በ መ ዝ ሙ ር  ብ ቻ  የ ም ና ው ቀ ው  ደ ረ ጀ  ከ በ ደ

derejerev

ወንድማችን ዘማሪ ደረጀ ከበደ በፖለቲካና በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ አስተያየቱን መሠንዘር ከጀመረ ዓመት ሆኖታል። የፌስቡክ ታዳሚዎቹ፣ "ይኸ እርሱ አይደለም፣ በስሙ የሚነግዱ ግለሰቦች ናቸው" ወይም "ደረጀ እዚህ ዓይነት ውስጥ ባይጠላለፍ መልካም ነው" ወይም “ዶ/ር እንኳን የፌስቡክ ገጽህ ጓደኞች ልንሆን መድረክ ላይ ቆመህ ስታገለግል እንኳን ለማየት” ያልታደልን ነን እያሉ ነው። "እኔ ደረጀ ነኝ" ቢላቸውም፣ "በቪዲዮ ፊትህን አሳየንና፣ ድምጽህን አሰማንና እንጂ አናምንም" ብለዋል። ይኸ ሁሉ የሚያሳየው፣ ደረጀ ዓመታት ነጒደው እንኳ በሕዝብ ዘንድ ያሳደረው ፍቅር አለመደብዘዙን ነው። የእግዚአብሔር ጸጋ እውነትም አያረጅም፣ አያስረጅም!

ደረጀ ከጅምሩ፣ “ፖስት የማደርጋቸው አስተያየቶችና ፅሁፎች የማይመቻችሁ ወገኖች ሰላማችሁ እንዳይደፈርስ በፍቅር ራሳችሁን ከገፁ ማግለል ትችላላችሁ” ብሏቸዋል። አባባሉ ግን ጥያቄ ያስነሳል። ለምሳሌ፣ መብትን በፍቅር ስለ መያዝ ምን ይነግረናል? መብት ዕንቅፋት ሲሆንስ? (1ኛ ቆሮንቶስ 8፡9) በቀደመው ጥሪ ጸንቶ ማገልገል እንዴት ይቻላል? (1ኛ ቆሮንቶስ 12ራእይ 2፡4፣5) ከስደት ዘመን ይልቅ በ “ሰላምና ነጻነት” ዘመን እነዚህን ጥያቄዎች መጠየቅ ግድ ነው።

ደረጀ ፈር ቀዳጅ ነው፤ ዓይነተኛ ነው። ይህን በተለየ መንገድ የተረዳሁት ያሳተማቸውን ዘጠኝ አልበሞች በቅደም ተከተል ደርድሬ ለሰዓታት ባዳመጥኩ ጊዜ ነው። ረጅም “የክርስቲያን ጒዞ” እንደ መጓዝ ነው። ከርቀት ኮረብታን እንደ ማየት፣ አልፎ ወደ ኋላ መመልከት። ለምለም ሣር፣ ወንዝ፣ ቀጥሎ ምድረበዳ። ደስታ፣ ግራ መጋባት፤ የጠራ ሰማይ፣ የፀሐይ ሐሩር፣ ዶፍ፣ ነፋስ፣ ጠመዝማዛ፣ ጨለማ ሌት፣ አቀበት ቊልቊለት፣ ወዘተ። ብቻ የተዓምር ጒዞ፣ መንገድ ላይ ያላስቀረ ጒዞ። ወንጌል የምንለው እኮ ያንኑ አንድ መልእክት መላልሰን መስማቱና ማሰማቱን ነው። ኢየሱስ ስለ ኃጢአት ሞተ፣ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተነሳ፤ የኃጢአት ስርየትና ይቅርታ በእርሱ በማመን ብቻ ይገኛል፤ ተመልሶ ይመጣል፤ የሰሙ ላልሰሙ የምሕረት አዋጅ ያሰሙ። ይኸው ነው! (የሐዋርያት ሥራ 2፡16-42)

ለደረጀ የተሰጠችው የፈጠራ ችሎታ ረቂቅ ነች። ጌታ ካስነሳቸው መሓል መሆኑ አጠያያቂ ሆኖ አያውቅም። ያልተለመዱ አቀራረቦቹ እርግጥ ትችት አስነስተውበት ያውቃሉ፤ ኋላ ግን በብዙ ተወዳጅነትና ተደማጭነትን አትርፈውለታል። ይኸ የፈር ቀዳጆች አንድ መለያቸው ነው፤ ፈር ቀዳጆች የሰው ፊት እያዩ አይጓዙም፤ በተያዘው ብቻ አይረኩም፣ ይልቅ ወዳልተዳሰሱ ክፍሎች ይሸጋገራሉ፤ ለትርፍና ለሙገሳ ነፍሳቸውንና ጸጋቸውን አይሸቃቅጡም። መንፈስ እንደ መራቸው እንደ ለገሣቸው ጥበብ ይራመዳሉ፣ ካስፈለገ ጦም ያድራሉ። ነቀፌታ ሲነሳባቸው ጸጋ ይቀበላሉ፣ በዚያ ጸጋ ሌላ የጥበብ ሥራ ይፈጥራሉ። አንዳንዴም ለአያያዝ ያስቸግራሉ!

ደረጀ፣ ቅዱስ ዝማሬን በክራር ዘምሮአል፣ በሬጌ፣ በያሬድ ስልት፣ በሳክስፎን፣ በኦርጋን፣ በኪቦርድ፣ የቀደሙ ዝማሬዎችን በአዲስ መልክ ሪሚክስ አድርጓቸዋል። መዝሙሩ ያስደንሳል ተብሎ ተተችቷል (የዛሬውን አላየን)፤ ለቊጥር ሦስት አልበም ኦርጋን የተጫወተለት ዓለማዊ ነው ተብሎ ተተችቷል፤ ወዘተ። በዘመናዊ መሳሪያ ስልት “የሱስ ነጃላታ” “ሁምናኮቲን ሚቲ አፉራሳቲኒ” “ዝንጀሮ አይደለሁም” (በደርግ ዘመን የዳርዊንን ቀዳማይ ዝንጀሮ ትምህርት ለመቃወም)፤ “ሞኝ ነው አልተማረም አሉኝ” (ወንጌል ማመን መኃይምነት ነው ሲሉ ለነበሩ ምላሽ)፤ “የመሠረት ድንጋይ የቃል ኪዳን መሥራች፣ አማኑኤል” (በህወሓት ዘመን የተራባውን ግብረ ሰዶም ለመቃወም)፤ “የሰው አስታማሚ ውሱን ነው ስልቹ” (ጠያቂ ላጡ በህመም ለሚማቅቁ)፣ ወዘተ። በሌላ አነጋገር፣ ደረጀ ተጽእኖ ያልፈጠረበትን ዘመናዊ ዝማሬና ስልት ማሰብ ቀላል አይሆንም። ልዩነቱ፣ ደረጀ እንደ ዛሬዎቹ ብዙዎች ሳይሆን በቅኔ ውበቱ፣ በቅላጼው፣ በርክርኩና በቅንብሩ፣ ከሁሉም ይልቅ ደግሞ በጸጋው ጥራት የደረጀ መሆኑ ነው። ከአርባ አምስት ዓመት በኋላ የዝማሬዎቹ ኃይል አለመንጠፍ ምሥጢሩ ይኸው ነው!

ደረጀ በጌታ ቤትና በስተውጭ ያሉትን ምስኪኖች እንዳንረሳ በዝማሬ ኅሊናችንን ሲቀሰቅስ ኖሯል። ቅዱስ ዝማሬ ግን ዞሮ ዞሮ እግዚአብሔር አብ፣ እግዚአብሔር ወልድ፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ፣ አንድ አምላክን ማስመለክ፣ ወደ እውቀቱ ሙላት ማድረስ ነው። አለዚያ “በመጠጥ ደስታ ይገኛል ብላችሁ፣ መጠን አትለፉ ትቃጠላላችሁ” ከሚል መልካም ምክር አይሻልም! ኢየሱስን ከማወደስ ውጭ ቅዱስ ዝማሬ ብሎ የለም!

* * * *

ደረጀ፣ አዲስ ምዕራፍ በፌስቡክ ገጽ ገልጦ እያስነበበን ነው። ፖለቲካ መቀላቀሉ፣ ዝማሬው ያስተሳሰረውን ያህል የሚበታትን እንዳይሆን በአንዳንዶች ዘንድ ሥጋት ፈጥሯል። ደረጀ ለዚህ የሰጠው ምላሽ፣ “የፌስቡክ ገፅ የከፈትኩት አዳዲስ ወቅታዊ መዝሙሮች ሳዘጋጅ ለማስተላለፍና በሃገራችን ፖሊቲካ ውስጥ ደግሞ ያለኝን ነቀፌታም ሆነ ድጋፍ እንዲሁም አስተያየት ለማስቀመጫ እንዲሆነኝ ነው። ይህንን ውሳኔ ለማድረግ ዘመናት ወስደውብኛል። ስለዚህ እናንት ወገኖቼ በመዝሙር ብቻ የምታውቁኝ ባለኝ ጠንካራ የፖሊቲካ አቁዋም ግር ያላችሁ እንዳላችሁ ተረድቼአለሁ። ያንንም በደንብ እረዳለሁ። ምንም እንኩዋ ሁላችንም ፕሮቴስታንቶች ብንሆንም የተለያየን ሰዎች ነን” የሚል ነው። (ሜይ 28/2020፤ የግርጌ ሠረዝ የኔ ነው)

በኢትዮፕያንቸርች ላይ እንዳስነበብነው፣ ወንጌላውያን ነፍሳትን ከገሃነመ እሳት ከመንጠቅ ውጭ በፖለቲካ፣ በኪነጥበብ እና በምሑራዊ ምርምርና አመራሮች ብዙም ሳንሳተፍ እንደ ኖርን፣ የሰማዩን ከምድሩ ነጣጥለን፣ ድንቊርናና ድህነትን ታቅፈን እንደ ኖርን፣ እንዲያውም ድህነት ለኃይማኖት ይጠቅማል ስንል ከርመን ዛሬ ወደ ብልጽግና ወንጌል ፈጥነን እንደ ተሸጋገርን፣ ጥለናት ለምንሄድ ዓለም ላንጨነቅ የነ ሃል ሊንድሴን የዘመን ፍጻሜ ቀመር ስንጠባበቅ፣ ነገረ መለኮት የሰይጣን ምግባር እንጂ የእግዚአብሔርን ቃል ለማወቅ ጠቀሜታው ሳይገባን እንደ ኖርን ገልጸናል። ይህን ስንል ሚዛናዊነትን አልጠበቀም ለማለት እንጂ ከዓለም ጋር አለመነካካታችንን በጅምላ ለመኮነን አይደለም። ካነሳን አይቀር፣ የያኔውን ክርስቲያናዊ ፍቅር፣ የጸሎት ትጋት፣ የጸጋውን ኃይል ሥራዎች፣ በዓለም ፊት የለየለት አቋምና ለጌታ ስም የነበረውን አክብሮት ስናስብ ሐዘን ይገባናል። በሁለት ትውልድ ያን ጸጋ ጥለን ሠልጥነን፣ በአልባሳት፣ በማእረግ አገልግል ጋጋታ፣ በሰሜን አሜሪካኖች ግርግር ተውጠን የቤተ መንግሥትን ደጅ ስንጠና ማየት ሌላ ሐዘን ይፈጥርብናል።

ታዲያ በደረጀ ፌስቡክ መጻጽፎች ላይ ምን ምልከታ ሊኖረን ይችላል? የምንሰማቸውን ግራ መጋባቶችስ እንዴት እንቃኛቸው? ለዚህ ምላሽ እንዲሆነን ከሜይ 2019 እስከ ሜይ 2020 ደረጀ በገጹ ላይ የለጠፋቸውን ጽሑፎች በሙሉ አውርደን ሳንጨምር ሳንቀንስ እንገመግማለን። ወንድማችን ግምገማውን ከማተማችን በፊት ምላሽ እንዲሰጥበት ልናገኘው በብዙ ሞክረን አልተሳካልንም። ለማንኛውም፣ የለጠፋቸውን አስተያየቶቹን ብዙዎች ስላነበቡት ሙከራችን አለመሳካቱ የሚያጎድለው ነገር የለም፤ ከንግዲህም ምላሹን ለመለጠፍ ፈቃደኞች ነን። ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን።

* * * *

የመጀመሪያው ጥያቄ ይህ ነው፦ የወንድማችን የደረጀ አስተያየት/ትንታኔ በታመነ መረጃ ተደግፏል ወይስ የግል አስተያየት ብቻ ነው? “የግል” አስተያየት መሆኑ ከተጠያቂነት ያድናል? አስተያየቱ ግምታዊና ግብታዊ ብቻ ከሆነስ ከሌሎች አስተያየት በምን ይለያል? ደረጀን ልንሰማው የምንገደደው በዘማሪነቱ ባካበተው ዝና ወይስ በምሑራዊ አመለካከቱም ጭምር? ወይስ በሁለቱም? ባጭሩ በምን ሥልጣን ነው የሚለንን የሚለን? ለምሳሌ፣ ዶ/ር ወዳጀነህ መሃረነ በተለያዩ መድረኮች ደጋግም በህክምና ሳይንስ፣ በሳይኮሎጂና በነገረ መለኮት የምስክር ወረቀቶችና ልምዶችን እንዳካበተ ነግሮናል። ወንድማችን ደረጀም ጥያቄአችንን ቀድሞ ያሰበበት ይመስላል። ሥልጠናዎቹ በምንና ለምን ያህል ጊዜ እንደሆኑ ባያስታውቀንም፣ ከፌስቡኩ መነሻ ገጽ ላይ ሥልጠና የተቀበለባቸውን ተቋማት፣ አንድሩስ ዩኒቨርሲቲ፣ ኖቫ ሳውዝኢስተርን ዩኒቨርሲቲ፣ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሳውዝ ዳኮታ፣ ሉተር ሴሚነሪ ሲል አስቀምጦልናል። እንግዲያስ ብዙ ከተሰጠው ብዙ ይፈለግበታል እንበል? (ሉቃስ 12፡48)

ትምህርትና ሥልጠና አይጠቅምም ማለት አይምሰልብንና፣ የዘመኑ ዲፕሎማና ዲግሪ ነገር ሲታሰብ አንድ ዋነኛ ጥያቄ ያጭራል፦ ለክርስቶስ ተከታይ የሥልጣን ምንጭ ከየት ነው? ያስ ሥልጣን እንዴትና በምን አኳኋን ይገለጻል? አንድ ባለሥልጣን የሚናገረውን አበክሮ ማወቅ፣ በጥንቃቄና ግልጽ በሆነ መልኩ ማስረዳት መቻል እና ከተከለለት አለማለፍ ይጠበቅበታል። በዚህ ጒዳይ ኢየሱስና ተከታዮቹ ያስተማሩትን መከለስ የሚጠቁመን ነገር አለው። ሊቃናት ፈሪሳውያን ኢየሱስን ጠየቁት፦ “እነዚህን በምን ሥልጣን ታደርጋለህ? ወይስ እነዚህን ለማድረግ ይህን ሥልጣን ማን ሰጠህ? አሉት።” (ማርቆስ 11:28-33) እኛ ሳንፈቅድ፤ ከታወቁ ተቋማትና ምሑራን እጅ ምስክር ወረቀት ሳይኖርህ ለምን ታስተምራለህ ነው ነገሩ። “ኢየሱስም ይህን ነገር በጨረሰ ጊዜ ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ፤ እንደ ጻፎቻቸው ሳይሆን እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበርና።” (ማቴዎስ 7፡28፣29)

“ኢየሱስም። እኔም አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፥ እናንተም መልሱልኝ፥ እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ። የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበረችን ወይስ ከሰው? መልሱልኝ አላቸው። እርስ በርሳቸውም ሲነጋገሩ። ከሰማይ ነው ብንል። እንግዲያውስ ስለ ምን አላመናችሁበትም? ይለናል፤ ነገር ግን። ከሰው ነው እንበልን? አሉ፤ ሁሉ ዮሐንስን በእውነት እንደ ነቢይ ያዩት ነበርና ሕዝቡን ፈሩ። ለኢየሱስም መልሰው። አናውቅም አሉት ኢየሱስም። እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም አላቸው።”

የኢየሱስ ሥልጣን ከላይ ነው! ሁሉን የሚገዛ ሥልጣን ነው! ይህን እውነት ለመቀበል ስላልፈቀዱ ምድራውያን ብቻ ሆነው እንደ ቀሩ እንመለከታለን። ምልልሱ ሌላም ቊምነገር ቋጥሯል፦ እውነት የምትገለጠው ለቅኖችና ለትሑቶች ነው። ትሑታንና ቅኖች፣ መስዋእት ለመክፈል የተዘጋጁ ብቻ የጌታ ሥልጣን መተላለፊያ ናቸው! ለኢየሱስ ያልተገዛ ሥልጣን ዓላማውን የሳተ ሥልጣን ነው። በአሁኑ ወቅት በወንጌላውያን መሓል ተናግሮ የሚደመጥ መሪ የጠፋው ለዚህ ነው!

ይህን ያስተዋለ ጳውሎስ፣ በስመ ጥር መምህር ገማልያል እጅ የሠለጠነ፣ በዘመኑ ከነበሩ ከሮም ታላላቆች ከነ ሴኔካና ሲሰሮ ተርታ የሚደመር ጳውሎስ፣ ቢያስፈልግ ትውልዱን መቍጠር የሚችል ግን የናቀ ጳውሎስ፣ “በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቈጥራለሁ … ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ፥ … በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ … ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበር፤” ይለናል (ፊልጵ 3:4-14፤1ኛ ቆሮ 2:2)

ሁለተኛው ጥያቄ፣ “አዕማድ መስለው የሚታዩትን” (ገላትያ 2፡9) እና ብሩህ አእምሮ የተለገሳቸውን እንዴት እንያዛቸው የሚል ነው? በመጀመሪያ በአክብሮትና በፍቅር ነው። በረከቶቻችንና መሪዎቻችን ስለሆኑ። ያ ማለት ንግግራቸውን ሳንፈትሽ እናስተጋባ ማለት አይደለም። የሰውን፣ የዓለምን፣ የጨለማን መንፈስ እውቀት የሚሽር የሚመረምር ወደ እውነት ሁሉ የሚመራ መንፈስ ቅዱስ ውስጣችን አለን። ደግሞ፣ እንዳይስቱ በጸሎትና በምክር ልንጠብቃቸው ይገባል። ቢወድቁ ውድቀታችን ነው፤ ቢከብሩ ክብራችን፤ ይልቊን ክብሩ ሁሉን ገዥ ለሆነው ለጌታችን ነው!

የወንድማችን ደረጀን ፌስቡክ ገጽ አከታትሎ ላነበበ አንዳንዱ ክፍል በታላቅ ቊጣ (ጥላቻ ላለማለት) እንደ ተጻፈ ያስታውቃል። እርግጥ አልፎ አልፎ ለጸሎት የሚጋብዙ መደምደሚያዎችም ታክለዋል። ለመሆኑ ቊጣ/ጥላቻና ጸሎት አብሮ ይሄዳል? ቊጣው ያነጣጠረው በጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ላይ ነው። “አቢይ” 54 ጊዜ ተጠቅሷል፤ ሲጠቅስ ባብዛኛው፣ ዐቢይ አማራ ላይ በደል አድርሰዋል፤ ለኦሮሞ አድልተዋል ብሎ ነው፤ “አማራ” 81 ጊዜ ተጠቅሷል። ከአሉባልታ ባለፈ ግን መረጃ የለም። “ኢትዮጵያ” 54 ጊዜ ተጠቅሷል። እነዚህ አኃዞች በጸሐፊው እይታ የጎሉትን አሳቦች ይጠቊሙናል። ከዚህ የተነሳ በአንዳንዶች ዘንድ “አማራ፣ አማራ” ማለቱ ለምንድነው? የሚል ጥያቄ አጭሯል። ውሎ አድሮ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያስከትለውን ያልታሰበ አሉታዊ ተጽእኖ መገመት ይቻላል። (የኔ ቢጤና ደረጀ ሲናገር እኲል እንደመጣለን ማለት ራስን ማታለል ነው!) ደረጀም ይህንን ለመከላከል ይመስላል “ስትደግፉም ስትነቅፉም በምግባርና በተግባር ይሁን እንጅ በጎሳ፣ በቁዋንቁዋ ወይም በሃይማኖት አጋርነት አይሁን!” (ማስጠንቀቂያው የተጻፈው በዓመቱ፣ ሜይ 4/2020 ነው፤) በአንጻሩ፣ “ብሄርተኛና ለብሄሩ ተሙዋጋች አንድ አይደሉም” ብሎ (ማርች 16/2020) የጻፈው ሌላኛው ሙግቱ እንዳሰበው አሳማኝ አይደለም። ለዚህ ምክንያቶቹ፦ አንድ፣ የኢትዮጵያውያን አእምሮ ሲፈጠር በብሔርና በጎጥ የዳበረ በመሆኑ፣ (ህወሓት የነበረውን ቀሰቀሰ እንጂ አዲስ ነገር አላመጣም!)። ሁለት፣ ለገዛ ብሄር መሟገት በአምሳለ እግዚአብሔር የተፈጠረን ሁሉ ይገነዘባል ማለት ባለመሆኑ! ሰው ለተባለ መሟገት ይልቅ ሁሉን ይገነዘባል! ደረጀም ብሄሩን የጠቆመን ይመስላል፤ ያም ቢሆን፣ ከአገላለጽ ሊሆን ስለሚችል፣ ዘረኛ ነው ብለን ከመደምደማችን በፊት ጊዜ እንስጠው።

የብሔር ፖለቲካን ቀስቅሶ በፈለጉት ሰዓት ማዳፈን ቀላል አይሆንም። ታዳሚዎቹ ከሰጡት አስተያየት መሓል እንዲህ የሚሉ ይገኙበታል፤

  • “በዶ/ር ደረጄ ስም የምትነግድ ነፍጠኛ የኦሮሞ ጠላት!!! ነፍጠኛ ወራሪ ነፍጠኛ ነፍሰ በላ ነፍጠኛ ዉሸታም This is Amhara::” (ማርች 2/2020)
  • (ፌብርዌር 28/2020) ደግሞ፣ “የእውነት የዘማሪ ደረጀ ፔጅ ነው ምክንያቱም አልመስል አለኝ መንፈሳዊነት ጨርሶ የለውም ዘረኝነት የተንፀባረቀበት ፅሁፍ ነው”
  • “ዶ/ር ደረጀ በመጀመሪያ በዝማሬ አገልግሎትህ የግጥም፣ የዜማ፣እና ትንቢታዊ እና ጥልቅ መልእክቶችህ እና ቁጥብነት እና የቃላት ምርጫህ አድናቂ ነኝ። ባቀረብከው የፓለቲካ ትንታኔ ግን አልተስማማሁም።” (ፌብርዌሪ 28/2020)

የራሳቸው ጒዳይ ብሎ ማለፍ ይቻላል፣ ጸልዮ አቀራረብን ማቃናትም ይቻላል። ደረጀ ስለ አገሩ ብርቱ ስሜት እንዳለው የታወቀ ነው። “ከአድማስ ማዶ ያለች ምድሬ የማስባት፣ እትብቴ ስወለድ የተቀበረባት፣ በቊጣው በትር ተመትታ እያለቀሰች፣ ከአሳቤስ መች ተለየች፣ ከጭንቀቴስ መች ተለየች፣ ከጸሎቴስ መች ተለየች...” የምትል የማትረሳ ዝማሬ ዘምሯል!

ከላይ እንዳነሳነው፣ ለሠነዘራቸው አስተያየቶች በቂ መረጃ አቅርቧል? የምንሰማቸውን ያልተጨበጡ ወሬዎች፣ ያልጸኑትን የሚያስቱና የሚያባብሱ መረጃዎችን እንዳናስተጋባ መጠንቀቅ ይኖርብናል። ባሳትንበት አንደበት መልሰን ወንጌል ለማስተማር ተኣማኒነት ይነሳናልና! በአንጻሩ፣ በወቅቱ ጒዳዮች ላይ የሚሳተፍ፣ በትችት ብቻ ሳይወሰን ሀ/ የነገሮችን ታሪካዊና ወቅታዊ ዐውድ መረዳት ይኖርበታል፣ ለ/ ነቀፌታ ብቻ ሳይሆን አማራጭ መፍትሔዎችንም ማቅረብ፣ ሐ/ ተቃውሞ ቢነሳ ለመመከት መዘጋጀት ግድ ነው። መተቸት ቀላል ነው፣ ብዙዎችም ተለቅቀውበታል፤ የኢንዱስትሪ ጎጆ ቀልሰውበታል።

ደረጀ ምሑራንን በጽኑ ወርፎአቸዋል፤ በዚህም ራሱን ለውረፋ አጋልጧል! ህገ መንግሥትን፣ አገር አስተዳደርን፣ ፓርቲ አደረጃጀትን፣ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ የኢሕአዴግን አመሠራረት፣ የህወሓትን ክንውኖችን፣ ወዘተ በመተቸቱ። ወንድም ደረጀ ግምገማችንን በቅንነት ተመልክቶ መድረኩን እንዲያደራጅበት፣ መረጃ ከሳሳባቸው ድምዳሜዎቹ ጥቂቶቹን እንጠቅስና እንጨርሳለን፦

1/ ህገ መንግሥቱን በተመለከተ፤ እውነት “ህገመንግስቱን እንተርጉም ብለው በየመድረኩ ላይ የሚነዘንዙን የተገዙ ምሁራን ናቸው?” (ይልቅ ሕዝብ በመገናኛ ብዙሐን እየተከታተለ ህግ አዋቂዎችን ማነጋገር አስተማሪነቱ ጥሩ ጅማሬ ነው ማለት አይቀልም?) ህገ መንግሥቱ እውነት “ከአስር የማይበልጡ ሰዎች በምርቃና የፃፉት” ነው? “ኢትዮጵያን እወዳለሁ የሚል ህገ መንግሥቱን ይጥላ?” (ሜይ 24/2020) ሕዝብ ህገ መንግሥቱን ጠልቶት “ቆሻሻ ቅርጫት ውስጥ ከተጣለ” ሽብር እንጂ ምን ይጠበቃል? በነገራችን ላይ፣ ህገ መንግሥቱ እንዲህም እንኳ አናካሽ ሆኖ ለ "አናሳ" ብሔረሰቦች ያስገኘውን እውቅናና ተሳትፎ ችላ ልንል አንችልም፣ አይገባም!

2/ ኢሕአዴግ/ህወሓት የጎሳ ፖለቲካን በማስፋፋት ምንኛ አገር እንደ ጎዳ አገር አውቆ የጨረሰው ነው፤ እውነት ግን ኢሕአዴግ/ህወሓት “እስከ 5 ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጎቻችንን” ፈጅቷል? በየቀኑ 500 ዜጎችን ፈጀ ቢባል እንኳ በ25 ዓመት 4 ሚሊዮን ተኩል ብቻ ይሆናል! እውነት “የዘር ማጥፋት ወንጀል እየተፈፀመባቸው ያሉ አማራዎች በሺ ሳይሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው?” (ጁን 5/2020)

3/ እውነት ዶ/ ዐቢይ “አላማው ከእነመለስ ዜናዊ ሃሳብ ጋር ድርና ማግን ያህል የተሳሰረ ነው? ታላቂቱ ትግራይ እንዳሉ አሱም በመጨረሽ ታላቂቱ ኦሮምያ ነው ህልሙ?” “እንደመር እያለ፣ ኢትዮጵያ አትፈርስም እያለ፣ ህዝበኛ እየመሰለ፣ ሃገራችንን የሚበታትን ፈንጂ ላይ አስቀምጡዋት፣ እሱ ግን በሰከነና በተጠና አሰራር የቆመለትን አጀንዳ ቀስ በቀስ እየፈፀመና እያስፈፀመ ነው ያለው?” (ሜይ 24/2020)

የሚበታትን ፈንጂ ላይ አገሪቷን አስቀምጦ እርሱ ክንፍ አውጥቶ የአገሪቷን ትልቁን ስባሪ ይዞ ሊያመልጥ ነው ማለት ነው? እንዲያው ሲታሰብ ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ ህወሓት ከአበሮቹ ጋር ያመሳቀላትን አገር ዐቢይ በሦስት ዓመት ሁሉን ሽሮ አዲሲቱን ኢየሩሳሌምን እንዲመሠርት ነው የተጠበቀው?

4/ እውነት “ዶ/ር አቢይ ፣ ከንቲባ ታከለ ኡማ እና ኦቦ ለማ መገርሳ የሃገሪቱዋ ዋና አሽከርካሪዎች ሶስቱም የፕሮቴሥታንት እምነት ተከታዮች ወይም በእኛ ሃገር አጠራር ጴንጤቆስጤዎች ... የተረኝነት ፖሊቲካ ህልማቸው ደርሶ ወያኔ በ28 አመታት ውስጥ እንኩዋን ያልደረሰበትን የጭካኔ እርካብ እነሱ በሁለት አመታት መድረስ ብቻ ሳይሆን አልፈውት ሄደዋል? ጥድፊያ ላይ ናቸው?” (ሜይ 4/2020)

እውነት “የእነ ዶ/ር አቢይ ግሩፕ ነፍጠኛውን ሰብረናል በሚል ምናብ እየዋዠቁ ስላሉ በ 15ኛውና በ 16ኛው ክፍለ ዘመን እንዳደረጉት ህዝብን ከመኖሪያው እያፈናቀሉ ኦሮሞዎችን የማስፈር ዘመቻቸውን እያፋጠኑት ነው? ... (እውነት) ዛሬ የሚፈፅሙት ጭካኔዎች እግዚአብሄር የለም ባለው በኮሚኒስት ደርግም አልተፈፀሙም?”

የ15ኛውና የ16ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ የዛሬዋን ኢትዮጵያን ትመስል ነበር ማለት ነው?

5/ እውነት “ኢትዮጵያ ለብዙ ሺህ ዘመናት የታወቀችበትን የአራዊቱን ንጉስ አንበሳን ትቶ ፒኮክ የተባለችውን ጥላ ቢስ ወፍ ከፍ ባለ ስፍራ ያውም በቤተመንግስታችን ላይ ምን ቆርጦአቸው ሰቀሉብን? (እውነት) ... ጠ/ሚኒስትሩ ... ከግብረ ሰዶማውያን የተገባላቸው ኢኮኖሚያዊ ወይም ፖለቲካዊ ድጋፍ አለ? ወይስ የኢትዮጵያን እሴት የማጥፋትና በኦሮሙማ እሴት የመተካት አንዱ ዘመቻ ነው?” (ኤፕሪል 30/2020) ባጭሩ፣ ለናሙና ከላይ የጠቀስናቸው የተጋነኑ፣ ከእውነት የራቊ ናቸው።

አንበሳ ፈርሶ በፒኮክ ተተካ የሚለውን ወሬ በአብዛኛው ያስፋፋው ሳተናው መጽሔት ነው። ፒኮኳ “አንድነት ፓርክ” ሲታነጽ አንደኛው በር መግቢያ ላይ የተደረገች ነች እንጂ ሌሎች አንበሶች ተወግደው አይደለም። እርግጥ ነው ዶ/ር ዐቢይ በ እርካብና መንበር ላይ ስለ አንበሳ ያላቸውን የግላቸውን አስተያየት አስፍረዋል። ባጭሩ፣ ውዝግቡ የተጋነነ ነው። ፒኮክ በቻይና በሕንድ በእስራኤል (1ኛ ነገሥት 10፡22፤ 2ኛ ዜና 9፡22)፤ በጥንት ክርስቲያኖች ዘንድ የምትታወቀው በዘላለማዊነት ተምሳሌትነቷ ነው። በኢትዮጵያ ገዳማት፣ በብራና መጻሕፍትና በአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም ተጠቅሳ ትታወቃለች። ለትችት ካልሆነ በተቀር የአሜሪካ ሰሞነኛ ግብረሰዶማውያንን እማኝ መጥራት አግባብ አይደለም። መልካሙን የሚያጠለሹ ለምስክር አይበቁም! በተረፈ፣ ዶ/ር ዐቢይ፣ ከሰዶማውያን የገንዘብ ድጋፍ ተገባላቸው ማለት ተገቢ ያልሆነ ትችት ነው!

* * * *

ኢትዮፕያንቸርች፣ ስለ ዶ/ር ዐቢይ አስተዳደር፣ ህወሓት ገና ሥልጣን ላይ ከነበረበት ዘመን ጀምሮ በተለያዩ አገራዊዓለም አቀፋዊማህበራዊመንፈሳዊ ጒዳዮች ላይ ስንጽፍ አስራ አምስተኛ ዓመታችንን ይዘናል። ወንድማችን ደረጀ በዚህ መልኩ መሳተፉ ልክ ነው ልክ አይደለም ለማለት ኃላፊነቱ የርሱ እንጂ የኛ አይደለም። ሆኖም፣ የተጠራነው አንደኛችን ለሌላው “ጠባቂ” እንድንሆን ስለሆነ፣ አስተያየታችን እነሆ፦

ውድ ወንድም ደረጀ ከበደ፣ 1/ ጽሑፎችህ ከእውነቱ እንዳይንሸራተቱ ብዙ ጥናት እና ብዙ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብሃል። “በቀን እስከ 10 ሰአት ሰርቼ ስለምገባ ብዙ ትርፍ ጊዜ የለኝም” ብለሃል። ሁለት ወዶ አይሆንም። ከተበላሸ በኋላ ለማቃናት ከመሯሯጥ ቀድሞ ማሰብ፤ “በጨዋነትና በበሰለ መንገድ” የሰዎችን ክብር የማይነኩ አገላለጾችን መጠቀም ይበጃል (ሜይ 28/2020)፤ 2/ በጌታ መንግሥት ውስጥ ልንፈጽማቸው የተሰጡን ዋነኛ የጸጋ ሥራዎች ለእያንዳንዳችን አሉ። ጸጋ ልዩ ልዩ ነው፤ አገልግሎትም። ክርስቶስን ያመንን የቀደመውን ጥሪአችንን በጥንቃቄ ከመያዝ ውጭ አማራጭ የለንም። ዘመንህን ሙሉ በጌታ ያካበትከው ጸጋ እንዳይበተን፣ ማንነትህ እንዳይደበዝዝና እንዳያጠራጥር መጣር ማስተዋል ነው። ከሁለቱ ሲል ሁለቱን ማጣት አለ።  አንተም እንደምትረዳው ማሕበራዊ ሚድያ ከጠቀሜታው ባላነሰ አፍራሽ ምግባሮችን በፍጥነት በማራባት፣ ጫፍ ይዞ በመሮጥ ኃይሉ እንዳስፈራራን ነው! በማሕበራዊ ሚድያ ማንም የተለቀቀባቸውን ሥራዎችህን በባለቤትነት መቆጣጠር ይኖርብሃል። ስለ ግጥም አጻጻፍ፣ ስለ ዜማ አወጣጥ፣ ወዘተ ማብራሪያ፣ በቃሉ ምክር የምትለግስበት፣ ወዘተ፣ ዐምድ ይኑርህ። እግዚአብሔር ለበረታ በረከት ያብቃህ።

ምትኩ አዲሱ

ሰኔ 4/2012 ዓ.ም.