ወንጌላውያን መቸ ይሆን የምንማር?

ፊደል

አገራችን በጎሣና በቋንቋ በተከፋፈለች ማግሥት፣ ቤተክርስቲያንም በቋንቋና በጎሣ ተከፋፈለች። ምድር በሕዝባዊ ቊጣ ተናጠች። የዶ/ር ዐቢይ መንግሥት ነውጡን በ “መደመር” ለማዳፈን የተፈጠረ መንግሥት ነው። “መደመር” በተራው ምን ውጤት ያስከትል ይሆን? ወንጌላውያን ከ “ነጻነት” ዘመን ምንም ሳንማር ወደ ቤተመንግሥተኛነት ተሸጋገርን ይሆን?

በደርግ ዘመን የለየለት አቋም መውሰድ እንጂ መሓል ሠፋሪ ክርስትና አያዋጣም ነበር። አብዮቱንና የሠርቶ አደሩን ፓርቲ የማይደግፍ ሁሉ ተቃዋሚ ነው። ሁሉም ነገር ለአብዮቱ ነው፤ ልብስና አሞሌ ጨው ለአብዮቱ ነው። ኃይማኖትም። ሕይወትም። አይሆንም ያሉ ታሠሩ፣ ተሰደዱ። ቤተክርስቲያኖች ተወረሱ።

ህወሓት/ኢሕአዴግ ከደርግ ጣቃ ተቀድዶ የወጣ ነው። ደርግ፣ ሠርቶ አደር/አርሶ አደር ተጨቋኝ፤ ባላባትና ኢምፔሪያሊስት ጨቋኝ ነው አለን። በአገራችንና በዓለም ዙሪያ የታየው ችግር የዘር ሳይሆን የመደብና የርእዮተ ዓለም ነው አለ። ቤተክርስቲያንም ጠላትዋን ለይታ አወቀች። እግዚአብሔር የለም ከሚል ወዲያ ጠላት ማን ነው?

ህወሓት/ኢሕአዴግ ምድሪቱን በጎሳ፣ በቋንቋ ዘጠኝ ቦታ ከለለ። እኲልነት፣ ነጻነት ብሎ አወጀ። ሕዝቡ ተተረማመሰ። ደርግ ሲፈርስ፣ ፈንጠዚያውን እንጂ ቤተክርስቲያን የሚጠብቃትን አላጤነች። ተራዋን በጎሳ፣ በቋንቋ፣ በአስተምህሮና በአደረጃጀት ተተረማመሰች። ካልለየለት ወዳጅ ይልቅ የለየለት ጠላት ተሻለ!

ደርግ፣ ሳንሡር አድራጊ ራሱ ነበር። ‘አሳባዊነት’ ን አልቀበልም አለ፤ የባህል አብዮት ይህን አይፈቅድም፣ ከዚህ አትለፍ አለ። ህወሓት/ኢሕአዴግ ደግሞ፣ ነጻ ነህ፣ እንደ ደርግ ሳንሡር ብዬ አላስቸግርህም፤ በያለህበት ራስህን ሳንሡር አድርግ አለ። ተላለፍክ ብሎ እንዳፈቀደ ለማገድ አመቻቸ። ሕዝቡ በፍርሓት ተሳሠረ። የኃይማኖት ዳይሬክቶሬት ተቋቋመ፤ መንግሥት በቤተክርስቲያንና በመስጊድ ጒዳይ ውስጥ ዋነኛ ተሳታፊ ሆነ፤ ከአፄዎች ጀምሮ እስከ ዛሬ የተለወጠ ነገር የለም።

አጥቢያ ቤተክርስቲያን ቀድሞ ትመራ የነበረው በሽማግሌዎችና በአገልጋዮች ጣምራ አመራር ነበር። ፓስተር ወይም ሐዋርያ ወይም (እንደ ስሙ አበዛዝ) ብቻውን በአጥቢያ ላይ መሰየም ተጀመረ። ትልቅ ነኝ የሚሉ አገልጋዮች ተነሱ። ባለራእይ እኔ ነኝ፣ አትድረሱብኝ መጣ። ቀጥሎ፣ አንዱ አገልጋይ በብዙ አብያተክርስቲያናት ላይ የበላይ መሆን ተጀመረ። ግለሰቦች ገነኑ፤ ቤተክርስቲያን የግል ይዞታና ውርስ መሰለች። አንዳንዶችን ምድር አልበቃቸው አለች። ግራ ቀኛቸውን የማያውቁ ተበራከቱ።

በጎሠኛ ክልል ያልተነካካ አገልግሎት ማግኘት አቃተ። የ “ሚኒስትሪዎች” መበራከት የክርስቶስን ቤተክርስቲያን ሥልጣንና ህልውና ተቀናቀነ፤ ምእመን እና ገቢ በመሻማቱ የቤተክርስቲያን አቅሟና ምስክርነቷ ደበዘዘ። የምናየው ትርምስ መዘናጋቷ ያስከተለው ነው! በሙሉ ወንጌል፣ በቃለ ሕይወት፣ በመካነ ኢየሱስ፣ ወዘተ፣ የተከሰተው ሽኲቻና የከረረ ጠብ በአብዛኛው ጎሠኛነት፣ የሥልጣን ጥመኛነትና የአስተምህሮ መመናመን ያስከተለው ነው። የሰይጣንም እጅ አይጠፋም። መሪዎች ከኃላፊነታቸው ተዘናግተው ሲሻኮቱ፣ በክፍተቱ እግዚአብሔርን በስልክ አናገርነው የሚሉ ተበራከቱ። በጎቹን ማስጣል ቀርቶ “ፍቅርና መቻቻል” የሚሉት ድርድር ተጀመረ። እንደ ፖለቲከኞቹ ሁሉ ዝነኛ ‘አገልግሎቶች’ ተለጣፊ ተደረጉ። መነሻ አሳቡ ያው ሥልጣንና ገቢ ነው።

- - - -

ዶ/ር ዐቢይ ሃያ ሰባት ዓመት የኖረን የ “ክልል” ቊጥር በ “መደመር” ለመቀናነስ ዝተዋል። በጎ ጅማሬዎች አልታዩም አንልም። ሥጋታችን “መደመር” የህወሓት/ኢሕአዴግ “ክልል” ግልባጭ እንዳይሆን ነው። መንግሥት የቤተክርስቲያንን ሥራ ሊሠራ የሰላም ሚንስቴር መ/ቤት አቋቊሟል! ዶ/ር ዐቢይ “የመደመርን” አብዮት ለማቀጣጠል አንድ ሚሊዮን ኮፒ መጽሐፋቸውን በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በእንግሊዝኛ ቻይና አሳትመዋል (የሊቀመንበር ማኦ ጼቱንግን ትንሿን ቀይ መጽሐፍ ወይም የኮሎኔል ጋዳፊን አረንጓዴ መጽሐፍ ያስታውሷል)። ምን ያህል ይሳካላቸው ይሆን? አንድነታችንን ለማጠናከር “አንድነት ፓርክ” አስገንብተውልናል። የ “ብልጽግና ፓርቲ” የክርስትና አባት ለመሆን በቅተዋል። (ብልጽግና ፓርቲ ከብልጽግና ወንጌል ጋር ይያያዝ ይሆን? አእምሮአችን በብልጽግና አሳብ ቢሞላ ሥራ አጥነት ይወገዳል? አገር የዘረፉ፣ የዘረፉትን ለአገር “ብልጽግና” ካዋሉ ምሕረት ይደረግላቸዋል?)

ልዩ ልዩ መሆን ውበት ነው። የአንጃ ፖለቲከኞች ያያያዘንን ታሪክ አሳስተውና አረሳስተው ደም አፋስሰዋል። አሁን ደግሞ ልዩነታችንን አናጒላ፤ አንድነታችን ይብለጥብን ተብለናል። የነእስክንድር "አንድነት፣ ኢትዮጵያዊነት" ከነዶ/ር ዐቢይ "ኢትዮጵያዊነት፣ አንድነት" ጋር ሊስማማ ለምን እንዳልቻለ ግልጽ አይደለም። "መደመር" በቤተክርስቲያን ላይ ምን ዓይነት ጫና፣ ምን አሉታዊ ተጽእኖ ቋጥሯል? ወንጌላውያን መሪዎች ይህን ያሰቡበት አይመስሉም። እንዲያውም ዶ/ር ዐቢይ ቤተመንግሥት በጠሩት ስብሰባ ላይ፣ እኛ አልቻልንበትም “መፍትሔ ብለን የምናምነው (እርስዎ) እንዲያደራጁን ብቻ ነው” የሚል አስገራሚ ቃል አሰምተዋል! በ “ቄሣር” ፊት ዘውዳቸውን አውልቀው አኑረው ይሆን? የዶ/ር ዐቢይ እናት ሰባተኛው ንጉሥ አንተ ነህ ያሉት ትንቢት ተፈጽሞ ይሆን?

 crown polisen tt

“መደመር” ሲታይ መልካም ይመስላል። መተባበርን፣ መፈቃቀርን፣ አንድነትን ሰይጣን ካልሆነ ማ ይጠላል? አንድነት ግን በእውነት ላይ ካልተመሠረተ፣ እውነተኛ አንድነት ሊመጣ አይችልም። ህወሓት/ኢሕአዴግ፣ አናሳውም ብዙኃኑም እኲል ነው ብሎ አወጀ። ሕጻንም እንኳ እንደሚገነዘበው፣ በቊጥር አሥር የማይሞሉና ሺህዎች እኲል ሊሆኑ አይችሉም። እውነትን በክልል መሸንሸን ተጀመረ። አዳዲስ ካርታዎችና የመማሪያ መጻሕፍት ለየመንደሩ ተፈጠረ። እውነቱን አለማወቅና የታወቀውን እውነት መካድ ተጀመረ።

ኃያላን በያሉበት የየራሳቸውን እውነት ሲፈጥሩ ኖረዋል። የኃያላን እውነት ኃይል ነው፤ እርግጫ ነው። ሰላም፣ እኲልነት፣ ዲሞክራሲ፣ አንድነት፣ ነጻነት ይላሉ፤ ህግ ይደነግጋሉ። የሚሰብኩት እውነት፣ የሚደነግጉት ህግ ግን መርጠው የሚስማማቸውን ብቻ ነው። ሕዝብ ድምጹን ሰጥቶ መሪዎቹን ይምረጥ ይላሉ፤ ሕዝቡ እነዚህን እንጂ እናንተን አልፈልግም ሲላቸው፤ አይ፣ ያለ እኛማ እንዴት ይሆናል፤ እዚህ ቊምነገር ላይ ያደረስንህ እኛው ሆነን? ይላሉ። እንዲያውም ቊጣ ቊጣ ይላቸዋል። ስንት ውለታ ለዋልንልህ፣ ብናሥርህ፣ ልማት ለማፋጠን ከቀዬህ ላይ ብናፈናቅልህ፣ ብንሠርቅ እንኳ ውለታ ቢስ ልትሆን ይገባል? ይላሉ!

ኃያላን እውነትን አያውቋትም። የያዙትን ስለሚያፋልስባቸው እውነቱን ማወቅ አይፈልጉም። ኢየሱስ፣ ለጲላጦስ (ለሮም መንግሥት) ከሰጠው መልስ ውጭ ቤተክርስቲያን የከበረ መልስ የላትም!

“ጲላጦስም እንደ ገና ወደ ገዡ ግቢ ገባና ኢየሱስን ጠርቶ። የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን? አለው። ኢየሱስም መልሶ። አንተ ይህን የምትለው ከራስህ ነውን ወይስ ሌሎች ስለ እኔ ነገሩህን? አለው። ጲላጦስ መልሶ። እኔ አይሁዳዊ ነኝን? ወገኖችህና የካህናት አለቆች ለእኔ አሳልፈው ሰጡህ፤ ምን አድርገሃል? አለው። ኢየሱስም መልሶ። መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴስ ከዚህ ዓለም ብትሆን፥ ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም አለው። ጲላጦስም። እንግዲያ ንጉሥ ነህን? አለው። ኢየሱስም መልሶ። እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ አንተ ትላለህ። እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል አለው። ጲላጦስ። እውነት ምንድር ነው? አለው።” (ዮሐንስ 18፡33-38)

እውነት፣ የድርጅት ወይም የሰው አእምሮ ውጤት አይደለም፤ ሰው ሆኖ የተገለጠው ኢየሱስ እራሱ ነው (ዮሐንስ 14፡6)። ሁሉም ነገር በርሱ ትይዩ፣ በርሱ ብርሃን ይመረመራል። አንድነት በቅድሚያ ከኢየሱስ ጋራ መስማማት ነው፤ ከዚያ በሰዎች ግንኙነቶች ይከሰታል። በሌላ አነጋገር፣ ከእውነት ያልሆነ ኢየሱስን መስማት አይሻም።

የሥልጣን አሠላለፍና ማህበራዊ አደረጃጀት፣ የእውነት መታያና መፈተኛ ነው። ምድራዊ ሥልጣን ረግጦ በመግዛት ነው። ሰማያዊ ሥልጣን ለተገለጠው እውነት በመገዛት፣ እግዚአብሔርና ሰውን በማገልገል ነው። ቤተክርስቲያን የእውነት መገኛ ነችና በእውነት ላይ የሚቀልዱትን፣ ስብዕናን የሚያዋርዱትን ለመገሠጽ ሥልጣን ተሰጥቷታል።

“ማናቸውም ታላቅ ሆኖ እንዲቈጠር በመካከላቸው ክርክር ሆነ። እንዲህም አላቸው። የአሕዛብ ነገሥታት ይገዙአቸዋል፥ በላያቸውም የሚሠለጥኑት ቸርነት አድራጊዎች ይባላሉ። እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ፤ ነገር ግን ከእናንተ ታላቅ የሆነ በመካከላችሁ እንደ ታናሽ፥ የሚገዛም እንደሚያገለግል ይሁን።” (ሉቃስ 22፡24-26)

“መደመር” ለቤተክርስቲያን የሚጨምርላት አዲስ እውነት የለም! በህወሓት/ኢሕአዴግ ዘመን የእውነት ሚዛን በመዛባቱ ወላይታውም፣ ትግራዩም፣ አማራውም፣ አፋሩም፣ ነቢያትና ሐዋርያቱም፣ የየራሳቸውን እውነት አንግበው አትድረስብኝ አልደርስብህም ተባባሉ። ሐዋርያው እና ዘማሪው፣ ፈትቼ ባገባ ላንተ ምንህ ነው ማለት አመጡ? ለእኔና ለአምላኬ ተውልኝ፣ ደስ ካሰኘኝ ምን ቸገረህ? ይልቅ ምሰሶ ዐይንህ ውስጥ ይታየኛል ተባባሉ።

“መደመር” በብዙ ጸሎትና በምክክር ሊመረመር ይገባል የምንለው ለዚህ ነው። ዐቢይ በጠሩት ስብሰባ ላይ የተናገሩት ሁሉ በጎ ነው፤ ስውር አጀንዳ ያራምዳሉ ብሎ መጠርጠር ያዳግታል። እንዲያውም ከዚህ ቀደም በባለሥልጣኖች ዘንድ ያልታየ የሕዝብ አገልጋይነትን ፍሬ እያሳዩን ይገኛሉ። በጎ የመሰለ ሁሉ ውጤቱም በጎ ይሆናል ማለት ግን አለማስተዋል ነው። ዐቢይ እንዲህ ብለው ነበር፣

“ህገ መንግሥቱ ኃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ ናቸው የሚል ድንጋጌ አስቀምጧል። በርግጥ ህገ መንግሥቱ ያን ድንጋጌ ካስቀመጠ በኋላ ብዙ አገር እንዳለው ልምድ ዝርዝር ህግ አላወጣም። ዝርዝር ህግ ካላወጣ በስተቀረ በአንድ ቤት የሚኖሩ ሁለት ዋና ዋና ምሰሶዎች ግንኙነት የላቸውም የሚል ድንጋጌ በቂ አይደለም። ዝርዝር ህግ በምን በምን ጒዳይ ይገናኛሉ የሚለውን አሜሪካ እንዳለው እንግሊዝ እንዳለው እኛም ጋ ህግ ያስፈልጋል። ዩኒፎርም የሆነ ኃይማኖት ተቋማትና መንግሥት መካከል በሰላም ጒዳይ በልማት ጒዳይ በማህበረሰብ ግንባታ ጒዳይ እንዴት ነው እየተገናኙ ሥራ የሚሠሩት የሚለውን የሚያሳይ ህግ ያስፈልጋል። ምክንያቱም የእምነት ተቋማት የሚጋሩት ዜጎችን ነው፤ መንግሥት የሚጠቀመው እነሱን ዜጎች ነው። የእምነት ተቋማት የሚጠቀሙት የአገር ሃብት ነው፤ መንግሥት የሚጠቀመው የአገር ሃብት ነው። እና ቢያንስ ፕሮግራም እንኳን ፕሮግራም እንኳን ማቀናጀት ካልቻልን፣ አንዱ ባንዱ ጣልቃ አይገባም ስለ ተባለ ብቻ ብንተው ሥራ አይሠራም...”

መንግሥት በህገ መንግሥት እስከተዳደረ/እስካስተዳደረ ድረስ የተደነገጉ መብቶችን ከማስከበር አልፎ በቤተክርስቲያን መንፈሳዊ/ማህበራዊ ተግባራት ውስጥ ጣልቃ መግባቱን በጥንቃቄ መመርመር ያሻል። ቤተክርስቲያን ተቀዳሚ ተልእኮዋን አጥርታ ማወቅ ይኖርባታል። ቤተክርስቲያን የመንግሥት ሚኒስቴር መ/ቤት አይደለችም። የገዥ ፓርቲ አባል ወይም ተላላኪ ለመሆን አልተጠራችም። ዛሬ አብያተክርስቲያናት በዓለም ካለመነካካት ጠርዝ ዘልለው በሁለት ትውልድ የቤተመንግሥት ታዳሚና የመንግሥት አፈ ቀላጤ ወደ መሆን ተሸጋግረዋል! ሥልጣን አያሳሳም ማለት ራስን መሸንገል ነው። (ማቴዎስ 4፡8-10)

“አሜሪካ እንዳው፣ እንግሊዝ እንዳው” አባባል ግልጽ መደረግ ይኖርበታል። የእንግሊዝ (ዘውዳዊ) መንግሥት የ(አንግሊካን) ቤተክርስቲያን የበላይ ጠባቂ ነው። ‘የእምነት ነጻነት’ ብለው ከአራት መቶ ዓመት በፊት ከእንግሊዝ ወደ አሜሪካ የፈለሱት የዛሬ አሜሪካኖች፣ መንግሥት በኃይማኖት ጒዳይ ጣልቃ አይግባ፤ መንግሥትና ቤተክርስቲያን ይለያዩ ቢሉም፣ ከአርባ ዓመታት ወዲህ የፖለቲካ ተሳትፎአቸው ከመጠናከር አልፎ የሪፐብሊከን ፓርቲ ምርኲዝ ሆነዋል። ምስክርነታቸው በዚያው ልክ በዘረኝነት፣ በጠበኛነት፣ በፍቅረ ንዋይ ጠልሽቶ ለወንጌል ሥራ እንቅፋት ሆነዋል። በዐቢይ ሥልጣን መያዝ ምክንያት በአብያተክርስቲያናት የታየው ፈጣን ለውጥ እጅግ አሳሳቢ ነው። “መልካም ወጣት ለኢትዮጵያ አንድነት” በመንግሥት ድጎማ መንቀሳቀሱ የወንጌሉንና የፖለቲካውን ድንበር አደብዝዟል። የባለ“ሚኒስትሪዎች” ቊጥር መበራከትና ከፖለቲከኞች ጋር መተሻሸት፣ በቤተክርስቲያን ታሪክ ላይ በጎ ያልሆነ አሻራ የሚጥል ነው። በህወሓት/ኢሕአዴግ ዘመን ሕዝቡን በ“ሰላምና ብልጽግና” ያባበሉ ተገልብጠው “ብልጽግና ሰላም” ማለታቸው ውጤቱ አለመታመን፣ ለረብ መሳሳት፣ ለሥልጣን መሯሯጥ ነው። በኤርትራና ኢትዮጵያ ስምምነት ማግሥት የታየው ግርግር ማስተዋል የጎደለው ትእይንት ነው።

 

ዐቢይ ጁላይ 27/2018 ኋይት ሃውስ ተገኝተው ከአቻቸው ከትረምፕ ጋር ሳይሆን ከትረምፕ ምክትል ፔንስ ጋር መወያየታቸው፣ ትረምፕ የነጋዴ እንጂ የወንጌል አማኝ አንደበት ስላልተካናቸው፣ ዐቢይና ፔንስ ወንጌል አማኝ መሆናቸውን ከእሳቤ በማስገባት ነው። ነጋዴ የሚያዋጣውን ብቻ ያያል፤ በቃሉ ላይታመን ይችላል። ፖለቲከኛም እንደዚሁ ነው! የፔንስ ፖለቲከኛነት እንጂ ወንጌል አማኝነት ቅድሚያ ሊሰጠው እንደማይገባ ዐቢይ ይታጣቸዋል አንልም። ታዋቂው መጽሔት “ክርስቲአኒቲ ቱዴይ” እንኳ “የኢትዮጵያ ወንጌል አማኝ ጠ/ሚ የኖቤል ተሸላሚ ሆነ” ሲል ዘግቦ ነበር። የጠ/ሚ ዐቢይ ወንጌል አማንያንን ለፖለቲካ ማሠለፍ፤ የወንጌል አማንያንም ቤተመንግሥት ወጣ ገባ ማለት፣ ከዚህ ቀደም ያልነበረ፣ ቆይቶ የወንጌልን ንጽሕና የሚያጎድፍ አካሄድ ነው። በጌታ ፀባዖት ፊት መቅረብ ለለመደ ቤተመንግሥት ያንስበታል።

የሰሜን አሜሪካ ወንጌላውያንን አዘማመርና አምልኮ መኮረጅ ሳያንስ ፖለቲካውንም መጨመር በጽድቅና በቅድስና ገና የሚያስከፍለው ብዙ ዋጋ አለ። ቤተክርስቲያን/አማንያን ከዓለም ይውጡ አይደለም ነገሩ። ነገሩ፣ ምሪታቸውን ከዓለም አይቀበሉ ነው! ችግሩ በወንጌል/በቤተክርስቲያን ስም መደረጉ ነው። እስከ ዘመነ ደርግ ቤተክርስቲያን (በተለይ) ከዓለም የፖለቲካ እድፍ እንዳትነካካ ጥንቃቄ ታደርግ ነበር። አማንያንም ምስክርነታቸውን ጠብቀው በተለያዩ መስኮች አገራቸውን ያገለግሉ ነበር። የአሁኑ አዝማሚያ የቀድሞው ተቃራኒ ነው! ፓርላማ እንገባለን፤ እኛ ሳንስማማ ምንም ጠብ አይልም ያሉን ነቢያት፣ ትንቢታቸው ስለ ዘገየባቸው ራሳችን እንፈጽመው ብለው የተነሱ መስሏል!

ከእስራኤሉ ጠ/ሚ ናታንያሁ ጋር የሚደረጉ ስምምነቶች የትንቢት ፍጻሜ ማፋጠኛ እንደሆኑ መታሰብ የለባቸውም። እርግጥ ነው እግዚአብሔር በፖለቲካም ውስጥ ይሠራል። ናታንያሁ ሆኑ ፔንስ የማታ ማታ ዓላማቸው የፓርቲአቸውን እና የአገራቸውን ጥቅም ማስከበር ነው! ናታንያሁ የተከሰሱበትን ወንጀል ለማዘናጋት፣ እንደ አሜሪካ አቻቸው፣ በተራቸው ፍልስጤማውያንን እና ስደተኛውን በሕዝብ ፊት በማዋረድ ላይ ተሰማርተዋል። የአሜሪካ ወንጌላውያንም ግፉን እንደ ጽድቅ ቆጥረው የሁለቱን አገር መሪዎች ሥልጣን ላይ ለማሰንበት እየተሯሯጡ ይገኛሉ። ናታንያሁ፣ ስደተኞችን ለሚቀበል አገር በገንዘብ መዋዋል ጀምረዋል። ሯንዳ $5000 በነፍስ ወከፍ ተስማምታለች! ዐቢይ ለናታንያሁ የገቡት ቃል በምሥጢር ተይዟል። የናታንያሁ መንግሥት ስደተኛውን በማባረር ለሚተባበር ዜጋ $8700 መስጠት ጀምሯል። ለመሆኑ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ስደተኛ ምን ይላል?

“በአገራችሁ ውስጥ ከእናንተ ጋር እንግዳ ቢቀመጥ ግፍ አታድርጉበት። እናንተ በግብፅ ምድር እንግዶች ነበራችሁና ከእናንተ ጋር የሚቀመጥ እንግዳ እንደ አገር ልጅ ይሁንላችሁ፥ እርሱንም እንደ ራስህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ” (ሌዋውያን 19፡33-34)። “መምህር ሆይ፥ ከሕግ ማናቸይቱ ትእዛዝ ታላቅ ናት? ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ አለው። ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርስዋም። ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት። በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል።” (ማቴዎስ 22፡36-40)

ወንጌላውያን ቆም ብለን ለማሰብ ጊዜ አጥተናል። የወንድማችን የዮሴፍ ቤተመንግሥት ነው እያልን ገባ ወጣ አብዝተናል። ሙሴ የእግዚአብሔርን ጥሪ ለመፈጸም አስቀድሞ ቤተመንግሥት ጥሎ መውጣት እንደነበረበት ትዝም አላለን! በየአደባባዩ የድጋፍ ሰልፍ እያልን ሕዝብ እንሰበስባለን። በስብከታችንም ብልጽግና ብልጽግና “ክብርና ሞገስ ለዐቢይ ይሁን” እንላለን።

ምትኩ አዲሱ

ጥር 22/2012 ዓ.ም.

የማለዳ ድባብ | ከየት ተገኘሽ ሳልል | ቋንቋን በቋንቋ | ስደተኛውና አምላኩ | ሞት እና ፕሮፌሰር | የድመትና ያይጥ ፍቅር | የልማት መሠረቱ መታመን ነው | ጒግል እንደ አዋቂ | ቆመህ እያየህ | ለመቶ ሚሊዮን የአገሬ ሕዝብ | ትዝብቶች ከ “አባቴ ያቺን ሰዓት” | ይድረስ ለቴዲ አፍሮ | ችግሩ አልተፈታ | ጸሎትና ስፖርት | መጠየቅ ክልክል ነው? | የሺህ ጋብቻ ወይስ ቅዱስ ጋብቻ? | መሬት መሬት ሲያይ | ልቤ ከብዷል ዛሬ | ቸር ወሬ አሰማኝ | መንበርና እርካብ | ጒዞዬ | ፓትርያርክ በዕጣ | ባንተ በኲል ስትቦረቡር | Land of the Shy, Home of the Brave