ethpn rulers

~ የ መ ሪ ነ ት  አ በ ሳ ~

ም ት ኩ  አ ዲ ሱ

መሪነት፣ የነገሮችን አካሄድና ፍጻሜ ከጅምሩ ለተለሙ ነው። መሪነት፣ ዐይናቸውን ከግባቸው ላይ ሳያነሡ በየእርከኑ ሁኔታን ለሚያቃኑ ነው። መሪነት፣ ምሥጋናን ለሚጋሩ ነው። መሪነት፣ ውርደት ውርደቱን ማንም እንደማይጋራቸው ለተገነዘቡ ነው።

የመሪዎች አበሳ የሚጀምረው ዓላማቸውን ግልጽ ሳያደርጉ ሲቀር፣ ዓላማቸውን እንደየሁኔታው ደጋግመው ሳያጠሩ ሲቀር፣ ተቀናቃኞች ለሚነዙት ወሬ እጅበጅ ምላሽ ሳይሰጡ ሲቀር ነው። አበሳ የሚበዛው፣ ሁለት ወገን ለማስደሰት ሁለት ፊት ሲያሳዩ ነው!

ጋንዲም ምንሊክም አንድነት መሆን አይቻልም። ብዙዎች ሞክረው ከሽፎባቸዋል። በሰላም ጀምሮ ህግ ወደማስከበር ዘመቻ ከተሄደ በኋላ፣ የተነሣበትንም ከግብ ሳያደርስ መደራደር የባሰ ፈተና አለበት። ትርፉ ለህገ ወጡ ወገን ፋታ እና እውቅና መስጠት ነው። ህግ አስከብራለሁ ባለው ወገን ላይ አለመተማመንን መፍጠር ነው።

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ የህወሓትን ህገ ወጥ አካሄድ ለመግታት ያስጀመሩት ዘመቻ በዚህ ዐይን ሊታይ ይገባል። ሰኔ 9/2012 በፓትርያርክ ማትያስ የተመራ ሃምሳ ሁለት የሀገር ሽማግሌዎች ቡድን መቀሌ ድረስ ተጒዞ ከህወሓት መሪዎች ጋር ተነጋግሮ ነበር። የህወሓት መሪዎች የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሥልጣን ከተቀሙ በኋላ፣ ይቅር ለእግዚአብሔር እንደማያውቃቸው የአርባ አምስት ዓመት ታሪካቸው እየመሰከረ፣ ተመልሰን አብረን እንሠራለን ይላሉ ብሎ ማሰብ ከጅምሩ መኻን ነበር። ሃያ ሰባት ዓመት የማይጋሩትን ሥልጣን ለምደው? ሦስት ተከታታይ ሰኔዎችን ከአዲስ አበባ እስከ ሻሸመኔ እስከ ቤንሻንጒል እስከ አምቦ እስከ ባህርዳር በአንድ ጀምበር በአንድ ስልት ሽብር አቀጣጥለው?

የሚገርመው፣ በእግዚአብሔር ስም እና በእርቀ ሰላም ጀምሮ ወደ ጦርነት የማምራት ታሪካችን ነው። አፄ ዮሐንስ በቴዎድሮስ ላይ፣ ምንሊክ በዮሐንስ ላይ፣ ኃይለሥላሴ በኢያሱና በዘውዲቱ ላይ፣ ደርግ በኃይለሥላሴ ላይ። መለስ በደርግ፣ በኢሳይያስ፣ በኦነግ፣ በህወሓት ላይ፣ በቅንጅት ላይ፣ በአሜሪካኖች ላይ ያሳዩት ስልት የቊንጮነቱን ሥፍራ አድሏቸዋል። ኢሳይያስ በደርግ ላይ በአትላንታ። ኢሳይያስ በመለስ ላይ በአዲስ አበባ። የደርግ “ያለምንም ደም” ደምበደም ተጠናቀቀ። በ67 ጄኔራል አማን አንዶም አቆርደት ላይ “ኢትዮጵያ ትቅደም! ኤርትራ ትቅደም!” ያሉበት ጒዞ ቦሌ ሳይደርሱ ክተት አዋጅ መታወጁ! አሜሪካኖችና እንግሊዞች ያካሄዱት የ1983ቱ የለንደን የሰላም ድርድር መለስ እና ኢሳይያስን በድል አድራጊነት አዲስ አበባ አገባ። በዓመቱ ዶ/ር በረከት ሃብተሥላሴ ያቀናበሩት “የሰላም ኮንፈረንስ” አሰብን መርቆ፣ በግብጽና በመለስ ረቂቅ ብልኃት በ1985 አገረ ኤርትራን አቋቋመ። ህወሓትን ያለተቀናቃኝ በትረሥልጣን አስጨበጠ። ዘጠኝ ክልሎችን ጎሣ በጎሣ አጠረ። ሁለት ዓመት በፈጀ ጦርነት 80 ሺህ ወጣት አወደመ። በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ስም የማያቋርጥ ዛቻ ዘመቻ፣ በሽብርተኛነት እስር ቤት፣ በኮማንድ ፖስት ረገጣ ገባ። ሁላቸውም ሰላም! ሰላም! አሉ። ሕዝቡን አታለሉ። አሁንስ ምን ልዩ ነገር ይጠበቃል? ወይስ ገና የምናየው ቀርቷል?

አንድ ነገር ግልጽ ነው። የዶ/ር ዐቢይ መንግሥት ያቀደውን ዘመቻ ቀድሞ ለህወሓት ሹክ ያላቸው ሰው አለ! ህወሓት በሰሜኑ እዝ እና በአካባቢው ትውልደ ትግራይ ያልሆኑትን ለይቶ ያለርኅራኄ መጨፍጨፉና እንደ ባዕድ ጦር መጋዘን መዝረፉ ይህን ያስረዳል።

የዐቢይ መንግሥት “ህግ የማስከበር ዘመቻ”፦ የሰላምን መንገድ ሞክረናል፤ ውርድ ከራሴ ብሏል። “ሠላሳ፣ አርባ” የህወሓት መሪዎችን ወደ ፍርድ ለማቅረብ የተገባው ቃል እንደተባለው አይጠናቀቅ ይሆን? ይድረስ ለክቡር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ። የውጭዎች ዲፕሎማሲና የንደራደር ግርግር ከንግዲህ “እንቅልፍ ነው እሚያስወስድህ”፦

“ዝም አልኳቸው ዝም ይበሉኝ | ትቻቸዋለሁ ይተውኝ
አልነካቸውም አይንኩኝ” | ብለህ፤ ተገልለህ ርቀህ
እውነት ይተውኛል ብለህ | እንዴት ተስፋ ታደርጋለህ?!...
ተስፋ አርገህስ ምን ልትሆን፤ ወይስ ተስፋው ምን ሊሆንህ?
እንቅልፍ እንጂ የሚያስወስድህ።
«አልጠራቸውም አይጥሩኝ | አይንኩኝ ስሜን አያንሱኝ»
ብለህ እንዴት ትመኛለህ፣ እንደማይተዉህ ስታውቀው
የተወጋ በቅቶት ቢኛ፣ የወጋ መች እንቅልፍ አለው
የጅምሩን ካልጨረሰው?

የተበደለ ቢችልም | ቢሸሽግም ቢደብቅም
የበደለ ዝም አይልም።
እንዴት አስችሎት ዝም ይበል? ለፍልፎ ከማስለፍለፉ
አደል እንዴ የሱ ቤዛ፣ የበደሉ ጥቅም የግፉ
ሰላም ለመንሣት አደል ትርፉ?...
ዝምማ ካለ ጒድ ፈላ | ነገር በጤና ሲብላላ
እያደር ሲጣራ ኋላ | ግፉ ይፋ ይሆናላ!...

የተበደለ ቢችልም | ቢሸሽግም ቢደብቅም

የበደለ ዝም አይልም።

እንዴት አስችሎት ዝም ይበል? ለፍልፎ ከማስለፍለፉ

አደል እንዴ የሱ ቤዛ፣ የበደሉ ጥቅም የግፉ

ሰላም ለመንሣት አደል ትርፉ?...

ዝምማ ካለ ጒድ ፈላ | ነገር በጤና ሲብላላ

እያደር ሲጣራ ኋላ | ግፉ ይፋ ይሆናላ!...

[እሳት ወይ አበባ፣ ገጽ 136—138፤ 1999 እትም]

© ምትኩ አዲሱ፣ ኅዳር ፪፭/፪፻፩፫ ዓ.ም.

ጭራቆቻችን