ስደተኛውና አምላኩ

 ከ"የስደተኛው ማስታወሻ" ም. 33/34 ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

ጋዜጠኛ ተስፋዬ ገብረአብ በ "የስደተኛው ማስታወሻ" [2006] መጽሐፉ ላይ "ፍቅር በለጠ" እና "ህሊና እንደ አምላክ" [ምዕራፍ 33፣34] በተሰኙ ተያያዥ ርዕሶች ሥር ስለ ክርስትና ሃይማኖት ያለውን መረዳት አስፍሯል። ጴንጤዋን "ፍቅር በለጠ" ን እንደ መስተዋት ይዞልን የሃይማኖትን አስተምህሮዎች ሊያስረዳን ሞክሯል። በዚህ ሐተታዊ ግምገማ ሁለት አሳቦችን እናነሳለን፦ 1/ "ፍቅር በለጠ" እና የያዘችው ሃይማኖት ምን ይመስላሉ? 2/ ጋዜጠኛው/ደራሲው በእጁ የያዘው መስተዋት የራሱን ማንነት እንዴት ይገልጠዋል? በመጨረሻም፣ ስለ ደራሲውና ሥራዎቹ አጭር አሠሳ አድርገን እንደመድማለን።

ደራሲው በ1987 ዓ.ም. ወደ አሜሪካ ለጉዳይ በተጓዘበት ወቅት ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የምትሰራ "አንዲት ሴት" ዲሲ አሜሪካ "ፍቅር በለጠ" ለተሰኘች ዘመዷ በእጁ ፖስታ እንደላከችና ሲደርስ ዘመድ የተባለችው "ለረጅም ጊዜ ያላያት" ጎረቤቱ ሆና እንዳገኛት የሚገልጽ ሐተታ ነው። ከዚያ በመነሳት ያደረገችለትን መስተንግዶና ጨዋታቸውን ያጋራናል።

"ፍቅር በለጠ" ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን ልትወስደው ደጋግማ ጠይቃው "ከአንድ ጊዜ በላይ" አብሯት ሄዷል። "ፍቅር" ሁለት ልጆች አሏት። በዕድሜ ከደራሲው ትበልጣለች። አሜሪካ በተገናኙበት በ1987 ዓ.ም ደራሲው 27 ዓመቱ ነው፤ "ገና ኮረዳ ትመስያለሽ" ይላታል [ገጽ 349]። ወደ አሜሪካ የመጣችውም ከሁለት ልጆቿ ጋር ነው። ባል ይኑራት፣ ትፍታ፣ ይሙት አልተገለጸም። አሜሪካን አገር በገባ "በነጋታው" ደወሎላት፤ በጠቆመችው አድራሻ መሠረት አፓርታማዋ ደረሰ። በር ላይ የተጋጋለ ሰላምታ እየተለዋወጡ "በሃይለኛ ስሜትና መንፈስ ተሞልታ ... ይሄ የጌታ ኢየሱስ ተአምር መሆን አለበት። አንተን ይህን ፖስታ አስይዞ ወደዚህ ቤት የላከበት ምክንያትና አላማ ይኖረዋል" አለች። ሁለቱ እንዲገናኙ የታቀደ ነገር ይኖር ይሆን? ወደ ውስጥ እንደ ገቡ አንድ ሳሎን፣ አንድ መኝታ ቤት፣ አንድ ወጥቤት አፓርታማዋን ታስጎበኘው ጀመረች። "ቤትሽ ደ'ሞ በጣም ያምራል" ይላታል። "ስለ ቤት እቃዎቿ ታብራራለት ጀመር" [ገጽ349]። ሶፋው ንፁህ ቆዳ ሆኖ ትክክለኛ ዋጋው 1500 ዶላር ነው፤ የገዛችው ግን በ700 ዶላር ነው። የወለሉ እንጨት ከብራዚል፤ ሹካና ማንካያዎቹ የማይዝጉ ሆነው ከህንድ፤ ሳህኖቹ ከፖርቱጋል [ኋይት ሃውስ ካሉት ጋር ይመሳሰላሉ]፤ የመኝታ ፍራሹ በዓለም ምርጥ ከተባሉት ሁለተኛ ነው፤ ብርድ ልብሱ ከግብፅ ጥጥ የተሠራ ነው። ከዚያ ወደ ወጥ ቤት አመሩ። መሳቢያዎቹን ከፋፍታ ቅመማ ቅመሙን "አንድ ባንድ" አሳየችው። ለእንግዳ "ቤት ያፈራውን" ማቅረብ የተለመደ ቢሆንም፣ "ምን አይነት ምግብ ልስራልህ?" ብላ ጠየቀችኝ [ገጽ351]። "ፍቅር በለጠ" ጴንጤ መሆኗ ከተለምዶ ውጭ የማድረግን ጸጋ አጎናጽፏት ይሆን? ወይስ፣ ተስፋዬ ሴቶች ገና ሲያዩኝ የሚማረኩልኝ ዓይነት ነኝ ለማለት ፈልጎ ነው?

"ሽሮው በመሰራት ላይ ሳለ [ ] ስለ ቁሳቁሶቹና ስለ ቅመማ ቅመሞቹ የምትነግረኝ ሊያልቅ ስላልቻለ የወሬ ማርሽ ቀየርኩ፣ ጠጉርሽ በጣም ያምራል ... ዊግ ነው የሚመስለው ... ማረጋገጥ ከፈለግህ ንካው አለች" [ገጽ 351-2]። ደራሲውና "ፍቅር" ትውውቃቸው ቤተክርስቲያን እንዲሄድ ደጋግማ ከጠየቀችው ውጭ መጠነኛ እንደ ሆነ ነግሮናል። ጎረቤቱ ሆና ከአገር መውጣቷን እንኳ አላወቀም። ስሟ ፖስታው ላይ ተጽፎ እያየ ያቺ ጎረቤቴ ትሆናለች ብሎ አልጠረጠረም። ሰላምታ ተለዋውጦ አንድ መኝታ፣ አንድ ሳሎን፣ አንድ ወጥቤት የዲሲ አፓርታማ ለመጎብኘት 30 ደቂቃ ፈጀ ቢባል፤ በደረሰ በ30 ደቂቃ ውስጥ ከኋላዋ ቆሞ ጠጉሯን እየነካካ ጊዜዋን እንዴት እንደምታሳልፍ፣ ስለም/ማታነበው መጽሐፍ፣ ስለምትከታተለው ሚድያ፣ ስለ ራሱ የእምነት ጉዞ፣ "የተወላገደ ሸሚዙን እያቃናች" [ገጽ 352] ስለ ሰጠችው ምክር፣ ጌታ ስላሳያት ተአምር፣ ጌታ እንዴት እንደተናገራት፣ ወዘተ አወራን ይለናል። የ "ፍቅር በለጠ" ሁለት ልጆቿ አብረዋት ይኑሩ አልተገለጸም። ከአገሩ ህግ አንጻር መኝታ ቤቱ አንድ ብቻ መሆኑ አብረው አይኖሩም የሚለውን ግምት ይደግፋል። ከመስተንግዶው ባል እንዳላት አይመስልም።

ወጡ እስከሚሠራ ለጠየቃት ሦስት ተከታታይ ጥያቄዎች እስቲ ምላሾቿን እናጢን። ጥያቄዎቹ፣ "ትርፍ ጊዜሽን በምን ታሳልፊያለሽ?" "ታነቢያለሽ?" እና "ሜዲያ ትከታተያለሽ?" የሚሉ ናቸው። ለሦስቱም ጥያቄዎች የ"ፍቅር" መልስ ሃይማኖት፣ ዕድሜ፣ ጾታና ጎሳ ሳይለይ የሚታየውን አገራዊ ሁኔታ አጉልቶ አውጥቶታል። ጴንጤዎች ሊለዩ ይገባልና፣ ዓለማዊነትና ቁሳቁስ ማግበስበስ ኑሮአቸውንና ንግግራቸውን መያዙ የሚያምም እውነት፣ ትክክለኛ ትዝብት ነው። "ፍቅር" ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ አታነብብም። በአብዛኛው ከብልጽግናና ከዓለማዊ አስተሳሰብ ያልራቀ ትምህርት ከሚያስተጋቡ ከክርስቲያን ቻነሎች ውጭ አታይም። ከመጽሐፍ ቅዱስ ሌላ "ፉርሽካ" ማንበብ ለርሷ መቀላቀል ነው። ፖለቲካ ዋጋ የለውም። ብዙ ማንበብ "እምነትን ገድሎ ለሰይጣን ይሰጣል።" የማታውቀው ሰው ገንዘብ እንደሚያወርሳት ጌታ በግልጽ ነግሮአት በጸሎት እየጠበቀች ነው።

"ጌታ በግልጽ ነገረኝ" ስላለችው፣ "ይቅርታ አድርጊልኝና ቃል በቃል ምን አለሽ?" ይላታል። "በቀጥታ ነው ጌታ የሚነግረኝ። የህልም ተሰጥኦም አለኝ። የውርሱን የነገረኝ ግን በጸሎት ጊዜ ነው። ውርስ እንደማገኝ የሚገልጽ መልእክት ወደ ልቤ መጣ። 'ገንዘቡ እጅሽ ሲገባ የምነግርሽ ቦታ ሄደሽ የወደቁ ልጆችን ታነሺያለሽ' ብሎ ነገረኝ" ትለዋለች [ገጽ 353-4]። "ፍቅር" ለማን መቼና እንዴት ምን ማለት እንዳለባት የማታስተውል፣ አእምሮዋን የጣለች ሆና እናገኛታለን። ደራሲው "የተቸገሩ ልጆች አምላክ በሌላ መንገድ ሊረዳቸው አይችልም ነበር?" ይላታል። ስትመልስ፣ እግዚአብሔር "ዮሴፍ በባርነት እንዲሸጥ ያደረገው፣ ሊያነሳው ስለ ፈለገ ነው" ትላለች [ገጽ354]። አፏ ውስጥ ይጨምር እርሷው ትበለው ዮሴፍን የግብጽ ጠቅላይ ሚንስትር ሊያደርገው በባርነት እንዲሸጥ ፈቀደ ማለት የታሪኩን ይዘት ማዛባት ነው። ያዕቆብ ከልጆቹ ሁሉ ዮሴፍን ያስበልጥ ነበርና፤ ወንድሞቹ በዮሴፍ ይቀኑበት ነበር። ዮሴፍ ህልም አለመ። በህልሙም እናትና አባቱ ወንድሞቹም ሳይቀሩ ለርሱ ሲሰግዱ ተመለከተ። ባለማስተዋል ይህንን ህልም ለሁሉም ማውራት ጀመረ። አጋጣሚ ሲያገኙ ወንድሞቹ ሊገድሉት ጉድጓድ ውስጥ ጣሉት፣ ኋላ ግን ከምንገድለው ትንሽ ገንዘብ እናትርፍበት ብለው ለተላላፊ እስማኤላውያን ነጋዴዎች ሸጡት [ዘፍጥረት 37]። በሌላ አነጋገር፣ በዮሴፍ ላይ በደረሰው መከራ ውስጥ የወላጆቹ ልጆቻቸውን ማበላለጥ፣ የወንድሞቹ ቅናትና የዮሴፍ አለማስተዋል አስተዋጽኦ አድርጓል ማለት ነው። ሰው ለክፉ ያደረገበትን እግዚአብሔር ለበጎ እንደ ለወጠው፤ እግዚአብሔር በህልም ያሳየውን ዕውን እንዳደረገ ዮሴፍ ያስተዋለው ኋላ ቆይቶ ነው። ዮሴፍን ሊያነሳው ስለ ፈለገ ለባርነት ዳረገው ማለት ታሪኩን ማዛባት ነው ያልነው ለዚህ ነው።

 

* * * *

ምግቡ ደርሶ በሉ። የበሉት ግን በሸክላ ሳህኖቹ ሳይሆን ለቤተኛ በሚቀርብ ተበልቶበት በሚጣል ፕላስቲክ ሳህን ነው። "ፍቅር" ሳህኖቿን ትወዳለች፤ "በትንሹም በትልቁም" ልታወጣቸው አትፈልግም። አፍ አውጥታ ፖስታ ላመጣላት እንግዳ "ደግሞ ማጠቡም ያሰለቻል ... የእቃ ማጠቢያው ኬሚካል በጊዜ ብዛት ጣቶቼን እንዳያበላሽ ብዬ ነው [ገጽ 355]" ትለዋለች።

የተቀረው ክፍል [ገጽ 355-7] ከ "ህሊና እንደ አምላክ" [ም.34] ጋር የተያያዘ ስለሆነ ኋላ እንመለስበታለን። በቅድሚያ ግን "ፍቅር"ን ክርስትናን ለማሳያ እንደ መስተዋት ሲጠቀምባት፣ ያው የያዘው መስተዋት እራሱን እንዴት ገለጠው የሚለውን እንመልከት። ደራሲው "በእምነት ጉዳይ አክራሪ አይደለሁም" ይለናል [ገጽ 348]። ካቶሊክ፣ ፕሮቴስታንት ፣ ጀሆቫ እና ኦርቶዶክስ መሆን ለርሱ "አክራሪ" መሆን ነው። እነዚህ ሃይማኖቶች በርሱ ዘንድ "ተመሳሳይ" ናቸው። በምን በምን ይመሳሰላሉ? በምንስ ይለያያሉ? አይነግረንም። መንግሥትም "ሃይማኖት አይለያየንም" በሚል ሽፋን ዓላማውን ሊያራምድ የሞከረባቸው ወቅቶች ነበሩ። የሚገርመው ግን የተጠቀሱት የእምነት ክፍሎች በደራሲውና በመንግሥት ዐይን ራሳቸውን የማይመለከቱ መሆናቸው ነው። "በማንኛውም የእምነት ቦታ ገብቼ ጸሎት ለማድረስ የሚያስችል ችሎታና ሚዛናዊ ስሜት ነበረኝ" ይለናል [ገጽ 348-9]። ካቶሊኩም ጋ እንደ ካቶሊክ፣ ጀሆቫውም ጋ እንደ ጀሆቫ መሆን እችላለሁ እያለን ነው? "አክራሪ" አይደለሁም፤ "ችሎታና ሚዛናዊ ስሜት" ነበረኝ ሲል ከየሃይማኖቱ ድንጋጌ ውጭ የማድረግ "ችሎታ" አለኝ ማለቱ ነው? የራሱ "ችሎታና ሚዛናዊ ስሜት" በየሃይማኖቱ ላይ ተጽዕኖ የሚያደርግ ከሆነስ ከሚተቸው "አክራሪነት" በምን ይለያል? "ሚዛናዊነቱ" የየሃይማኖቶች አስተምህሮ ለኔ መስማማታቸው ላይ ነው እያለን ነው። "በራሴ መንገድ" ሲለን "ክራይላሶ" ሦስት ጊዜ አልልም፣ ሁለቴ ይበቃል ሊል ነው። የሃይማኖትን ድንጋጌ ወደ ጎን አድርጎ የራሱን ማቆም ይሻል [ገጽ 359]። "አንተ ሙሉ ሰው ነህ። የነገሩህን ብቻ አትቀበል። የልብህን ድምጽ አዳምጥ። ከውስጥህ የምትሰማው እሱ እውነት ነው ..." [ገጽ 365]። አንድን ማኅበረሰብ የሚያያዘው እያንዳንዱ ዜጋ በነፍስ ወከፍ የመሰለውን ሲያደርግ አይደለም። የጸኑ፣ ሁሉም በጋራ ሊቀበላቸው የተገባ መመሪያዎች አሉና። የግል አመለካከትም እንዳለ ሁሉ፣ ሃይማኖት የሚጋራው ከሌለ የቆመለትን ሥርዓት እንደሚገባ መፈጸም ያዳግተዋል።

ደራሲው "ከአንድ ጊዜ በላይ" ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን "ፍቅር" ጋብዛው ሄዷል። ሰላም በሕይወቱ የለም፣ "እኔ ያጣሁትን መንፈሳዊ ሰላም ይህች ሴት ብቻዋን ጠቅልላ እንደ ያዘችው አልተጠራጠርኩም" [ገጽ 349]። መጽሐፍ ቅዱስ "ድሮ" [በልጅነቱ] አንብቦአል፤ አንዳንዱን ክፍል ደግሞታል። "ጎረምሳ ሳለ ይጸልይ" ነበር [ገጽ 355]። ዛሬ የማመን ኃይሉ ደክሟል፤ ወደ ነበረበት መመለስ አቅቶታል [ገጽ 352]። ከመድከሙ አስቀድሞ የነበረበትን ሁኔታ ግን አላስረዳም። ይልቅ ወደ ኋላ የተመለሰበትን አንድ ምክንያት "ሰዎች አምላክ ነገረኝ" የሚሉት ከህሊናቸው ጋር የሚያደርጉትን ንግግር እንደ ሆነ ስለ ደረስኩበት ነው" ይለናል [ገጽ355]። ጥልቅ የሆኑ የሕይወት ጥያቄዎች ያሉት ሰው ነው። የሕይወት ነገር የተወሳሰበበት ሰው ነው። በምዕራፉ መግቢያ ላይ ለምሳሌ፣ የማረፊያ በቀለን ግጥም ቆንጽሎ አመልክቷል፦ "ይበቃኛል በርግጥ - ግማሽህን ማየት / ግማሽ በመሆኑ - ሰው የመሆን እውነት።" ነገሮች የተከደነና የተገለጠ ክፍል አላቸው። የተከደነውን ክፍል በጥያቄ ብዛት ለመረዳት ይጥራል። መጠየቅ ግን ግማሽ ቁምነገር ነው፤ ሌላኛው ቁምነገር መረጃ ያለው መልስ ሲገኝ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን ነው።

"ጣፋጭ ቦዘና ሽሮ" በመመገብ ላይ እያሉ ድንገት ሳታስበው "ጎጃሜ ነሽ እንዴ?" ይላታል። የጠየቀበት ምክንያቱ "ስምሽ ትርጉም አለው ብዬ ነው" [ገጽ 354]። ቀድሞውኑ ስም ያወጣላት እራሱ ደራሲው እንደ ሆነ አንርሳ፤ ይኸው አጠራርና ጎጃሜነት አማረ ተግባሩ በጻፈው መጽሐፍ ላይ እንዲህ ተጠቅሷል፤ "አይ ደብሬ! መወለድ እኮ ቋንቋ ነው። እኛስ ቢሆን ጎጃምን ጥለነው አይደል የወጣን! ይልቅስ ፍቅር ይበልጣል ልጄ!" ["ያንዲት ምድር ልጆች" ቅጽ 1፣ 2ኛ እትም፣ 2000 ዓ.ም፤ ገጽ 36]። "ያንዲት ምድር ልጆች" እና "የስደተኛው" ም. 32 "የአንድ አባት ልጆች" የርዕሶቹና ባህርያቱ መመሳሰል ባጋጣሚ ነው?

"ማስታወሻዎቹ እውነተኛ ታሪኮች፣ በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረቱ ትረካዎች ናቸውና ...ሊገመት በሚችለው ምክንያት የምስጋና ስሞችን ከመዘርዘር ተቆጥቤያለሁ።" [ገጽ 5-6]። ከ"ፍቅር በለጠ" ይልቅ የጎጃሜነት ጥያቄ ለደራሲው ቁምነገር እንደ ሆነ እንመለከታለን። ሌላኛው፣ በርሷ የምናየውን ቅንነት በርሱ አለማየታችን ነው፤ "ወሬ ለመቀየር" ለሚጠይቃት ጥያቄ "የተደበላለቀ አሰልቺ" ምላሽ እንደ ሰጠችው ደጋግሞ ይነግረናል [ገጽ 351፣ 353፣ 354]። አብሯት ሆኖ አብሯት የለም።

"ጌታ ነገረኝ" የሚለው አባባል ደራሲውን ጥያቄ ያጭርበታል። "ለኔ ለምንድነው አምላክ የሆነ ነገር የማይነግረኝ? እያልኩ እጨነቅ ነበር" [ገጽ 355]። ለዚህ ላስጨነቀው ጥያቄ ከመጽሐፍ ቅዱስና "ጀርመን አገር ከሚገኙ የጴንጤ ፓስተሮች" መልስ ይሻል። "በመጨረሻ የደረስኩበት መደምደሚያ የአምላክ ድምጽ የሚባለው፣ 'ህሊና' መሆኑን ነበር" [ገጽ 355]። ስለ መደምደሚያው እርግጠኛ አይመስልም [ገጽ 357]። እስቲ ደረስኩበት ስለሚለው የጠቀሳቸውን ሁለት ምንጮች እንመርምር። "መንፈሳችን ከመንፈሱ ጋር አንድ ላይ ሆነ የሚለው የቅዱስ መጽሐፍ አባባል ይህንኑ ያጠናክራል" [ገጽ 355]። እንዲህ የሚል ጥቅስ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጻፈም። ምናልባት የሚቀራረብ ጥቅስ "የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል" የሚለው ነው [ሮሜ 8:16]። ደራሲው ለጥያቄው መልስ ለመሻት ወደ ትክክለኛው ምንጭ ቢሄድም መልሱ ካሰበው ጋር ስላልገጠመ ለማሻሻል የተገደደ ይመስላል፤ ወይም ለማጣራት ሰንፎ ነው እንበል። ይህንን በማድረጉ የአገራችን የተማረው ክፍል ስለ ሃይማኖት ያለውን አስተሳሰብ ከሞላ ጎደል አንጸባርቋል። "የተማረው" ክፍል ሃይማኖት ጋ ሲደርስ ወይ ፈጽሞ ይርቃል፣ ላሰበው ተግባር ሊያውለው ይሻል፤ ሃይማኖት ለብቻው መያዝ ያለበት ነው ይላል። ወይም ጨርሶ ይንቃል፣ ያንቋሽሻል ወይም ያለ ጥያቄ ይቀበላል። የሚገርመው ይህ አመለካከት በወንጌል አማንያንም ዘንድ በብዛት መታየቱ ነው። ምክንያቱ ዞሮ ዞሮ የትምህርትና የሃይማኖት ተቋማት ቁንጽልና ወጥ እንጂ ሁለገብና ተፎካካሪ አመለካከት እንዲዳብር የማያበረታታ መርሆ ማራመዳቸው ነው። ሁለተኛውስ ምንጭ? "ክርስቲያኖች 'ጌታ ነገረኝ' የሚሉት እውነት እንዳልሆነ እናውቃለን" ይላል በጀርመን አገር የሚገኘው [ስሙን ያልጠቀሰው፣ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ] የጴንጤዎች ፓስተር [ገጽ 355]። ፓስተሩ ይህን ይበል ወይም ደራሲው አፉ ላይ ያርግለት እርግጠኛ መሆን አይቻልም። ቀጥሎ፣ "ስህተት መሆኑን መግለጽ ግን አንችልም። ምክንያቱም ሰፊ ቁጥር ያላቸው አማኞቻችን በዚህ መንገድ ቀጥለዋል። ስህተቱን ማስተካከል ወይም ለማረም መሞከር መጠራጠርን ስለሚያስከትል ዝም ማለቱን መርጠናል ..." [ገጽ 355-6]። ፓስተሩ እራሱ ያልገባው፣ የተጠራለትን እውነት ከማስተማር ይልቅ ለምቾቱ የተገዛ ተመሳስሎ መኖርን የመረጠ ዘመኑ ካፈላቸው መሃል መሆኑን ላፍታ አይጠረጥርም። ሊሰማ የሚሻውን መልስ ስለ ሰጠው ብቻ ሙሉ ለሙሉ አምኖ ይቀበላል። እውነቱን እያወቀ የሚያታልል ሰውን ምስክርነት ይዞ አደባባይ መውጣቱ ከፓስተሩ ይልቅ ደራሲውን ትዝብት ላይ ይጥለዋል። ከመጽሐፍ ቅዱስና ከሌሎች ለንደን፣ አዲስ አበባ፣ ኬንያ፣ አዋሳ፣ አድዋ፣ አስመራ ከሚገኙ ጴንጤዎች ወይም ከጀርመናውያን ከግብጻውያን ከእንግሊዛውያን ከሆላንዳውያን ጴንጤዎች ጠይቆ ለማመሳከር ያደረገውን ጥረት አናይም። ከዚህ ድምዳሜ በመነሳት ህሊና ሰውን በጎን ከክፉ እንዲዳኝ ለሰው የተሰጠው ሳይሆን አምላክ ነው ይለናል። ትንሽ ቢጥር ኖሮ ስለ ህሊና ትክክሉን በተረዳ። ስለ በደል "የህሊና ጸጸት" አለ [1ኛ ሳሙኤል 25፡31]፤ "የህሊና ወቀሳ" አለ [ዮሐንስ 8፡9]፤ በጎ በማድረግ "መልካም ህሊና" አለ [የሐዋርያት ሥራ 23:1]፤ የ "ህሊና" ምስክር፣ ክስ፣ ማመካኘት አለ [ሮሜ 2:15]፤ ደካማ፣ በጎ የረከሰ "ህሊና" አለ [1ኛ ቆሮንቶስ 8፣ ቲቶ 1:15፣ ]። ህሊና ይቆሽሻል፣ ይሞታል፤ ይነጻል፣ ሕያው ይሆናል፤ ሰው ልክ ነው ብሎ የያዘው ልክ አለመሆኑን መረዳት ይጀምራል። "ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ህሊናችሁን ያነጻ ይሆን? [ዕብራውያን 9፡14]። ህሊና አምላክ ለሰው የሰጠው እንጂ እራሱ አምላክ እንዳልሆነ በተገነዘበ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ "በክርስቶስ ሆኜ እውነትን እናገራለሁ፤ አልዋሽምም፤ ሕሊናዬም በመንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልኛል" [ሮሜ 9፦1-2] ሲለን። ከሥላሴዎች አንዱ መንፈስ ቅዱስና የጳውሎስ ሕሊና የተለያዩ እንጂ አንድ እንዳልሆኑ ግልጽ ነው። የጥሬ ቃሉን ፍቺ መመልከትም አንድ መፍትሔ ይሰጥ ነበር። አንድ ደራሲ የሚጠቀማቸውን ቃላት ትክክለኛ ትርጉም፣ በአንባቢው አእምሮ የሚያቀርቡትን አሳብ ቀድሞ መገንዘብ ይኖርበታል። ህሊና፦ ክፉና ደግን የሚያስለይ አእምሮ ወይም ልቡና። በሰሩት ጥፋት ወይም ስሕተተ የሚመጣ ጸጸት፣ የህሊና ወቀሳ ይባላል። ድምጽ ሳያሰሙ የሚደረግ ጸሎት፣ የህሊና ጸሎት ይባላል። የማያመዛዝን፣ የማያገናዝብ፣ ይሉኝታ የሌለው ህሊና ቢስ ይባላል [መዝገበ ቃላት 1993፤ የበዓሉ ግርማን "የህሊና ደወል" ይመልከቱ]።

የህሊናን መሠረተ ትርጉም ስቷልና፣ ለማስረጃነት "ጅብ ህሊና የለውም፣ ህሊናውን የገደለ ሰው ከጅብ ይመሳሰላል" ይለናል [ገጽ 357]። "እግዚአብሔር" "አላህ" "ዋቄፈታ" "ይሆዋ" የፈጣሪ ስሞች ቢሆኑም "ዞሮ ዞሮ መቀመጫ ቦታው ህሊናችን ውስጥ ነው። ወይም አምላክ ራሱ ህሊና ነው" [ገጽ 357]። እንግዲህ ከሳቱ አይቀር መሳት እንዲህ ነው። ከዚህ ከ "ህሊናዊው አምላክ" ጋር በሰፊው እንደሚያወጋ ይነግረናል። ሆኖም ይህ "የሚያነጋግረኝ መንፈስ የኢየሱስ ነው ለማለት ማረጋገጫ የለኝም" ይለናል። "ፍቅር በለጠ"ንና ዕቃዎቿን በማሰብ ይመስላል፣ እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሰበትን እንዲህ ሲል ገልጾታል፣ "አንዳንድ የማውቃቸው ጴንጤዎች ኢየሱስን ከአምላክነት ወደ ሎሌነት ዝቅ እንዳደረጉት ታዝቤ ነበር። 'ኢየሱስ አገልጋይ ነው' የሚለውን አባባል በትክክል ባለመገንዘብ ተላላኪያቸው አድርገውታል። ስለ ቁሳቁሶች ዋጋ ለአማኞቹ ለመንገር የሚሯሯጥ አምላክ በርግጥም የንግድ ወኪል እንጂ አምላክ ሊባል አይችልም። ስለሆነም እኔ በምናብ የምስለው አምላክ ከዚህ ዓይነቱ አምላክ ፍጹም የተለየ ነበር" [ገጽ 357]። ይህን የሚያነብቡ አማንያን፣ በተለይ የቤተክርስቲያን መሪዎች በአጽንኦት እነዚህን የጽድቅ ክሶች መመርመርና መመዘን ይኖርባቸዋል። በአንጻሩ፣ ደራሲው ልኩን አውቆ ላለመቀበል በጥቂቶች ውስጥ ባየው ድክመት እያሳበበና እያመካኘስ ቢሆን! "እነርሱም ሕሊናቸው ሲመሰክርላቸው፥ አሳባቸውም እርስ በርሳቸው ሲካሰስ ወይም ሲያመካኝ በልባቸው የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉ [ሮሜ 2:15]።"

ህሊናና አምላክ አንድ ናቸው ብሎናልና፣ ወደ ኋላ ተመልሶ "ወደ ሃይማኖት ያዘነበለ" ታናሽ ወንድሙ አባቱን የጠየቀውን ጥያቄ ያነሳልናል። አባቱ የመለሱለት አጥጋቢ አለመሆኑን ብቻ ሳይሆን የማይመስል እንደ ሆነ ሊጠቁመን ሞክሯል [ገጽ359]። ቢሆንም ደራሲው በገባው መጠን የጸሎትን አስፈላጊነትና የፈጣሪን መንገድ ይበልጥ ለማወቅ የሚሻ ይመስላል። ከዚህ ክፍል ልብ የሚነካና የደራሲውን ስብእና እርቃን ያወጣ ነገር ቢኖር የሚከተለው ነው፣ "ሆላንድ ከገባሁ በኋላ ግን በተለይ በበጋው ወራት የሳምንቱ ማብቂያ ላይ በራሴ መንገድ ጸሎት ማድረስ ጀመርኩ። በምዕራብ ዞይስ መውጫ ከወንዙ ዳርቻ አንዲት ሰው ሰራሽ ኮረብታ አለች። አልፎ አልፎ ወደ ኮረብታዋ ሄጄ ጫፉ ላይ ቁጭ በማለት ጸሎት አደርሳለሁ" [ገጽ 359]። ከላይ ህሊናና አምላክ አንድ ናቸው ሲለን የነበረውን ዘንግቶት ይመስላል፣ "የፈጠረኝ አንድ እውቀት ያለው ሃያል አምላክ መኖሩን አምናለሁ" ይለናል [ገጽ 359]። ህሊናዬ ፈጠረኝ ማለቱ ይመስላል።

ስለ "ፈጣሪ" በተለይ ተጽእኖ አደረጉብኝ ከሚላቸው መጻሕፍት ተነስቶ ጥቂት ሊያስረዳን ሞክሯል። ሆኖም ብዙ ሳይቆይ "ፈጣሪ" ነው ያለን በራሱ አምሳል የተፈጠረ፣ የአሳቡና የምኞቱ ውጤት እንደ ሆነ እንመለከታለን። የጸሎቱ ቀጥተኛነትና ግልጽነት ጸሎትን ለሚያወሳስቡ ወይም እግዚአብሔር ካልጮኹ አይሰማም ብለው ለሚያስቡ ጥሩ እርምት ይሆናል።
"ጌታ ሆይ፣ ይኸው መጣሁ? ብዬ ጸሎቴን ጀመርኩ።
አምላክ ምናባዊ መልስ ሰጠኝ፣ "ሰውዬው! እንዴት ሰነበትክ?"
"መሰንበቻዬን መች ጠፍቶህ? ያው በር ዘግቶ መጻፍ ነው፤ ማንበብ ነው፣ ሲደብረኝ ወጣ እላለሁ፣ እንዲሁ ቀኑ ያልፋል።" ["ፍቅር በለጠ"ን "ትርፍ ጊዜሽን በምን ታሳልፊያለሽ?" ሲላት "እንዴት እንደሚያልፍ እንኳ አላውቀውም። ሰኞ ብሎ አርብ ነው። በጋ እያልክ በረዶ ይመጣል" ብላው ነበር [ገጽ 352]። ሁለቱም የስደት ኑሮን መራራ ገጽታ፣ ብቸኝነትን አንጀት በሚበላ ቃል ይገልጹታል።
"ፈተና መውደቅ እያበዛህ ነው፣ ምን ይሻልሃል?"
"ማን ፈተናህን ያልፋል? እንኳን ያንተን የሰዎችን ፈተናም ማለፍ ከብዶኛል።"
"ምን ልርዳህ ታዲያ ለዛሬ?"
"አይ እንድናወጋ ብዬ ነው የመጣሁት። ጊዜ ካለህ ስላንተ አንድ ነገር ላጫውትህ።"

wikimedia drawing

ደራሲው ምንጩን ሲጠቅስ አሻሽሎ፣ ሳያጣራና በቸልተኛነት አመቻችቶ ነው ወዳልነው ነጥብ እንመለስ።
• "መንፈሳችን ከመንፈሱ ጋር አንድ ላይ ሆነ የሚለው የቅዱስ መጽሐፍ አባባል ይህንኑ ያጠናክራል" ይለናል [ገጽ 355]፤ ጥቅሱ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጻፈም።
• ስሙን ያልጠቀሰው የጴንጤዎች ፓስተር "ጌታ ተናገረኝ" የሚለው አባባል "ስህተት መሆኑን መግለጽ ግን አንችልም..." [ገጽ 355-6] የሚለው በዶስቶየቪስኪ "ብራዘርስ ካራማዞፍ" ላይ ሚትያና አልዮሻ ስለ ራኪቲን ካወጉት ጋር ቃል በቃል ይመሳሰላል።
• ለአምላክ፣ ያሳቀኝን ነገር ልንገርህ፣ የጥንት እንግሊዞች ወደ ዘመቻ ሲሄዱ "አምላክ ሆይ! - በርግጥ አምላክ ከሆንክ / ነፍሴን ተቀበላት! -በርግጥም ነፍስ ካለኝ" ይላሉ ይለዋል [ገጽ 360]። ጸሎቱና "ፈጣሪም በጣም ሳቀ" የሚለው ቃል በቃል ዊልያም ኪንግ በ 1819 [በአውሮጳ] "ፖሊቲካል ኤንድ ሊተረሪ አኔክዶትስ ኦፍ ሂስ ኦውን ታይምስ ብሎ ገጽ 7 – 9 ላይ ካሰፈረው ጋር ይመሳሰላል። እራት ግብዣ ላይ፣ በውጊያ ሰዓት በጣም አጭሩ ጸሎት የቱ ነው ሲባባሉ፣ ፌዙን ተናገረ የሚባለው ሰር ዊልያም ዊንደም ነው። ከፌዙ በኋላ "ሁሉም ሳቁ" ይላል። በሥፍራው የነበረ ጳጳስ አተንበሪ በግሳጼ መልክ፣ አጭሩ ጸሎት "አምላክ ሆይ! በውጊያ ሰዓት እኔ ብረሳህ አንተ ግን አትርሳኝ" ነው ብሎ እርምት መስጠቱን ደራሲ ተስፋዬ አይነግረንም።
• ጸሎቱን ሲቀጥል፣ "ጠይቁ! ብለሃል። ምን እንድንጠይቅህ ትጠብቃለህ?" አምላክ ሲመልስ፣ "ጠይቁ ማለቴ ዳቦ አይደለም። አዳምና ሄዋን ከገነት ሲባረሩ ዳቦ በነጻ የማግኘቱ ነገር አብቅቶለታል" ይለናል [ገጽ 362]። ደራሲው አሁንም በግምት እንጂ አጣርቶ አይደለም፦ "የዕለት እንጀራችንን ስጠን ለዛሬ" የሚለው አትሥሩ ሳይሆን፤ ከመጨነቅ ይልቅ ታመኑ፤ አእዋፍን የሚመግበው የሰማይ አባታችሁ ስለ እናንተ ያስባል ማለቱ ነው። አዳምና ሄዋንን በገነት ሲያኖራቸው እንዲሠሩ እንጂ በነጻ ዳቦ እንዲበሉ አይደለም፤ ሥራን የፈጠረው እግዚአብሔር ነው፤ "እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ወስዶ ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በዔድን ገነት አኖረው [ዘፍጥረት 2:15]" ይላልና።
• እንግሊዛዊው ሶመርሴት ሞም አምላክ "ኮመን ሴንስ የለውም" ብሏል? [ገጽ 362] አላለም። ያለው "በእግዚአብሔር ማመን የኮመን ሴንስ ጉዳይ አይደለም" ነው። ሶመርሴት ይህን ያለው እምነትን ለማንቋሸሽ ነው፤ እምነት የስሜት ጉዳይ እንጂ የማስተዋል ጉዳይ አይደለም ለማለት ነው።
• እግዚአብሔርን በምናቡ፣ ስለ መኖርህ "የማያሻማ ምልክት ሰጥተህ ለምን አትገላግለንም?" [ገጽ362] ይለዋል። ለምልክትማ ኢየሱስን ልኮ ብዙዎች አላመኑበትም። በዐይናቸው ፊት ሙታንን አስነሳ፤ ዕውራንን አበራ፤ በአጋንንት የታሠሩትን ነጻ አወጣ፣ ወዘተ። "ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር። በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም። የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ...መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው [ዮሐንስ ወንጌል 1፡1-18]።" ደራሲው የጠየቀው ጥያቄ ያረጀ ነው። ከኢየሱስ ደቀመዛሙርት ፊሊጶስ "ጌታ ሆይ፣ አብን አሳየንና ይበቃናል አለው። ኢየሱስም አለው፦ አንተ ፊሊጶስ፣ ይህን ያህል ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፣ እንዴትስ አብን አሳየን ትላለህ?" አለው [ዮሐንስ 14፡6-9]። መረጃ ቀርቦለት ላለማመን የወሰነን መርዳት አይቻልም። የቀረበውን መረጃ መቀበል የአስተሳሰብንና የሕይወትን አቅጣጫ ስለሚያስቀይር አንዳንዶች ፈቃደኛ አይሆኑም። የሕይወትን ትርጉም ለማወቅ የሚሻውን ያህል፤ ደራሲው ሌሎች ብዙ ብዙ ጥያቄዎችን ሲጠይቅ አንዱን ብቻ ሳይጠይቅ እንደ ቀረ እንመለከታለን። ያም ጥያቄ "ኢየሱስ ማነው?" የሚለው ነው። ኢየሱስ ስለ ራሱ ምን ብሏል? አብረውት የኖሩ፣ ያዩትና የሰሙትስ? ቅድም እንዳልነው ጥያቄ መጠየቅ ብቻውን አይበቃም፤ የቀረቡ መረጃዎችን በጥንቃቄ መመርመርን ይጠይቃል። ከሌሎች የሕይወት ልምድ ምስክርነት መሻትን ይጠይቃል። ከዚህ ባላነሰ ደግሞ እውነቱን ለማወቅ ጥማቱና ፈቃደኛነት ሊታከልበት ይገባል።
• [ረቂቅ] "እውቀት የፈጠረ አንድ ሌላ አዋቂ የግድ መኖር አለበት ... በርግጥም አንድ ኃያል መሃንዲስ አለ [ገጽ 363]።" ይህ "አንድ ኃይል" ከርሱ በስተውጭ ነው። ይህን አምላክ ከራሱ ህሊና ለይቶ ማየት አልቻለም። በምናቡ እንዳስረዳን ራሱን እንደ አምላክ በመቁጠር ነው። ይህ ዓይነቱ አምላክ ፈጣሪ ሳይሆን ፍጡር ነው። የሰው እጅ ሥራ ወይም ጣኦት ነው።
• ዶስቶየቭስኪስ "አምላክን እኛ ፈጠርነው እንጂ እሱ አልፈጠረንም" ብሏል? [ገጽ 364]። ቅድም በጠቀስነው "ብራዘርስ ካራማዞፍ" ላይ [ክፍል 4፣ ንኡስ ክፍል 11፣ ምዕራፍ 4] የተጠቀሰው ግን "እግዚአብሔር ከሌለ ሰውን የሚያግደው ምንም የለም" የሚል ነው። ተናጋሪው ከሃዲው ኢቫን ሲሆን፣ ሰው ማለቂያ ከሌለው ጥፋት እንዲጠበቅ የእግዚአብሔር መኖር አስፈላጊ ነው ማለቱ ነው።
• "አካሌም በፊትህ እንደ ኢምንት ነው። ሕያው የሆነ ሰው ሁሉ በእውነት ከንቱ ብቻ ነው" የሚለውን ጥቅስ ወስዶ ይመስላል እግዚአብሔርን "ቁጫጭ" አልከኝ ይላል። "ጭቃ ሠሪውን፦ ምን ትሠራለህ? ወይስ ሥራህ። እጅ የለውም ይላልን? ... ወደ ሸክላ ሠሪው ቤትም ወረድሁ፥ እነሆም፥ ሥራውን በመንኰራኵር ላይ ይሠራ ነበር። ከጭቃም ይሠራው የነበረ ዕቃ በሸክላ ሠሪው እጅ ተበላሸ፥ ሸክላ ሠሪውም እንደ ወደደ መልሶ ሌላ ዕቃ አድርጎ ሠራው። የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ይህ ሸክላ ሠሪ እንደሚሠራ በውኑ እኔ በእናንተ ዘንድ መሥራት አይቻለኝምን? እነሆ፥ ጭቃው በሸክላ ሠሪ እጅ እንዳለ፥ እንዲሁ እናንተ በእኔ እጅ አላችሁ [ኢሳይያስ 45:9፤ ኤርምያስ 18:3-6]።" ያዛባው ትርጉም ሳያንስ፣ ጨምሮ "ቁጫጭና ጀበና" አልከኝ ወደ ማለት ይዛመታል። ቀጥሎ፣ "እኛ ላንተ ማጣፈጫ ቃሪያና ቲማቲም ነን?" ብሎ የተነሳበትን ቁምነገር ወደ ተራ ሹፈት ያወርደዋል። በዚህም እግዚአብሔር ሰውን በአምሳሉ ክቡር አድርጎ እንደ ፈጠረው፣ ሰው ባለመታዘዙ ከክብሩ እንደ ተዋረደ፣ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ወደ ክብሩ የሚመለስበት መንገድ እንደ ተከፈተ የሚያስተምረውን ዋነኛ ትምህርት ዘንግቶትና ስቶት እናያለን።
• ፈላስፋው ኒቸስ "እግዚአብሔርን ወደ ምድር ያመጣው ፍርሃት ነው" ብሏል? [ገጽ 365]። ኒቸ ያለው ክርስትናን መጣል ክርስቲያናዊ ስነ ምግባርን መጣል ነው፤ ያም ወደ አለመተማመን፣ ወደ ጥፋት፣ ብርቱው ደካማውን ወደ መረጋገጥ ያመራል ነው። ኒቸ "እግዚአብሔር ሞቷል" ብሎ ያወጀው ነው። በአውሮጳ አቆጣጠር በ1900 ዓ.ም አብዶ ሞቷል። ሌሎች እንደ ታዘቡት የሞተው ኒቸ እንጂ፤ ሞተ ያለው እግዚአብሔርማ ዛሬም በመላው ዓለም ሕዝቦች ዘንድ ህያው ሆኖ ይታወቃል።

ሌሎች ያላሉትን ወይም ያሉትን በሚፈልገው መንገድ አሻሽሎ ማቅረቡ ደራሲው የራሱን ድምጽ ከመስማት አልፎ አሳቡን ላመነጩትና ለአንባቢዎቹ ግድ እንደሌለው ያሳያል። የዚህ ትርፉ አለመታመን ነው። እርግጥ ደራሲው ፈላስፋ ወይም የስነመለኮት ሊቅ አይደለም። ጥናትና ምርምር የሚጠይቀውን መስፈርት አላሟላም። አንድ ሰው በሁሉም መስክ ሊጠበብ ስለማይችል ስላልተረዳቸው ጉዳዮች ከተረዱት ዋነኞች አመስግኖ መዋስ ያለ ነገር ነው። ከሚያነባቸው መጻሕፍት እየቀነጫጨበ፣ እየጣጣፈ የሚፈልገውን አሳብ ብቻ ወስዶ የማይፈልገውን ወደ ጎን አድርጎ ያነጋግረናል። የእምነትን [የክርስትናን] አስተምህሮ በተመለከተ ከታመኑ ምንጮች በቅድሚያ ጠንቅቆ መረዳት ለማስረዳትና ለመሞገት ቁልፍ ነው። በ "የስደተኛው ማስታወሻ" ደራሲው ራሱን ሆኖ እንጂ በፈጠራቸው ገጸ ባህርያት በኩል እያነጋገረን እንዳልሆነ ገልጾልናል። ራሱን ያቀረበልን መንፈሳዊ እውነቶችን ለመረዳት በሚጠይቅ ሰው ተመስሎ ነው። ሐቁ ግን የምንሰማው ድምጽ የራሱ ሳይሆን የሌሎች ድምጽ ነው። በሌላ አነጋገር፣ የቀረቡልን ጥያቄዎች የጋዜጠኛ ተስፋዬ ጥያቄዎች አይመስሉም፤ በሌሎች ተመስሎ ሊያነጋግረን ለምን እንደ መረጠ ግልጽ አይደለም። ለምሳሌ፣ ከአምላክ ጋር የተነጋገረባቸው ምናቦች ከ "ሁሉ አምላክ ነው" አራማጁ አሜሪካዊ ኒል ዶናልድ ዎልሽ "ኮንቨርሴሽንስ ዊዝ ጎድ" ላይ የተወሰዱ ናቸው [ወርልድትራከር ዶት ኦርግ፣ በአውሮጳ 1995፣ ለምሳሌ ገጽ 11-13 ይመልከቱ]። ከላይ "ማስታወሻዎቹ እውነተኛ ታሪኮች፣ በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረቱ ትረካዎች ናቸው" ብሎን ነበር [ገጽ 5-6]። በ"ፍቅር በለጠ" እና "ህሊና እንደ አምላክ" የተካተቱት መረጃዎች ግን የተዋሳቸው እንደ ሆኑ አይተናል። የመጣጣፍ ችግር፣ አንድን አሳብ ሲዋስ የተዋሰበትን ጊዜና ሥፍራ አያስታውስም፤ ላዋሰው የሚገባውን ምስጋና ሳይሰጥ የራስ አድርጎ ማቅረቡ ላይ ነው።

 

* * * *

የሞትና የፍርሃትን ጥያቄ ሲያነሳ፣ ጥያቄውን ለመመለስ የሚያስፈልገውን መረጃ አይሰበስብም። እግዚአብሔርን "ለምን ታስፈራራናለህ?" ሲለው [ገጽ 362] የአዳምና የሄዋንን ፍርሃትና መደበቅ ሳያጤን ነው፤ "አዳምና ሚስቱም ከእግዚአብሔር ከአምላክ ፊት በገነት ዛፎች መካከል ተሸሸጉ። እግዚአብሔር አምላክም አዳምን ጠርቶ። ወዴት ነህ? አለው። እርሱም አለ። በገነት ድምፅህን ሰማሁ፤ ዕራቁቴንም ስለ ሆንሁ ፈራሁ፥ ተሸሸግሁም። እግዚአብሔርም አለው። ዕራቁትህን እንደ ሆንህ ማን ነገረህ? ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍ በውኑ በላህን? [ዘፍጥረት 3:8-10]።" አዳምና ሄዋን እግዚአብሔርን ስላልታዘዙ ፈሩ፤ ፍርሃት የአለመታዘዝ ኃጢአት ውጤት ነው። እግዚአብሔርን አታስፈልገኝም የማለት ውጤት ነው። እግዚአብሔር የሚያስፈራራ የሚመስለው ኃጢአት በመካከል ስለ ገባ ነው፤ በሰውና በአምላኩ መካከል ርቀትና ባዳነት ስለ ተፈጠረ ነው። ለቀረቡትማ ፍቅር እንጂ ፍርሃት የለባቸውም።

እግዚአብሔር የሚሸሸውን ፈልጎ የሚያገኝ አምላክ ነው። የሰው ልጅ [ኢየሱስ] የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአልና [ሉቃስ 19:10]። በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ እግዚአብሔር ቅርበቱን መሐሪነቱን ስለ ኃጢአት ይቅርታ አድራጊነቱን ገልጿል። የሰው ድርሻ፣ ይቅር በለኝ፣ ሰላምህን ሕይወትህን አጎናጽፈኝ ማለት ነው። የክርስትና መሠረቱ ይኸው ነው። ደራሲው ስላላጣራ የእግዚአብሔርን ባህርይ አዛብቶት እናያለን። ላለማመንና ለመንቀፍ መብቱ ቢሆንም የሌላውን አቋም ማዛባት ግን መብቱ አይሆንም፤ ያስጠይቃል፤ መታመንን ይነሳል።

ጥቂት ስለ ተስፋዬ ገብረአብና ሥራዎቹ። በመጀመሪያ፣ ይህ ግለሰብ ስለሻው ነገር የመጻፍ፣ ስለ ማንነት ጥያቄ የማንሳት መብቱ ሊከበርለት ይገባል። የራሳችን መብት እንዲከበርልን የምንሻውን ያህል የሌላውን የማክበር ግዴታ አለብን። የሻውን መጻፉ ለመማማር እንደ ጠቀመ መረሳት የለበትም። ሁለተኛ፣ ተስፋዬ በቅድሚያ የጋዜጠኛ ፖለቲከኛ ነው። የጋዜጠኛ ፖለቲከኛ ድርጊቱን ሳያዛባ ዘግቦ ዳኝነቱን ለአንባቢ እንደ መተው ዘገባውን ጨምሮበትና ቀንሶለት የራሱን አሳብ ማስፈጸም ይሻል። ከአሳቡ ጋር የማይስማማውን አይታገስም፣ ይወርፋል። የሚጽፋቸው በጥርጣሬ ለመታየታቸው፤ ከሚያስተላልፋቸው መልእክቶች ባላነሰ ደራሲው ራሱ መነጋገሪያ ለመሆኑ ይህ አንዱና ዋነኛው ምክንያት ነው። ሦስተኛ፣ አሳቡን ቀላልና ግልጽ በሆነ መንገድ የመግለጽ ችሎታ አለው። ያም ማለት በሚጽፋቸው ጽሑፎች የሚያስተላልፋቸው መልእክቶች ለሚያታግለንና ለምንጋራው ምድራዊ ኑሮ አዲስ ራእይ በመፈንጠቅ ስብእናችንን ያጸናሉ ወይም ያንጻሉ ማለት አይደለም። ይልቅ የምንገኝበትን ዘመን ከመዋጀት ይልቅ ብሶቶችን እየለቃቀመ በመቀስቀስ ወደ ኋላ ሲመልሰን በብዙዎች ተስተውሏል። ካለፈው ስሕተት መማር ስሕተቱ እንዳይደገም ይጠቅማል ቢባልም ብሶትን ማባባስ ግን ወደ ኋላ ከመመለስና ዛሬን ከማባከን በተቀር ፋይዳ አይኖረውም። የስድሳ ስድስቱ አብዮት ፊውዳሊዝም ኢምፔሪያሊዝም ይህን ያን አረገን እያለ እንዳንጠይቅ አፍኖ ዘመናችንን እንደ ዘረፈን ሁሉ። ዛሬም ይህ ጎሳ ያ ጎሳ እያልን በጋራ ልንጋፈጣቸው የሚገቡንን ችላ እንዳልን ሁሉ ማለት ነው። አራተኛ፣ የጋዜጠኛ ፖለቲከኛነቱ ለስነ ጽሑፍ ሊያበረክተው የሚችለውን ድርሻ እንዳያብብ አዘግይቶበታል። እውነት የምትገለጠው መንገድ ለሚለቁላት ትሑታን እንጂ ለሚጋፏት አይደለም።

* * * *

ስለ ሰው ልጅና ስለ ራሱ ማንነትና መብት ሲጽፍ በዘር ለያይቶ ነው። በጎሣ ፖለቲካ ላይ ማተኮሩ ደግሞ ሳያስፈልግ ቃላተኛ አድርጎታል። ለምሳሌ፤ አሁን ወደሚኖርበት ኔዘርላንድስ እንደ ደረሰ ወደ ስደተኛ ካምፕ ያደረገውን የእግር ጉዞ "መንገዱ ላይ ሰው አይታይም። መኪና የለም" ሲል ገልጾታል፤ አጭርም ቢሆን ምን ማለቱ እንደ ሆነ ለማንም ግልጽ ነው ["ስደተኛው" ገጽ 9]። ደራሲው ግን ሳያበቃ "እንደ አማራ አገር እረኞች ላሟ ርቃ ስትሄድ፣ 'ሃይ! ነይ ተመለሽ ቡሬ' የሚል ዜማዊ ድምፅ በርቀት አይሰማም። አካባቢው እንደ ገልማ ቃሉ ፀጥ ያለ ነው" ብሎ በማራዘም ይዞት በመጣው የጎሣ መነጽር ያስቃኘናል። ለዚያውም ከአውሮጳ ሕዝቦችንና አስተሳሰቦችን በማስተናገድ በሰብአዊነት ተምሳሌትነት በምትታወቅ በኔዘርላንድስ! ስለዚሁ አቋሙ ተጠይቆ "ስለ ዘር መነጋገር ወቅቱ ያመጣው አጀንዳ ነው" ብሏል["ላይፍ" መጽሔት 2006]። በሌላ አነጋገር፣ ደራሲው በደርግ ዘመንና አሁን በሚገዛው መንግሥት ውስጥ የነበረው ሚና ተገቢ ነው እያለን ነው። አቤ ጉበኛ "አልወለድም" ን ሀዲስ "ፍቅር እስከ መቃብር" ን ሲጽፉ የተገኙበትን ዘመን ብቻ ማስተጋባታቸው ሳይሆን ከዚያ በወጣ አዲስ ራእይ መፈንጠቃቸው ነው። ደጋግሞ የሚያነሳው በአሉ ግርማ ሕይወቱን ያጣበት ምክንያት የተዘነጋው ይመስላል። እርሱ ግን በደርግ፣ ከዚያም "ተራሮችን ባንቀጠቀጠ ትውልድ" ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ ሲሠራ ከቆየ በኋላ፣ውስጥ አዋቂዎች እንደሚነግሩን በሌሎች ላይ የደረሰውን እስርና መንገላታት ሳያይ በመንግሥት እውቅና ውጭ አገር ተደላድሎ መኖር ከጀመረ አሁን 14 ዓመታት ሆኖታል። በስደት መጽሐፍ ጽፎ ማሳተምና ከአገር አገር መጓዝ ችሏል። አምስተኛ፣ ከአገር ርቆ መኖሩ ደግሞ በአጻጻፉ ላይ የራሱ የሆነ ጥቁር ጥላ መጣል ጀምሯል። ያም ከሚጽፍለት ሕዝብ መሃል አለመገኘት በቋንቋውና በአስተሳሰቡ ላይ ለውጥ እያመጣ፣ የእንግሊዞችን አባባል በአማርኛ ለመጻፍ ተገድዷል። ለምሳሌ፣
[ገጽ 9]፣ "የትሮፒካል የአየር ጠባይ ስር ተወልጄ ያደግሁ" [I was born under a tropical climate]
"ጭንቅላታቸውን ተናግረው አያውቅም" [never spoke their mind]
[ገጽ 396]፣ "እባክህ ብቻዬን ተወኝ" [please leave me alone]
[ገጽ 365]፣ የልብህን ድምጽ አዳምጥ [listen to your heart]

ይህንኑ በመገንዘብ ይመስላል፣ ለ "ላይፍ" በሰጠው ቃለ ምልልስ ላይ "እንደ በፊቱ ለአማርኛ ጽሑፍ ቅርብ አይደለሁም - የሚታተሙ መጻሕፍትን እንደ ልቤ አላገኝም" ይልና ቀጥሎ፤ "አማርኛ ጠላት ስለ በዛበት ስነ ጽሑፍም ባለቤት አጥቷል" ይለናል [ቅጽ 7፣ ቁ. 116/2006]። አምሃ አስፋው ደግሞ ኢትዮጵያ ተመላልሶ የተገነዘበው አማርኛ ስነ ጽሑፍ እያበበ መምጣቱን ነው [ኢትዮሚድያ መጋቢት/2006 ቅጽ ይመልከቱ]። በተጨማሪ ሱቢ2000 ዶት ኮም ድረ ገጽ በ2000፣ 2001 እና 2002 ዓ.ም በአማርኛ 226 መጻሕፍትና 148 ፊልሞች አገር ውስጥ መታተማቸውን የዘገበው ማረጋገጫ ይሆነናል።

 

* * * *

ተስፋዬ ከበአሉ ግርማና ደጋግሞ ከሚጠራቸው ደራስያን ጥላ ሥር ወጥቶ የራሱን ፈር መቅደድ አለመቻሉ ሌላው ጉዳይ ነው [ዛሬም እንኳ "ኦሮማይ በአሉ" ይላል፣ ም. 23]። በ "የስደተኛው" 39ኙም ምዕራፎች ውስጥ ከ39 የማያንሱ ደራስያን ተጠቅሰዋል። የተስፋዬ መጽሐፎች የኢትዮጵያ ደራስያን ስም ማውጫ እስኪመስሉ ድረስ ስምና ሥራቸውን ቆንጽሎ አቅርቦልናል፤ ደራሲያኑ ከመተቸት ለመታቀባቸው አንዱ ምክንያት መሞገሳቸው ይሆን? ጊዜ ለመሻማት ጥቂት ምሳሌዎችን እንጥቀስ። በአሉ "ደራሲው" ላለው ተስፋዬ "የደራሲው ማስታወሻ" ብሏል። ልዩነቱ በአሉ ስለ ሌላ ሰው [ደራሲ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር] ሲጽፍ ተስፋዬ ግን የጻፈው ስለ ራሱ ነው። በአሉ ስለ "ሮማን ኀለተወርቅ" [ኦሮማይ፣ 2ኛ እትም፣ ገጽ 1-13] ሲያወሳ ተስፋዬ ስለ "ፍቅር በለጠ" ጽፏል [ም.33]። ሮማንና ፍቅር ሁለቱም ረጅም ጠጉር አላቸው፤ ሁለቱም ጴንጤዎች ናቸው፤ ሁለቱም ወንድ ጓደኞቻቸውን ጴንጤ ለማድረግ ይሞክራሉ፤ ሁለቱም ስለ ፖለቲካና ኃይማኖት ያወሳሉ፤ ሁለቱም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ስለ ፈውስና ጸሎት ይወያያሉ። ከላይ ስለ እምነቱ ሲጽፍ "ተጽእኖ ያደረጉብኝ በርካታ መጻሕፍት አሉ" ብሎን ነበር [ገጽ 359]። ይህ የአሳብ መመሳሰል ግን አጋጣሚ ብቻ ሊሆን አይችልም። ለማንኛውም፣ የበአሉ ተጽዕኖ ይኸና ጉልህ ሆኖ ሳለ ለ "ላይፍ" መጽሔት በሰጠው ቃለ ምልልስ፣ ተጽዕኖ ያሳደሩብኝ የሩሲያ ወርቃማ ዘመን ደራሲያን ናቸው በማለት ርቀት ለመፍጠር ሞክሯል።

ታዳጊ ደራሲ ከነባሩ ልምድና ስልት መቅዳት ያለ ነገር ነው። ቼኾቭ ጀማሪ ጸሐፊ በነበረበት ወቅት ለምሳሌ ከርሱ የገነኑት የጻፉትን አጫጭር ታሪኮች መላልሶ ቃል በቃል እየጻፈ ስልታቸውን ያጠና ነበር። ኋላ ግን ከራሱ አልፎ "ቼኾቫዊ" ሊባል የቻለ ስም ለራሱ ሊያንጽ ችሏል። ተስፋዬን ብዙ ግፊቶች ተጭነውታል። አንዱ እያረጁና ቦታና ዘመን እያራራቃቸው ከሚገኙ ከቢሾፍቱ ትዝታዎችና ሕዝብ አውቆ ከጨረሳቸው የመንግሥት "ምሥጢሮች" እስር መውጣት ነው። ሌላው በስደት ምድር በስደተኛው ማኅበረሰብ ዘንድ መደመጥና መታመን መቻል ነው። ቋንቋ ዝብርቅርቁ በወጣበት ምድር ማለት ነው። ለመታመን በመረጃ አሰባሰብ ዙሪያ ብዙ ጥንቃቄ ማስፈለጉን መረዳት ነው። ውጭ አገር መረጃ ከምንጩ ያለ ፈቃድ መውሰድ ወይም የደራሲን አቋም ማዛባት እንደሚያስጠይቅ መረዳት ነው። ተስፋዬን በቀጥታና በተዘዋዋሪ ከነባርና በሕይወት ካሉ ኢትዮጵያውያን ጸሐፍት ደረጃ ማወዳደር ሌላ ያልታሰበ ጫና ይፈጥርበታል። ደግነቱ፣ ይህን በመረዳት ይመስላል፣ ራሱ ተስፋዬ እንዲህ ብሎናል፦ "ከበአሉ ግርማ እና ከብርሃኑ ዘርይሁን ጋር እያወዳደሩኝ ሲፅፉ ግን በውነቱ ተሳቅቄያለሁ። ትሁት ለመሆን ብዬ አይደለም። በብዙ መለኪያዎች ብርሃኑና በአሉ የተሟሉና የተዋጣላቸው ደራስያን ነበሩ። እኔ ራሴን ከነሱ ተርታ የማስቀመጥ ድፍረት የለኝም። ጀማሪ ነኝ። ወደፊት ጥሩ ጥሩ የስነፅሁፍ ስራዎችን ለመስራት አሳብ አለኝ።" [ኢትዮፎረም ቃለ ምልልስ፣ የካቲት 19/2001]። አሁን የቀረው ጥሩ የስነ ጽሑፍ ስራዎችን መስራት ነው። ለዚህም ሦስት አማራጮች አሉት። በእንግሊዝኛ መጻፍ፣ በአማርኛ መጻፍ፣ በኦሮሚኛ መጻፍ። ስለ እንግሊዝኛው ከዚህ ቀደም ያስነበበው ጽሑፍ ስለሌለ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። የኦሮምኛ ዕውቀቱ በቂ አለመሆኑን የዐይነ ስወሩ አዝማሪ የገቢሳ ሙለታን ዘፈን ተርጉሞ አሳይቶናል [እግዚአብሔር እንጂ ጎሬ አይደለም፤ ጠመንጃ አንግቷል እንጂ አልደቀነም፤ ጸሐፊ እንጂ ትኋን አይደለም፣ ወዘተ፤ "የስደተኛው ማስታወሻ" ምዕራፍ 15፣ ገጽ182]። በተካነበት አማርኛ ለመቀጠልና ስነ ጽሑፋዊ ጥልቀት ለመጎናጸፍ ራሱን ካሰረበት "ፖለቲካ ብቻ" አመለካከትና መረጃቸው ከሳሳ "ግለት ብቻ" ሥራዎች መላቀቅ ይኖርበታል። ለዚህም የዕውቅ ደራሲያንን ሥራ ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ መመለስ መነሻ ሊሆነው ይችላል። 

~ ምትኩ አዲሱ

ኅብር ሕይወቴ| የማርያም ታላቅ አእምሮከየት ተገኘሽ ሳልል | ቋንቋን በቋንቋ | ስደተኛውና አምላኩ | ሞት እና ፕሮፌሰር | መንበርና እርካብ | Land of the Shy, Home of the Brave | የማለዳ ድባብ