ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም መኖር
ተድላ ሲማ
ክፍል አንድ
“ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ … ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን ተከታተሉ … “በነፍሳችሁ ጨው ይኑርባችሁ፥ እርስ በርሳችሁም ተስማሙ … በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ” (ሮሜ 12፡18፤ዕብራውያን 12፡14፤ ማርቆስ 9:50፤ ኤፌሶን 4:3)።
እነዚህ ጥቅሶች የሚያስገነዝቡን ከሰዎች ጋር በሰላም መኖራችን የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን ነው።ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእኛ በኩል ምን እናድርግ? ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእኛ በኩል ልንተገብራቸው ወይም ልንሆናቸው የሚገቡ ነጥቦች ከዚህ በታች ተብራርተዋል።
ሰዎችና ድርጊታቸውን በቅንነት እንረዳ፤ ቅኖች እንሁን
እግዚአብሔር በባህሪው ቅን አምላክ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር ሲናገር፥ “እርሱ አምላክ ነው።ሥራውም ፍጹም ነው፤መንገዱም ሁሉ የቀና ነው። የታመነ አምላክ ክፋትም የሌለበት እርሱ እውነተኛና ቅን ነው” ይላል (ዘዳግም 32፡4)። እግዚአብሔር ቅን ስለ ሆነ ነው እኛን ጠማሞቹን በፍቅር ተቀብሎ ሰው ያደረገን። እርሱ በቅንነቱ ሰው የተፋቸውን ሰዎች ተቀብሎ መልካም ሰዎች ያደርጋቸዋል፤ የወደቁትን ያነሣል።
እኛም የሰዎችን ድርጊት ስናይ በቅንነት እንረዳ።ቅንነት ማለት ደደብነት ማለት አይደለም፤ ሞኝ መሆን ማለትም አይደለም። ቅን ሰዎች ነገሮችን አቅንተው የሚያዩ ናቸው። ቅን ሰዎች ከሰዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት በአብዛኛው ጤናማ ነው። በአንጻሩ ደግሞ ነገሮችን በቅንነት የማያዩ ወይም አጣምመው የሚረዱ ሰዎች በአብዛኛው ከሰዎች ጋር የመጋጨት ዝንባሌ ይታይባቸዋል። ቅንነት በረከትም አለው።የእግዚአብሔር ቃል “እርሱ ለቅኖች ደኅንነትን ያከማቻል“ ይላል (ምሳሌ 2፡7)። በተጨማሪም የእግዚአብሔር ቃል “እግዚአብሔር የጽድቅ ጋሻዬ ነው፤ ልበ ቅኖችን የሚያድናቸው” ይላል (መዝ.7:10)።
ቅንነትን ለማስረዳት አንድ ምሳሌ እንይ፦ አንድ የምናውቀው ሰው መንገድ ላይ አይተነው ሰላም ሳይለን ቢቀር ጉዳዩን በቅንነት ካየነው “ሳያስተውለኝ ቀርቶ ነው እንጂ ሰላም ይለኝ ነበር“ ማለት እንችላለን።ወይም ነገሩን አጣምመን “ኮርቶ ነው የዘጋኝ“ ልንል እንችላለን።
ቅንነት የጎደላቸው ሰዎች ብዙ ጊዜ በመሠለኝ ነው አስተያየት የሚሠጡት። የመሠላቸውን ነገር እንደ እውነት ይናገራሉ። ከዚህም የተነሣ ወደ ተሳሳተ ድምዳሜ ይደርሳሉ፤ ቅን ሰዎች ግን የነገሮችን አዎንታዊ ገጽታ ማየት ይቀናቸዋል። ስለዚህ ተጨማሪ እርምጃ በመሄድ የመሰላቸው ነገር እውነት ይሁን አይሁን ያጣራሉ። ለጤናማ ግንኙነት ቅንነት (ነገሮችንና ሁኔታዎችን አቅንቶ መመልከት) እጅግ ጠቃሚ ነው።
ስላደረግነው ነገር ሙሉ መግለጫ እንስጥ፤ እንናበብ
አንድ ነገር ስናደርግ ሰዎች በተሳሳተ መንገድ እንደ ተረዱን ከተገነዘብን፥ ጊዜ ወስደን ስላደረግነው ነገር ማብራሪያ መስጠት አለብን። ሰዎች ሙሉ መረጃ ከሌላቸው ወደ ተሳሳተ ድምዳሜ ሊደርሱ ይችላሉ።ስለዚህ ያደረግነውን ነገር ለምን እንዳደረግን ሙሉ መግለጫ በመስጠት መናበብ መቻል አለብን። ያን ጊዜ ሰዎች ስለ ሆነው ነገር ወይም ስለ ተደረገው ነገር የጠራ ግንዛቤ ስለሚኖራቸው ግንኙነታችን ጤናማ ሆኖ መቀጠል ይችላል። ሰዎች በባህሪያቸው ከነዚህ ከሦስቱ በአንዱ ውስጥ ይመደባሉ፥ ሀ) በራስ ተነሳሽ ለ) ሲነገራቸው የሚነሳሱ ሐ) ተነግሯቸውም የማይነሳሱ፤
ሀ) በራስ ተነሳሽ የሆኑ ሰዎች፦ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ችግሮችን ለመፍታት የማንንም አነሳሽነት አይጠብቁም፤ በራሳቸው የሚንቀሳቀሱ ናቸው። ሁኔታዎች እየተበላሹ እንደ ሆነ ሲገባቸው ወዲያው የእርምት እርምጃ በመውሰድ ነገሮች በጤናማ መንገድ እንዲሄዱ የሚያደርጉ ናቸው። ከሌሎች ጋር ባላቸው ግንኙነት አንድ ሰው እንዳዘነባቸው ከተገነዘቡ፥ ወዲያው ስልክ በመደወል ወይም ያን ሰው በአካል በማግኘት ችግሩን ለመፍታት ይንቀሳቀሳሉ። ከዚህም የተነሣ ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ ከመሆናቸው በፊት መፍትሔ ያበጁለታል። መቼም ሁላችንም እንደዚህ ዓይነት ባህሪ የተላበስን ሰዎች ብንሆን እጅግ መልካም ነበር፤ እውነታው ግን እንደዚያ አይደለም።
ለ) ሲነገራቸው የሚነሳሱ ሰዎች፦ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች እንደ መጀመሪያዎቹ በራሳቸው መነሳሳት ባይሆንላቸውም፥ ችግር መኖሩ ሲነገራቸው ወዲያው እርምጃ የሚወስዱ ናቸው። “እገሌ’ኮ ተቀይሞሃል ሲባሉ “ወዲያው ችግሩን ለመፍታት መንቀሳቀስ ይጀምራሉ። የመጀመሪያው ዓይነት ሰዎች ችግሩን ራሳቸው አነፍንፈው ያገኙታል። ዙሪያቸውን በሚገባ ይቃኛሉ፤ ነገሮች የተበላሸ መሆኑን በንስር ዓይን ያዩና ወዲያው እርምት ይወስዳሉ። ሁለተኛው ዓይነት ሰዎች ግን የዚህ ዓይነት ስጦታ የላቸውም። ሆኖም ግን ስለ ችግሩ መረጃ ባገኙ ጊዜ ወዲያው ይንቀሳቀሳሉ፤ በመሆኑም ጥሩ ውጤት ያስገኛሉ።
ሐ) ተነግሯቸውም የማይነሳሱ ሰዎች፦ እንደዚህ ኣይነት ሰዎች ችግር እንዳለ ቢነገራቸውም ችግሩን ለመፍታት ምንም እርምጃ የማይወስዱ ሰዎች ናቸው። ለምሳሌ “እገሌ ተቀይሞሃል” ሲባሉ “የራሱ ጉዳይ” ይላሉ ማለት ነው። ችግሮችን በጊዜው ስለማይፈቱ ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጪ ይሆናሉ። ችግሮች ሊፈቱ በማይቻልበት ወይም ለመፍታት በሚያስቸግርበት ሁኔታ እንዲገኙ ዕድል ይሰጣሉ። በፍጹም እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ልንሆን አይገባም።
ባንድ ወቅት የተከሰተ አንድ ነገር እዚህ’ጋ ማንሳቱ ሊጠቅም ይችላል። የተወሰኑ ወገኖች በአንድነት ሆነን የጸሎት ጊዜ ነበረን። እዚያ ፕሮግራም ላይ ከሚካፈሉት ቅዱሳን መካከል ሁለት እህቶች የጸሎት ጊዜው እንዳበቃ እንደሚገናኙ ተቀጣጥረው ነበር። ሆኖም ጸሎቱ እየተካሔደ እያለ ለአንደኛዋ እህት ከልጇ ት/ቤት ስልክ ይደወልና ልጇ መጥፋቱ ይነግራታል። እናት በዚህ ጊዜ ደንግጣ ወደ ልጇ ት/ቤት ትከንፋለች። ት/ቤት ስትደርስ ልጁ አለመጥፋቱን ታረጋግጣለች። ከቤተሰብ ውስጥ ሌላ ሰው ቤት እንደ ወሰደው ትረዳለች። እናት የልጇን ሁኔታ እያጣራች እያለ የጸሎት ፕሮግራሙ ያበቃል። ከዚህች እናት ጋር ቀጠሮ የነበራት እህት ከጸሎቱ በኋላ ያችን እናት ከሰዎች መካከል ትፈልጋታለች። ሳታገኛት ስትቀር ብስጭት ብላ ወደ ቤቷ ትሄዳለች። ይህን ሁኔታ ለማስተካከል ምን መደረግ ይኖርበታል? ከሁለቱም እህቶች ሊደረግ የሚጠበቅ ነገር አለ። ያቺ እናት ልጇን አግኝታ ከተረጋጋች በኋላ ስልክ በመደወል ቀጠሮውን እንዳልረሳችውና የልጇ መጥፋት ከት/ቤት እንደ ተደወለላትና ደንግጣ ጸሎቱን አቋርጣ መሄዷን ማስረዳት ይጠበቅባታል። ይህ መናበብ ይባላል። ሌላኛው እህት ደግሞ ሁኔታውን ሳታጣራ ብስጭት ብላ ወደ ቤቷ ከመሄድ በቅንነት "እህቴ ምን ገጥሟት ይሆን ቀጠሯችንን የረሳችው?" ብላ ስልክ በመደወል ብታጣራ መልካም ነው።
ጥቃቅን የሚመስሉ ነገሮች በግንኙነት ውስጥ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። ስልክ በመደወል ብቻ ሊስተካከሉ የሚችሉ ብዙ ነገሮች በዳተኝነታችንና በስንፍናችን ምክንያት ለጤናማ ግንኙነታችን ሳንካ ሆነዋል። በመሆኑም ዳተኞችና ሰነፎች ልንሆን አይገባም። “የራሱ ጉዳይ፥ የራሷ ጉዳይ” ከሚለው ትዕቢተኛ አመለካከት በመውጣት ትሁታን ልንሆን ይገባል። ቅኖችና ትሁቶች ብዙ ጊዜ ከሰዎች ጋር ሲጋጩ አይስተዋልም። በአንፃሩ ትዕቢተኞችና ቅንነት የጎደላቸው ሰዎች ከሰዎች ጋር ሲናቆሩ ዘመናቸውን ሲፈጁ ይስተዋላል፤ ሰላማቸውን ያጣሉ። እግዚአብሔር ማስተዋልን ይስጠን!
ለእኛ ሙሉ ዕድገት የሌሎች እገዛ አስፈላጊ መሆኑን መገንዘብ
እኛ ሁሉን ቻዮች አይደለንም። ዕድገታችን ሙሉ እንዲሆን ከፈለግን፥ ለሌሎች ፀጋ፥ ሥጦታና ችሎታ ዕውቅና በመስጠት በተከፈተ ልብ ሆነን ከሌሎች ልናገኘው የሚገባንን ሁሉ ማግኘት አለብን። ሶቅራጥስ እንዲህ ብሏል፥ “በጣም አዋቂ ሰዎች ከሁሉ ሰውና ከሁሉም ሁኔታ ትምህርትን ይገበያሉ፤ መካከለኛ እውቀት ያላቸው ሰዎች ከልምድ ይማራሉ። አላዋቂ ሰዎች ግን ሁሉን እንደሚያውቁ ስለሚያስቡ ከማንም እይማሩም። “በነገር ሁሉ ሙሉ ሆነን እንድንገኝ ከሌሎች ትምህርት ወይም ማንኛውንም እገዛ ለማግኘት የተዘጋጀን መሆን አለብን። በሰው እድገት ውስጥ ሦስት ደረጃዎች አሉ፦ የጥገኝነት ጊዜ፤ ራስን የመቻል ጊዜ፤ ራስን ከቻሉ በኋላ ሌሎች ራስን ከቻሉ ሰዎች ጋር በመተጋገዝ ወደ ላቀ እድገት መድረስ። ይህ እድገት አካላዊ፥ አእምሯዊ፥ መንፈሳዊ እና ከሌሎች ጋር ያለንንም ግንኙነት ይመለከታል። በጥገኝነት ጊዜ ለሁሉ ነገር የሌሎቸ እገዛ የሚያስፈልገንና የምንፈልግበት ወቅት ነው። የሌሎችን እገዛ በዚህ ወቅት ካላገኘን እንጎዳለን። ህፃን ልጅ አንገቱን እንኳን ለማንሳት የሌሎች እገዛ የሚያስፈልገው ወቅት አለ።በተመሳሳይ ሁኔታ በብዙ የሕይወታችን አቅጣጫ ጤናማና ሙሉ እድገት እንዲኖረን፥ በሌሎች ልንታገዝ ይገባል። በተገቢው ጊዜ አስፈላጊውን እገዛ ካገኘን ጊዜውን ጠብቆ በራሳችን እንቆማለን። እድገት ደስ ያሰኛል፤ በአንፃሩ አለማደግ ያሳዝናል። በራስ መቆም ወይም ራስን መቻል ግን የእድገት መጨረሻ አይደለም። ከሌሎች ራስን ከቻሉ ሰዎች ጋር በሚያስፈልገው ሁሉ ስንተጋገዝ ወደ ላቀ እድገት እንደርሳለን። ወደ ልቀት የምንደርሰው እኛ በጎደልንበት ነገር ከሌሎች እገዛ ለማግኘት የምንሻና የተዘጋጀን ከሆነ ብቻ ነው።
ሰው በራሱ በጣም ውስን ነው። ሌሎች ያስፈልጉታል። የሌሎችን እገዛ ለመቀበል የማይፈልጉ ሰዎች በብዙ ነገር ይገደባሉ። ሊደርሱበት ወደሚገባቸው ከፍታ በተገቢው ጊዜ መድረስ አይችሉም። ዐይን የቱንም ያህል ጠቃሚ ቢሆን ያው ዐይን ብቻ እንጂ ጆሮ መሆን አይችልም፤ የአፍንጫንም ተግባር ሊወ-ጣ አይችልም። ዐይን ቆሻሻ ገብቶበት ቢያሳክከው ራሱን በራሱ ማከክ አይችልም። የግድ ጣት ያስፈልገዋል። ውስን ነው ማለት ነው። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደ ዐይን እንቆጠር ይሆናል። ያ ማለት ግን የሌሎች ብልቶችን ተግባር ማከናወን እንችላለን ማለት አይደለም። እናስተውል! ዐይን በመሆናችን የሌሎችን ብልቶች ተግባር እንዳንንቅ! ዐይን ከመሆን ውጪ የሌላ የየትኛውንም ብልት ሥራ መሥራት አንችልም። በመሆኑም ለሌሎች በቤተክርስቲያን ውስጥ ላሉ ቅዱሳንና አገልግሎታቸው አክብሮትና ዋጋ ልንሰጥ ይገባል። በእነርሱም ልንገለገል ይገባል። ዐይን እግር መሆን አይችልም! አንድ ሥፍራ ለመድረስ እግርን መጠቀም ይኖርበታል። ስለዚህ ሁልጊዜ የሌሎችን እገዛ አስፈላጊነት ልንረዳ ይገባል።
ጌታ ሙሉ ሰው ወደ መሆን የሚያደርሰን የሌሎችን ፀጋ፥ እውቀትና ችሎታ ተጠቅሞ መሆኑን አንዘንጋ።በአገልግሎታቸው የተጠቀምንባቸውን ቅዱሳን እስኪ ላንዳፍታ እናስብ። ምን ያህል ጌታ በእነርሱ አገልግሎት ተጠቅሞ እንዳሳደግንና እንደ ባረከን እናሰላስል። ስለ እነርሱ እግዚአብሔርን ልናመሰግን ይገባል። ጌታ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያከማቸን በሰጠን ፀጋ እርስ በርስ እንድንተናነጽና እንድንበረታታ ነው እንጂ እንድንፎካከር አይደለም። “ድፍረት የሌላቸውን አጽኑአቸው፤ ለደካሞች ትጉላቸው” (1ኛ ተሰ.5፡14) ሲል ቃሉ የአንዳችን ብርታት የሌሎችን ድካም መደገፍ እንዳለበት ያሳስበናል።
ብርታት ከተሰማን ለደከመው ልንጸልይለት እንጂ ልንፈርድበት አይገባም። የወንድሞቻችንን እና የእህቶቻችንን ጉድለት ልንሞላ ጌታ እንዳበረታን ልንገነዘብ ይገባል። አንዳችን በሌላችን ተረድተን ወደ ሙላቱ ልክ እንድንደርስ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። ይህ ከገባን እርስ በርስ እየተመካካን አንታበይም። ይልቁንም ባልንጀራችን ከእኛ እንደሚሻል በትሕትና በመቁጠር ለመማማር የተዘጋጀ ልብ ይዘን እንቀርባለን እንጂ። ለሌሎች ሥጦታና ችሎታም ተገቢውን ዋጋ በመሥጠት በእነርሱ ለመገልገል ቅቡል ልብ ይዘን እንቀርባለን። ይህ ሲሆን እድገታችን በአንድ ሥፍራ አይገታም። ልቀን እንሄዳለን።
ሰዎች የተለያዩ መሆናቸውን መቀበል
እኛ ሰዎች እንደ ባቄላ አንድ ዓይነት አይደለንም። የተለያየ ሥጦታ፥ ችሎታ፥ ፍላጎት ወዘተ ያለን ነን። “እንደ እኔ መሆን አለብህ፤ እንደ እኔ ማሰብ አለብህ፤ እይታህ ሁሉ እንደ እኔ ዓይነት መሆን አለበት” የሚሉ አስተሳሰቦች ልዩነትን ካለመቀበል የሚመጡ ናቸው። “ባልና ሚስት ከአንድ ወንዝ ይቀዳሉ” የሚል ብሂል አለ። ይህ ከእውነት የራቀ አባባል ነው። ባልና ሚስት በጣም የተለያዩ ናቸው። እስኪ እናስብ። የባልየው ወላጆች፥ ባልየው ያደገበት አካባቢው ተጽዕኖ ማለትም ያደገበት ሰፈር፥ ጓደኞቹ የፈጠሩበት ተፅዕኖ (በጎም መጥፎም)፥ ትምህርት ቤቱ፥ ገጠመኞቹ ወዘተ በአብዛኛው ከባለቤቱ የተለየ ነው የሚሆነው፤ የሷም እንደዚያው። እንዴት ታዲያ ባልና ሚስት አንድ ዓይነት ሊሆኑ ይችላሉ? መለያየታቸው ግን እንደ ሳንካ ወይም ጎጂ ነገር ሊታይ አይገባውም። ባል ሚስትን፥ “እንደ እኔ ማሰብ አለብሽ፤ ሁሉ ነገርሽ እኔን መምሰል አለበት” ወይም ሚስት ባልን፥ “እንደ እኔ መሆን አለብህ፤ እንደ እኔ ካልሆንክ ሞቼ እገኛለው” የምትል ከሆነ፥ ያ ቤት የምድር ሲኦል ነው የሚሆነው። ይህ ልዩነትን ካለመቀበል የሚከሰት ነው። ሰው ከእኛ የተለየ ሲሆን “ጉድ!” ልንል አይገባም።
በልጆቻችን መካከል እንኳን የጎላ ልዩነት እንዳለ ማወቅና መገንዘብ ሙሉ ሰብዕና ያላቸው ልጆችን ለማሳደግ እጅግ ጠቃሚ ነው። “እንደ እገሌ መሆን አለብህ፤ እሱ ጎበዝ ነው፤ አንተ ግን ሰነፍ ነህ፤ አንተ ቀልቃላ ነህ፤ እርሱ ግን አርፎ ቁጭ ይላል” እያልን ልጆቻችንን ማነፃፀር በጣም ጉዳት አለው።የልጆቻችንን የተለያዩ ተሰጥዎች ለማየት ዐይናችንን መክፈት ሲገባን “እንደ እገሌ ሁን” በሚል አመለካከት ተሸብበን የልጆቻችንን የተለየ ማንነት ሳናውቅ አድገው ከቤት ይወጣሉ። የአንዱን ልጅ ማንነት ወይም ስብዕና በአንዱ ውስጥ ለመጨፍለቅ የምናደርገው አካሄድ ልጆቻችንን ከመጥቀም ይልቅ እየጎዳቸው ሄዶ በመጨረሻም በራሳቸው የማይተማመኑና በእኛም ላይ የሚያዝኑ ይሆናሉ። ይመረሩብናል፤ይወቅሱናል። የ 40 እና የ50 ዓመት ጎልማሶች ሆነው እንኳን በወላጆቻቸው ላይ ምርር የሚሉ ሰዎች ገጥመውኛል።
ይህንን ትምህርት አንዴ በዝዋይ ከተማ በምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አስተምሬ እንደ ጨረስኩ አንድ በዕድሜ ጠና ያሉ ሰው ሰላም ካሉኝ በኋላ ከዚህ የሚከተለውን በፀፀት አወጉኝ፥ “ባለቤቴን ለብዙ ዓመታት እንደ በደልኳት ዛሬ ገባኝ። እንደ እኔ መሆን አለብሽ እያልኩ በጣም ስጫናት ነው የኖርኩት፤እንዳሰቃየኋት ዛሬ ገባኝ። በጣም ነው የተሠማኝ።” እኚህ ሰው ልዩነት ወንጀል አለመሆኑን መገንዘባቸውና ባለቤታቸውንም መበደላቸውን ማወቃቸው መልካም ነው። መቼም ባለቤታቸውን ከዚያ በኋላ እንደ ቀድሞ እንደማይበድሏቸው ተስፋ አደርጋለሁ። በሌላ ጊዜ ደግሞ አዲስ አበባ በምትገኝ በአንዲት የመካነ ኢየሱስ አጥቢያ ቤተ ክርሰቲያን ውስጥ ላሉ ወገኖች በተዘጋጀ የትምህርት ጊዜ ይህንኑ አሳብ ካስተማርኩ በኋላ፥ አንድ ወንድም ከዚህ የሚከተለውን አጫወተኝ፥ “ዛሬ ወደዚህ ትምህርት ሥፍራ ከመምጣቴ በፊት ልጄን ገረፍኩት። ቅልቅል የሚል ልጅ ስለ ሆነ ከእህቱ በጣም ይለያል። ለምን እንደ እሷ አትሆንም። አንተ እርሳስህን ሁልጊዜ ትጥላለህ በማለት መታሁት። ለካ ልጆች የተለያዩ ናቸው። ልጄን በመምታቴ በጣም ፀፅቶኛል። ልጆቻችን ለካ የተለያዩ ናቸው! ከተፈጥሮው ውጪ እንዲሆን እያስገደድኩት መሆኑን ተረዳሁ።”
አንድ ጊዜ ባንድ በሙዚቃ መሣሪያ ብቻ በሚቀርብ ኮንሰርት ላይ ለመገኘት ሰዎች የመግቢያ ትኬታቸውን ገዝተው ወደ ሙዚቃ ማሳያው ሥፍራ ገቡ። ሙዚቀኞችም መድረኩ ላይ ሥፍራቸውን በመያዝ የሙዚቃ ዝግጅታቸውን ማቅረብ ጀመሩ። ሙዚቃውን የሚመራው ሰው ግን ሙዚቃው አልጥም ይለዋል። እስኪ እንደገና ጀምሩ ብሎ ያስጀምራል። አሁንም አንድ ነገር እንደ ጎደለው ይሰማዋል። ከዚያ ተመልካቾቹን ይቅርታ በመጠየቅ የመድረኩን መጋረጃ ይዘጉና የተፈጠረውን ችግር ለማወቅ የሙዚቃው መሪ ሁሉንም የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾች መቃኘት ይጀምራል። ከዚያ አንድ ነገር ያስተውላል። ልምምዱን ካደረጉት ተጫዋችች ውስጥ አንዱ ሰው ጎድሎ ነበር። ወዴት እንደ ሄደ ሌሎቹን ተጫዋቾች ይጠይቃል። ሁሉም አብሯቸው እንደ ነበረና ሲሄድ እንዳላዩት በመገረም ይመልሳሉ። ከዚያም የሙዚቃው መሪ ወደ ተመልካቾቹ በመመለስ ከአቅም በላይ የሆነ የቴክኒክ ችግር እንደ ገጠማቸው በመግለጽ ከፍ ያለ ይቅርታ ጠይቆ በሌላ ጊዜ ሳይከፍሉ ዝግጅቱን እንደሚያቀርቡላቸው በማሳወቅ ዝግጅቱ እንዲቋረጥ ያደርጋል። ከዚያ ያን ሰው አግኝተው ለምን እንደ ቀረ ሲጠይቁት:- “እኔ የምጫወተው የሙዚቃ መሣሪያ እንደ እናንተ ትልቅ ስላልሆነ እዚያ ዝግጅት ላይ እኔ ተጫወትኩ አልተጫወትኩ ምንም የማመጣው ለውጥ አይኖርም? ብዬ ነው ሳልነግራችው የቀረሁት” በማለት መለሰ። ከዚያ ጓደኞቹ በሱ መቅረት ምክንያት ዝግጅቱ ተሠርዞ ወደ ሌላ ቀን እንደ ተሸጋገረ ሲነግሩት በጣም ተገረመ። እኔ እጠቅማለሁ ማለት ነው? እስከ ዛሬ ማንም እንደምጠቅም የነገረኝ የለም። ትንሿ የሙዚቃ መሣሪያዬ በናንተ ትላልቅ መሳሪያዎች የምትሸፈን ስለ መሠልኝ ተገኘሁ አልተገኘሁ የማመጣው ለውጥ አይኖርም ብዬ ነው ሳልናገር ሹልክ ብዬ የወጣሁት” አላቸው። ከዚህ ምሳሌ የምንማረው ምንድነው? ሁሉም ሰው የተለያየ ስጦታ እንዳለውና ጠቃሚ እንደ ሆነ መገንዘብ አለብን።ጠቃሚነታቸውንም ልንነግራቸው ይገባል። ልዩነቶችን እንቀበልና እናክብር። ማናችንም ማንንም አንተካም። ዐይን እግርን አይተካም። እጅ ምላስን አይተካም። ሁላቸውም የየራሳቸው ጥቅምና ተግባር ነው ያላቸው። ሁላቸውም ለርስ በርሳቸው ያስፈልጋሉ።
በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተለያዩ የአገልግሎት ክፍሎች ውስጥ ስናገለግል የተለያዩ አሳቦች እንዲንሸራሸሩ መፍቀድ አለብን። የእኔ ብቻ አሳብ ይሁን ማለት አምባገነንነት ነው። አንድ ሰው የእኔ አሳብ ብቻ ይሁን ካለ ታዲያ ኮሚቴ መሰብሰብ ለምን አስፈለገ? ያ ሰው ብቻውን ኮሚቴ ይሁና! የኮሚቴ ወይም በቡድን የመሥራት ትልቁ መርህ በአሳብ ብዝሃነት ውስጥ ሁላችንም ተጠቃሚ የምንሆንበት የደረጀና የጎለመሠ አሳብ ይዞ ለመውጣት ነው። ስለዚህ ሁልጊዜ የተለያየ አሳቦች እንዲንሸራሸሩ በመፍቀድ የተሻለ ነገር ይዘን ልንወጣ ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፥ “መልካም ምክር ከሌለ ዘንድ ሕዝብ ይወድቃል፤ በመካሮች ብዛት ግን ደኅንነት ይሆናል” (ምሳሌ 11፡14)።
የመፍትሔ ሰዎች ልንሆን ይገባል
እግዚአብሔር የመፍትሔ አምላክ ነው። እኛም እንደ አምላካችን የመፍትሔው አካል ነው መሆን ያለብን። የሰው ልጅ በኃጢአት በወደቀ ጊዜ እርቃኑን ለመሸፈን ቅጠል ሲያገለድም፥ ጌታ ቆዳ አለበሰው። ቅጠሉ ዘለቄታ የሌለው ቶሎ የሚበጫጨቅ ነበር። ሰይጣን ካሳተው በኋላ ጥሎት ነው የሄደው። ጌታ ነው የወደቀበት ድረስ መጥቶ እርቃኑን የሸፈነለት። “ኢየሱስ የአለም ብርሃን ናችሁ፤ የምድር ጨው ናችሁ” ሲለን ለጨለመባት አለም ብርሃን እነድፈነጥቅላትና ለመረረው ሕይወቷ ጣዕም እንድንሰጥ ነው። በሌላ አባባል መፍትሔ እንድንሆንላት ነው።
ኢየሱስ በኃጢአት ለወደቀች አለም መድሐኒት (መፍትሔ) ለመሆን ነው የመጣው። ክርስቲያኖች ላለንበት አካባቢ የመፍትሔ ሰዎች ልንሆን ይገባል እንጂ ችግር ፈጣሪ መሆን የለብንም። አስታራቂዎች እንጂ አጣዮች ልንሆን አይገባም። ታራቂ እንጂ ነገረኛ መሆን የለብንም። የሚያንጸውን እንጂ የሚያፈርሰውን መናገር የለብንም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፥ “ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ” (ኤፌሶን 4፡29)።
ጥሩ አድማጭ ልንሆን ይገባል
ሰዎች መደመጥ ይሻሉ። ስናዳምጥ ሰዎች ለማለት የሚፈልጉትን ለመረዳት በማሰብ መሆን አለበት።በአብዛኛው በሁለት ሰዎች መካከል የአሳብ ልዩነት ሲኖርና ሲነጋገሩ አንደኛው ወገን ሌላኛውን ከመስማት ይልቅ ምን እንደሚመልስ ነው የሚያስበው። ለሦሰት ሰዓት ከተነጋገሩ በኋላ እንኳን ላይደማመጡ ይችላሉ። ማዳመጥ ማለት አለመናገር ብቻ ማለት አይደለም። ሌላው ሲናገር ሊል የፈለገውን መረዳት ማለት ነው። ከተናጋሪው አሳብ ጋር የማንስማማ እንኳ ቢሆን፣ ለማለት የፈለገውን መረዳት ማዳመጥ ይባላል፤ ያን የምናደርግ ከሆነ እያዳመጥን ነው ማለት ነው። አንዳንድ ሰዎች ብዙ ብሶት አለባቸው። “ያድማጭ ያለ” የሚል ጩኸት ውስጣቸው ያሰማል። ዝም ብለን በጥሞና ብናዳምጣቸው እረፍት ሊያገኙ ይችላሉ። ችግራቸውን መፍታት ባንችል እንኳን ስላደመጥናቸው ብቻ “እፎይ” ይላሉ። ታፍነው ነበር፤ ይተነፍሳሉ።
ስዎችን ጊዜ ወስደን የምናደምጣቸው ከሆነ፥ እነሱም እኛን ለመስማት ፈቃደኛ ይሆናሉ። እኛ ብቻ እንናገር የምንል ከሆነ ግን የሰሙን ቢመስለንም እንኳን አያዳምጡንም። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ፥ ለቁጣም የዘገየ ይሁን” በማለት ያዝዘናል (ያዕቆብ 1፡19)። ከአንድ ሰው ጋር በአንድ አሳብ ካልተስማማን፥ አሳቡን እንድናገኝለት አስተውለን እንስማው። ምንድነው ያበሳጨው? ለምን እንዲህ ሊሆን ቻለ? ብለን በመጠየቅ የችግሩን ምክንያት ነቅሰን ለማውጣት እንሞክር። ያን የምናደርግ ከሆነ እያዳመጥን ነው ማለት ነው።
ስህተታችንን ማመንና ይቅርታ መጠየቅ
ስህተት ስንሠራ ስህተታችንን ማመንና ይቅርታ መጠየቅ አለብን። ሰዎች የሚያበሳጫቸው መሳሳታችን ብቻ ሳይሆን፥ ስህተታችንን አለማመናችንን ነው። “ደግሞ ድርቅናው” ይላሉ፤ መሳሳቱ ሳያንሰው ማለታቸው ነው። አዳም በተሳሳተ ጊዜ ስህተቱን ከማመን ይልቅ ምክንያት ሠጠ፤ ሔዋንም እንደዚያው። ሆኖም ግን ከተጠያቂነት ሊያመልጡ አልቻሉም። ለስህተታቸው ኃላፊነት አልወሰዱም። “ይቅርታ፥ አጥፍቻለው” ስንል ጭቅጭቁ ሁሉ ይቆማል።
ስህተት አድራጊውን ከስህተቱ ለይተን እንናገር
አንድ ሰው ስህተት ሲሰራ ስህተቱን ከሰውዬው ለይተን ማየት ይገባል። “አንተ የማትረባ ሰው ነህ” ማለትና “የማይረባ ነገር ነው ያደረግከው” ማለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። “ውሸታም ነህ” ማለትና “ውሸት ተናገርክ” ማለት በጣም ይለያያል። በተለይ በምንበሳጭበት ጊዜ ቃላቶችን ለመምረጥ ስለምንቸገር ሰውን ልናስቀይም እንችላለን። ስሜታችን እስኪበርድ ድረስ ባንናገር ይመረጣል። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ራሳችንን ስናገኘው በውስጣችን “ጌታ ሆይ! እርዳኝ” ብሎ መጸለዩ ጥሩ ነው። ስንጸልይ እንሰክናለን፤ ቃላት መርጠን መናገር በምንችልበት የስሜት ሁኔታ ውስጥ እንድንገኝ ይረዳናል። በተበሳጨን ጊዜ የተበሳጨንበትን ሰው ባናገኘው ይመረጣል። በቁጣ ስሜት ውስጥ ሆነን የተበሳጨንበትን ሰው ካገኘነው ግን ራሳችንን እንድንገዛ በውስጣችን የተማጽኖ ጸሎት ወደ ጌታ ማድረጉ ጥሩ ነው። ጌታ ይረዳናል።
የመጨረሻው ክፍል ይከተላል
ኅብር ሕይወቴ | የማርያም ታላቅ አእምሮ | ከየት ተገኘሽ ሳልል | ቋንቋን በቋንቋ | ስደተኛውና አምላኩ | ሞት እና ፕሮፌሰር | መንበርና እርካብ | Land of the Shy, Home of the Brave | የማለዳ ድባብ እሳት ነው በእሳት ነው