ወንጌል ወይስ ሌላ ወንጌል?

በበለጠ ደሳለኝ

belete1እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁ ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና (ማቴ 11፡28-30)።

እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፣ ወደ ውኃ ኑ፣ ገንዘብም የሌላችሁ ኑና ግዙ፣ ብሉም፤ ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ግዙ። …አድምጡኝ፣ በረከትንም ብሉ፣ ሰውነታችሁም በጮማ ደስ ይበለው (ኢሳ 55፡1-3)።

እነዚህ ሁለት ጥቅሶች ኃጢአት በመሥራቱ ከእግዚአብሔር ክብር የጎደለውንና የጠፋውን የሰው ልጅ፣ እግዚአብሔር በልጁ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደ ዘላለም መንግሥቱ የጋበዘበት የጸጋ፣ የሰላምና የዕርቅ ወንጌል መልዕክቶች ናቸው። ይህ ወንጌል የሚያምኑትን ሁሉ በእምነት የሚያድን የእግዚአብሔር ኃይል፣ ከድነትም በኋላ በእምነት የሚያኖር የእግዚአብሔር ጸጋ፣ ከእምነት ወደ እምነት የሚያሸጋግር የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው፤ የሚገኘውም በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ብቻ ነው (ሮሜ 1፡16-17፤ 3፡22)። አማኝ በቅድስናና በመታዘዝ በመኖር በሰማይ ያለችው የእግዚአብሔር ፈቃድ በምድር እንድትሆን በቃልም በሕይወትም መዳኑን በእምነቱ እንዲያጸባርቅ ይህ ወንጌል ያዝዛል። ባለንበት ዘመን የሚታየው የክርስትና ሕይወት ልምምድ፣ የሚተላለፉት የወንጌል መልዕክቶች ይህንን እምነትና እውነት አያንጸባርቁም።

የሚያድን እምነት በአፍ “በክርስቶስ አምናለሁ” ከማለት ያልፋል። የሚያድን እምነት በመታዘዝ የማይደገፍ የአዕምሮ መስማማት ብቻ አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አዳኝ ብቻ ሳይሆን የሕይወት ጌታ፣ ፍጹም አዛዥና ባለሥልጣን አድርጎ እጅ መስጠትን ይጠይቃል። የክርስቶስን ጌትነት ተረድቶ ለጌትነቱ በፍጹም ታማኝነት መገዛትንና ጌታ ከባሮቹ የሚጠብቀውን ተግባራዊ መታዘዝን ማሟላትን ያቅፋል። በክርስቶስ ውስጥ መኖርን፣ በቅድስና መመላለስን፣ በክርስቶስ ምክንያት በሚመጣ መከራ ውስጥ መጽናትን፣ በቃልም በሕይወትም የክርስቶስን ወንጌል መመስከርን ይጨምራል። አማኝ በድነት ቃል ኪዳን የተቀበለውን ኃላፊነት ማክበርን ያካትታል። የሚያድን እምነት ይህ ነው፤ የክርስቶስ ወንጌል ይህንን እውነት ከሰዎች ይጠይቃል።

በአብያተ ክርስቲያናት፣ በኮንፈረንሶች፣ በሬድዮ፣ በቴሌቪዢን፣ በመጽሐፍ፣ በመጽሔት፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጊዜ፣ በሰንበት ትምህርት፣ በአጠቃላይ ስለ ወንጌል በሚነገርበት ቦታ ሁሉ የሚተላለፈው ወንጌል በአብዛኛው ለክርስቶስ መታዘዝን የሚያደክም፣ የተከለሰ ወንጌል ነው። ክርስቶስ ያስተማረው፣ ሐዋርያቱ ዋጋ የከፈሉበት፣ እና ክርስቶስን እንደ አዳኝነቱና እንደ ጌትነቱ የተቀበሉት የእግዚአብሔር ቅሬታዎች በቃልም በሕይወትም ያስተላለፉልን የጠራ ወንጌል አይደለም። ከላይ ከተጻፈው ጥቅስ “…አሳርፋችኋለሁ፣ ለነፍሳችሁ ዕረፍትን ታገኛላችሁ …ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ግዙ፤…አድምጡኝ፣ በረከትንም ብሉ፣ ሰውነታችሁም በጮማ ደስ ይበለው” የመሳሰሉት ሐረጎች ጎልተው ሲሰበኩ፣ “ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ፣ ከእኔም ተማሩ” የመሳሰሉት ሐረጎች ግን ይታለፋሉ። በገላትያ የነበሩት የአይሁድ ክርስቲያኖች መታዘዝን ለማጉላት በክርስቶስ የጸጋ ወንጌል ላይ የሙሴ ሕግ ተጨምሮ መጠበቅ አለበት በማለታቸው ሐዋርያው ጳውሎስ ትምህርታቸው “ልዩ ወንጌል” እንደ ሆነ በማውገዝ ይህንን ትምህርት ባስተማሩትና በተከተሉት ላይ መርገምን ጠርቶባቸዋል (ገላ 1፡6-9)። ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ ዘመን በሕይወት ቢኖር ምን ይል ይሆን?

“የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች፣ ንስሐ ግቡ፣ በወንጌልም እመኑ” (ማር 1፡15) የሚለው የወንጌል እውነት “መግሥተ ሰማያት አሁኑኑ በምድር ናት” በሚል የስሕተት ትምህርት ተተክቷል። “ብልና ዝገት በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሰርቁት ዘንድ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ” (ማቴ 6፡20) የሚለው የጌታ ትዕዛዝ “በአዳም ኃጢአት ምክንያት ያጣኸውን የገነት ምቾት በሕይወት ዘመንህ ታገኛለህ፣ አንበጦችና ኩብኩባዎች የበሉብህ የዓለም ብልጽግና ሁሉ በክርስቶስ ብታምን ይመለሱልሃል” በሚሉ ለሰሚዎች አዳማዊ ምኞቶችና ጊዜያዊ ድሎት ተስፋ በሚሰጥ ምኞታዊ ወንጌል ተተክቷል። በአንዳንድ “የእምነት አስተማሪዎች” ዘንድ፣ በምድራዊ ሀብት ያልተባረከ፣ በጸሎት ኃይል ያልተፈወሰ ወይም በመከራ ውስጥ ያለ አማኝ እምነተ-ደካማ ክርስቲያን ተብሎ ይቆጠራል።

“በከንቱ ወይም በነጻ ተቀበላችሁ፣ በነጻ ስጡ” (ማቴ 10፡8) የሚለው እውነት “ለዚህ መልእክት ይህን ያህል ክፈሉ፣ የመዝሙርና የመልእክት ካሴት ግዙ፣ መጥተን ብናገለግላችሁ ስንት ይከፈለናል?” በሚሉ የጥቅም ማግኛ ማስታወቂያዎች ተተክተዋል። የእግዚአብሔር ቃል በጥራት በጽሑፍና በተለያዩ ማሠራጫዎች፣ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም በአነስተኛ ዋጋ ላልደረሳቸው ሰዎች ማቅረቡ የሚደገፍ ነው። የሚታየው ግን ይህንን አይመስልም፤ ይልቁን፣ “የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር” የሚለውን ጥቅስ እየጠቀሱ የእግዚአብሔርን ቃል ለምድራዊ ኑሮ ማትረፊያ አድርገውታል፤ ሕዝቡም ያለምንም ጥያቄ ይከተላቸዋል። “ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው …ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም” የሚለው ተረስቷል (1ኛ ጢሞ 6፡6-7)። ድህነትን ለመስበክ ሳይሆን ጽድቁንና መንግሥቱን ማስቀደም እንዳለብን ለመግለጽ ነው። ጽድቁንና መንግሥቱን ለሚያስቀድሙ ሌላው እንደሚከተላቸው፣ የወንጌልን ሥራ ለሚሠሩ ሁሉ እግዚአብሔር ከባለጸግነቱ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ እንዲሚሞላባቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ነው (ማቴዎስ 6፡33፤ ፊልጵስዩስ 4፡19)።

የወንጌል አቀራረብ እግዚአብሔር ለሰዎች እንደሚያስፈልጋቸው ሳይሆን ሰዎች ለእግዚአብሔር እንደሚያስፈልጉት ሆኖ ነው። እግዚአብሔር ከሰዎች የሚያገኘው የተደበቀ ጥቅም እንዳለና ያንን ጥቅም ለማግኘት የሰውን ልጅ አባብሎ ወደ መንግሥቱ የሚያገባበት ወንጌል እንደ ሆነ ተድርጎ ይቀርባል። የእግዚአብሔር ፈቃድ በምድር እንዲከናወን ሳይሆን በጸጋ ድኛለሁ የሚል ሰው ሁሉ የሥጋ ምኞቱ፣ ሰለ ገንዘብ መመካቱ፣ የዓይን አምሮቱን የሚያገኝበት ምኞቱን መቀስቀሻ ሆኗል። የእግዚአብሔር ጸጋ የምኞት ማግኛ ርካሽ ነገር እንደ ሆነ ይመስላል። በአጠቃላይ የክርስቲያኖች ምድራዊም ፍላጎቶች መሟላት ከእግዚአብሔር ክብር መገለጥ እና ከነፍሳት መዳን ይልቅ ቅድሚያ የተሰጠበት ወንጌል መስሏል።

“ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፣ ማለት የእግዚአብሔር ወራሾች ነን” ጎልቶና ተደጋግሞ ይሰበካል (ሮሜ 8፡17)። ይህም የእግዚአብሔር ልጆች መቸገር አይኖርባቸውም ለማሰኘት ነው። የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን ወራሾች መሆናችን እውነት ሲሆን፣ “አብረን ደግሞ እንድንከብር አብረን መከራን ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን” የሚለው ክፍል ግን ይዘለላል። ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ “ይህም ርስት በመጨረሻው ዘመን ይገለጥ ዘንድ ለተዘጋጀ መዳን በእግዚአብሔር ኃይል ለተጠበቃችሁ ለእናንተ በሰማይ ቀርቶላችኋል፣ በዚህም እጅግ ደስ ይላችኋል” (1ኛ ጴጥ 1፡4) በማለት በዕብራውያን 11 ላይ ለምሳሌነት እንደ ተጠቀሱት የእምነትና የመታዘዝ አርበኞች ተስፋችንን በትዕግሥት፣ በመጽናትና በሐሴት እንድንጠብቅ ያበረታታናል።

አባካኙ ልጅ፣ “አባቴ ሆይ፣ ከገንዘብህ ድርሻዬን (አሁኑኑ) ስጠኝ” እንዳለ ሁሉ፣ አገልጋዮች፣ ለሥጋም ሆነ ለነፍስ ወዲያውኑ እርካታ የሚሰጥ ወንጌልን በሚመስል ምኞታዊ መልዕክት፣ የሰማውን ሁሉ ለማመን የሚወድን ልብ ይማርካሉ (ሉቃ 15፡12)።

ድነት ከሰው ጥረት ውጭ በእግዚአብሔር ጸጋ፣ በክርስቶስ ሥራ፣ በእምነት በነጻ የተሰጠ የእግዚአብሔር ፍጹም ስጦታ ነው። ይህንን እውነት ሳይገነዘብ የእግዚአብሔር ፍጡር ብቻ ከመሆን አልፎ የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆን የሚችል ማንም የለም። ይህ ዘላለማዊ እውነት ነው። ኃጢአተኛነቱን ተገንዝቦ፣ በበደሉ ምክንያት መሞቱን አውቆ፣ የሕይወትን ውኃ ተጠምቶ፣ የሕይወትን እንጀራ ተርቦ፣ በራስ ጥረት ሕግን ጠብቆ መጽደቅ እንደማይቻል ተረድቶ፣ ከዚህ አዳማዊ ጎስቋላ ሥጋ ማን ያድነኛል በማለት የክርስቶስ ያለህ ብሎ በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ወደ እግዚአብሔር በመምጣት የክርስቶስን ጽድቅ ለሚቀበል ኃጢአተኛ፣ ይህ አድራጎቱ ሥራ አይደለም። የዘላለም ሕይወት የጸጋ ስጦታ እንጂ ሥራ አይደለም።

የክርስቶስን ወንጌልና ጥሪ ተረድተው በትሕትና ወደ እርሱ ለሚመጡት እግዚአብሔር እንደ ባለጠግነቱ መጠን፣ በክብር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ (ፈውስም፣ ብልጽግናም፣ የጸጋ ስጦታዎችም፣ ሰላምም፣ ዕረፍትም፣ ወዘተ. ) ይሞላባቸዋል (ፊል 4፡19)። እነዚህ ስጦታዎች በክርስቶስ ሆኖ ለጠየቀ፣ ለፈለገ፣ ለተጠማ፣ ለደከመ፣ ወደርሱ ለመጣ፣ የተሰጡ ተስፋዎች ሲሆኑ፣ ግባቸውም ለእግዚአብሔር ክብር፣ ለሰው ልጆች በረከት፣ በሰማይ ያለችውን የእግዚአብሔርን ፈቃድ በምድር ለማጉላት ነው። እንጂ እግዚአብሔር ይህንን ቢያደርግልኝ እኔ ደግሞ ያንን አደርግለታለሁ በሚል የልብ ዝንባሌ ከእግዚአብሔር ጋር ለምድራዊ ጥቅም ለሚደራደሩት አይደለም። ለወንጌል አገልግሎት ብትሰጥ 30፣ 60፣ 100 እጥፍ ይመለስልሃል፣ በማለት የሰውን ልጅ የስግብግብነት ምኞት በእግዚአብሔር ቃል ባልተደገፈ ተስፋ ለሟሟላት ለሚተጉት አይደለም። የክርስቶስ ወንጌል እንዲህ ዓይነቱን ስግብግብነት አያስተምርም።

ከላይ በተጠቀሱት ጊዜያዊና ምድራዊ ተስፋዎች አባብለው፣ “ኢየሱስ ጌታ እንደሆነ በአፍህ ብትመሰክር …ትድናለህ” ይላሉ፤ “እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሳው በልብህ ብታምን” የሚለውን ያስቀራሉ [ሮሜ 10፡9]። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ዋስትናን በመስጠት በግማሽ ወንጌል ብዙዎችን ያስታሉ። “በመንፈስ ቅዱስ ካልሆነ ኢየሱስ ጌታ ነው” ሊል ማንም ስለማይችል፣ “ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ ነው” ብትል መንፈስ ቅዱስ ባንተ እንዳለ ማረጋገጫውን አሟልተሃል ስለሚሏቸው፣ “ኢየሱስ ጌታ ነው” በማለት ክርስቲያኖች በተሰበሰቡበት ከፍ ባለ ድምጽ ያስታጋባሉ። ይህንንም የመዳናቸውና በመንፈስ ቅዱስ የመሞላታቸው ምልክት አድርገው ይቀበሉታል። የአንድ አማኝ የድነቱና በመንፈስ ቅዱስ መሞላቱ ማረጋገጫ በመድረክ ላይ “ኢየሱስ ጌታ ነው” በማለቱ ላይ ብቻ የተመሠረተ ከሆነ ለዚህ ሰው ሊታዘን ይገባል።

በጣም ለተራበ ወይም ለቸገረ ጣዖት አምላኪ ወይም እግዚአብሔር የለም ባይ፣ “ኢየሱስ ጌታ ነው” ብትል ሃያ ዶላር እሰጥሃለሁ ብንለው ያለምንም ማወላወል “ኢየሱስ ጌታ ነው” ሊል እንደሚችል አልጠራጠርም። ነገር ግን በልብ ያልታመነ ምስክርነት ከአፍ ሲወጣ ኃይል የሌለው ግማሽ ወንጌል፣ የተጣመመ ወንጌል፣ ልዩ ወንጌል እንጂ ዘላቂና ሕይወት ለዋጭ አይሆንም። ብዙዎችም ፈጥነው ይህን ወደ መሰለ ወንጌል ተላልፈዋል፤ ይህ የክርስቶስ ወንጌል አይደለም፣ እንዲህ ዓይነቱን ወንጌል ለሚሰብኩት ደግሞ የሚያስፈራ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል (ገላትያ 1፡6-8)።

የአገልግሎታቸውን መሳካትና የእምነታቸውን ጠንካራነት ለመግለጽ “ጌታ ሆይ! በስምህ ትንቢት ተናግረናል፣ በስምህ አጋንንትን አስወጥተናል” ላሉት ሰዎች ኢየሱስ ሲመልስ፣ “ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! የሚለኝ ሁሉ ወደ አባቴ መንግሥት አይገባም፣ ሂዱ፣ አላወቅኋችሁም” ይላቸዋል (ማቴ 7፡21-23)። በሆሴዕ 2፡16፣“አባብላታለሁ፣ ወደ ምድረ በዳም እጠራታለሁ፣ ለልቧም እናገራታለሁ …” እንደ ተጻፈ፣ እግዚአብሔር አባብሎ ቢጠራንም ለልባችን ሊናገረን ነው።

ለዚህ በየዕለቱ ኃይል እየጨመረና እያደገ ለሚሄድ ሁኔታ ችግሩ የሰባኪዎችና የአስተማሪዎች ብቻ አይደለም፤ የምዕመኑም ነው። የክርስቶስን ወንጌል፣ በረከቱን እንጂ ግዴታውን አይረዱም፤ ብልጽግናውን እንጂ የመስቀሉን ሕይወት አይገነዘቡም፤ ፍቅሩን እንጂ ፍርዱን አያስተውሉም፤ ምድራዊ ትርፉን እንጂ ክርስትናና አገልግሎቱ የሚያስከፍለውን ዋጋ አያጤኑም። ስለዚህም እየሰሙ አያስተውሉም፣ እያዩ አይመለከቱም፣ እያነበቡ አይረዱም። ቢሰሙም፣ ቢያዩም፣ ቢያነብቡም ለመረዳትና በሕይወታቸው ተግባራዊ ለማድረግ ሳይሆን ወዲያው ለሌላ ለማስተማርና የዕውቀታቸውን ጥልቀትና የመንፈሳዊነታቸውን መጠን ለሌሎች ለመግለጽ ነው። ስለዚህም የልባቸውን ምኞት የሚነግሯቸውን አገልጋዮች ይፈልጋሉ፣ ያዘጋጃሉ፣ ይከተላሉ።    ይቀጥላል

ፓስተር በለጠ ደሳለኝ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ ናቸው።