መንፈሳዊ ውጊያ

ተድላ ሲማ

tedlapic2ስለ መንፈሳዊ ውጊያ ስናስብ ውጊያችን በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ድል ከተመታ ጠላት ጋር መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ስለ ጌታ ኢየሱስ ድል መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ድል በመንሳት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው” (ቆላ 2፡15)። “እርሱም (ክርስቶስ) መላእክት፣ ሥልጣናት፣ ኃይላትም ከተገዙለት በኋላ ወደ ሰማይ ሄዶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ” (1ኛ ጴጥ 3፡22)። ሰይጣንን በተመለከተ በክርስቲያኖች ዘንድ ሁለት ዓይነት የተሳሳተ ጽንፈኛ አስተሳሰብ ሲንጸባረቅ ይስተዋላል። አንደኛው ክፍል ሰይጣንን ሁሉን ቻይ እንደሆነና በአንድ ጊዜ በሁሉም ሥፍራ እንደሚገኝ ዓይነት አድርጎ የሚያስብ ይመስላል። እንደዚህ ዓይነት ሰዎች የጌታን ችሎታ ለሰይጣን ይሰጡታል። ሁሌ የሚያስቡት ስለ ሰይጣን ነው። አብዝተው ሰይጣን ስለ ሰራው ሥራ ይናገራሉ። ሰይጣን ራሱ ስለ ራሱ ብቻ እንድናስብ ይፈልጋል። የጌታን ታላቅነትና የማዳኑን ሥራ ለማወጅ እንጂ የሰይጣንን ዝና ልናወራ አልተጠራንም። ሰይጣን ኃይል ቢኖረውም ውስን ፍጡር ነው። በአንድ ጊዜ በሁሉም ሥፍራ አይገኝም። ከዚህም የተነሣ ለተለያየ የክፋት ተልዕኮው ከሥፍራ ሥፍራ መንቀሳቀስ ግድ ይለዋል (ኢዮብ 1፡7)። ለዓመጽ ሥራው ክፉ መናፍስትን በተለያየ ሥፍራ ያሰማራል (ኤፌሶን 6፡12)። ሰይጣን በአንድ የጌታ መልአክ ተይዞ የሚታሰር መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ይነግረናል፦ “የጥልቁንም መክፈቻና ታላቁን ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ የቀደመውንም እባብ ዘንዶውን እርሱም ዲያብሎስና ሰይጣን የተባለውን ያዘው፤ ሺህ ዓመትም አስረው፤ ወደ ጥልቅም ጣለው፤አሕዛብንም ወደ ፊት እንዳያስት ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በእርሱ ላይ ዘግቶ ማኅተም አደረገበት (ራእይ 20፡1-3)።” ጌታ አእላፋት ጊዜ አእላፋት መላእክት እንዳሉት ቃሉ ያስተምረናል (ራእይ 5:11)። ሆኖም ግን አንድ የጌታ መልአክ ሰይጣንን እንደሚያስረው ከላይ የተጠቀሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ይነግረናል። በመሆኑም ሰይጣንን ከጌታ ጋር በኃይል እንደሚስተካከል አድርገን ልናስብ አይገባም። ሁለተኛው ዓይነት ጽንፈኛ አስተሳሰብ ደግሞ ለሰይጣን ምንም ግምት ያለመስጠት ነው። ለእንደዚህ ዓይነት ክርስቲያኖች ሰይጣን ያለም አይመስልም። እንደዚህ ዓይነት ክርስቲያኖች አንዴም ሰይጣንን ሲቃወሙት አይስተዋልም። መጽሐፍ ቅዱስ ግን የሰይጣንን መኖር አስረግጦ በመናገር እንድንቃወመው ያዘናል (ኤፌሶን 6:10-18)።

ስለ ሰይጣን ሚዛናዊ አስተሳሰብ ሊኖረን ይገባል። የሌለውን ችሎታ ልንቸረው አይገባም። አሠራሩንም ባለማወቅ ጭራሽ የለም ማለትም ለሰይጣን የስህተት አሠራር መጋለጥን ያመጣል። “በሰይጣን እንዳንታለል የእርሱን አሳብ አንስተውምና (2ኛቆሮ2:11)።” ሰይጣን የእግዚአብሔርና የጌታ ልጆች የእኛም ጠላት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ አስረግጦ ይናገራል (1ኛ ጴጥ 5:8-9)። በዚህ አጭር ጽሑፍ ሰይጣንን እንዴት መዋጋት እንደሚገባን ለማሳየት ተሞክሯል። በመጀመሪያ ግን ሰይጣን በክርስቲያን ላይ ሥልጣን አለውን? ሥልጣን ከሌለው ታዲያ እንዴት ነው ኃይሉን ለማሳረፍ መንገድ የሚያገኘው የሚለውን መመልከቱ ይጠቅማል። ሰይጣን በክርስቲያን ላይ ሥልጣን አለው? ሰይጣን በክርስቲያን ላይ አንዳች ሥልጣን (ህጋዊ መብት) የለውም፤ በመሆኑም ኃይሉን እንዳሻው በእኛ ላይ የማሳረፍ መብት የለውም። “እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን” ይላል (ቆላስይስ 1:13-14)። እግዚአብሔር አንድያ ልጁን በመስቀል ላይ እንዲሞት አሳልፎ በመስጠት የኃጢአት ዕዳችን እንዲከፈል በማድረግ ከጨለማው ሥልጣን አስመልጦን ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፍልሶናል። በክርስቶስ ሥራ በማመናችን የእግዚአብሔር ልጆች የመሆን ሥልጣን ተሰጠን (ዮሐ1:12)። ሰይጣን በኛ ላይ ሥልጣን ሊኖረው ይቅርና እንደሁም እኛ ክርስቲያኖች በሰይጣን ላይ ሥልጣን እንዳለን የሚከተለው ክፍል ያስረግጣል፥ “እነሆ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፥የሚጎዳችሁም ምንም የለም (ሉቃስ10:19)።” ሰይጣን በክርስቲያን ላይ ሥልጣን ከሌለው ታዲያ እንዴት ነው ሊያጠቃን የሚችለው? ወይም እንዴት ነው ብዙ ክርስቲያኖች በሰይጣን ጥቃት ውስጥ ሲወድቁ የሚስተዋለው? የሚለው ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ክርስቲያኖች በጠላት ጥቃት ውስጥ የሚወድቁት ሽንገላውን ተቀብለው ለሰይጣን በር ሲከፍቱለት ወይም ሥፍራ ሲሰጡት ነው። በመሆኑም ቃሉ “የዲያቢሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ” ይላል (ኤፌሶን 6፤11)። አዳምና ሔዋን በሰይጣን ሽንገላ ተታለው በመውደቃቸው የጠላት ፈቃድ ተፈጸመባቸው (ዘፍጥረት 3:1-7፤ኤፌሶን 2፡1-2)። ሰይጣን የሚያጠቃን በሽንገላው በመታለል በር ስንከፍትለት ነው። ሰይጣንን በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚጠቀሱትን አሳቦች ማጤኑ ስለ ሰይጣን አሰራር ለመረዳት ጠቃሚ ነው።

“የዲያቢሎስን ሽንገላ” (ኤፌሶን 6:11)፤ “አሕዛብንም ወደ ፊት እንዳያስት” (ራእይ 20:3)፤ “በሰይጣን እንዳንታለል” (2ኛ ቆሮ 2:11)፤ “ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና” (2 ቆሮ11:14)፤ “ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና” (ዮሐ 8:44)፤ “በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት” (2ኛ ቆሮ.11:3)። ሽንገላ፥እንዳያስት፥ እንዳንታልል፥ እንዲመስል ይለውጣል፥ ሐሰት፥ ሐሰተኛና በተንኮሉ እንዳሳታት የሚሉት ቃላት ስለ ሰይጣን ማንነትና አሠራር ገላጭ መሆናቸውን መገንዘብ ይኖርብናል። ስለዚህ ዋናው የአሠራሩ ባህሪ ማሳት፥ማስመሰል፥ማታለልና፥መሸንገል መሆኑን ልናስተውል ይገባል። በአንጻሩ ደግሞ የጌታ ኢየሱስ ኃይል በሕይወታችን የሚሠራው እውነትን ስንቀበል ነው፦ “እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም አርነት ያወጣችኋል (ዮሐንስ 8፡32)።” የእውነት እውቀት የነጻነት ሕይወት እንድንለማመድ ይረዳል። የእግዚአብሔርን ቃል እውነት ተቀብለን በሕይወታችን ስንተገብረው ነጻነታችን እየጨመረ ይሄዳል፤ የሰይጣንን ውሸት ስንቀበል ግን የጭቆና ኃይሉ በላያችን ያርፋል። በመሆኑም ጌታ ከሰይጣን ውሸትና ሽንገላ የምንጠበቅበትን ማስተዋልና ጥበብ እንዲሰጠን ልንጸልይ ይገባል። ቃሉ “በሰይጣን እንዳንታለል የእርሱን ሃሳብ አንስተውም” (2ኛ ቆሮንቶስ 2:11) ይላል። በሰይጣን እንዳንታለል የሚረዳን የጌታ ሃሳብ የሆነውን የጌታን ቃል መታዘዝ ነው (1ኛ ቆሮ 2:16)። “እባብ (ሰይጣን) በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት …” (2ኛ ቆሮ 11፡3) እንደሚል ቃሉ ለሰይጣን ስህተት አሠራር አልፈን እንዳንሰጥ ከጌታ ዘንድ ሁል ጊዜ ጥበብን ልንጠይቅ ይገባል።

አእምሯችንን ወይም አስተሳሰባችንን ሰይጣን ምሽጉ አድርጎ እንዳይቆጣጠረው ከፍተኛ ጥንቃቄና ውጊያ ልናደርግ ይገባል። የእግዚአብሔር ቃል “በሰው ልማድ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንሆን እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፤ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤ የሰውንም ሃሳብ፥በእግዚአብሔር እውቀት ላይ የሚነሳውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን፤ ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን” (2ቆሮ10፤4-5) ይላል። ከፍተኛ ውጊያ የሚካሄድበት የሕይወታችን ክፍል አእምሯችን ነው። አሳባችንን ለመቆጣጠር በጨለማው ኃይል ከፍተኛ ትግል ይካሄዳል። አእምሯችንን እንደ ምሽጉ አድርጎ ለመቆጣጠር ጠላት የማያነሳው ድንጋይ የማይቆፍረው ጉድጓድ የለም። በመሆኑም አሳባችንን በእግዚአብሔር ቃል በመሙላት የታደሰ አእምሮ ሊኖረን ግድ ይላል። በታደሰ አእምሮ ውስጥ ሰይጣን ምንም ስፍራ አያገኝም። በአሮጌው አስተሳሰብ የሚመራ ወይም በቃሉ ያልታደሰ አእምሮ ያለው ክርስቲያን የጠላትን ሃሳብ ያስተናግዳል። ከጠላት የሆኑና ለሰይጣን የሚመቹ ሀሳቦችን ሁሉ ማርከን ለክርስቶስ ማስገዛት አለብን። በእግዚአብሔር እውቀት ላይ የሚነሳ ሃሳብ ወደ አእምሯችን ብቅ ሲል ለክርስቶስ እንዲገዛ ልንማርከው ይገባል። ያ ሲሆን ሰይጣን በሕይወታችን ለመሥራት ዕድል ያጣል፤ ሰላማችን፥ ነጻነታችንና በረከታችን ይጨምራል። አእምሯችንን በተመለከተ ሰይጣን ሁለት ነገር ማድረግ እንደሚችል ከመጽሐፍ ቅዱስ እንረዳለን፦ አንደኛ፣ አሳቡን ወደ አእምሯችን ሊልክ ይችላል፤ “ዲያብሎስ በስምኦን ልጅ በአስቆርቱ ይሁዳ ልብ (አእምሮ) አሳልፎ እንዲሰጠው አሳብ ካገባ በኋላ …” (ዮሐንስ 13፤2) ይላል። በመሆኑም ወደ አእምሯችን የሚላኩ ሃሳቦችን ሁሉ ልንመረምር ይገባል። ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የማይስማሙ ከሆነ ወዲውኑ ልንጥላቸው ይገባል። ጠላት የራሱን ክፉ አሳቦች ወደ አአምሯችን ብልጭ ካደረገ በኋላ ከእግዚአብሔር ነው ብለን እንድንቀበል ይሸነግለናል። አንዳንድ የዋህ ቅዱሳን በጸሎት ላይ ሳሉ የመጣ ሃሳብ ሁሉ ከጌታ ነው ብለው ያስባሉ። ይህ ግን ስህተት ነው። ለጸሎት ተንበርክከንም እንኳ ሰይጣን ሀሳቡን ወደ አእምሯችን ሊልክ ይችላል። ስለዚህ ሃሳቡ በየትኛውም ሰዓት፣ በማናቸውም ቦታ ይምጣ በሚገባ ልንፈትሸው ይገባል። ሁለተኛ፣ ሰይጣን በውስጣችን እንዲቆይ የማይፈልገውን ሃሳብ ከአእምሯችን ውስጥ ይሰርቃል። የምንባረክባቸውን ሃሳቦች፥ መልካም ራእዮችና የሚያጽናኑ ነገሮችን ከአእምሯችን በመንጠቅ በምትኩ የሚያስጨንቁንንና የሚያረክሱንን ሃሳቦች ወደ አእምሯችን ይልካል። በሉቃስ 8፡12 ላይ “ዲያብሎስ ይመጣል፤ አምነውም እንዳይድኑ ቃሉን ከልባቸው (ከአእምሯቸው) ይወስዳል” ይላል። ብዙ ቅዱሳን አእምሯቸው በሰይጣን የተጠቃ ነው። በተሰበሰበ አእምሮ አንድ ገጽ ጽሑፍ እንኳ ማንበብ አይችሉም። የማይፈልጓቸው እልፍ አሳቦች ወደ አእምሯቸው ይጎርፋሉ። ቃሉን ሲሰሙ የተለያዩ አሳቦች እየመጡ የሚሰሙት ቃል እንዲያመልጣቸው ያደርጋሉ። የዚህ ሁሉ አሳብ ምንጩ ከየት ነው? ከዲያቢሎስ መሆኑ ምንም ጥርጥር ሊገባን አይገባም። አእምሯችንን እኛ ነን ወይስ ሌላ ኃይል የሚቆጣጠረው? ያስብላል። የቀደመው እባብ (ሰይጣን)፣ ሔዋንን በኤደን ገነት ያሳተው የውሸት ሃሳብ በመስጠት ነበር። “አትሞቱም …እንደ እግዚአብሔር ትሆናላችሁ” የሚል ሃሳብ ለሔዋን አቀረበላት። ሔዋን የሳተችው፥ ሁሉ በሞላበት በኤደን ገነት ነው። ጌታ ኢየሱስ ግን በምድረ በዳ በራበው ወቅት እንኳ ከሰይጣን የቀረበለትን ድንጋይ ወደ ዳቦ የመቀየር ሃሳብ በእግዚአብሔር ቃል በመዋጋት አሸነፈ። በተጨማሪም እራሱን ከመቅደስ ጫፍ ላይ እንዲወረውር ለሰይጣንም እንዲሰግድ አሳብ ቀርቦለት ነበር። ለሰይጣን እንዲሰግድ የቀረበለት ሃሳብ ከጉርሻ ጋር ነበር። ሁሉንም ግን በቃሉ ሰይፍ በመዋጋት አሸነፈ። ሰይጣንን እንዴት እንቃወመው? የእግዚአብሔር ቃል፣ “ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሻሻል” ይላል (ያዕቆብ 4፤7-8)። ዲያብሎስን ለመቃወም ምን ዓይነት ስልት ብንከተል መልካም ነው? ከዚህ በታች ሰይጣንን ለመቃወም ወይም ለመዋጋት የሚረዱ ሰባት ስልቶች ተዘርዝረው ተብራርተዋል።  

ሀ. ለሰይጣን ዕድል ፈንታ (መቆሚያ) መከልከል። የእግዚአብሔር ቃል “ለዲያብሎስ ዕድል ፈንታ/መቆሚያ አትስጡት” ይላል (ኤፌን 4፤27)። ለዲያብሎስ እድል ፈንታ የሚሰጡትን ነገሮች ከሕይወታችን በማስወገድ ዲያብሎስ የሚሰራበትን መንገድ በማሳጣት ልንቃወም ይገባል።ይህ ሲሆን ሰይጣን ወደ ሕይወታችን የሚገባበትን በር ሁሉ መዝጋት ያስችለናል። ለሰይጣን መቆሚያ የሚሆኑ ነገሮች ወይም መግቢያ በሮች ምን ምን ናቸው? ዘጠኙን ከዚህ በታች እንመለከታለን።

1. ተናዝዘን ያልተውነው ኃጢአት። በግልጽም ሆነ በስውር የምንለማመደውና ተናዝዘን ያልተውነው ኃጢአት ለሰይጣን መቆሚያ ይሆናል። እንዲህ ያለው ኃጢአት ለሰይጣን በር በመክፈት ሰይጣን በሕይወታችን ላይ ጎጂ ተጽእኖ እንዲያመጣ ዕድል ይሰጠዋል። በሽታን፣የሕይወት ድርቀትንና ሌሎች አሉታዊ ነገሮችን ወደ ሕይወታችን እንዲልክ በር ይከፍትለታል፤ በመሆኑም በእግዚአብሔር ኃይል ተረድተን፣ ከማናቸውም ኃጢአት በመላቀቅ ለሰይጣን ዕድል ልንነፍገው ይገባል። ኃጢአት ከሠራንም ወዲያው በመናዘዝና ንስሐ በመግባት የበደላችንን ስርየት ከጌታ ማግኝት አለብን (1ኛ ዮሐ 1:9)። መናዘዝ ማለት የሠራነውን በደል ለጌታ መንገር ማለት ሲሆን ንስሐ መግባት ማለት ደግሞ ከኃጢአት መንገዳችን መመለስና የጽድቅ ሕይወት መኖር ማለት ነው። የምንወደው ኃጢአት ካለም በግልጽ ጌታ ከሕይወታችን እንዲነቅልልን ልንማጸነው ይገባል። ያን ኃጢአት የምንጠላበትንና የምንከዳበትን ጸጋ ጌታ ይሰጠናል። በክርስቶስ በኩል የተገለጸው ጸጋ ይህን እንድናደርግ ያስችለናል። “ይህም ጸጋ ኃጢአተኛነትንና ዓለማዊ ምኞትን ክደን የተባረከውን ተስፋችንን፣ እርሱም የታላቁን የአምላካችንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ፣ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል (ቲቶ 2፡12-13)።” ከጌታ ጸጋ የተነሳ ከተሸናፊነት ወጥተን የድል ሕይወት መለማመድ እንችላለን። አንዳንድ ክርስቲያኖች በዓለም ሳሉ የተለማመዱት ኃጢአት ለምሳሌ ሴጋ፣ ግብረ ሰዶማዊነት፣ ዝሙት፣ ሲጋራ ማጨስ፣ ሐሺሽ መውሰድ፥ መጠጥ መጠጣትና የመሳሰሉት ክፉ ልምዶች በጌታ ቤት ውስጥ ሲኖሩም የድል ሕይወት እንዳይለማመዱ ሳንካ ሲሆኑባቸው ይስተዋላል። ሆኖም ግን በጾምና በጸሎት፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይልና በቅዱሳን የምልጃ ጸሎት እንዲህ ዓይነት ሰዎች ፈጽመው ነጻ ሊወጡ ይችላሉ። እስራኤልን ከፈርዖን ቀንበር ያላቀቀ ጌታ፥ ኃጢአተኞችንም ከኃጢአት ቀንበር በትንሳኤው ኃይል ዛሬም ይፈታል። ብዙዎቻችን ለጌታ ነጻ አውጪ ኃይል ምስክሮች ነን፤ ከብዙ የኃጢአት እስራት ፈቶ ለክብሩ ምስጋና አቁሞናል። እግዚአብሔር ይመስገን። ፈርዖን እስራኤላውያን የግብፅን ምድር ለቅቀው ሲወጡ ያለ የሌለ ኃይሉን አስተባብሮ ወደ ባርነት ሕይወታቸው ሊመልሳቸው እንደዘመተ፣ ቅዱሳን የሰይጣንን የኃጢአት ቀንበር ወዲያ አሽቀንጥረው በመጣል የቅድስና ኑሮ መኖር ሲጀምሩ ሰይጣን ባለ በሌለ ኃይሉ በመዝመት ወደ ተላቀቁት ኃጢአት ሊመልሳቸው መጣሩ አይቀርም። ሆኖም ግን ጸንተው ሲቃወሙት እንደ ቃሉ ከእነርሱ ይሻሻል። እነርሱም በጌታቸው ኃይል ተደግፈው የጽድቅ ኑሮ መኖር ይጀምራሉ። ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን! ደም እስከማፍሰስ ድረስ ከኃጢአት ጋር ገና አልተጋደልንም፤ አልተቃወምንም (ዕብራውያን 12፡ 4)። ስለዚህ ኃጢአትን ለመተው የጨከነ ልብ ሊኖረን ይገባል፤ ይህ ሲሆን ጠላት መቆሚያ ስለሚያጣ እሱን ለመቃወም ትክክለኛ ቦታችንን እንይዛለን።

2. ማናቸውም ጥንቆላ ነክ ነገሮች (ዕቃዎችን) ወደ ቤት ማስገባት። የእግዚአብሔር ቃል “እንደ እርሱ ርጉም እንዳትሆን ርጉምን ነገር ወደ ቤትህ አታግባ፤ ተጸየፈው፣ ጥላው” ይላል (ዘዳግም 7፡26)። እንደ ጨሌ፣ የኮከብ ቆጣሪ ጋዜጣ፣ የክህደት መጻሕፍት፣ የአምልኮተ ሰይጣን መጻሕፍት፣ ወሲብ ቀስቃሽ ፊልሞች፣ ምስሎች፣ ጽሑፎች (ፖርኖግራፊ)፣ ወዘተ ፈቅደን ወደ ቤታችን ማስገባትና መጠቀም ለሰይጣን ጥቃት ራሳችንን እንድናጋልጥ ያደርገናል። ወሲብ ቀስቃሽ ምስሎችንና ፊልሞችን የሚመለከት ክርስቲያን የዝሙትና የሴሰኝነት መንፈስ ቢዋጋው ምንም አይገርምም። እንደነዚህ ያሉ ዕቃዎችን አውጥተን መጣል ወይም ማቃጠል ይገባል። “ከአስማተኞችም ብዙዎቹ መጽሐፋቸውን ሰብስበው በሰው ሁሉ ፊት አቃጠሉት (የሐዋ ሥራ 19:19)።” ቤታችን ከማናቸውም የጠላት መጠቀሚያ ከሆነ ነገር የጸዳ ሊሆን ይገባል።

3. ይቅር የማይል ልብ። ይቅር የማይል ልብ ሰይጣን ወደ ሕይወታችን እንዲገባ በር ከፋች ነው። ሰዎች በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ምክንያቶች ይበድሉን ይሆናል። ቁርሾ ወይም ቂም መያዝ ለሰይጣን አሠራር ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። ቆሻሻ ቦታ ዝንቦችን እንደሚስብ ሁሉ ጥላቻ የተሞላ ልብም አጋንንትንና ክፉ ተጽእኖአቸውን ይስባል። በአንጻሩ ፍቅር የተሞላ ልብ ለሰይጣን አሠራር ምቹ አይደለም። ለዚህ ነው መጽሐፍ ቅዱስ በተለይም አዲስ ኪዳን ስለ ፍቅር አብዝቶ የሚያስተምረው። የበደሉንን ሁሉ ይቅር በማለት ለጠላት ዕድል ፈንታ ልንነፍገው ይገባል። የበደሉንን ሰዎች እየባረክን እንጸልይላቸው። ያን ጊዜ ልባችን ከጥላቻ ስሜት ይፈወሳል፤ የምንጸልይለትን ሰው መጥላት አንችልምና። ምክንያቱም ጸሎት ወይም ምልጃ የፍቅር ቋንቋ ነው። ጠላት የበደሉንን ሰዎች እያስታወሰ ሊያውከን ሲፈልግ ወዲያውኑ ስለ እነዚያ ሰዎች መማለድ እንጀምር።  ጌታ እንዲባርካቸው እንጸልይ። የሰይጣን አሳብ ይከሽፋል፤ ምክንያቱም ሰይጣን ለማንም እንዲጸለይ ስለማይፈልግ ነው። ስለበደሉን ሰዎች ከልብ በምንጸልይበት ጊዜ ጌታ እኛንም የምንጸልይላቸውንም ሰዎች እንደሚባርክ ሰይጣን ያውቃል። ስለዚህ እግዚአብሔር ፍቅር እንዲሞላን ልንጸልይ ይገባል። ጌታ ኢየሱስ ለሰቀሉት ሰዎች “የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” በማለት የጸለየው ስለሚወዳቸው ነው። “ጌታ ሆይ የበደሉኝን ሁሉ ይቅር እንድላቸው በፍቅርህ ሙላኝ” ብለን ልንጸልይ ይገባል። ጌታ ጸሎታችንን ሰምቶ በፍቅሩ ይሞላናል። ሰዎች ሲበድሉን ለመበቀል አንሂድ። ይቅር አለማለት በቀልን መሞላት ነው። በዘዳግም 32፡35 ላይ ጌታ በቀልና ፍርድ የእርሱ እንደሆኑ ተናግሯል። ስለዚህ ሰዎችን በመጥላትና በማስወገድ አንበቀላቸው። አንሠራቸው፤ እንፍታቸው። እኛም በጥላቻ አንታሰር። ይልቁን በመባረክና ስለ እነርሱ በመማለድ እንፈታ። ያን ጊዜ ነገራችን ሁሉ ይለቀቃል። ሰዎችን ይቅር የማንል ከሆነ እግዚአብሔርም ኃጢአታችንን ይቅር አይልም። ኃጢአታችን ይቅር ካልተባለ ደግሞ የጸሎት መልሳችን ይያዛል (ማር 11፡25-26)። በአንድ ወቅት በአሜሪካን ሀገር እግዚአብሔር በፈውስ ሥጦታ ይጠቀምበት የነበረ ጆን ዉምበር የተባለ ሰው ዘንድ እንዲጸልይላት አንዲት በጨጓራ በሽታ ትሰቃይ የነበረች ወጣት መጣች። እጁን ጭኖ ሲጸልይላት የጌታ መንፈስ “እናቷ” የሚል ድምጽ አመጣለት። የጨጓራ በሽታና እናቷ ምን ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚችል ስላልገባው ጸልዮ አሰናበታት። ልጅቷ ግን ከበሽታዋ ስላልተፈወሰች እንደገና በሌላ ቀን ለጸሎት ወደ አገልጋዩ መጣች። ሲጸልይላት ሳለም አሁንም በድጋሚ የጌታ መንፈስ “እናቷ” የሚል ድምጽ አመጣለት። በዚህን ጊዜ ጸሎቱን አቆመና ልጅቷን ስለ እናቷ ጠየቃት። እሷም በመበሳጨት “የእናቴን ነገር አታንሳብኝ፤ በጣም ራስ ወዳድ ሴት ናት፤ አልወዳትም፤ በአምስት ዓመቴ ነው ጥላኝ የጠፋችው፤ በብዙ ሥቃይ ነው ያደግሁት፤ ስለዚህ እጠላታለሁ። ስለ እርሷ እንዲነሳብኝም አልፈልግም” አለችው። ይህም የእግዚአብሔር ሰው ይቅር ማለት እንዳለባትና ይህን ባታደርግ ግን የእርሷም በረከት (ጤንነት) እንደማይለቀቅ ነገራት። ከብዙ ትግል በኋላ ልጅቱ የአገልጋዩን ምክር ሰምታ እናቷን ይቅር አለች። ከዚያ አገልጋዩ ሲጸልይላት ወዲያውኑ ልትፈወስ ችላለች። ለዚህ ነው የእግዚአብሔር ቃል “እናንተ ይቅር ባትሉ በሰማያት ያለው አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም” በማለት የሚያስጠነቅቀን (ማር 11፡26)።

4. ማንኛውም ክፉ ሃሳብ። የተለያዩ ክፉና ንጹህ ያልሆኑ ሃሳቦች ከወደቀው ሥጋችን (አዳማዊ ባሕሪያችን) ወይም ከክፉ መናፍስት ወደ አእምሯችን ሊላኩ ይችላሉ። የመጣውን ሃሳብ ሁሉ ማሰላሰል የለብንም። ክፉና መጥፎ አሳቦችን ወዲያውኑ ልናስወግዳቸው ይገባል። በእርግጥ አእምሮን እንዳያስብ ማድረግ አይቻልም፤ ነገር ግን ቃሉ ማሰብ የሚገቡንን ነገሮች በተመለከተ እንዲህ ይለናል፥ “እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን እነዚህን አስቡ (ፊልጵስዮስ 4፡8)።” “ወፎች ከራስህ በላይ እንዳይበሩ ልታግዳቸው አትችልም፤ ነገር ግን ጎጇቸውን በራስህ ላይ እንዳይሠሩ ልትከለክላቸው ትችላለህ” ይላል የምዕራባውያን ብሂል። በመሆኑም የተለያዩ ሃሳቦች ከጠላትም ከየትም ወደ አእምሯችን ሊላኩ ይችላሉ፤ መጠንቀቅ ያለብን ጉዳይ ተቀብለን ማሰላሰልና በአእምሯችን ስፍራ መስጠት የሌለብን መሆኑን ነው። ይህን ማድረግ በራሳችን ላይ ዓመጽና እርኩሰት ሌላም ከንቱ የማያንጽ ሃሳብ ጎጆ እንዲሠራ ፈቀድን ማለት ነው። አሳባችን እንዳይፋንን ራሳችንን ልንገዛ ይገባል። የተሠጠን የማሰብ ችሎታ ፍሬ ከርሲኪውን ሁሉ እንድናስብ ልቅ እንዲያደርገን ልንፈቅድለት አይገባም። ጤናማውንና የሚያንጸውን ብቻ ልናስብና ልናሰላስል ይገባል።    ይቀጥላል