ሐተታ ግምገማ

ሕይወት ቢራቢሮ’ እንደ ክርስቲያናዊ ምናብ

ጸጋዬ ገብረመድኅን ለብዙዎቻችን ይጠጥርብናል። የጠጠረብን በሩቁ ፈርተን ስለቆምን ይሆን? ሰውን መልመድ እኮ ጊዜና ትእግስት ይጠይቃል፤ መውደድ ብቻ ቶሎ ያግባባል። የአገራችን ሕዝብ አስተሳሰብ፣ አኗኗርና ህልውና በኃይማኖት የታነጸና የታጠረ በመሆኑ፣ ጸጋዬን ለመረዳት ቍልፉ፣ ሥራዎቹን ደጋግሞ ማንበብና የሕዝቡን ባህል፣ መልክዓ ምድሩንና ኃይማኖቱን ጠንቅቆ መረዳት ነው። ጸጋዬ በሥራዎቹ ሁሉ፣ ሕዝቡን አክብሮ እየዘከረው መልሶ የሰብዓዊነቱን ገጽታዎች በቴአትር ፈለግ በርብሮ የቅኔ ቅርስ ትቶልናል።

‘ሕይወት ቢራቢሮ’ ከጸጋዬ ቅኔዎች መሓል በዋነኛነት የሚጠቀስ ነው። ግጥሙ እንደ ተቀሩቱ ሁሉ በውበትና በጥልቀት የታነጸ ሲሆን፣ ከሌሎች ግጥሞቹ በተለየ መንገድ “የሕይወት መገኛዋ ከወደ ዬት ነው? ግሥጋሴዋስ ወደ ዬት ነው? ሰው ማን ነው? አለኝታው ምንድነው?” ይለናል።

የግጥሙ ስልትና ውበት ከነ ከበደ ሚካኤል ፍልስፍናዊ ትረካ ጋር ቢመሳሰልም[ሀ]፣ የጸጋዬ በሦስት መንገድ ይለያል፦ ሰብአዊነትን ከሠፈር እስከ አህጉር፣ ከአህጉር እስከ አህጉራት ድረስ ማስተሳሰሩ። ጥንትን ወደ ዛሬና ዛሬን ወደ ጥንት ማሸጋገሩ። በዚያው ልክ ስለ እውነት፣ ስለ ፍትሕ፣ ስለ እኵልነት፣ ስለ ነጻነት፣ ስለ ተፈጥሮ አድናቆት፣ ስለ አገር [መልክዓ ምድር] ፍቅር፣ ስለ ዘላለማዊነት፣ ስለ ሞት፣ ስለ አንድነት፣ ወዘተ ማውጋቱ[ለ]፤ በዚህም ያሰለቸና ያናከሰ ጠባብ መንደርተኛነታችንን መዋጋቱ። ሁለተኛ፣ ከለመድናቸው የወል ቤት ቅኝት ሌላ “የጸጋዬ ቤት” [ስምንትዮሽ] ቀመር መፍጠሩ። በመጨረሻም፣ ጽሑፎቹ መጽሐፍ ቅዱስን በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ ማጣቀሳቸው ነው። ይህ የመጨረሻው ነጥብ የጸጋዬን ጽሑፎች ‘መንፈሳዊነት’ ይበልጥ ጒልህ ያደርገዋል[ሐ]። ‘መንፈሳዊ’ በዚህ አገባቡ፣ በዐይነ ሥጋ የማይታየውን ይገነዘባል፣ በሚታየው አይረካም ወይም አይወሰንም፤ ባለፈው ላይ ተመርኵዞ የወደፊቱን ያበስራል፤ የሕይወትን ጥልቅ ምሥጢርና አጭርነት፣ የፍጥረትን ውስብስብነትና የራሱን ህልውና ለመረዳት ይጥራል ማለት ነው።  

መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ፣ በድምፀትና በተዘዋዋሪ የተመለከተባቸው ሥፍራዎች፦ 1/ ይኸ ይሆን አልፋ-ኦሜጋ?[ራእይ 1፡8]፤ 2/ ይኸ ይሆን አስቀድሞ ቃል?[ዮሐንስ 1፡1]፤ 3/ “ታላቅ ተራራ ሆይ፥ አንተ ምንድር ነህ? በዘሩባቤል ፊት ደልዳላ ሜዳ ትሆናለህ”[ትንቢተ ዘካርያስ 4፡7] = “አዋሽ ሕመምህ ምንድነው? ሕመምክስ አንተስ ምንድነህ? | ከውሀ ወዝ የተለየ፣ መቸስ ልዩ ንግርት የለህ”[አዋሽ፤ገጽ 97]፤ 4/ ክርስቲያናዊ አስተሳሰቦች በተዘዋዋሪ የተገለጹባቸው ቃላት ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፦ ጸጋ፣ ሞገስ፦ ይህም ስጦታ እንጂ በራስ የሚገኝ ስላለመሆኑ፣ የሚለበስ ስለመሆኑ። “ፀሐይ የኀዘን ማቅ አጥልቃ” ይላል[ራእይ 6፡12]። ብርሃንና ጭለማ ገናናነታቸውና ተፈራራቂነታቸው ተደጋግሞ ተገልጿል፦ በርቶ፣ ተጥለቅልቆ፣ ጮራ፣ መንጸባርቅ፣ ፀሐይ፣ ፈገግታ፣ ቀን፣ ብልጭታ፣ ውጋጋን፣ ንጋት። ሲመሽ፣ ሌት። ሞትና ሕይወት፤ በጋና ክረምት፤ ደስታና ኅዘን፤ ሰማይና ምድር። ግማደ መስቀል። ጽዋ፤ ፍስሃ፤ ሢሳይ…

ቢራቢሮ ሕይወት

ቢራቢሮ2የቢራቢሮ “ልደትና ዕድሜዋ” አራት የዕድገት ደረጃ አለው። ቢራቢሮ፣ ውል-ውል ብን-ብን የምትል ተንሳፋፊ፣ እንደ ጢስ፣ እንደ ላባ ገላ የቀለላት ነች። አካሄዷን ማወቅና መከታተል ያዳግታል። እርሷን ለመያዝ፤ ብዙ ማድፈጥ፣ “እንደ ልጅ” ለውበት መገዛትን ይጠይቃል። ሲቀርቧት አታስፈራም፤ ዐመድ ስለ ለበሰች ለአያያዝ አትመችም። ባለቅኔው ከሕይወት ጋር ያመሳሰላት ለዚህ ይሆን? ቢራቢሮ ከአበባው ላይ፣ምን አይተሽ ነው ከቅጠሉ | ከቄጠማው፣ ከለምለሙ፣ ሰምረሽ፣ አቅፈሽ መመሰሉ … አበባው ምድሩን ሲንተራስ፣ ያፈር ጽዋ ዕረፍቱን ሲገድፍ | ቢራቢሮ ያንቺስ ሞገስ፣ ለምንድነው አብሮ እሚረግፍ?

ቢራቢሮ፣ ምግቧን ከአበባ አበባ እየዘመተች ትቀስማለች፤ እግረ መንገድ እያዳቀለች ሕይወትን ታራባለች። ሥፍራ አትመርጥ፤ ከጕድፍ ላይ ተነሥታ ከሚያማምሩና ሽታቸው ከሚያውድ ዕፀዋት ላይ ታርፋለች። ረጋፊ ሆና፣ በረጋፊ ቀለማት አሸብርቃለች። የጥንት ግሪኰች፣ ውበትንና የሰውን ነፍስ በቢራቢሮ የመሰሉት፣ በሚታየውና በሚያልፈው ውስጥ የማይታየውና የማያልፈው ተሠውሮአልና ነው፤ የሚታየው ደብዛዛ፣ የማይታየው ግን ብሩህና ኦርጂናሌ ስለሆነ ነው።

ሕይወት ቢራቢሮ

ባለቅኔው፣ ሕይወት የምንላት አላፊ ስለሆነች አይተማመንባትም። ቢራቢሮን እንድታመላክተው ይማጸናታል። እስቲ አስተምሪኝ ቢራቢሮ | ሰው ለመባል አለኝታዬ | ቀድሞ የት ነው መነሻዬ | ሲመሽ የት ነው መድረሻዬ?… ። መነሻና መድረሻ እንዳለ አይክድም። ሕይወት ዑደት እንጂ አቅጣጫዋ ወጥ እንደሆነ አይገምትም። የፍጥረት ሂደት ይቀያየራል፦ ይነሣል፣ ይሮጣል፣ ይደፋል። ወዴት ነው የሚሮጠው? ደፋ ቀና የሚለው መውጫ ጠፍቶት ነው? ሲነሣ ሲሮጥ ሲደፋ፣ ሲያጋድል ሲያባዛ ሚዛን… | ሊፍተለተል ይወለዳል፣ ሳይነቃ ይወድማል ይባላል | ልደቱ ዕድሜና ሞቱ፣ አለማቋረጥ ይጓዛል …። በሕይወት ጅማሬና ፍጻሜ ጉዳይ ማብራሪያ ይሻል፦ ሲተረትማ ሲወጋ፣ ከየብልጭታው ውጋጋን | የሰው የአራዊት የአእዋፍ፣ ውስብስብ ነገደ ጉንዳን | ሲነሣ ሲሮጥ ሲደፋ፣ ሲያጋድል ሲያባዛ ሚዛን | በማይመጠን ታላቅ ኃይል፣ በተፈጥሮ ግዙፍ ሥልጣን | ሊፍተለተል ይወለዳል፣ ሳይነቃ ይወድማል ይባላል… | ሲነገር እንደ ሰማነው…። ይጠይቃል፤ መልስ ግን አይሰጠንም። ባለቅኔ ተግባሩ ማብራት፣ ራእይ ማወጅ እንጂ እጅ ይዞ መምራት አይደለም። ባለቅኔ ባለ ራእይ ነው። ራእዩን ከመፈንጠቅ ወዲያ አፈጻጸሙን መተርጎም ድርሻው አይደለም፤ አለዚያ ፕሮፓጋንዳ ይሆንበታል። የምናውቀውን እውነት፣ የምናየውን ዓለም ከመልመድ ብዛት ድንቅኛነቱን እንዳንዘነጋ ጠርዞ በማፈራረቅ፣ ገጽታውን በማቀያየር እንደ አዲስ ያቀርብልናል። በተፋፈገ ክፍል ውስጥ ለከረምንና በልማድ ብዛት ለተዘናጋን፣ መስኮቱን ከፈት አድርጎ ንጹሕ አየር ያስተነፍሰናል።

ጸጋዬ መነጋገሪያ በሆነን በዚህ ግጥም ውስጥ ዝናብ እና ዝንብን፣ ፀሐይ እና ጐርፍን፣ አበባ እና እሳትን፣ ዕንባ እና ዶፍን፣ ጐጆ እና መስክን፣ በርኖሰ እና የኀዘንን ማቅ፣ ወዘተ እያነጻጸረ፣ እያጣመረ፣ እያመሳሰለ ዓለም የንፅፅርና የተቃርኖ መፋለምያ መስክ ነች ይለናል። ሕይወት አላፊ ነው፤ “ሲመሽ፣ ሲሸሽ፣ ስትከንፍ፣ ሲረግፍ፣ ሲገፍ፣ አለፈ” ይለናል። ‘ቢራቢሮነት’ የተወሰነለት ሂደት ቢኖረውም፣ አስተማማኝነት አይታይበትም። የሕይወት ግሥጋሴ ከተቀጠረለት አያመልጥም። ይህንን እውነት ልብ በሚወጋ ስንኝ ይገልጸዋል፣ ቢራቢሮ ሆኖ እማይበር | ፀደይ ሆኖ የሚዘልቅ የለም … | ይሁን ያለን ዲበ-ኵሉ፣ የኑሮ ግማደ መስቀል | ለካ እንዲያው ነው መርበትበቱ፣ ሥረ-ቃሉ ላይነቀል?… 

ግጥሙን በመገረም ዝግታ ጥያቄ ይከፍታል። ቢራቢሮ ከአበባው ላይ፣ ምን አይተሽ ነው ከቅጠሉ | ከቄጠማው፣ ከለምለሙ፣ ሰምረሽ፣ አቅፈሽ መመሰሉ …። መደምደሚያው ምላሽ ሳያገኝ፣ የጥያቄውን ደጅ በመሻቱ ትይዩ ገርገብ አድርጎ ይተወዋል። ሊደርስበት የሚናፍቀውን፣ ግን ያልተቻለውን እያሰበ ይወተውታል፤ በእግረ-አሳቡ ይዳስሳል… ምን አለበት ላንዲት ሰሞን | ቢራቢሮ እኔ አንቺን ብሆን? የሕይወት ትርጉም በመነሻና በመድረሻዋ ሳይሆን በተገኘንበት ነው ማለቱ ይሆን? ስንኞቹን የደጋገማቸው የሰው ሕይወት እንደ ንጋትና እንደ ምሽት በድግግሞሽ የታጠረ ስለሆነ ይሆን?

የግጥሙ ‘መንፈሳዊነት’ ምን ያስረዳናል?

ስለ ‘ሕይወት ቢራቢሮ’ ቢያንስ ሶስት ቁም ነገሮችን መገንዘብ ይቻላል። የመጀመሪያው፣ ባለ ቅኔው የተገኘበትን ባሕል ሕዝብና መልክዓ ምድር ጠንቅቆ ማወቁ፤ በሰማው ሳይወሰን፣ በመላ ሕዋሳቶቹ አጣጥሞ ማወቁ። ሁለተኛ፣ የሕዝቡን ቋንቋና ባሕል አለመናቁና ማክበሩ። እራሱ ቢጠራጠርም፣ ሕዝቡ ግን ልክ ነው ብሎ የተቀበለውን እምነቱን እንደገና እንዲመረምር መጋበዙ። ሲተረትማ ሲወጋ… | ሲነገር እንደ ሰማነው...። ሦስተኛ፣ እውነትን ለማወቅ መሻቱ። ሰው ሁሉ ዘላለማዊውን ለመረዳት በውስጡ ጥልቅ ጥማት አለው። “እግዚአብሔርም ከጥንት ጀምሮ እስከ ፍጻሜ ድረስ የሠራውን ሥራ ሰው መርምሮ እንዳያገኝ ዘላለምነትን በልቡ ሰጠው” [መጽሐፈ መክብብ 3፡11]። ጥማቱም በሆነ ባልሆነው አይረካም። ሊያረካው ቢችል ያ ነገር ከእርሱ ውጭ ነው፣ ፍለጋውም የሚያስከትለው ረሐብ ከቶ ብርቱ ነው። ባለቅኔው ካሠረው ሥጋ ነጻ ለመውጣት ወድዶ ይቃትታል። ምን አለበት ላንዲት ሰሞን | ቢራቢሮ እኔ አንቺን ብሆን | በፍስሃሽ ብጥለቀለቅ፣ ብነግሥባት ባንቺ ጽዮን? | ጸጋ ሞገስሽን ለብሼ፣ እኔ ባንቺ ስም አልፌ | እኔ ባየርሽ ሰፍፌ | እኔ ባክናፍሽ ከንፌ | ምን አለበት ቢራቢሮ፣ … አንቺ ቀለም ለበስ ቅጠል | የብርሃን ጮራ ጠለል | ተወርዋሪ ሲሣይ መሰል፣ | ምን አለበት ቢራቢሮ፣ ዕድልሽን እኔ ብታደል?…

እውነትና ሕይወት

በሕይወት ጉዳይ፣ ልንጠይቅ ሲገባ የዘነጋናቸው ወይም ማንም እንዳያነሳብን የምንሸሻቸው ጥያቄዎች አሉ? ጥያቄዎቹን ባልተጋፈጥናቸው መጠን ዕውሮች እስረኞች ነን! የወገኖቻችንን አስተሳሰብ ባሕልና አኗኗር ጠንቅቀን አውቀናል? ወይስ ንቀናል? እውነትን በእግር በፈረስ በነፍስ ፈላልገናል ወይስ ከመቀያየጥ ብዛት ውሸት ተመችቶናል? ከአማርኛ ይልቅ እንግሊዝኛ እየሸነቆሩ ግራ የሚያጋቡ መብዛታቸው ምክንያቱ ለምን ይሆን? የመልእክታችን መዘበራረቅስ? በእውቀታቸውና በ “መንፈሳዊነታቸው”  ከፍታ፣ ያልሆኑትን እየሆኑ ቋንቋቸው ግራ ያጋባ መብዛታቸውስ? ዕድልሽ የዋዛም አይደል | ክፉ ፈተና ነው መምሰል፤… | በርቺ እንግዲህ ቢራቢሮ፣ ክረምት ላንች ብቻ አለፈ | መስሎ አላድር ያለውማ፣ በጐርፍ ዘቅጦ ጐረፈ …

ግልጽ ቋንቋ

የጸጋዬ ቃላት ምርጥ፣ ውብና ጥራት ያላቸው፣ ዘመን ያስረጁ ቃላት ናቸው። ዛሬም እንኳ፣ ከምናውቀውና ከምንረዳው ተነሥቶ አብረነው እንድንጓዝ ይጋብዘናል። ዶፍ እና ጎርፍ አይተናል። ክረምትን አስታውሰን ልጅነታችንን በደስታ ቃኝተናል። ላንቺ ይብላኝልኝ እንጂ፣ ለኔስ ክረምት ደረሰ | በሰማያት ዕንባ ምድርን ሊጠርግ እያግበሰበሰ | አበባውን እንደጕድፍ፣ ጕድፉን ከዝንብ ጋር ሲያስስ | ሁሉን እኩል ሲያግበሰብስ | አጥርና ጐጆ ሲድስ | ሜዳውን በደለል ሲምስ | ግንዱን በዶፍ ሲገረስስ …። በናፍቆታችን በኩል ቀርቦ የዘዬው ምርኮኛ አድርጎናልና፣ እንሰማዋለን። ከላይ እንዳልነው፣ የጠብቅነውን መልስ አይሰጠን ይሆናል፤ የያዝነውን እውነት ላለመመርመር ግን አማራጭ አይተውልንም።

ቋንቋ፣ አሳብ ለመቀባበልና ለሌሎች አክብሮት ማሳያ በመሆኑ፣ አፍ ከፈታበት ሌላ፣ ሌላ ቋንቋ መማር ጠቀሜታው ብዙ ነው። ሌላ ኢትዮጵያዊ ቋንቋ ለመማር ፈቃደኞች ብንሆን፣ እርስበርስ ያለንን ፍቅርና አክብሮት ማሳያ በሆነልን! እውነቱን ለማወቅና፣ ዋጋ ቢያስከፍልም፣ ከእውነት ጋር ተስማምተን ለመኖር የምንሻ ሕዝቦች ነን? እንደ እንግሊዝኛው፣ አማርኛ፣ በተለይ ኦሮምኛ ለመናገር ርብርቦሽ ቢጀመርስ? የጓዳችንን ሳናቃና እንደሚቀናን እንዴት ገመትን? ተቋማት የሚያሠለጥኗቸው፣ ለአገራቸው ባዕድና ያልተፈተነ የውጭ ባሕል አግበስባሾችና አራማጆች እንዳይሆኑ ምን ጥንቃቄ ይወሰድ? አድማጭ ካልተረዳን ችግሩ ያለው እኛው ጋ ነው። ከአገር መሪ የማይጠበቅና የሚጠበቅ ቋንቋ አለ። ጥራዝነጠቅነትና ያልተኖረ ኃይማኖት ባማሩ ቃላት ቢዥጎደጎዱ ውጤቱ መናቆርና መደናቆር ነው። ከጸጋዬ ቅኔ አንዲቷ ቃል ብትወገድና ብትለወጥ የግጥሙ ቃናና ማዕረግ ይወርዳል። ቢራቢሮ ከአበባው ላይ፣ ምን አይተሽ ነው ከቅጠሉ | ከቄጠማው፣ ከለምለሙ፣ ሰምረሽ አቅፈሽ መመሰሉ …

ምትኩ አዲሱ

ጥቅምት 2010 ዓ.ም

የግርጌ ማስታወሻ፣

‘ሕይወት ቢራቢሮ’ ን መንግሥቱ ገዳሙ እንዳነበበው ለማድመጥ እዚህ ይጫኑ። ይህ ጽሑፍ በ2002 ዓ.ም ከታተመው ታርሞ የቀረበ ነው።

[1] እሳት ወይ አበባ፣ ገጽ 57-62፤ 1966 ዓ.ም. ብ/ሰ/ማ/ቤ፣ አ/አ። “ስድሳ ስድስት” ሕዝባዊ አብዮት የፈነዳበት ዘመን መሆኑን ልብ ይሏል። “እሳት ወይ አበባ” ምርጫ ቀረበልን፤ እሳት መረጥን፣ በእሳት መጫወት ዐመድ እንደሚያስታቅፍ፣ እሳት ያገኘውን ሳይመርጥ እንደሚፈጅ አልታየንም። እነሆ፣ አበባ ሳናይ ዘመናት አለፉብን። [ሀ] በጥበብ በዘዴ | ቀይና አረንጓዴ | ብጫ ሰማያዊ | ጥቁር ሐምራዊ | ከያይነቱ ቀለም | የጐደላት የለም | ሆኖ የደመቀ | እያብረቀረቀ | መልኳ እጅግ አምሮ | ጥልፉ ተነባብሮ | መጣች ቢራቢሮ! … [ለ] የፍጥረትን መነሻ፣ የታሪክን መሠረት በመመርመርና የኃይማኖትን አኳኋን በማገናዘብ ጸጋዬ ከሌሎች በወርድና በስፋት ይጠልቃል ለማለት እንጂ ሌሎች ሕይወትን አልመረመሩም ለማለት አይደለም። የሰሎሞን ዴሬሣን፣ የመንግስቱ ለማና የገብረ ክርስቶስ ደስታን ሥራዎች ይመልከቱ። [ሐ] ባለቅኔው በዋሽንግተን ዲሲ አሜሪካ በተደረገ ስብሰባ ላይ፦ “በተኣምር አታምኑም? እኔ በተኣምር አምናለሁ፣ ራእይ እኮ ተአምር ነው” ብሎ ነበር [ደብተራው ዶት ኮም፤ ህዳር 14/1995 ዓ.ም. ከ 6፡15-8፡03 ባሉ ደቂቃዎች ያድምጡ]።

 

ቀላሉን መንገድ | የማለዳ ድባብ | ከየት ተገኘሽ ሳልል | ቋንቋን በቋንቋ | ስደተኛውና አምላኩ | ሞት እና ፕሮፌሰር | የድመትና ያይጥ ፍቅር | የልማት መሠረቱ መታመን ነው | ጒግል እንደ አዋቂ | ቆመህ እያየህ | ለመቶ ሚሊዮን የአገሬ ሕዝብ | ትዝብቶች ከ “አባቴ ያቺን ሰዓት” | ይድረስ ለቴዲ አፍሮ | ችግሩ አልተፈታ | በፎቶ ኢትዮጵያና እንግሊዝ | ጸሎትና ስፖርት | መጠየቅ ክልክል ነው? | የሺህ ጋብቻ ወይስ ቅዱስ ጋብቻ? | መሬት መሬት ሲያይ | ልቤ ከብዷል ዛሬ | ቸር ወሬ አሰማኝ | መንበርና እርካብ | ጒዞዬ | ፓትርያርክ በዕጣ | ባንተ በኲል ስትቦረቡር | Land of the Shy, Home of the Brave