ተሃድሶ ወይስ ተሃድሶ?

printingpress

ተሃድሶ በተሃድሶ ሆነናል። መንግሥት የኢኮኖሚ ተራራ ጫፍ ላይ ሊያወጣን ያስጀመረንን ጒዞ “ህዳሴ” ብሎታል። የኃይል ማመንጫውን “ህዳሴ ግድብ።” እስር ቤት የወረወራቸውን የ “ተሃድሶ” ሥልጠና ሰጥቶ ፈትቷል። “ጥልቅ ተሃድሶ” ራሱን በራሱ የሚያጸዳበት ብልሃቱ ነው።

ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ደግሞ “ተሃድሶ ተሃድሶ” በሚሉና በሚቃወሙ መሓል ተወጥራለች፤ ሃራጥቃ ተሃድሶ ላስቀየሟት የወጣላቸው ስም ነው። እነዚህን ሁሉ ጒዳዮች ዛሬ አናነሳቸውም።

ዛሬ የምናነሳው ስለ ፕሮቴስታንታዊ ተሃድሶ ነው። ወንጌል አማኞች የሆንን (እንደ ጥሩ ኢትዮጵያዊ) አንድን አስተምህሮ ስንቀበል ግልብጥ ብለን ወጥተን ነው፤ ሌላ አዲስ አስተምህሮ ብቅ ብሎ የያዝነውን እስኪያስጥለን። ይህ “የሐበሻ ሕመማችን” ነው። “የመሪ ያለህ” ከታተመ፣ “የአገር ያለህ” “የፍትህ ያለህ” “የወንድ ልጅ ያለህ” ይከተላል። ይኸ በጥልቅ ያለማሰብ፣ ያለመመካከርና የአሳብ ድህነት ምልክት ነው።

በ1960ዎቹ፣ ቲ ኤል ኦስበርን፣ ካትሪን ኲልማን፣ ኦራል ሮበርትስ ነበሩ። ካትሪን ኲልማንን በሴትነትዋ ምንም ያላሉ መሪዎቻችን፣ የእህቶቻችን ጸጋቸው እንኳ እየመሰከረ፣ “ወንጌላዊ” ቀርቶ “ዲቊና” ቢያምራቸው ጒድ ይፈላ ነበር። የእህቶች አገልግሎት ከስልክ ተቀባይነት፣ ከኳየር፣ ከ "ሕጻናት አገልግሎት"፣ ከሻይ ቀጂነት አያልፍም ነበር! ዛሬም እንኳ በየዩቱብ ቲቪ ጣቢያ ረከቦት ዘርግተው መድረክ ያሟሙቃሉ! ነቢዪት ዘማሪት መጋቢ(ት) ተብለው አደባባይ ከወጡት ውጭ በዋነኛ ኮሚቴዎች ላይ የተሰየሙ በፖሊስ ተፈልገው አይገኙም!

በ1970ዎቹ ሃል ሊን(ድ)ሲ፣ ዋችመን ኒ፣ ፍራንኪልን ሆል፣ ዴሬክ ፕሪንስ ነበሩ። በ1980ዎቹ ዮንጊ ቾ፣ ቲም ላሄይ፣ ጂሚ ስዋገርት፣ ኬኔት ሄግን፣ ቤኒ ሂን ነበሩ። ከዚያ ቦንኬ፣ ቲዲ ጄክስ፣ ቲቢ ኤን፣ ቲቢ ጃሽዋ፣ ወዘተ። ሁሉም “ፈረንጆች”። በዋነኛነት ዛሬ ድረስ የሚጠቀሱ ጥቅሶች ደግሞ ነበሩ፦ ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ። (ኢሳ 54፡13) ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች። (መዝሙር 68፡31) እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም። (1ኛ ዮሐንስ 2፡20፣27) ጥቅሶቹ ትክክልና ተገቢ ጥቅሶች ናቸው፤ ችግሩ በቊንጽል እንጂ በቃሉ ሙላትና በታሪክ ላይ አለመመስረታቸው ነው (የሐዋ. ሥራ 20፡27) ችግሩ ለስንፍና፣ ለቤተክርስቲያን ላለመገዛት እና የተመረጥን ሕዝብ ነን ለማለት መዋላቸው ነው። ልምምድ አስፈላጊ ነው፤ መንፈስ ቅዱስም አስተማሪ ነው፤ ያለ ሕይወት ልምድ ዶክትሪን ብቻውን ምውት ነውና። በአንጻሩ፣ ልምድ ብቻውን ያለ ዶክትሪን፣ ቦይ እንደሌለው ጎርፍ ነው፤ ብዙ ጥፋት ያስከትላል። እየሆነ ያለውም ይኸው ነው።

እነ ቄስ ማርቲን ሉተር (መካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን፣ ቃለ ሕይወት) “ቃል፣ ቃል፣ ዶክትሪን፣ ዶክትሪን” ስለሚሉ እንደ ሙሉ ወንጌል (መንፈስ መንፈስ፣ ልምምድ ልምምድ) ማለት ስለማያበዙ በጥርጣሬ ይታዩ ነበር። ዛሬ ዘመኑ ተለውጦ! አንዳንዶች አንዴ “መንፈስ ነን” ሲሉ፣ የክርስቶስን ማኅበር ሲያነዋውጡ፣ ጭፈራ ሲያበዙ፣ ሕዝብ ተራቊቶ መሪዎች ሲበለጽጉ፣ የ “ዶክትሪን ያለህ” አስብሏል!

ዛሬ “ሪፎርሜሽን” ወይም “ተሃድሶ ቲኦሎጂ” እየጎላ መጥቷል። ለጌታ ክብር ይግባውና ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ት/ቤቶች በዘመናችን ተከፍተዋል። ቀድሞ የጌታን ቃል በጥልቀትና ከምንጩ ማጥናት ከመንፈሳዊነት መጒደል፣ አእምሮአዊነት/ሥጋዊነት ሲባል እንዳልነበር! የእግዚአብሔርን ምሥጢራት ለማወቅ መጓጓት ሰይጣናዊ ተብሎ እንዳልነበር! (መዝሙር 25፡14ኤፌሶን 3፡9) ዛሬ ደግሞ በተቃራኒው “ድግሪ” አለማወጅና አለመሞጋገስ ነውር መስሏል።

ጥያቄው ይህ ነው፦ ከ “መንፈስ መንፈስ” ወደ “ዶክትሪን ዶክትሪን” መፈናጠር እንዳናበዛ፣ ልምምድና ዶክትሪንን እንዴት በሚዛን እንያዝ?

የ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ተሃድሶ ንቅናቄ መሪዎች ማርቲን ሉተር፣ ካልቪን፣ እና ዝቪንግሊ የሐዋርያ ጳውሎስን መልእክቶች የተረጎሙት በአውሮጳዊ አእምሮ፣ በግሪክ ፍልስፍናዎችና ባህላዊ ተጽእኖ፣ በሮማ ካቶሊካዊት ግዛታዊ እይታ ውስጥ ታቅፈው ነው። ንቅናቄው፣ ከጀርመን፣ ከፈረንሳይ፣ ከሆላንድ፣ ከስዊትዘርላንድ፣ ከሮማ እና ከእንግሊዝ ፖለቲካዊና ኤኮኖሚያዊ ውጭ ሰፊውን የኦርቶዶክሱን ዓለም አይወክልም ነበር። የአውሮጳው ተሃድሶ የመጀመሪያውን መቶ ክፍለ ዘመን ታሪካዊ ዐውድ እንደሚገባ ስላላጤነ፤ የጳውሎስን አይሁዳዊነት ዘንግቶ፣ ጳውሎስን አይሁድ ጠል አመስሎታል። ቄስ ማርቲን ሉተር ግን አይሁድ ጠል መሆኑ ስውር አልነበረም።

በአሁኑ ወቅት በአገራችን ጎልተው የሚጠቀሱ የተሃድሶ መምህራን፣ ከቀደሙት፣ ጆን ዊንትሮፕ (እ. አውሮጳ 1588—1649) ጆናታን ኤድወርድስ (1703—1758)፤ በሕይወት ካሉት፣ ጆን ማካርተር፣ ስፕሮል (ሊገኒር ሚኒስትሪ)፣ ጆን ፓይፐር፣ አል ሞለር፣ ወዘተ፣ ናቸው።

የተሃድሶ አስተምህሮ መሠረቱ እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባው ቃል ኪዳን ነው (ዘፍጥረት ምዕራፍ 12, 15, 17፤ ገላትያ 3፡16) ይህ በራሱ አጠያያቂ አይደለም፤ እግዚአብሔር ከአሕዛብ አንድ አብርሃምን ጠራው፣ የተለየ ሕዝብ ሊያደርገው። ዓላማው በእርሱ በኲል ሰዎችን ሁሉ ወደ ራሱ መጥራት ነው። ሁሉ ከጠሪው ነው። ጠሪው ማንንም አይለይም፤ ኪዳኑንም አይለዋውጥም። የኪዳኑን ስጦታ መቀበል ብቻውን የእግዚአብሔር ሕዝብ ያደርጋል። ሆኖም፣ ሁለት ጒዳዮች መጤን ይኖርባቸዋል። አንደኛ፣ የተሃድሶ ታሪክና የተገኘበት ባህል ተጽእኖ ውጤት። ሁለተኛ፣ ዛሬ የሚታየው ስነ መለኮታዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዳራዎቹ።

የተሃድሶ ትምህርት በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ መነጽር ሲታይ ምን ይመስላል? ከአውሮጳውያኑና ከሰሜን አሜሪካኑ ክርስትና ይልቅ ባህላችን ለጥንት ምሥራቃዊት ቤተክርስቲያን ቋንቋና ልማድ የቀረበ መሆኑ የተሃድሶን ይዘት እንዴት ሊጠይቅና ሊያጠናክር ይችላል? ያለ በቂ ጥንቃቄ የተቀበልነው ምዕራባዊ ክርስትና ምን ዓይነት እርምት ይሰጠው? የተሃድሶ ትምህርት በተገኘባቸው አህጉራት ማህበራዊውን እውነታ እንዴት አበጀው ወይም ቀረጸው?

ከመጨረሻው ጥያቄ ብንጀምር፣ ዊንትሮፕም ኤድወርድስም ሰው ሁሉ በአምላክ አምሳል መፈጠሩን፣ የኅሊና ነጻነት መጎናፀፉንና በአምላክ ፊት እኲል መሆኑን መስክረዋል። በአስተምሮአቸው፣ የሚሆነው ሁሉ እግዚአብሔር እንደ ወሰነው ነው። እግዚአብሔር የሚድኑትን እና የሚጠፉትን አስቀድሞ አውቋቸዋል፤ እኛ ምርጦቹ ነን፤ እግዚአብሔር ያልመረጣቸው፣ ለጥፋት የመደባቸው አሉ። እኛን የመረጠ እግዚአብሔር አንዳንዶች “አናሳዎች”ን አልመረጣቸውም። ታዲያ ይኸ አተረጓጎም (“አናሳዎችን”) ባርያ አድርጎ ለመግዛትና ለመሸጥ አስችሎአቸው ነበር። እንግሊዞች ከአውሮጳ ፈልሰው አሜሪካ ሲሠፍሩ የእስራኤል ምርጦች ነን ብለው ነው (ውሸት ነው)። አፈናቅለው፣ ገድለውና አታልለው የወረሱትን ምድር በከነዓን ምድር መስለው ነው (ውሸት ነው)። አውሮጳውያኑ ባመጡት ፈንጣጣ የአገሬው ሕዝብ ሲያልቅ እግዚአብሔር እንድንስፋፋ ምልክት ሲሰጠን ነው አሉ (ውሸት ነው)።

ሰዘርን ባፕቲስቶች ወንጌልን በዓለም ዙሪያ ማዳረስ እና ጥቊሮችን ባርያ ማድረግ አይጣሉም ብለው ነበር። ዛሬም እንኳ ድርጅታዊ መዋቅራቸው ነጭና ጥቊር አማንያንን የለያየ ነው። እንደ አውሮጳ በ1973፣ ፕሬስብቴሪያን ቸርች ኦፍ አሜሪካ ከሰሜኑ ተከፍሎ በደቡባዊ የአሜሪካ ግዛት ሲደራጅ ጥቊር አማኝ ነጩን እንዳያስተምር፣ ሴት አማንያን በጒባኤ እንዳይጸልዩ ከልክሎ ነበር፤ ዛሬም ብዙ አልተለወጠም። የቀድሞዎቹ ሚሲዮናውያን ይዘው የመጡት ወንጌል ርዕዮተ ዓለማዊ ይዘቱ ምን እንደሚመስልና ምንጩ ግልጽ ይመስለናል! በሌላ አነጋገር፣ የተሃድሶን ትምህርት አተረጓጎም መመርመር፣ ከአገራችን እውነታዎች አንጻር፣ ይልቊን ከእግዚአብሔር ቃል አንጻር ብዙ ጸሎትና ምክክር ይጠይቃል። ከዚህ ቀደም በሌላ ሥፍራ እንዳልነው፣ የምዕራባውያንን የአስተምህሮ ዓሳ መብላት በብልሃት ነው!

አንድ ምሳሌ ብቻ እናንሳ። ዶ/ር ዌይን ግሩደም በአሜሪካ ወንጌላውያን ዘንድ የታወቁ የስነ መለኮት ሊቅ ናቸው። ደግሞ የዘረኛ፣ ሰው አዋራጅና ዋሾ ፕሬዚደንት ትረምፕ ደጋፊ ናቸው (አክብሮት ለመንሳት ሳይሆን በአደባባይ የተነገረ እና እውነት ስለሆነ ነው)። ዌይን ማንንም መደገፍ የዜግነት መብታቸው ስለሆነ አያስወነጅላቸውም። ችግሩ ትረምፕ ደቡባዊውን የአሜሪካ ድንበር በግንብ አጥራለሁ ባሉበት ወቅት በቅድሚያ ፍርሃት መንዛት ነበረባቸው፤ ትውልደ ስፓኒሽ እና ነጭ ዘር የሌለበትን ስደተኛ ሽብር ፈጣሪ፣ ሴት ልጅ ደፋሪ፣ ነፍሰ ገዳይ፣ ዕፅ ወሳጅ ብለው ፈረጁ። ነጮች በመኻንነትና በውርጃ መስፋፋት ከሠላሳ ዓመት በኋላ አናሳ እንደሚሆኑ ታውቋል። የህጻናት ንግድ የተጧጧፈው አንዱም ለዚህ ነው! በቊጥር አናሳነት ፍርኃት የተናወጠውን የአሜሪካን ገጠሬና ነጭ ወንጌላውያንን የኖረ ጥላቻ ቀሰቀሱ። የእነዚህን ድጋፍ ሳያገኙ ማሸነፍ እንደማይችሉ አውቀው ነበር። በዚህ ወቅት ነበር ግሩደም ብቅ ያሉት፤ ሕዝበ እስራኤል ከጠላቶቻቸው ጥቃት ለመዳን ከተሞቻቸውን በግንብ አጥረው ነበር አሉ። የትረምፕን እጅ በዘረኛ ስነ መለኮት ቅባት ቀብተው አበረቱ። አሜሪካኖችን ሕዝበ እስራኤል፣ ምድራቸውንም ከነዓን አስመሰሉ!

ከላይ የጠቀስናቸው የተሃድሶ መምህራን፣ ሰው ሁሉ በአምሳለ እግዜር የተፈጠረ ስለሆነ ክቡር ነው ብለው የሚያስተምሩ ናቸው። የስደተኞች ልጆች ከእናቶቻቸው ተነጥቀው እንደ አውሬ በሽቦ አጥር ውስጥ ሲቆለፍባቸው ሲታመሙና ሲሞቱ፣ ሴቶቻቸው ሲደፈሩ ምንም ያላሉ ናቸው። ኢየሱስ ወደ ግብጽ ሲሰደድ የኢሚግሬሽን ሕግ አልጣሰም፤ ሕግ የሚጥሱ ቢታሠሩ ቢባረሩ ትክክል ነው አሉ! ምኑን ከምኑ አገናኙ? የእግዚአብሔርን ቃል አስተካክሎ የማያውቀውን ምእመን ለማሳመን ግን በቂ ነበር። እውነቱ ምንድነው? እውነቱ ጥቁር መሆን ወንጀል አይደለም! አሜሪካ ስደተኛ የገነባት የስደተኛ መጠጊያ ነች፤ “ስደተኞች ነበራችሁና ስደተኛውን አትበድለው” (ዘጸአት 22፡21)፤ “እንግዳ” ሆኜ መጥቼ ነበር (ማቴዎስ 25፡35 45)፤ “እንግዶችን መቀበል አትርሱ፤ በዚህ አንዳንዶች ሳያውቁ መላእክትን እንግድነት ተቀብለዋል፤ ከእነርሱ ጋር እንደ ታሰረ ሆናችሁ እስሮችን አስቡ፥ የተጨነቁትንም ራሳችሁ ደግሞ በሥጋ እንዳለ ሆናችሁ አስቡ” (ዕብራውያን 13፡2 3)።

ነጭ የተሃድሶ መምህራን ድርጊታቸው ከወንጌል አስተምህሮ ጋር አልተስማማም። በሌላ አነጋገር ነጭ ያልሆነን ማጥላላትና መግፋት የመጣው የነጭ የበላይነት እንዲያንሠራራ ነው። ለዚህ አንደኛው ስልት መጽሐፍ ቅዱስን መጥቀስ ነው! የተሃድሶ ዶክትሪን በደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ መጠናከር ዋነኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው አንርሳ! አውሮጳውያን አፍሪካና ኤዥያን ቅኝ የገዙት በዚሁ ዶክትሪን ተንተርሰው እንደሆነ አንርሳ! ጥቁር ሕዝቦች ሙሉ ሰው ስላልሆኑ (ከእንስሳ ብዙም ስለማይሻሉ) ቢያንስ ቢያንስ ነፍሳቸውን እናድን፣ ከአውሬነት እናላቅቃቸው ነበር ግቡ! ቅኝ መግዛት ጥቊሩን ሕዝብ ከአውሬነቱ ለማላቀቅ የታሰብ የጽድቅ ሥራ መሆኑ ነው!!

ማንኛውም አስተምህሮ (ነገረ መለኮት) በጠንሳሹ ባህልና እሳቤ የተቀለመ ነው!! ተሃድሶ በመሠረቱ ጥሩ አስተምህሮ ነው፤ አማንያን ካህናት ናቸው፤ መዳን በኢየሱስ በማመን ብቻ በጸጋ ብቻ ነው። (ኤፌሶን 2፡8። 1ኛ ጴጥሮስ 2፡9) መርምሮና መርጦ መውሰድ ግን ግድ ነው! የተሃድሶ አስተምህሮ መሠረቱ አውሮጳዊ ነው። ጥንታዊት ቤተክርስቲያን የተገኘችበት ቀዳሚ ባህልና ታሪክ ደግሞ አሁዳዊ፣ ሮማዊና ግሪካዊ ነው። የኋለኛው ለቀደመው እርምት እንደ ሰጠ ሁሉ፣ በቀደመው የኋለኛውን መመርመር ግድ ነው!  

ሞትና ፕሮፌሰር

ምትኩ አዲሱ

ግንቦት 8/2012 ዓ.ም.