መስከረም፣ መስከረም

ኢዮሃ አበባዬ | መስከረም ጠባዬ
ኢዮሃ አበባዬ | መስከረም ጠባዬ ...

meskerem1የወራት ሁሉ ቁንጮ መስከረም። ግንቦት እሳት፣ ሰኔ ውኃ ነው። የኢትዮጵያ ምድር በእሳትና በውኃ ሳትጠመቅ እረፍት እና ልምላሜዋን አታጋራም። ከግንቦት ማብቂያ እስከ መስከረም መጀመሪያ ሦስት ወር ብቻ ቢሆንም፣ እስኪጠባ መጠበቁ ሦስት ዓመት ያስመስለዋል። የመከራ አንዱ ቀን እንደ ዘላለም ነው፤ እግሮቹም በብረት ሰንሰለት ከብደዋል። ደስታ ግን ክንፍ እንጂ እግር የለው።

ግንቦት ድርቅና ብክነት ነው። መስከረም እረፍትና ልምላሜ። ወራት መኳንንት ቢሆኑ መስከረም ንጉሥ ነው። መስከረም ደጅ ያስጠናል። ደጁን ካልከፈተ፣ ፊት ከነሳ ጥቅምትን ማየት አይቻል። አስራ ሁለቱን ወር እንደ ምን ተንፏቆ የደረሰ፣ አምስት እና ስድስት ቀን ጨምሮ ደጅ ይጠናል፤ ራሱንና ጓዳውን እንዲያዘገጃጅ ይገደዳል።

ይህን ያህል ርቀት ተጕዘው ለጥቂት ከደጅ የሚቀሩ አሉ። የሰኔ ጎርፍ ጠርጎ ወሰዳቸው የተባሉ ነፍስና ሥጋቸውን በጥርሳቸው አንጠልጥለው የሐምሌና የነሐሴን ሙላት ተሻገሩ። ሌላው ዳር ቆሞ የደረሱለትንና ያልደረሱለትን ምኞቶቹን ይከልሳል፤ ያመላልሳል። ሆያ ሆዬ ይላል። ሙልሙል ይጎረድማል።

እንደ ሞት ብቅ ይላል፤ መስከረም ሳይታሰብ ብቅ ይላል፤ እንዳላስጠበቀ ሌቱን ገስግሶ ከተፍ ይላል። ያለፈውን ዘመን አስረጅቶ ቀብሮ፣ አዲስ ሕይወት አዲስ ተስፋ ደግሶ ይቀበላል። “ሕይወት እነሆ!” ይላል።

መስከረም፣ እንቁጣጣሽ እንቁጣጣሽ ይላል፤ ጉዝጓዝ ሣር ትኵስ ቡና ይሸታል። እንኳን ደህና መጣሽ። ዓመት ዓመት ያምጣሽ፣

ኢዮሃ አበባዬ | መስከረም ጠባዬ
ኢዮሃ አበባዬ | መስከረም ጠባዬ
መስከረም ሲጠባ
ወደ አገሬ ልግባ ...

የግንቦት ሕጻናት ቢይና አፈር ያቦናሉ፣ አፈር ያፍሳሉ፤ ንፍሮና ቆሎ ያፍሳሉ፤ ጠግበው ቁቅ ይላሉ። የመስከረም ሕጻናት እሸት እሸት ይሸታሉ፤ ያስገሳሉ። ቄኪያቸውን ሰው አፍ ላይ ያስላሉ። አበባ ይስላሉ። አደይ አበባ ይለቅማሉ። ወረቀት ያቀልማሉ፤ ለክርስትና አባታቸው ለክርስትና እናታቸው ለሚወዱት አያታቸው ለሚያቀብጣቸው አጎታቸው ለአክስታቸው ለጎረቤታቸው ያበረክታሉ። ስሙኒ ይለቅማሉ። ሜንታ ከረሜላ ይመጠምጣሉ፤ በደስታ ከረሜላ ይደሰታሉ። ቼሬአሊያ ይኮረሽማሉ፤ ጮርናቄ ያላምጣሉ። ይሳሳቃሉ። እንደ ተርብ ይሯሯጣሉ። ግንባር ለግንባር ተላትመው ይላቀሳሉ። ይንከባለላሉ። ይንቦጫረቃሉ። ስሙኒአቸውን ደጋግመው ይቆጥራሉ። ከሸመቱበት ወዲህ ፍራንኩ ማቃጨሉ ለምን እንደ ቀነሰ በጥርጣሬ ያሰላሉ።

ከሐምሌና ከነሐሴ ጎርፍ የተረፉ ይሰባሰባሉ። በየቤቱ በየቤተክርስቲያኑ ይሰባሰባሉ። በየአደባባዩ ይጨፍራሉ። አክ እንትፍ ያበዛሉ። ይገባበዛሉ። ይጎራረሳሉ። በሞቅታ ይንገዳገዳሉ። ይደጋገፋሉ። ሰላምታ ይሰጣጣሉ። ተስፋ ይቀባበላሉ፤ ተስፋ እንደ ማይጉም ይቀባባሉ።

መስከረም ደስታ ነው፤ ልምላሜ ነው፤ ንጹሕ አየር ነው፤ ጤና ነው፤ ንቁ እርጥብ ፀሐይ ነው፤ ሰማያዊ ሰማይ ነው፤ የተባዘተ ጥሩ ጥጥ ብሩህ ደመና ነው። ብርሃንም እንደ ዝናብ፣ በታጨደ መስክ ላይ፥ በምድርም ላይ እንደሚንጠባጠብ ጠብታ ነው። የሚካበድ የአድማሳት ጥቁር ቡልኮ ወልቆ፣ እንቅልፍ የሚያስይዝ የሰላምና የሲሳይ ዝናብ ነው። ሰማይ የሚሰነጥቅ ጋራ የሚንድ የነጎድጓድ ድምጽ በወፎች ዝማሬ ሲተካ ነው። የደስታ ጅራፍ የሚያስያነጭ፣ የገደል ማሚቶ ኵልል ብሎ የወጣበት ጤዛ የሚያስመርቅ። መስከረም፣ ዳዊት የሚያስደግም ወር ነው፣

ምድርን ጎበኘሃት፣ አጠጣሃትም | ብልጥግናዋንም እጅግ አበዛህ
የእግዚአብሔር ወንዝ ውኃን የተመላ ነው | ምግባቸውን አዘጋጀህ፣ እንዲሁ ታሰናዳለህና
ትልምዋን ታረካለህ | ቦይዋንም ታስተካክላለህ
በነጠብጣብ ታለሰልሳታለህ | ቡቃያዋንም ትባርካለህ
በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ | ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል
የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ | ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ
ማሰማርያዎች መንጎችን ለበሱ | ሸለቆችም በእህል ተሸፈኑ
በደስታ ይጮኻሉ፣ ይዘምራሉም። [ዳዊት 65፡9-13]

meskerem2ደጁን አንኳኵተው ለከፈተላቸው መስከረም ግብዣው ብዙ ነው፤ ድግሱ የጦፈ። የጋመ በቆሎ እሸት ጥብስ። ቅቤ ልውስ አንጮቴና ቡነቀላ። ትኵስ አቦል ቡና ቅቤ በረካ። በአስራ ሁለት የጉራጌ መስቀል፣ በአስራ ስድስት ደመራ፣ በአስራ ሰባት ለተቀረነው መስቀል። ጠፍቶ የከረመው የሚገኝበት፣ እሳትና ዐመድ የተስማማበት። ግንቦት በፀሐይ እሳት ያቦነነውን፣ መስከረም በደመና እሳት አብርዶ ያሳርገዋል።

በአስራ ስምንት፣ ተማሪ ልብሱን አጥቦ ተስፋ ፍለጋ፣ እውቀት ፍለጋ ደብተሩን ይዞ ይራመዳል። ከጳጉሜ [ጳጉሜን፣ ቋቍሜ] መስከረም እስኪሸኝ፣ የአገር ሰላምታ እንደ በረቅ እንደ ነጎድጓድ ከቅርብና ከርቀት ይንጎደጎዳል፤ እንደ ምንጭ ውኃ እንደ ጅረት ይዥጎደጎዳል፦

እንኳን አደረሰህ ... እንኳን አደረሰሽ
እንኳን አደረሰሽ ... አሜን እንኳን አደረስዎ
እንኳን አደረሰዎ ... እንኳን አደረሰሽ
እንኳን አደረሳችሁ ... እንኳን አደረስዎ አባባ
ሃፒ ኒው ይር ማዘር ... ሃቢኑር ያርግሽ እቴ፣ እንኳን አደረሰሽ በዪልኝ እናትሽን
አደረሳችሁ ... ይመስገነው ... ክብሩ ይስፋ...

meskerem3መስከረም የወሮች ሁሉ ንጉሥ ነው። የኢትዮጵያ ክልሎች፣ ወረዳዎች፣ አደባባዮች፣ ቀዬዎች እና ጓዳዎች ይዘጋጁ፤ ከሩቅ እጅ ይንሱ፣ ከቅርብ እጅ ይንሱ። የሰላም እሳት ያጋዩ፣ ያደፈውን እና ያረጀውን ያቃጥሉ። የመስቀሉ እሳት ተውሳኩን ያጋይ! የአጋንንትን መንጋ ያክስም። የተስፋ ችቦ ይብራ። በአንድነት ሆ! ይበሉ። የደስታ ሆታቸውን ሸለቆ ሸንተረሩ ጋራና ፈፋው ተቀብሎ ያስተጋባ። “ምነው ተሽኮረመምሽ? እንደ መስቀል ወፍ የት ጠፍተሽ ከረምሽ?” ይባባሉ።

ኢዮሃ አበባዬ | መስከረም ጠባዬ
መስከረም ሲጠባ | አደይ ሲፈነዳ
እንኳን ሰው ዘመዱን | ይጠይቃል ባዳ

ለተቀረው ዓለም፣ አዲስ ዓመት ጥር ነው። ለኛ አዲስ፣ መስከረም ነው።

የ  ሰ ላ  ም  ና   የ  ም  ህ  ረ  ት   ዓ  መ  ት   ይ  ሁ  ን  ል  ን !

© ምትኩ አዲሱ

Image credit: skyscrapercity.com; googleimages.com

ቀላሉን መንገድ | የማለዳ ድባብ | ከየት ተገኘሽ ሳልል | ቋንቋን በቋንቋ | ስደተኛውና አምላኩ | ሞት እና ፕሮፌሰር | የድመትና ያይጥ ፍቅር | የልማት መሠረቱ መታመን ነው | ጒግል እንደ አዋቂ | ቆመህ እያየህ | ለመቶ ሚሊዮን የአገሬ ሕዝብ | ትዝብቶች ከ “አባቴ ያቺን ሰዓት” | ይድረስ ለቴዲ አፍሮ | ችግሩ አልተፈታ | በፎቶ ኢትዮጵያና እንግሊዝ | ጸሎትና ስፖርት | መጠየቅ ክልክል ነው? | የሺህ ጋብቻ ወይስ ቅዱስ ጋብቻ? | መሬት መሬት ሲያይ | ልቤ ከብዷል ዛሬ | ቸር ወሬ አሰማኝ | መንበርና እርካብ | ጒዞዬ | ፓትርያርክ በዕጣ | ባንተ በኲል ስትቦረቡር | Land of the Shy, Home of the Brave