የዶ/ር ዐ ቢ ይ  ፈ ተ ና ዎ ች

parkEth2

በጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ አመራር ላይ ከየአቅጣጫው የሚሠነዘረው ክስና ወቀሳ ለጒድ ነው። አንዳንዱ ተገቢ ነው፤ ለምሳሌ፣ ብቻቸውን ተዋናይ መምሰላቸው። በፖለቲካ ዓለም መምሰል መሆንም ነውና! “መደመር” እንዴትና በምን መልኩ እንደሆነ ገና ሳይታወቅ፣ ኖቤል በተሸለሙ ማግሥት፣ የመጽሐፋቸውን አንድ ሚሊዮን ኮፒ በእንግሊዝኛ፣ በአማርኛ፣ እና በኦሮምኛ ቻይና ታትሞ መሠራጨቱ በብዙዎች ዘንድ ዐቢይ/ኢሕአዴግ ወዴት? የሚል ጥያቄ ፈጥሯል። ከብዙ ተስፋ ሰጭ ንግግሮቻቸው መኻል ያልተተገበሩት ቊጥር መብዛት ሌላኛው ጥያቄ ነው። ይልቊን በአገራዊ ጒዳዮች ላይ በጊዜ ገለጻ አለመሰጠቱ ሕዝቡን ሥጋት ላይ ጥሏል፤ ተጻራሪ ዓላማ ያላቸው ተቃርኖውን እንዲያባብሱት ረድቷቸዋል። አንዳንዱ ወቀሳ መረጃ ቢስ ጥላቻና የሰነበተ የጎሣ ፖለቲካ ነው። ለምሳሌ፣ ጠ/ሚንስትሩ ህዝብ ካስመረረ ከህወሓት/ኢሕአዴግ መገኘታቸው፣ በኦሮሞ ፓርቲ መወከላቸው፣ የኦሮሞ ፓርቲ ከጧቱ በህወሓት/ኢሕአዴግ እስላም--ፕሮቴስታንት፣ ኦሮምያ--ቁቤ--ወለጋ--አርሲ--ቦረን፣ ወዘተ ተሰኝቶ መደራጀቱ፣ ጠ/ሚንስትሩ ከአማራ እና ከኦሮሞ መወለዳቸው፣ የፕሮቴስታንት አማኝ መሆናቸው ለጥርጣሬም ለሙገሳም ዳርጎአቸዋል። ህወሓት/ኢሕአዴግን ያሞግሱ የነበሩ ወንጌላውያንና ነቢያት ዐቢይንም እያሞገሱ ይገኛሉ።

ከሩቅና ከዳር ለተመለከተ ጠ/ሚንስትሩን ከባድ ኃላፊነት ተጭኖአቸዋል። የሃያ ሰባት ዓመት ውስብስብ ብሶት ቶሎ መልስ አለማግኘቱ፣ ከሥልጣብ እርካብ የተንሸራተቱት ሌት ተቀን በዘረጋጉት መስመር ወደ ቀድሞ ሥፍራቸው ለመመለስ መንቀሳቀሳቸውና አጋሮቻቸውን ማንቀሳቀሳቸው ለምናየው ውዥንብር ትልቅ አስተዋጽዖ አድርጓል። ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የሃያ ሰባት ዓመት ውትብትብ ይፈታ ማለት የተንጋደደ አስተሳሰብ ነው።

የሰሞኑ ወቀሳ ግን ከሌላው ጊዜ ይልቅ ከርሯል። ከወቀሳው በስተጀርባ ግለሰቦችና ቡድኖች የጋራ ጉዳዮችን ለይተው አውቀው በቅደም ተከተል እንደማስኬድ የየግል ጉዳያቸውን አንግበው ተሠልፈዋል። እነዚሁ ጠ/ሚ ዐቢይን ለጒዳይ አስፈጻሚነት ብቻ የፈለጓቸው ይመስላል! የክልል ኢትዮጵያዊ ሁሉ ጣቱን ሳያነሳ ራሱን አዛዥ አድርጎ ሾሟል! ታዛዡ ሁሌ ሌላው ሰው ነው! ለውዥንብሩ ተጠያቂውም ሌላው ሰው ነው!

ተለጉሞ ለኖረ የመናገር መብት መለቀቅ ውዥንብሩን አባብሶታል። ተጠያቂነት የሌለበት ስለሆነ መብቱ ከአፍራሽነት ሊያልፍ አልቻለም! በምህረት ወደ አገር የተመለሱት የደርጉ ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ ሰማይ ጥግ ሲያሞግሱ እንዳልነበረ ዛሬ በአደባባይ ዶ/ር አብይ ከሥልጣን ይነሱ እያሉ ነው። እርሳቸው የመሩትን ደርግ ሥልጣን ይልቀቅ ያሉ በዘመኑ የደረሰባቸውን ቢዘነጉ ነው! ወይም የዘነጋን መስሎአቸው ነው። የቀድሞ ጠ/ሚ መለስ ባለቤት ወ/ሮ አዜብም ዶ/ር ዐቢይ ብቃት ያንሳቸዋል ብለዋል፤ መለስን ለማግነን ይሆናል ብለን እንለፈው! ሌላኛው የቀድሞ ጠ/ሚ ኃይለማርያም የኋሊት ተመልሰው፣ 95 በመቶ እስረኛ የፈታሁ፣ ጥልቅ ተሓድሶ የጀመርኩ፣ ለዐቢይም ያመቻቸሁለት እኔው ነኝ እያሉ ነው። “ፖለቲካ በቃኝ፣ እግዚአብሔርን አገለግላለሁ” ያሉን የህወሓት/ኢሕአዴግ የቀድሞ ጠ/ሚ አቶ ታምራት ላይኔም የከረረ ግልጽ ደብዳቤ ለጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ልከዋል። ደብዳቤአቸው ባጭሩ “ቀደም ሲል እንዲህ ብዬ ነበር፤ ይኸዋ፣ ያልኩት ደረሰ!” የሚል ነው። ታምራት፣ ነገር እንደ ዛሬ ከመበላሸቱ አስቀድሞ ሥልጣን ላይ ሆነው ያላደረጉትን ለመምከር መጋበዛቸው ይልቅ ትዝብት ላይ ይጥላቸዋል። እርግጥ ያጠፋ ከጥፋቱ ከተማረና ቅን ከሆነ ተግሳጹ አይጠቅምም አይባልም። “እኚህ ሰው (ዐቢይ) እውነት ለኢትዮጵያ የቆሙ ናቸው ወይስ ከትግራይ ልሂቃን የበላይነት ወደ ኦሮሞ ልሂቃን የበላይነት፣ ለሌላ ተረኝነት የተነሱ መሪ ናቸው?” ካልሆነ “ዲያብሎሳውያን ኃይሎችን” ለምን አያስቆሙም? ታምራት ይህን የመሰለ ብዙ ብዙ ብለዋል፤ እንዲያውም ይህን ዓይነት ነቀፌታ ከሚያሰሙ ወገኖች ሙገሳ እየተቸራቸው ነው። የጎደፈ ታሪካቸውን ለማደስና ዳግመኛ የሥልጣን እርካብ ላይ ለመውጣት ዘመቻ ላይ ይሆኑ?

አቶ ታምራት “ፓለቲካ በቃኝ” ካሉ በኋላ በፖለቲካ መሳተፋቸውን እንደ ኃጢአት አንቆጥርባቸውም፤ ለአገር መቆርቆራቸው ሊሆን ይችላልና። ችግሩ ዳኛ ሆነው መቅረባቸው ላይ ነው፤ “[ዶ/ር ዐቢይ] ፈተናዎን መውደቅዎ እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙዎች ያዩት እውነታ ሆኗል። ሆኖም ግን በፈተና የወደቀ እንደ ወደቀ እንደማይቀር ከሌላ ሳይሆን እኔ ራሴ ከፈተና ወድቄ ያልቀረሁበትእንዲያውም በበለጠ ትምህርት የተነሳሁበት ምስክርነት ስላለኝ ወድቀው ይቀራሉ ብዬ ለመበየን የምዳዳበት የሞራል እሴት የለኝም” ብለዋል።

ታዲያ ዐቢይ ከወደቁበት ለመነሳት ምን ያድርጉ? ታምራት ለዚህም መልስ ይዘዋል። “የሚደነግጡ ከሆነ የሚያስደነግጥዎትን ጉዳይ ላንሳልዎ። እርስዎና ቡድንዎ እናምነዋለን፣ እንከተለዋለን የምትሉትን እግዚአብሄርን~ኢየሱስ ክርስቶስን በድብቅ ሳይሆን በአደባባይ ክዳችሁታል፤” የታምራት ብይን እውነት ከሆነ እውነትም የሚያስደነግጥ ነው። ልብን የሚያውቅ እግዚአብሔር ነውና፣ ውሸት ከሆነ ግን ለከሳሽ ወዮለት!

ለመሆኑ እንዴትና እንዴት አድርገው ነው ዐቢይ ኢየሱስ ክርስቶስን የካዱት? መልሱ፦ “እሬቻ የተባለውን የቃልቻ፣ የአቴቴና የዊችክራፍት መንፈስ፣ የወንዝና የቄጤማ አምላክ የፍቅርና የአንድነት ባህል ብሎ የዳቦ ስም ሰጥቶ መስቀል አደባባይ ላይ ህዝብ እንዲሰግድለት ባወጀው ጉባኤ ግምባር ቀደም ተካፋይ ሆናችኋል፤ በፊርማችሁ አጽድቃችኋል [እርሳቸው ፓትርያርክ መርቆሬዎስን በፊርማቸው እንዳስነሡ፤ ደርግ የነሳውን የኃይማኖት ነጻነት በፊርማዬ አቀዳጀሁ እንዳሉ!]፤ በፊታውራሪዎችዎ አማካይነት የእግዚአብሄር አምላክነት ተክዶ የእሬቻ አምላክ እንዲወደስ፣ ምልአተ ህዝቡ በጭፈራ እንዲያመልከው አስደርገዋል።”

አቶ ታምራት ሌላ ታሪካዊ ስህተት እየፈጸሙ እንደሆነ አልገባቸው ይሆን? ዐቢይ የግል እምነታቸውን በአገር ሁሉ ላይ መጫን አይችሉም እኮ! (“ኃይማኖት የግል ነው!”) ዐቢይ የሕዝብ ሁሉ እንጂ የአንድ ወገን ብቻ መሪ አይደሉም። የኢትዮጵያ ህዝብ ከጥንት የወረሳቸው እምነቶችና ባህሎች ባለቤት ነው። ታምራት አቴቴ፣ ቄጤማ፣ ቃልቻ የማያውቅ የአገራችንን ሕዝብ ሊጠቊሙን ይችላሉ? ቃልቻ፣ ቄጤማ ጎሣ ይለያል እንዳይሉን ብቻ!!

ከእግዚአብሔር ቃል የጠቃቀሷቸው ክፍሎች ዐውዱን የሳቱ፣ የዐቢይን የግል እምነት የማያንጸባርቁ ናቸው። “ለእሬቻ አምላክ ሰግደዋል። የእግዚአብሄርን ክብር በእሬቻ ለውጠዋል። የእርሱን አምላክነት ክደው የእሬቻን ጣኦት አምልከው አስመልከዋል።” እውነት ጠ/ሚ ዐቢይ የእግዚአብሔርን አምላክነት ክደው ጣኦት አምልከው አስመልከዋል? እሬቻ የተጀመረው በዐቢይ ዘመን ነው? ኢድ ላይ መገኘታቸውስ እስላም ያደርጋቸዋል ሊሉ ነው? መጽሐፈ ዘጸአትን ጠቅሰውልናል። “እግዚአብሄር አምላክህ እኔ ነኝ፤ ከኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ። በላይ በሰማይ ወይም በታች በምድር ካለው ወይም በውሃ ውስጥ ከሚኖሩት ነገሮች በማናቸውም ለራስህ ጣኦትን አታብጅ፤ አትስገድላቸው፤ አታምልካቸውም፤”(20፡2-5)

ያህዌ ህዝበ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት ሲያወጣ ሲና ላይ በሙሴ እጅ አሠርቱን ቃላት ሰጥቶት ነበር። ይህም ጣኦት ከሚያመልክ፣ ያህዌን ከማያውቅ ህዝብ ጋር እንዳይነካካ፣ ይልቅ በአኗኗሩ የተለየ ህዝብ መሆኑን እንዲመሰክር ነው። ዐቢይን በሙሴ ዐይን፣ የኢትዮጵያን ህዝበ ብሔር፣ በነገደ እስራኤል፣ ወይም በጣኦት አምላኪ ህዝብ መፈረጅ ትልቅ ስህተት ነው። ሰዎችን ወደ እውነተኛው ሐዋርያዊና ወንጌላዊ አምልኮ የምንጠራው በትእዛዝ ወይም በመኮነን ሳይሆን በፍቅርና በቅዱስ አኗኗር ነው። እሬቻ እንደ ሌሎች ኢትዮጵያዊ ባህሎችና እምነቶች ባዕድ አምልኮ የለበትም አንልም፤ ከመኸር በኋላ የሚመጣ ክብረ በዓል መሆኑ ግን ላፍታም መረሳት የለበትም። አደባባይ የወጣ ሁሉ ጣኦት አምላኪ ነው ማለት ያገጠጠ ውሸት ነው። እሬቻን ሲያከብሩ ቢሾፍቱ ላይ ያለቊት መቶዎች ዜጎች ህወሓት/ኢሕአዴግ/ኃይለማርያምን ለእግዚአብሔር ቀናዒ ያደርጋቸዋል ሊሉን እንዳይሆን!

ታምራት ቀጥለው፣ ኢየሱስን ስለ መከተልና ራስን ስለ መካድ (ሉቃስ ወንጌል 9፡23-25) ጠቅሰው፣ ዐቢይን “ለግል ተክለሰውነትዎና የስልጣንዎ አለም ለሚያተርፍልዎ ትርፍ ከቶ አይጨነቁ፤ በቅድሚያ ለእግዚአብሄር ቀጥሎ ደግሞ ለኢትዮጵያና ለህዝቧ ትክክል ለሆነው ነገር ብቻ እስቲ ለመኖር ይጀምሩ” ሲሉ መክረዋቸዋል። አባባላቸውን እንዴት በተግባር መተርጎም እንደሚቻል ግን አልገለጹም።

አቶ ታምራት ምድረ አሜሪካ ከገቡ ጀምሮ ውሎአቸው ከአሜሪካ ወንጌላውያን ጋር ሆኗል። ይኸ በራሱ ምንም ክፋት የለውም። ሆኖም የአሜሪካ ወንጌላውያንን ቀኝ አክራሪ ፖለቲካ ሳያስተውሉ የተቀበሉ ይመስላል። ነገሮችን ነጣጥሎ ከማየት ይልቅ ከተቀበሉት እምነት ውጭ ያለን ሁሉ በጅምላ መኮነን። የአሜሪካው ም/ፕሬዚደንት ፔንስ “በቅድሚያ ክርስቲያን ነኝ፣ ቀጥሎ ቀኝ ዘመም ፖለቲከኛ፣ ከዚያ ሪፓብሊካን ነኝ” ማለታቸው፣ ታምራትን “በቅድሚያ ለእግዚአብሄር ቀጥሎ ደግሞ ለኢትዮጵያና ለህዝቧ” እንዲሉ ያደረጋቸው ይመስላል። ዐቢይ በግላቸው እግዚአብሔርን አለማስቀደማቸውን የሚያውቅ እግዚአብሔር ብቻ ነው።

በሥልጣን አደረጃጀት ስትታይ አሜሪካ “የነጭ ክርስቲያን” አገር ነች፤ ኢትዮጵያን በዚያ ዐይን ማየት ስህተት ብቻ ሳይሆን አደገኛ ነው። ጆርጅ ቡሽ “የምታደንቀው ፈላስፋ ማን ነው?” ተብለው “ክርስቶስ ነው፤ ሕይወቴን ስለቀየረ” የሚል ምላሽ ሰጥተው ነበር። ሁለቱም ፕሬዚደንቶች በክርስቶስ ያመኑ አይደሉም አይደለም ነገሩ፤ ነገሩ፣ ግለሰቦቹ ይህን ያሉበት ምክንያቱ የወንጌላውያኑን ድምጽ ለማሸነፍ ነው፤ ሥልጣን ከያዙ በኋላ የተከተሏቸውን አውዳሚ ፖሊሲዎች አቶ ታምራት እንዴት ይሆን የሚተረጒሙት? በአንጻሩ፣ ዐቢይ ሥልጣን የያዙት በህዝብ ተመርጠው አይደለም፤ ቢመረጡ ኖሮም እንኳ እንደ አሜሪካኖቹ የኔን እምነት የያዛችሁ ምረጡኝ ማለት ነውርና አፍራሽ ፖለቲካ ይሆናል!

በወንጌል ማመኻኘት ማታለል፣ ቅን አለመሆን ነው። ፕሬዚደንት ትረምፕን ከነጭ ወንጌላውያን ያገኙት ሰማንያ አንድ በመቶ የምርጫ ድምጽ ለድል አብቅቶአቸዋል! የፕሬዚደንቱ ወንጌል ተጻራሪ ስነ ምግባር (ወንጌል አማኝ አለመሆናቸው፣ ስደተኛና ነጭ ያልሆነን ሁሉ ማዋረዳቸው፣ ወዘተ) ብዙ ነቀፌታ አስነስቶ ነበር፤ ያንን ለማርገብ ወንጌላውያኑ የኢየሩሳሌምን ቅጥር ባስገነባው በፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ መስለዋቸዋል። በሌላ አነጋገር፣ የአሜሪካ ባህላዊ/ፖለቲካዊ ክርስትና ለኢትዮጵያ ይስማማል ማለት የህዝቦችን ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ታሪክ አለመረዳት ነው።

አቶ ታምራት በአይሁዱ መርዶክዮስ ተመስለው፣ ጠ/ሚ ዐቢይን “አስቴር [በ]መርዶክዮስ ምክር ሰልፏን አስተካክላ አይሁድንም ራሷንም ከጥፋት ለማትረፍ ወሰነች፤ እግዚአብሔር ተጠቀመባት፤” እርስዎም ምክሬን ሰምተው አገራችንን ከጥፋት ይታደጉ ብለዋቸዋል (መጽሐፈ አስቴር 4፡13-14)። ነገር ከተባባሰ፣ ምነው ምክሬን በሰሙ ኖሮ ሊመጣ ነው! ይኸው ጥቅስ ፕሬዚደንት ትረምፕን እግዚአብሔር እንዳስነሳቸው ለማስረገጫ ውሏል፤ ይባስ የፕሬዚደንቱ ሴት ልጅ እና ባል በቅድስት ማርያምና በቅዱስ ዮሴፍ ተመስለዋል! እርግጥ የሚያነሳና የሚጥል እግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር ያስነሳቸው ደግሞ የርሱን ቅን ፍርድ ከመፈጸም ውጭ እንዳፈቀዳቸው ይሆናሉ ማለት አይደለም! (መዝሙር 62፡11፤ ዳንኤል 2፡21፤ 1ኛ ጴጥሮስ 5፡11፤ ሮሜ 13፡1:4)

ወንጌል ያለ ዐውዱ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲውል ይህን ይመስላል። እንደ ስል ቢላ፣ እንደ እሳት በሕጻን እጅ ይሆናል። ሕጻኑን ማስጣል ብዙ ጥንቃቄና የሕጻኑን ቀልብ የሚስብ ብልሃት መፍጠርን ይጠይቃል! ደግሞ ብዙ ብዙ ጸሎትን። ፈተናዎች ተጋርጠውብናል። ያለ ዶ/ር ዐቢይ መንቀሳቀስ የማይቻል መምሰል የለበትም፤ ቤተ መንግሥቱንና ቁልፍ ተቋማትን ከአሞጋሾችና ከአወዳሾች ማጽዳት፤ በተለይ ደግሞ የሕዝብ ግንኙነቱን ክፍል። በየመስኩ ችሎታ ላላቸው ዜጎች ኃላፊነትን ማጋራት ይኖርባቸዋል፤ ለምሳሌ፣ የህዳሴ ኃይል ማመንጫውን እንዲያሸማግሉ የውጭ ኃይላትን ጣልቃ ማስገባት ለትውልድ ፀፀት እንዳይሆን መጠንቀቅ፣ ከናስር ግብጽ (ዓለም ባንክ ከደገሰላቸው አንጻር)፣ ከዩክሬን፣ ከሶርያ፣ ከኢራቅ ተሞክሮዎች መማር ይጠቅማል።

ምትኩ አዲሱ

ጥቅምት 26/2012 ዓ.ም.

ዐቢይን በባራክ   ፖለቲከኛ ቀስ በቀስ   ያከበሩኝን አከብራለሁ   መንበርና እርካብ