? እንደ ዛሬ ስልክ፣ የመኪና መንገድ፣ አውሮፕላን በሌለበት፣ ድንቊርና በበዛበት ሕዝብ የምን አገር ዜጋ እንደሆነ በምን እንዲያውቅ ነው? ኃይለሥላሴ “በዚያው በጥንቱ ባህል ነው የቀጠሉት” (ገጽ 63) ብለውናል። ንጉሥ በንጉሣዊ ሥርዓትና ባህል እንጂ ድሮስ በምን ሊቀጥል ኖሯል? የህወሓት/ኢሕአዴግ "አብዮታዊ ዲሞክራሲ/ልማታዊ መንግሥት" የደርግ "አብዮት" ቅጥያ እንጂ ሌላ ምን ሊባል ይችላል?

ኃይለሥላሴ እውነት በትምህርት ቤቶች ፈንታ ቤተመንግሥት አሠሩ? ስድስት ኪሎ የነበረውን ቤተመንግሥታቸውን አይደል የመጀመሪያውን ዩኒቨርሲቲ ያደረጉት? የህወሓት/ኢሕአዴግን 'ትምህርት ያስፋፋን እኛ' ትርክት ለማጽናት ካልሆነ በስተቀር፣ ኃይለሥላሴና ዘመናዊ ትምህርትን መነጣጠል ወንጀል ነው!  ወቀሳው ባይሆን ፈጣን እድገት አላመጡም ቢሆን ያምራል! ካነሳን አይቀር፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቀድሞው ስሙ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተብሎ ይጠራ! የሚገርመው፣ ኃይለሥላሴ እና አንበሳ በቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ክብር መነፈጋቸው ሳያንስ ዛሬም መደገሙ ነው! መንግሥቱ ኃይለማርያም ያደረጉት ህወሓት/ኢሕአዴግ ካደረገው ምን ያህል ይራራቃል? መንግሥቱ በገዙበት ዘመን ዓለም በሁለት ካምፕ ተወጥራ ነበር፤ ከውስጥ አስፈሪ ርእዮተ ዓለማዊ ፍጥጫ ተደቅኖ ነበር። ዛሬም በመልክ እንጂ ተግዳሮቱ አልረገበም! (መንግሥቱ እንደ ህወሓት/ኢሕአዴግ ስሕተት አልፈጸሙም ለማለት አይደለም።) ለመሆኑ፣ ጠ/ሚ ዐቢይ የቀደሙትን መሪዎች በደል ሲዘረዝሩ እንዴትና ለምን ህወሓት/ኢሕአዴግን አልጨመሩም? 

ሁለተኛ፣ ስለ ወንድና እንስት አንበሳ ባህርይ ሲተርኩ፣ እንደ ተቃዋሚዎቻቸው ሁሉ፣ አንበሳ ሰብዓዊነት እንደሌለው የዘነጉ ይመስላል። የሰውን ባህርይ አንበሳ ውስጥ መፈላለግ አንበሳን ስብእና አያጎናጽፈውም! ሦስተኛ፣ የኖሩ ብሔራዊ ምልክቶች ውይይት ሳይደረግባቸው በዘፈቀደ መቀየር ለሚቀይረው አካል ተኣማኒነትን ሲነሳ፣ ዜጋን ባለቤትነት ይነፍጋል፤ ተቃውሞም ያስነሳል። አራተኛ፣ የቀደሙ መሪዎቻችን ሕዝብን ማማከር ሳያስፈልጋቸው ነው አንበሳን የተከሉት፤ አሁንም የተደረገው ይኸው ነው። አምስተኛ፣ ኃይማኖት እንደ ሶሻሊዝም ካፒታሊዝም ርእዮተ ዓለም ነው። የጠ/ሚሩ ሙግት አንበሳን በፒኮክ ለመተካት ብቻ የታቀደ መስሏል። እንስቷን አንበሳ ሠራተኛ፣ ወንዱን ከመተኛትና ከመሳረር ውጭ ሥራ ፈት አስመስለውታል። ስድስተኛ፣ በግፍ ላይ ለመነሳት አንበሳ ከጠቀመ ችግሩ ምኑ ላይ ነው? ሰባተኛ፣ መናቆር፣ ጠበኛነት፣ በኢትዮጵያ ብቻ አልተከሰተም። ሁሉ አንጻራዊ ነው። ሁሉ አንጻራዊ ነው። ጥንት አንበሳ ያስፈለገው፣ የገዥውን ዘላለማዊነት በተገዢው ውስጥ ለማስረጽ ነው። ዛሬ መንገዱ በኤኬ47 እና በዲጂታል ነው። በብሔር የበላይነት ለመግዛት የታሰበው በአንድ ገጽታው ከሽፏል እንበል?!

ስምንተኛ፣ ጀግና "አንበሳ" መውደድ (ማምለክ) የሰው ሁሉ ባህርይ ነው፤ ሰው አምላኪ ነው፤ እውነተኛውን አምላክ ሳያውቅ ላናሳ ፍጡራን እና እሳቤዎች ይንበረከካል። ዘጠነኛ፣ "ጀብዳዊ ጭካኔ"ን ለማስቀረት የአንበሳን ረብሸኛነት ሽረን ሰላምን በወፍ እንሞክር ነው? በ1921 ዓ.ም. ከባህር ማዶ ብቅ ያለችው "ንስረ መኮንን" አውሮፕላን ግን አንበሳ እንጂ አይስማማኝም ብላ መስክራለች! ባለ ንስሯ አሜሪካ እንዲህ ሠልጥናና በልጽጋም ማህበራዊ ሰላም በማጣት ከ163 አገሮች መሓል 128ኛ ነች፤ በሳውዲና በደቡብ አፍሪካ መሓል ማለት ነው፤ ኢትዮጵያ 131ኛ፤ ጋና 44ኛ፤ ኬንያ 119ኛ፤ ሶማልያ 163ኛ ነች። (ግሎባል ፒስ ኢንዴክስ፣ 2019) ፈርሃ እግዚአብሔር ጠፍቶ ሃብት፣ እውቀትና ህገ ደንብ ብቻውን አያዋጣም። ከአምስት አንድ አሜሪካዊ በአእምሮ/በመንፈስ ጭንቀት ማስታገሻ ኪኒን የሚንቀሳቀስ ነው። እኛም ዐይናችን እያየ የአሜሪካን ግልባጭ ካልሆንን ብለን እናስቸግራለን። ዜጋን ያላሳተፈ ልማት፣ ጥራት የሌላቸው የትምህርት ተቋማትና የፖለቲካ አደረጃጀቶችን እንፈጥራለን። የሞራል ብቃት የተጎናጸፉ ዜጎች እስካላፈራን ግን፣ መቸም መልካም መሪ አናፈራም፤ ግለኛነትን እንጂ አብሮነትን አንገነዘብም።  

Nisre Mekonnen2

አስረኛ፣ ሥልጣን “በግልበጣ ወይም በውርስ እንጂ በምርጫና በሕዝብ ፍላጎት አይደለም” ብለውናል። (ገጽ 49) ጣዎስ ትረዳን ይሆን? ጣዎሲት የ “መደመር” ምልክት ትሁን ካልን የርሷስ የወደፊት ዕጣ “በውርስ ወይስ በግልበጣ” ይጠናቀቅ? በዲሞክራሲ እመቤትነቷ የምትኩራራው አሜሪካ የሴቶችና የጥቊሮችን የመምረጥ መብት ካስከበረች ገና መቶ ዓመት አልሞላም! በደረስንበት የቀድሞውን መመዘን አግባብ የማይሆነው ለዚህ ነው። ዛሬ “ቊጢጥ በጣሽ፣ ፋቂ” አንልም። ዛሬ ትምክህተኛ፣ ፊዲስት፣ ወያኔ፣ ነፍጠኛ፣ መንጋ … ነው። ውጤቱ ያው ማድማት መደማማት ማዋረድ መዋረድ ራስን መካብ ትዕቢት ነው! እንግሊዝ ህንድ አሜሪካ፣ አፐር ክላስ ሎወር ክላስ፤ ሚድል ክላስ፣ ኢሚግራንት፤ ብላክ ኋይት፤ ከዚያ በጾታ በውፍረት፣ ማህበራዊ እርከኖችን አበጃጅተዋል። ከሰማይ በታች ምንም አዲስ ነገር የለም!

ጣዎስ በርራ እንደ መጣች በርራ ሂያጅ ነች። አንበሳን ግን አትመጥንም! ጠ/ሚሩ ለጣዎስ ሐውልት ማቆማቸው ብሔራዊ ውዝግብ ሊያስነሳ ባልተገባ። አሁንም ቢሆን መፍትሔው ቀላል ነው፦ ዜጋ ይጠየቅ፦ ከአንበሳ ከጣዎስ?

መንበርና እርካብ

ምትኩ አዲሱ

ሚያዝያ 30/2012 ዓ.ም.

Illustration credit: Malcolm Livingstone