መንገደኛ ሰው መንገደኛ

death

ሰው ሲወለድ መንገደኛ ነው። መንገደኛ ያልሆነ የለም። ሁሉም አንድ አቅጣጫ ይዞ ተጓዥ ነው። ይወለዳል። ያድጋል። ይሸመግላል። ይሞታል። ይቀበራል። አንዳንዱ ሳይወለድ ወይም እንደ ተወለደ ይሞታል። አብዛኛው አድጎ ይሞታል። የተቀረው ሸምግሎ። ብቻ ሁሉም ሟች ነው። መንገደኛው ሕዝብ ነው፣ የሚጓዘው ግን ለየብቻ ነው። ማንም ለማንም ጒዞውን አይጓዝለትም።

አብዛኛው ሰው ሟች መሆኑ አይታወሰውም። በሥራ ብዛት፣ በመዝናኛዎች ብዛት፣ በወዳጅ ብዛት፣ ባፈራው ንብረት ኑሮውን ያበጃጃል፤ ራሱን ያስደስታል፣ ያረሳሳል። ጤናው እየተዛባ ያስታውሰዋል እንጂ፤ ጉበቱ፣ አንጀቱ፣ ሃሞቱ፣ ራስ ምታቱ፣ ሳሉ፣ ቁርጥማቱ። ይኸ ሁሉ ሲሆን ጊዜ ቆሞ አይጠብቅም፣ ይገሰግሳል። እንደ ቀድሞ ሥራ ለመሥራት ጒልበት ያጣል፤ ያዝናኑት የነበሩት ዛሬ አያስደስቱትም፤ ምግብ እንኳ እንደ በፊቱ አይጣፍጠውም፤ ወዳጆቹ አንድባንድ ይሞታሉ። ብቻውን ይቀራል። ስለ ጤናው፣ ስለ ፍጻሜው ማሰብ ያዘወትራል። የቀድሞውን ማስታወስ ያበዛል፤ የበላውን መርሳት ይጀምራል። በሌላው ላይ ያይ የነበረውን በራሱ ላይ ያያል። አካሉ እንደሚያንጠባጥብ እንደወላለቀ ቤት ይሆንበታል። መራመድ ረጅም ጊዜ ይፈጅበታል። ዘመን ግን መሮጡን አያቆም፤ ወደ ፍጻሜ ይገሰግሳል። የመደበልን ዕድሜ ሰባ ዓመት፥ ቢበረታ ሰማንያ፤ ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው።

* * * *

ሰውዬው የመኪናውን ሞተር ቀስቅሶ አውራ መንገድ ላይ እንደ ወጣ። እግረኛ ወዳጁን ያገኛል፤

ወዳጁ፦ ወዴት ልትጓዝ ነው ጃል?

መንገዱን ይዤ ወደ ወሰደኝ ልሄድ፤

ወደ ወሰደኝ ማለት?

የት እንደሚወስደኝ አላውቅም፤ ስደርስ ምናልባት አውቅ ይሆናል፣ ቢል ጤነኛ ለመሆኑ ጥያቄ አይፈጥርም?

ለመንገደኛ መዳረሻውን አለማወቁ ዓላማ ቢስነት ነው፤ ለማወቅ አለመጣሩ ቂልነት ነው። ሲደርስ ምን እንደሚጠብቀው መገመት፤ ደርሶ የተመለሰ ሰው ይኖር እንደሆነ መረጃ መሰብሰብ ያስፈልጋል። አለዚያ መንከራተት ነው።

ትክክለኛ አድራሻ ይዞ እንኳ አንዳንዴ መንገድ መሳት አለ፤ እንዲጠቊሙን እርዳታ እንጠይቃለን፤ ወይም ወደ ተነሳንበት እንመለሳለን። ጒዞው ከገመትነው በላይ ጊዜ ሊፈጅ ይችላል። ወደ መጣንበት ሳንመለስ ከመንገድ መቅረት አለ።

የሕይወት ጒዞ እንደ እግር ጒዞ ፋታ አይሰጥም። ላደለው አርጅቶ መሞት መልካም ፍጻሜ ነው። ከሞት የሚያመልጥ የለም። ጒዞው ድንገት ሊቋረጥ ይችላል፤ ልምምጥ አያውቅ! የዝግጅት ብዛት አያዘገየው፣ አያስቀረው!

ምን ያህል ቢያምረው ሰው ጎልምሶ መልሶ ሕጻን አይሆንም፤ ሸምግሎ ጒርምስናን ዳግም አያያትም። አንዱን የእድሜ ጀምበር ሲሻገር ከኋላው ይቆለፍበታል። እድሜ እየገፈታተረ ያቻኲለዋል። ምን ያህል ጠንካራ ቢመስል፣ ብርታት እየከዳው እንጂ እየጨመረ አይሄድም።

የቅርብ ወዳጅህን፣ የምትሞት(ቺ) ይመስልሃ(ሻ)ል? ብለህ ጠይቅ። ሰዎች ሲሞቱ፤ በሣጥን ተደርገው ጒድጓድ ውስጥ ሲጣሉ፣ አፈር ሲጫንባቸው አይቻለሁ፤ እኔ ግን የምሞት አይመስለኝም ይላሉ? ከሞትኩ በኋላ ስለሚሆነው ምን አስጨነቀኝ? ያሳለፍኩት አነሰና ነው ስላላየሁት የምጨነቀው? የፈጠረኝ እርሱ ይጨነቅበት ሊሉ ይችላሉ። ያንተ፣ ያንቺ መልስ ምንድነው?

ሰው ሁሉ መንገደኛ ነው፤ መንገዱ ወዴት እንደሚወስድ የሚያውቅ ግን ጥቂት፣ እግዚአብሔር የልቡን ዐይን ያበራለት ሰው ነው። ወዴት እየሄድክ(ሽ) ነው? ከወዲያኛው ዓለም የመጣ መንገድ ጠቋሚ ይኖር እንደሆነስ?

የተለያዩ ሰዎች በተለያዩ ዘመናት የተለያየ ነገር ብለዋል። ኢየሱስ የተናገረውን የሚመስል ግን እስካሁን የለም፦ “ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም(ዮሐንስ ወንጌል 3፡13-21)። “... እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው። እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኵር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፥ እነሆ፥ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች (መላእክት) በአጠገባቸው ቆሙ ... ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው” (የሐዋርያት ሥራ 1፡9-11)። ዳግመኛ የሚመጣው በህያዋንና በሙታን ላይ ለመፍረድ ነው (የሐዋርያት ሥራ 10፡42፤ 2ኛ ጢሞቴዎስ 4፡1)

“[ኢየሱስ] ወደምሄድበት ታውቃላችሁ፥ መንገዱን ታውቃላችሁ [አላቸው]። ቶማስም። ጌታ ሆይ፥ ወደምትሄድበት አናውቅም፤ እንዴትስ መንገዱን እናውቃለን? አለው። ኢየሱስም። እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም ... እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና፤ አብም ስለ ወልድ እንዲከበር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ” (ዮሐንስ 14፡4-6፣13)

“በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ” ትልቅ የምሥራች ቃል ነው! መንገዱ ጠፍቶኛል የሚሉ ሁሉ ትልቅ ተስፋ አላቸው። እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ እኔን ብታምን(ኚ) የለመንከ(ሺ)ውን እሰጥሃ(ሻ)ለሁ ብሏላ! እስቲ ለምን(ኚ)ና ሞክረ(ሪ)ው!!

ከሰማይ የመጣውን፣ እውነተኛውን የሕይወት መንገድ አለመስማት ለዘላለም መጥፋት ነው፦ “ለሚናገረው እምቢ እንዳትሉ ተጠንቀቁ፤ እነዚያ (ሕዝበ እስራኤል) በምድር ላስረዳቸው እምቢ ባሉ ጊዜ ካላመለጡ፥ ከሰማይ ከመጣው ፈቀቅ የምንል እኛስ እንዴት እናመልጣለን?” (ዕብራዉያን 12:25)። ሰማይ እንደምናስበው ወዲያ ማዶ እንዳይመስለን፤ የሰማይ እና የምድር ድንበር ቅርብ ለቅርብ ሆኖ በማይታይ መጋረጃ ተጋርዷል (ሉቃስ 24፡13-31)።

* * * *

ሰው ሁሉ፣ ጊዜ ቆሞ የማይጠብቀው ተጓዥ መንገደኛ ነው። በጊዜ ጎዳና ላይ ተወልዶ ይነጒዳል። ባላሰበው ሰዓት፣ ባልጠበቀው አኳኋን “ደርሰሃል ውረድ!” ይባላል! አልወርድም ሊል ይችላል? አልተዘጋጀሁም፣ ሌላ ዕድል ይሰጠኝ ማለትስ? የሚመራውን ቶሎ ካላገኘ፣ ይህ ሰው መጥፋቱ ነው።

busLondonኢንተርኔትና ሴልፎን እንደ ዛሬ ምድር ዓለሙን ከማቆላለፉ በፊት እንግሊዝ አገር ለጒዳይ ሄጄ ነበር። አንዱን ቀን አንበሳ መሳይ አቶቡሳቸውን ተሳፍሬ ሎንዶንን ላይላቸው ወጣሁ። የቼልሲን ክለብ በስተ ግራ ቊልቊል እያየሁ አለፍኩ፤ የአንድ ሰዓት ያህል መንገድ ተጓዝኩ። በእግር ደግሞ ልሞክር ብዬ የአቶብሱን ቊጥር እና የአውራ መንገዱን ስም ማስታወሻ ይዤ ወረድኩ። ተዟዙሬ ቆይቼ ሲደክመኝ ወደ ተነሳሁበት አመራሁ። አቶቡሴ ብዙ ሳታስጠብቀኝ ደርሳልኝ ተሳፈርኩ። አንድ ሰዓት ያህል ተጉዤ። ሰው ሁሉ ተንጠባጥቦ አልቆ። እኔና ሾፌር ብቻ ቀረን። ሾፌር በኋላ መስታወት ያየኝ ኖሯል። በአሳብ ተውጬ ተዘናጋሁ ወይስ? ዞር ብሎ፣ ውረድ፣ ማዞርያ ደርሰናል አለኝ። ዙሪያዬን ባይ ባይ ... የማስታውስበት ምልክት ተነቃቅሎ የት ገባ? የቼልሲን ክለብ እንዳላለፍኩ እርግጠኛ ነበርኩ።

ሾፌሩን፣ ባተርሲ ድልድይ ጋ ነው የምወርደው እኮ፣ አልፌው ይሆን አልኩት። እግዜር ይስጠው፣ ነገሩ ገባውና ስልኩን አንስቶ ከፊት ያለውን አቶቡስ አስቁሞልኝ፣ ሩጠህ ያን አቶቡስ ተሳፈር አለኝ። ለካንስ የእንግሊዞች ቀኝ ለኛ ግራ ስለ ነበር፤ መንገዱን ሳልሻገር ተሳፍሬ በተቃራኒው አቅጣጫ ስጓዝ አገሬ ልገባ ምን ቀረኝ? ለካንስ ጒዞዬ እንዳሰብኩት ወደ ቤት እየወሰደኝ አልነበረም! የዚህ ትርጓሜ ምንድነው? ትርጓሜው፣ አቶቡስ መሳፈር ብቻውን ቤት አያደርስም ነው። ትርጓሜው ጥሩ መረጃና የሚታመን መሪ መያዝ ያሻል ነው። አለዚያ ድካም ነው፤ አለዚያ መጥፋት ነው። ይኸም የሕይወት ተምሳሌት ነው!

የተያያዝከ(ሺ)ው መንገድ ወዴት እየወሰደህ(ሽ) ነው? ትክክለኛ አድራሻ ይዘሃ(ሻ)ል? ትክክለኛ አድራሻ ለመያዝህ(ሽ) እርግጠኛ ነህ(ሽ)? “እውነተኛው የሕይወት መንገድ እኔ ነኝ” ብሎአል፣ ምን ትጠብቃለህ? ምን ትጠብቂአለሽ? በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ በዘመናት ሁሉ ይህን የምሥራች ቃል በሕይወታቸው ሞክረውት ፍቱንነቱን አረጋግጠዋል! አረጋገጥን የሚሉትን በመሥሪያ ቤት፣ በትምህርት ቤት፣ በስታዲየም፣ በቤተሰብህ መሓል አይተሃቸው ይሆናል። ኢየሱስ እንዲህ ይላል፦ “ሞቼም ነበርሁ እነሆም፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፥ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ ... ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል ... ወደ እኔ የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም (ራእይ 1፡18፤ ዮሐንስ ወንጌል 11፡25፤ 6፡37)

ፖለቲከኛ ቀስ በቀስ | ቀላሉን መንገድ | የማለዳ ድባብ | ከየት ተገኘሽ ሳልል | ቋንቋን በቋንቋ | ስደተኛውና አምላኩ | ሞት እና ፕሮፌሰር | ዐቢይን በባራክ

pic credit: googleimages