ሪሚክስ ይሉታል

Remix

በአገራችን፣ የቆዩ መዝሙሮችን በአዲስ መልክ ማቀናበርና መዘመር ከተጀመረ ሃያ አምስት ዓመት ያህል ሆኖታል። ይህን ባህል ሪሚክስ ይሉታል። ልምዱም ቃሉም ከምዕራቡ ወንጌላውያን የተወሰደ ነው፤ ምዕራቡ ወንጌላውያን ደግሞ ባህሉን የወሰዱት ከዓለማውያን ነው። ቴክኖሎጂ ባደገ መጠን ተግባሩን አቀላጥፎታል። ከዚያማ መቆሚያ የለው፤ ሮክ፣ ጋስፐል፤ ጃዝ፣ ብሉግራስ እያለ ይቀጥላል። ዘፋኝ = አርቲስት። ዘማሪ = ክርስቲያን አርቲስት ተሰኘ። ሮክ = ክርስቲያን ሮክ። ኮንሠርት = ክርስቲያን ኮንሠርት። ከበስተጀርባ እንዲህ ልበስ (በአንድ ቪዲዮ ላይ ሰባት ያማሩ የልብስ ዓይነቶችን ቆጥሬአለሁ)፣ ብላ/አትብላ፤ በል/አትበል፣ ና/ሂድ የሚሉ ነጋዴዎች ከህግ፣ ከመድረክና ከማስታወቂያ ባለሙያዎች ጋር ተሰለፉ። የመድረክ ዝግጅት ብቻውን ባለ ብዙ ወጪ/ገቢ መለስተኛ ኢንዱስትሪ ወጣው። ገበያተኛ እንዲስብ ክሮስኦቨር አሉ (ክሮስ፣ ድንበር ማደብዘዝ እንጂ መስቀል እንዳይመስለን፤ ሪሚክስ ዳግም መቀየጥ)። ምእመን በቀደሙ ዝማሬዎች መሰላቸቱን አይተው። ሲቀላቀል እንደሚያዋጣ አውቀው። ምእመን የተሰላቸው አንድ ጆሮ ለዓለም አንድ ጆሮ ለእግዚአብሔር በመስጠቱ እንደሆነ አልነገሩንም።

ለሦስት ወር የሙዚቃ መሳርያ ቢያርፍ፣ የመድረክ ላይ መብራትና ትርዒት ቢቋረጥ፣ ሕዝቡን አንድ ሰው ብቻ በዝማሬ ቢመራ፣ በዝግታ ማምለክ ቢጀመር ምን ውጤት ያስከተል ይሆን? (በሰማይም እንኳ እኲል ሰዓት ዝምታ ሆኗል፣ ራእይ 8፡1፤ ዕንባቆም 2፡20፤ ኢሳይያስ 30፡15፤ መዝሙር 46፡10፤ ያዕቆብ 1፡19ማቴዎስ 6፡7)። ለስድስት ወር፣ ግማሽ ሰዓት ፍጹም ጸጥታ አምልኮ ቢጀመር፣ ግማሽ ሰዓት ከዘፍጥረት እስከ ራእይ በተከታታይ የቃሉ ንባብ ቢጀመርስ?

ጥያቄው ዞሮ ዞሮ ይህ ነው፦ ዝማሬ ምን ዓይነት ስሜት፣ በምን መንፈስ፣ ምን ዓይነት መንፈስ እንዲቀሰቅስ ታስቧል? ግለሰቦችን ወይስ ኢየሱስን ያገንን?

ሪሚክስ ያስፈለገው የቀደሙ ዝማሬዎች (አሮጌዎቹ) ያልተወለወለ ቅንብራቸው ወጣቱን ስለማይጥመው እና ዓለማውያንን በ (ዘመናዊ) ወንጌል ለመማረክ ነው ሲባል እንሰማለን። በጎ አሳብ ነው። ሪሚክስ ያስፈለገው ችሎታ ለማስመስከር እንደ ሆነስ? የገቢ ምንጭ ፍለጋ እንደ ሆነስ? የድሮውን ከመነካካት፣ አዲስ መዝሙር በዘመናዊ መሳርያ መዘመር አይቀልም? ወጣቱ፣ እናት አባቶቹ ያወረሱትን ዝማሬዎች እንዳይረሳ ማድረግ ለምን ቅድሚያ አልተሰጠውም? ቅዱስ ዝማሬ የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታና በብዙ ጸሎት የተገኘ እስከ ሆነ ድረስ ዘመን ያስረጀዋልና ነው? የዳዊት በገና በያህዌ ስም ሲቀኝ ክፉን መንፈስ ከንጉሥ ላይ ያባርር ነበር! የእረኛው ዳዊት ወንጭፍ ካሸበረቀ የንጉሥ ሰይፍ ይልቅ ሽብርና ተግዳሮትን ያስወግድ ነበር (1ኛ ሳሙኤል 17፡38-40)።

ዘመናዊ ስርቅርቅታና ሽርፍርፍታ ጢሳጢስ ዝላይ የበዛባቸው ድምፃድምፆች ወንጌል ለማዳረስ ይዋሉ ማለት የራሱን ስውር አበሳ ቋጥሯል። የጥቊርና ነጭ ፈረንጅ ይሻላል የሚል መስሏል። የአልበም ሽያጭ አንዱ አበሳ ነው፤ በስርቅርቅርታው ተገን ዕውቅና መገብየት ሌላኛው አበሳ ነው፤ በጸጋ ታሽቶ ዘመን ያሻገረን በረከት ቅጥአንባር አሳጥቶ መበተን ሌላኛው ነው፤ የሌላን ሰው የፈጠራ ውጤት ያለ ድካም የራስ ማድረግ ሌላኛው ነው። ይህም ዓለማዊ ኮረብታ ላይ እንደ መክረም ነው። ኮረብታው ቊልቊለትም ስለ ሆነ አያስተማምንም። ዘሪቱ ከበደ ጢሳጢስና ዳንኪራ ትቼ ያልተነካካ የጥንቱን ዝማሬ ጠብቄ ብመጣ፤ ምን ጒድ ነው፤ ከከረምኩበት አይሻል ብዬ ከደጅ ተመልሻለሁ ብላለች።

ሪሚክስ የቅላጼ ውበትና ቅንብር ሊታይበት ይችላል፤ መቀደስን እና የቅኔን ውበት ግን አይተካም። እግዚአብሔር ከመቀደስ እንጂ ከድምጸ መረዋነት ጒዳይ የለውም። እግዚአብሔር ከመቀደስ እንጂ ከሙዚቃ ቅንብር ደንታ የለውም። የሙዚቃ ጋጋታ ይልቅ መንፈስ አደንዛዥ ዕጽ ሆኖ እንዳይሆን! ሙያ ያነሰው ሼፍ ምግቡ ላይ ቅባት ሞጅሮበት መቅኖ አሳጣው ነው ነገሩ፤ ጋጋታን ዝማሬ ነው አንበል!

ይህን ያስተዋሉ “ማኅሌት” አሰኝተው የሕይወት ምስክርነታቸው ላልጎደፈና ውብ ቅኔ ከውብ ሙዚቃ ጋር ለደረደሩ በያመቱ ዕውቅናና የዶላር ሽልማት መስጠት ጀምረዋል። በጎ አሳብ ነው እንበል፤ በጎ ነው ማለት ግን አሳቡ ችግር አያስከትልም ማለት አይምሰለን። ጥሩ ዘማርያንን ማበረታታት (ጥሩ ያልሆኑትን መገሠጽ) የቤተ ክርስቲያንን ድርሻ እንዴት ይሻማል ወይም ያጎለብታል? በአልበሞች ግብይት ላይ ተጽእኖ መፍጠሩስ? በሌላ አነጋገር፣ ተሸላሚ መሆን ካልተሸለሙት ይልቅ አልበም ያሸጣል፤ የአገልግሎት ጥሪ ያስገኛል ማለት ነው። ለቤተክርስቲያን ላለመገዛት የራሳቸውን ቤተ ክርስቲያን ላቋቋሙ፣ በማኅሌት አምሳያ የራሳቸውን ድርጅት እንዳይፈጥሩ ምን ያግዳቸዋል? ስለ ዘመረ ገንዘብ መሸለም፣ ዝማሬን ማትረፍያ ካደረገው በምን ይለያል? ለዘማሪ ደመወዙ በቅንነትና በጸጋ ብቻ መዘመሩ አይደለም ወይ?

አብዛኛዎቹ የአገራችን ዘማሪዎች ከቤተክርስቲያን ሥልጣን ሥር ላለመተዳደር ከወሰኑ ሰንብቷል። እንደ ፖለቲከኞቹ ሁሉ ክልል በክልል ሆነዋል። ዘማሪም ፓስተርም እንዳንሆን እስቲ ከልክሉንና እናያለን ብለው በስማቸው ቤተ ክርስቲያን ካቋቋሙ  ሰንብቷል። ንግድና ዝማሬ ከተጣመሩ ሰንብቷል። ቤተክርስቲያንም እኮ የወጣቱን አያያዝ አላወቀችበትም፤ ዘማሪያንም ኑሮአቸውን ማሸነፍ አለባቸው!

የምዕራቡ ወንጌላውያን አኳኋን ሥር ከሰደደ ሰንብቷል። ክብርና ታላቅነት ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለአርቲስትነት ከሆነ ሰንብቷል። ዝማሬ ልብ ውስጥ ሠርጾ ወደ አምላክ ማስቀናቱ ሳይሆን “ተወዳጅነቱ” (“ላይክ” ነቱ) መብዛቱ ተመርጧል፤ አልበም ለማሻሻጥ፣ ዘማሪን ለማግነን። (በዩቱብና በፌስቡክ የተለጠፉትን አስተያየቶች ያንብቡ።) ተወዳጅነት ደግሞ በፍራንክ ይከራያል፤ አንድ መቶ ላይክ” ከፍሎ አንድ መቶ ሺህ ማድረስ ተችሏል፤ ብዙዎች ተሠማርተውበታል። ይህ አካሄድ ስለ ዘማሪያኑ ሕይወትና መነሻ አሳብ ምን ይነግረናል? ጌታ በዓለማዊ ጥበብ ይከብር እንደ ሆነ እስቲ ይንገሩና!

ይህም ሆኖ እግዚአብሔር ይሠራል፤ ከልብ የቀረበን ዝማሬ ጌታ አይንቅም። በተረፈ፣ የቀደመውን አናደብዝዝ። አንድ ዝማሬ፣ ወዳጆቻችንን፣ የመከራ ወይም የምሥጋና ስሜቶችን፣ ክረምት ወይም በጋን፣ ደጋ ወይም ቆላን ያስታውሰናል። ትዝታዎቻችንን ዘመናዊ ማድረግ ወይም ጨርሶ መዘንጋት እውነትን  መርሳት ነው! ያካበትናቸውን ትዝታዎች በማሰባሰብ ወንድም ጌታያውቃልና እህት ብሩክታይት እየሠሩ ያሉትን ሳንጠቅስ ሳናበረታታ አናልፍም።

የተዋጣላቸው ዝማሬዎችን መዘመር አይቻልም አይደለም። ጥያቄው ቅዱስ ዝማሬ መዝናኛ እንዳይመስል ምን ጥንቃቄ ይወሰድ ነው። ጌታ ሁሉን ነገር አዲስ ሲያደርግ ያኔ ዝማሬአችንም ሙሉ፣ ዕጹብ ድንቅ ይሆናል፤ ከመላእክት ጋር እንዘምራለን (መዝሙረ ዳዊት 138፡1፤ ራእይ 14:315:1-4)። እስከዚያው አምላካችን ደካማ በሚመስል ነገር ውስጥ ኃይሉን ይገልጣል። ለቀደሙት፣ “እንዳሳየሁህ ምሳሌ እንድትሠራ ተጠንቀቅ” ብሎአቸው ነበር (ዘጸአት 25፡40)። ደግሞ “ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፥ ማስተዋልም ይጋርድሃል” ብሎአቸው ነበር (ምሳሌ 2፡11)። ከዚህ የተለየ እንዲለን አንጠብቅ።

ምትኩ አዲሱ

ታኅሣሥ 1/2012 ዓ.ም.

ቀላሉን መንገድ | የማለዳ ድባብ | ከየት ተገኘሽ ሳልል | ቋንቋን በቋንቋ | ስደተኛውና አምላኩ | ሞት እና ፕሮፌሰር | ሕይወት ቢራቢሮ