mwm

ፕ ሮ ፌ ሰ ር  መ ስ ፍ ን  ወ ል  ደ ማ ር ያ ም

1922--2013 ዓ.ም.

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በትናንትናው እለት በሞት ተለይተውናል። የሕይወታቸው መርህና ፍሬው ግን አብሮን ይኖራል። የቀድሞ ተማሪዎቻቸውና የደረሷቸው መጻሕፍት የኖሩለትን ዓላማ ይመሰክራሉ፤ ይልቊን ደግሞ የታገሉለት የአሳብ ነጻነት ዋነኛው ነው። ሳይቆጠቡ፣ ሳይታክቱና በነቀፌታ ሳይበገሩ የተረዱትን ለማስረዳት፣ ላመኑበት መስዋእት የከፈሉ ዓይነተኛ ኢትዮጵያዊ ናቸው። ከፋሺስት ኢጣልያ ወረራ ጀምሮ፣ የቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴን፣ የደርግና የኢሕአዴግን መንግሥታት በምድር ሥሪት፣ በሶሻሊስት ርእዮተ ዓለምና በዘር ፖለቲካ አመራራቸው ሲሳተፉበትና ሲሞግቱ ኖረዋል። አዲሱን ትውልድ በቋንቋው ያነጋገሩ፣ እንዲጠይቅና አገሩን ለማወቅ እንዲጥር፣ አሳብን በአሳብ እንጂ በኃይል እንዳይመክት ምሳሌ የተው ሰው ናቸው። ሕይወታቸውን በሦስት ቃል ማጠቃለል ቢቻል፣ "ከዳር ቆሜ አላይም!" የሚል ይመስለናል!

አገር ወዳድ ዜጎችና ፓርቲዎች፣ ለሕዝቦቿ መብት መከበር፣ እኲልነትና አብሮ መኖር የሚገዳቸው ሁሉ፣ የእኚህን ሰው ዓላማ የማስቀጠል ታሪካዊ ግዴታ አለባቸው። ከትውልድ ትውልድ እንደ ተስቦ እየተዛመተ፣ የልብና የአዕምሮ ስፋት ያልተቸረው የነውጥ ባህል እንጂ ሰላምን ሳያዩ ማለፋቸው ሊያሳፍረን፣ ሊቆጨን እና ሊያነሳሳን ይገባል! የአገራችን ሕዝቦች በሰላም የሚኖሩባትን ምድር ለመፍጠር ጊዜው አላለፈም! ጊዜው አሁን ነው!

ሞት ማለት፦

አለመናገር ነው ጭው ያለ ዝምታ...
የውሸት ልዩነት ተጋድሞ በተርታ...
ሞት ማለት፦
አይረገዝበት፤ አይወለድበት...
ውሸትና እውነት በማይበርድ ፍትወት የተሳሰሩበት
የድብቅብቅ ዓለም ምስጢር የበዛበት፤
ሁሉም በየጉድጓዱ የተሸሸገበት።
ሞት ማለት፦
ክብርና ውርደትን ለይቶ አለማወቅ...
ሞት ማለት...
ቡቃያው አያሸት፤ ፍሬው አይለመልም።
ዝናብ አይዘንብበት ድርቀት ነው ዘላለም።
ሞት ማለት፦ የሞት ሞት
አዕምሮ ፈራርሶ፤
ኅሊና በስብሶ፤
ሰውነት ረክሶ...
የሞት ሞት ይኸ ነው፤
ትንሳኤ የሌለው።

~ መወማ፣1967 ዓ.ም.

ሞት እና ፕሮፌሰር

ኑዛዜው ጥያቄ ነው