ይህን ጽሑፍ የለጠፍነው ከሦስት ዓመት በፊት ነበር፤
መስከረም 24/2014 ዓ.ም. ስለሚቋቋማው አዲስ መንግሥት
ሶሻል ሚድያ የሚያሠራጨውን ሐተታ በመመልከት ዳግመኛ ለአንባቢ አቅርበናል።

ርዕሰ አንቀጽ

ፖለቲከኛ ቀስ በቀስ ነብይ ነኝ ይላል

ሰውን በሥልጣን ማመን ሰውን አለማወቅ ነው! መካሪ ከሌለው፣ ምክር ካልሰማ፣ ተጠሪነትን ከናቀ፣ ጤነኛው ሰው ውሎ አድሮ ራእይና ቅዠቱን መለየት ያቅተውና ራሱን አምላክ ያደርጋል። ከአርባ ዓመት በላይ የታላቅነት፣ የህዳሴ፣ “የከፍታ” ምኞት ሰማን፤ እስካሁን በተስፋ እንጂ አንዱንም አላየን።

ካልረሳን፣ ከሐምሌ 26 እስከ ጳጉሜ 5/2009 ባለ10-ሁነት “የከፍታ ዘመን” ታውጆ ነበር።

ነሐሴ 26 2009 ዓ.ም የፍቅር ቀን፤ ነሐሴ 27 ቀን 2009 የእናቶችና ህጻናት ቀን፤ ነሐሴ 28 ቀን 2009 ዓ.ም የአረጋውያን ቀን፤ ነሐሴ 29 ቀን 2009 ዓ.ም የሰላም ቀን፤ ነሐሴ 30 ቀን 2009 ዓ.ም የንባብ ቀን፤ ጳጉሜ 1 ቀን 2009 ዓ.ም የአረንጓዴ ልማት ቀን፤ ጳጉሜ 2 ቀን 2009 ዓ.ም የመከባበር ቀን፤ ጳጉሜ 3 ቀን 2009 ዓ.ም የሀገር ፍቅር ቀን፤ ጳጉሜ 4 ቀን 2009 ዓ.ም የአንድነት ቀን፤ ጳጉሜ 5 ቀን 2009 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቀን። [“የፍቅር ቀን” ምንድነው? ምን ይደረግበታል?]

በዓመቱ፣ አራተኛው ፓትርያርክ መርቆሬዎስ እና ስድስተኛው ማትያስ በመንግሥት አስታራቂነት መንጋዎቻቸውን አስማሙ። በዚያው የዮሐንስና የምኒልክ የ1870 ዓ.ም. የቦሩ ሜዳ ታሪክ ተደገመ። ሁለት ፓትርያርክ በአንድ መንበር ግን ተሰምቶ አያውቅም!

በዓመቱ፣ በአገራችን የመጀመሪያው የሰላም ሚኒስቴር መ/ቤት ተቋቋመ! መንግሥት የቤተክርስቲያንን ሥራ ጨምሮ ሊሠራ ይሆን? አንድ ነገር ግልጽ ይሁን፣ መንግሥት በቤተክርስቲያን ጉዳይ ጣልቃ መግባቱ ለቤተክርስቲያን አይበጃትም! ቤተክርስቲያን በጠባብ መንገድ መጓዟ ብቻ ነው ብርታቷና ክብሯ። የተናቁ ምዕመን ዓለምን አናወጡ። ሕዝብ ያከብራቸው ነበር። ከኢየሱስ በቀር ለቄሳር አንሰግድም ብለው በቊም ነደዱ፣ ተሰደዱ፣ ለአናብስት ተጣሉ። የሮም ገዥ ቆስጠንጢኖስ በመስቀል አመነ፤ ቤተክርስቲያንና መንግሥትን አስማማ። ቤተክርስቲያን፣ መንግሥት ሲበድል የመገሠጽ ሥልጣኗን በዚያው ተቀማች።

በአስራ አንደኛው ምዕተ ዓመት (ከ1096 – 1271 እ.አ) የአውሮጳ ክርስቲያኖች ኢየሩሳሌምን ነጻ ለማውጣት ዘመቱ፤ ሦስት ሺህ ሦስት መቶ ስልሳ ኪሎ ሜትር በእግር ተጓዙ። ብዙ ይሁዲዎችና ሙስሊሞችን ገደሉ። በኢየሩሳሌም፣ በትሪፖሊ፣ በአንጾክያና ኢዴሳ ቱርክ ከተሞች ላይ ነገሡ። በወንጌል ያሳብቡ እንጂ መነሻቸው ስስት ነበር። ስስት። ክርስቶስን አይወክሉም ነበር፣ በመስቀል ስም ነግደው በለጸጉ።

ዛሬስ ምን ያህል ርቀን ሄደናል? በአሜሪካ (በኢትዮጵያ) የምናየው ነው። መቶ የአሜሪካ ነጭ ወንጌላውያን መሪዎች ዘረኛ ትረምፕን ለመምረጥ ሰኔ 2016 (እ.አ) ዴንቨር ላይ ተዋዋሉ፤ ትረምፕ ወንጌል አማኝ ናቸው ብለው አወጁ። ተከታዮቻቸውን በነጭነት ወንጌል አባበሉ። ትረምፕ ሲያሸነፉ 81 በመቶ ድምጽ ያገኙት ከነጭ ወንጌላውያን ነበር። ብዙዎች ዛሬ የወንጌልን ንጽሕና አዋርደው ከጥቅምና ከይሉኝታ ለመላቀቅ ኃይል አጥተዋል። ከሰማያዊ ጥሪ ተዘናግተዋል። የትረምፕን ከትዳር ውጭ መባለግ = ‘ሥራቸውን እንዳያከናውኑ አያግዳቸውም፣ ሁሉም የሚያደርገው ነው’ አሉላቸው፤ የትረምፕን ዘረኛ ስድብና የማያቋርጥ ውሸት = ‘ግልጽ መሆናቸው ነው’ ብለው መሰከሩ! “ዲያቢሎስ እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ ወሰደው፥ የዓለምን መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውንም አሳይቶ። ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ አለው።” አውሮጳ (ሃንጋሪ፣ ሆላንድ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ አውስትራልያ፣ ራሽያ፣ ወዘተ) ዜጋ ለማነሳሳትና ከእስላምና ከአፍሪካ አገራት የሚፈልሱትን ለማገድ፣ ትቶት የኖረውን የ “ክርስቲያን” ባንዲራ ዳግም እያውለበለበ ነው።

በወንጌል የፖለቲካ ጫወታ፣ ለወንጌልም ለፖለቲካም አይመች። ዕንቊላል ቀስ በቀስ በእግሩ ይሄዳል፤ ፖለቲከኛ ነብይ ነኝ ይላል! የኢትዮጵያ ወንጌላዉያን ከአሜሪካ ቲቪ ወንጌላዉያን ጋር መዋላቸው መታመንን ነስቶአቸው ይሆን? “ተደምረናል!” እንዴት ይተርጎም? የምእመን ቊጥር፣ የነብያት ዓይነትና ስስት የቤተክርስቲያንን ሥልጣን በአደባባይ ሲያዘርፏት እያየን ነው። የወቅቱ መነጋገሪያ፣ ዘይት፣ ውሃ፣ አፈርና አልቤርጎ አለመሸጥና አለማከራየት ሆኗል! የማይመች ባልንጀርነት ፍሬ አልባ ያደርጋል። “የዚህ ዓለም ልጆች ለትውልዳቸው ከብርሃን ልጆች ይልቅ ልባሞች ናቸው።” (ሉቃስ 16፡8) የወንጌላውያን ጥያቄ ሊሆን የሚገባው የነበረ ይህ ነው፦ ኢየሱስን ወይስ ሰውን ያገንናል? የወንጌልን ንጽሕና ይቀናቀናል ወይስ ያቀናል? በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረን ሰው ያከብራል ወይስ ያዋርዳል?

. . . .

የዛምብያ ፕሬዚደንት ችሉባ (1991 – 2002 እ.አ) ጴንጤቆስጤአዊ አማኝ ነኝ ብሎ ተነሳ። የመንደር ነብያት ከፍ ከፍ አደረጉት። ዛምብያን “የክርስቲያን አገር” አሰኝቶ ህገ መንግሥቱን ለወጠ። እግዚአብሔር ቀብቶኛል አለ። ሚስቱን ፈትቶ ሌላ አገባ። ምንም ያልነበረው ሠርቶ አደር፣ ንብረቱ እጅግ በዝቶ 46 ሚሊዮን ዶላር ደረሰለት፤ በሌብነት ያከማቸው ነበረ። የኬንያ ዑሑሩ ኬንያታም ኬንያ “የክርስቲያን አገር” ነች አለ። የቡሩንዲ ፕሬዚደንት ንኵሩንዚዛማ ህገ መንግሥቱን ለውጦ እስከ 2034 (እስከ 80ኛ ዓመቴ) እገዛለሁ ብሏል። (80 መድረሱን እንኳ እግዜር ያውቃል።) ጥያቄ ያነሳ፣ “በሽብርተኛነት” አበሳውን ያያታል። “ሃሌሉያ” አሰኝቶ የግሉን የእግር ኳስ ክለብ አደራጅቷል። “ሃሌሉያ”ን ማን ይድፈር? “ሃሌሉያ” የተሸነፈ እለት አጫዋቹ ዳኛ በድብደባ ቢያበቃለት ደስታውን አይችለው!

“እግዚአብሔር ቀብቶኛል” በሥልጣን ለመርጋትና ለሌብነት አመቸ። የናይጄሪያ ጉድለክ ጆነተን (ከ2010 – 2015 እ.አ.) በኢየሱስ ተመሰለ። የኡጋንዳ ሙሴቬኒ ለምን ይቅርባቸው? ወንጌል አማኝ ነኝ አሉ። ሲገዙ 32ኛ ዓመታቸውን ይዘው፣ የነገሥታት ንጉሥ (በቋንቋቸው “ሳባጋቤ”) ልባል ብለዋል። ሳባጋቤ ለነገሩ ከሙጋቤ ይገጥማል፣ ሳባጋቤ - ሙጋቤ።

ዶ/ር ዐብይ አሕመድ፣ እናታቸው (ነፍስ ይማር) “ሰባተኛው ንጉሥ” ይሏቸው ነበረ። (1.ቴዎድሮስ፣ 2.ዮሐንስ፣ 3.ምንሊክ፣ 4.ኢያሱ፣ 5.ዘውዲቱ፣ 6.ኃይለሥላሴ፣ 7.ዐብይ።) በንግግራቸው አስታውሰው እናታቸውን ዘክረዋቸዋል። ሳናስበው ወደ ንጉሣዊ አገዛዝ ልንመለስ ይሆን?

የሩዋንዳ ካጋሜ የአሜሪካ ወንጌላውያን ስንት ጉድ አድበስብሰውላቸው ሥልጣናቸው ተራዝሞላቸዋል። እነዚሁ፣ እንደ አውሮጳዉያን አያቶቻቸው ሥልጣንና ንግድ አሳስቶአቸው፣ የካጋሜ በትረ ሥልጣን ራእዩ እስኪፈጸም መርጋት አለበት ብለው የአርባ ቀን ጸሎትና ፕሮፓጋንዳ አካሂደዋል። ካጋሜ ከሰባት ዓመት በፊት መውረድ ነበረባቸው። ቀድመው “2020 ራእይ!” አወጁ! አሜሪካዊውን ፓስተርና የሪፓብሊካን ፓርቲ ደጋፊ ሪክ ዋረንን በመንግሥት ሄሊቆጵጠር እንደ አገር መሪ አንበሸበሹት፤ ሪክ የነደፈው “የሰላም ፕላን” መተግበሩ፣ ከሃያ አምስት ዓመት በፊት የተከሰተው እልቂት እንዳይደገም ይጠቅማል ብሎ ሰባበከ። ካጋሜ ከአናሳ ቱትሲ ጎሳ ናቸው (ከመቶ 15ቱን እጅ)፤ የሁቱዎች ብዛት ከመቶ 84 እጅ ነው። ዛሬ በሩዋንዳ የጎሳ ሕዝብ ብዛት ማንሳት በህግ ተከልክሏል። ከግማሽ በላይ የፓርላማ ወንበር ለሴቶች ተከልሏል። ካጋሜ፣ ተቃዋሚአቸውን አስገድለው፣ አስረው፣ ከአገር አሸሽተው፣ እስከ 2034 እ.አ ለመግዛት ህገ መንግሥቱን አመቻችተዋል። በ “ሰላም ፕላን”፣ በንግድና በሴት ፓርላማ አባላት ስም ቅስም የለሽ ምእራባውያንን አጋር አድርገዋል። የሪክ ዋረን ጣልቃ ገብነት ግን በአገሬው ዘንድ ቅሬታ አስከትሏል።

የአሜሪካ ሰዘርን ባፕቲስት ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ብዙ ውጣ ውረድ ገጥሟቸዋል። ጥቍሮችን በባርነት መግዛት ወንጌል ከመስበክ አያግድም ሲሉ ኖረው፣ በድለናል፣ ይቅርታ፣ ማለታቸው ቀዳሚ ነው። ቀጥሎ፣ ከጥቍር አሜሪካውያን ጋር ሕብረት ፈጥረናል አሉ። በ173 ዓመት ታሪካቸው፣ የመጀመሪያውን ጥቍር ለሁለት ዓመት በመሪነት ሾሙ። ለጥቍሮች ያላቸው አናሳ ግምት ግን እንደ እባብ አድብቶ ኖሮ ትረምፕ ብቅ ሲሉ ቀና አለ፤ ነጭ አውሮጳዊ ደም የሌለበትን መናደፍ ጀመረ! ወጣት ኮበለለባቸው፤ ገቢ አሽቆለቆለ። አገር ውስጥ የሚሠራ እያለ፣ ባህር ማዶ ምን ወሰደን እንዳላሉ፣ ወደ አፍሪቃና ኤሽያ በብዛት ተንቀሳቀሱ። በዚሁ ድረገጽ “በቤተክርስቲያን ስም” በሚል ርእስ እንዳመለከትነው ማርስ ሂል የተሰኘ በኢትዮጵያና በህንድ ስም 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ዶላር አሰባስቦ አንድ ሚሊዮን የማትሞላ፣ የበለጠውን ለህንድ ቆንጥሮ፣ የተቀረውን ኪሱ ከትቷል። የሰዘርን ባፕቲስት ኮንቬንሽን ፕሬዚደንት በወንጌልና በአስቸኳይ እርዳታ ስም ኢትዮጵያ ድረስ ተጕዘው ፓርላማ ውስጥ አፈ-ጉባኤ አባዱላ ገመዳ ላይ እጃቸውን ጭነው ጸሎት ማድረሳቸው በዚሁ መስመር የሚቀኝ ነው። አቶ ኃይለማርያምና አባዱላ ከወንጌል ሸቃጩ ከማላዊው ቡሽሪ ጋር እጅለጅ ተያይዘው አደባባይ መውጣታቸው፣ የፖለቲካ ጭንቅና አለማስተዋል ያመጣው ነው ብለን እንለፈው።

rick

ጠ/ሚ ዐብይ የእምነት ሰው ናቸው ተብለናል። እግዚአብሔርን የሚፈሩ ይብዙልን! ኃይለማርያም አማኝ ነኝ ማለታቸው ግን ፋይዳው ምን ነበር? በመገናኛ ብዙሃን ቀርበው ከተናገሩት አንጻር፣ አማኝ መሆናቸውን ባይገልጹ ይሻል ነበር የሚሉ አሉ፤ ብቃት እንጂ ጎሳና ኃይማኖት የመሪ መለኪያ መሆን አይገባምና። ዐብይ የኢትዮጵያ ሁሉ መሪ ነኝ ብለዋል። አመራራቸውም ለጊዜው ይህንኑ እየመሰከረ ይገኛል።

. . . .

ይድረስ ለጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ። ግሪኩ ደይደሎስ ከእስር ቤት ለማምለጫ ክንፍ አበጀ ይባላል፤ ለልጁ ለኢካሮስም እንደዚሁ ከላይ በላባና በሲባጎ፣ መሠረቱን ከሰም አድርጎ ክንፍ አበጀለት። እንደ አባት እንዲህ ሲል መከረው፦ ልጄ፣ በጣም በከፍታ አትብረር፣ ክንፍህን የፀሐይ ሙቀት እንዳያቀልጥብህ፤ በዝቅታም አትብረር፣ ላባህን የባህር እንፏሎት እንዳያረጥብብህ፤ ቀልሎህ ወይ ከብዶህ ከሰማይ ተወርውረህ እንዳትወድቅ። ባጭሩ፣ ንቍ ሁን፤ ማንነትክን አትዘንጋ ብሎ መከረው።

መሪ ራሱን ብቸኛ ተዋናይ አድርጎ ማሰቡ አደጋ አለበት። በየእርከኑ ተተኪ የማያፈራ መሪ እራሱንና የሚመራውን ማህበረሰብ ያመክናል፡፡ ከቅርብ ታሪካችን እንማር፡፡ ሊመክሩት፣ ሲያስፈልግም ሊቃወሙት ለሚችሉ ብቊና ታማኝ አማካሪዎች ሥልጣን ማጋራት፣ ራሱንና የሚመራቸውን ከአደጋ ለመጠበቅና ዓላማውን ለማስቀጠል ብልኃቱ ነው። መሪ ማንነቱንና ተልእኮውን ላፍታ መዘንጋት የለበትም። “በከንቱ … ሰይፍ አይታጠቅምና … ቍጣውን ለማሳየት ክፉ አድራጊውን የሚበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ ነው። (ሮሜ 13:4) ሰይፍ በእጁ ይዞ የማይጠቀምበት ወይም ለከንቱ ረብ የሚሳሳ መሪ ፍጻሜው አያምርም። (1ኛ ሳሙ 15) … እግዚአብሔር የኃይልን በትር ከጽዮን ይልክልሃል፤ በጠላቶችህም መካከል ግዛ!” (መዝ 110፡2)

ደግሞ መሪ፣ ሰይፍ ሁለት አፍ እንዳለው ላፍታ መርሳት የለበትም!                                                                                                                                                                                                           

10/3/2018 (ኅዳር 2/2011 ዓ. ም.)

ዐብይን በባራክ ያንብቡ