ር ዕ ሰ  አ ን ቀ ጽ

ሁለተኛ ጊዜማ ነገር አለ

ከስምንት ወራት በኋላ፣ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ የካቲት 16/2012 ዓ.ም፣ ሺህ ከሚያህሉ ወንጌላውያን መሪዎች ጋር በቤተመንግሥት ሁለተኛ ስብሰባ አድርገዋል (ከቀድሞው እጥፍ ማለት ነው)። የወንጌላውያኑ እርስበርስ አለመግባባት ግን ከስምንት ወር በፊት እንደነበረው ነው፤ አልተለወጠም።

ሁለተኛው ስብሰባ እንደ መጀመሪያው ታሪካዊም አሳዛኝም ነው። ታሪካዊነቱ ጠ/ሚንስትሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት እያለባቸው ጊዜአቸውን ለዚህ ጒዳይ ማዋላቸው እና የጒዳዩን ክብደት ተረድተው መፍትሔ ለማፈላለግ መፍቀዳቸው ነው። ይህን ቅንነት እግዚአብሔር ይቊጠርላቸው። የሚያሳዝነውና የሚያሳፍረው፣ የቤተክርስቲያን መሪዎች የመንግሥት እጅ ሳይገባበት በራሳቸው መስማማት አለመቻላቸው ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ መሪዎች፣ የክርስቶስን ቤተክርስቲያን ገበና በዓለም ፊት ማዋረዳቸውን ለመውቀስ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “አሳፍራችሁ ዘንድ ይህን እላለሁ። እንደዚህ ነውን? በወንድሞች መካከል ሽማግሌ ሊሆን የሚችል አንድ አስተዋይ ሰው በእናንተ ዘንድ አይገኝምን? ነገር ግን ወንድም ወንድሙን ይከሳል፥ ይህም በማያምኑ ፊት ይደረጋልን? እንግዲህ ፈጽሞ የእርስ በርስ ሙግት እንዳለባችሁ በእናንተ ጉድለት ነው። ብትበደሉ አይሻልምን? ብትታለሉስ አይሻልምን?” (1ኛ ቆሮንቶስ 6፡5-7)። ጠ/ሚ ዐቢይ ከሓዲ አለመሆናቸው ይህን እውነት ለአፍታ እንኳ አይለውጠውም!

ሌላኛው አሳዛኝ ነገር፣ ፍ/ቤት ስንጓተት ከነበርንበት ዘመን ምንም አለመማራችን ነው። ሌላኛው፣ የቤተክርስቲያን ጒዳይ በግለሰቦች ውሳኔና እይታ መታገቱ ነው። ነገሮችን "መንፈሳዊ" ማስመሰልና ማወሳሰብ አይጠቅምም። በቅድሚያ የተከሰተውን ችግር በወሬ፣ በአንጀኛ ስሜት ሳይሆን በጸሎትና በትእግስት አጥርቶ ማወቅ ያሻል። ነገሮችን ከቤተክርስቲያን ጥሪና ተልእኮ አንጻር ማየት፤ ሁኔታው የወንጌልን ብርሃን፣ ክብርና ንጽሕና ያጎድፋል ወይስ ያጠራል? ለብቻ መቅረት ካስፈለገ ለዚህም እንኳ ቆርጠናል? እግዚአብሔር ያለእኛም ወይም ባልታሰቡ በሌሎች መሥራት እንደሚችል አውቀናል? ዘመናችን እና ማስተዋላችን አጭር እንደሆነ ተገንዝበናል? ጒዳዮችን እንደየክብደታቸው ቅደም ተከተል አስይዘናል? ሁኔታዎች እያስከተሉ ያለውን ውጤት አጢነናል? ሳይቋጩ ሲቀሩ ችግሮች መልካቸውን ባፋጣኝ እየለወጡ እንደሚሄዱ ተገንዝበናል? የመንጋውስ መወናበድ አሳስቦናል?

እግዚአብሔር መሥራት ሲጀምር የቤተክርስቲያን መሪዎች አሁን ያቀረቡትን ምክንያት ለመደርደር እንኳ ፋታ አይሰጣቸውም። እግዚአብሔር ዞር ማድረግም እንደሚችል ዘንግተን ይሆን? (መዝሙር 75፡6-7፤ ዳንኤል 2፡21)። “ይህ የምሰማብህ ምንድር ነው? ወደ ፊት ለእኔ መጋቢ ልትሆን አትችልምና የመጋቢነትህን ሂሳብ አስረክበኝ አለው” (ሉቃስ 16፡1-2)። እዚህስ ደረጃ ላይ የደረስነው በወቅቱ ሊወሰዱ የተገባቸው እርምጃዎች ባለመወሰዳቸው አደል?

ችግሩ ዞሮ ዞሮ ከመሪዎች ጀርባ ላይ አይወርድም። ማመካኘት አይቻልም። የቲኦሎጂ ጠጒር ስንጠቃ አያዘልቅም። ቤት እየተቃጠለ ይኸ ሁሉ ዋጋ የለውም። ጥፋት ሳይበረታ ምን ይደረግ? መሪዎች ሥልጣናቸውን መልቀቃቸው መፍትሔውን የሚያቃርብ ቢሆን ዝግጁና ፈቃደኛ ናቸው? መሪዎች ከመሞጋገስ አልፈው ልኩን ይነጋገራሉ? የሰው ወይስ የእግዚአብሔር ፍርሓት ገዝቷቸዋል? ወንጌላውያንን የሚያስማሙ የማይደራደሩባቸው አስተምህሮዎች የትኞቹ ናቸው? ዐይናችንን በገድላችንና በቊጥራችን ብዛት ላይ አድርገን ይሆን?

ለእግዚአብሔር የሚሳነው የለም። እግዚአብሔር ስለ ቤቱ ይገድደዋል። ስለ ስሙ ለክብሩ የሚሆነውን ያደርጋል። መፍትሔው እንዴት እና መቸ እንደሚከሰት ግን በእኛ ዘንድ የሚያውቅ የለም! ብቻ መፍትሔውን አስደንጋጭ አያድርገው፤ በሰላም ያርገው!

የማለዳ ድባብ | ከየት ተገኘሽ ሳልል | ቋንቋን በቋንቋ | ለመቶ ሚሊዮን የአገሬ ሕዝብ | ትዝብቶች ከ “አባቴ ያቺን ሰዓት” | የሺህ ጋብቻ ወይስ ቅዱስ ጋብቻ? | መንበርና እርካብ | ጒዞዬ | Land of the Shy, Home of the Brave |Lent as a Way of Life | Evening Sun